የኢትዮጵያ የግብፅና የሱዳን ተደራዳሪዎች በህዳሴው ግድብ ላይ የቀረቡ ሁለት ምክረ ሐሳቦችን እንዲያጠኑ የተመረጡት የውጭ ኩባንያዎች ያቀረቡት የዋጋና የቴክኒክ ሰነድ ላይ ለመወሰን ሐምሌ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በሱዳን ካርቱም ይገናኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በዚህ የሦስትዮሽ የጋራ ስብሰባ ላይ ለመገኘትም በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ የተመራው የኢትዮጵያ የቴክኒክ ቡድን ወደ ሱዳን ካርቱም ባለፈው ማክሰኞ አቅንቷል፡፡
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መጀመሩን ተከትሎ ከግብፅ በኩል የተነሳውን ተቃውሞ በሰላማዊ መንገድ ለመመለስ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ባለሙያዎችን በመጋበዝ የኃይል ማመንጫ ግድቡ ግንባታ አጠቃላይ ሁኔታዎች እንዲጠኑ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ከሁለት ዓመት በፊት የጥናት ግኝታቸውን ይፋ ያደጉት ባለሙያዎች ግድቡ በታችኛው የዓባይ ተፋሰስ አገሮች ላይ ጉልህ ጉዳት እንደማያደርስ ይፋ አድርገዋል፡፡ ይሁን እንጂ የፕሮጀክቱ ኃይድሮ ስሙሌሽን ሞዴል ማለትም የውኃ አሞላልና አለቃቀቅ በተለያዩ የዝናብ ወቅቶች ምን ይመስላል የሚለው የኢትዮጵያ ጥናት መተማመንን እንዲፈጥር፣ በሦስቱ አገሮች በጋራ በድጋሚ ቢጠና የሚል ምክረ ሐሳብ ማቅረቡ ይታወሳል፡፡
በተጨማሪም የፕሮጀክቱ ዕውን መሆን በሱዳንና ግብፅ ላይ የሚፈጥረው አካባቢያዊና ማኅበራዊ ተፅዕኖ ምን ይመስላል የሚለው የኢትዮጵያ ጥናት ቢኖርም፣ በሦስቱ አገሮች ዘንድ መተማመንን እንዲፈጥር በጋራ ቢጠና የሚል ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡
ይህንን ምክረ ሐሳብ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ በወሰነው መሠረት፣ ጥናቱ በዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት እንዲጠና መወሰኑ ይታወሳል፡፡
ይህንን ኃላፊነትም ወደ ተግባር ለመለወጥ ሦስቱ አገሮች እያንዳንዳቸው በወከሏቸው አራት አራት ባለሙያዎች አማካይነት ዓለም አቀፍ ጨረታ ወጥቶ ከተወዳደሩ ኩባንያዎች መካከል፣ የፈረንሳዩ ቢአርኤል ኢንጂነርስ የተባለ ኩባንያ ጥናቱን በዋናነት እንዲያካሂድ ባለፈው ሚያዝያ አዲስ አበባ ላይ ተወስኗል፡፡
ቢአርኤል ኢንጂነርስ በዋናነት ሁለቱን ጥናቶች ቢያካሂድም፣ የተወሰኑ የጥናት ክፍሎችን የኔዘርላንድ ኩባንያ ለሆነው ዴልታ ሬዝ እንዲሰጥ በግብፅ ብቸኛ ግፊት በመጨረሻ ተቀባይነት ማግኘቱ ይታወቃል፡፡
ኩባንያዎቹ መመረጣቸውን እንዲያውቁ ከተደረገ በኋላ ለሦስቱም አገሮች ባቀረቡት የፋይናንስና የቴክኒክ ፕሮፖዛል ላይ ግን፣ የሦስቱ አገሮች ባለሙያዎች ስምምነት ላይ መድረስ አልቻሉም፡፡
የሦስቱ አገሮች የባለሙያዎች ቡድን ከአንድ ወር በፊት በግብፅ ካይሮ ከተማ ተገናኝቶ የነበረ ቢሆንም፣ ለሁለት ቀናት ያደረገው ውይይት ያለ ስምምነት ተጠናቋል፡፡ ያለመግባባት ምንጩ ምን እንደሆነ ተደራዳሪዎቹም ሆነ የውኃ ሚኒስትሮቹ ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ምንጮች ግን ኩባንያዎቹ ያቀረቡት የፋይናንስ ጥያቄ የመከራከሪያው ጭብጥ እንዳልሆነ አረጋግጠዋል፡፡ አጥኚዎቹ ያቀረቡት የቴክኒክ ፕሮፖዛል ላይ በግብፅ በኩል የቀረበው ተጨማሪ ጥያቄ የክርክሩ ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በካይሮ ውይይት ላይ አጥኚዎች በአስረጂነት ያልተገኙ መሆኑን የጠቀሱት ምንጮች፣ አለመግባባቱን ለመፍታት ሐምሌ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚጀመረው የሱዳን ውይይት ላይ የአጥኚ ቡድኑ ተወካዮች ይገኛሉ ተብሏል፡፡