– መንግሥት ገና በድርድር ላይ መሆኑን ተከራክሯል
የአሜሪካው ብላክ ስቶን ኩባንያ ከጂቡቲ እስከ አዋሽ ባለው መስመር ላይ ይዘረጋዋል ተብሎ የታሰበው፣ በቅርቡ አዲስ አበባ ይመጣሉ የተባሉ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ይመክሩበታል የተባለው የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ጥያቄ አስነሳ፡፡
መንግሥት ግዙፍ ጭነቶችን ከጂቡቲ ወደብ ወደ አገር ውስጥ ለማጓጓዝ እንዲያስችሉት ከሚዘረጋቸው መሠረተ ልማቶች መካከል የባቡር ትራንስፖርት ትልቁን ቦታ ይይዛል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን በነዳጅ ማስተላለፊያ አማካይነት ነዳጅ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ከአሜሪካ ይመጣል የተባለው ብላክ ስቶንና ሊያከናውን ያሰበው ግንባታ ካሳሰባቸውና የመንግሥት ኃላፊዎችን ስለጉዳዩ አሳሳቢነት ከጠየቁት መካከል፣ የናሽናል ኦይል ኩባንያ (ኖክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ጥላሁን ናቸው፡፡ እሳቸው መንግሥት ነዳጅ ለማጓጓዝ ከጂቡቲ እስከ አዲስ አበባ ይዘረጋል ያለው ፕሮጀክት ሊታሰብበት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
መንግሥት የነዳጅ ማስተላለፊያ ከመገንባት ይልቅ የነዳጅ ማጣሪያ በጂቡቲ ወደብ ላይ ቢገነባ የተሻለ እንደሚሆን የተናገሩት አቶ ታደሰ፣ የነዳጅ ማጣሪያውና ማስተላለፊያው አብረው ካልተገነቡ በቀር የነዳጅ ማስተላለፊያ ብቻ መገንባቱ ለአገሪቱ የሚያስገኘው የረባ ጥቅም እንደሌለም አስታውቀዋል፡፡ ድፍድፍ ነዳጅ በሚኖርበት አካባቢ የነዳጅ ማጣሪያ መትከል ለአገሪቱ ትልቅ ጥቅም እንደሚያስገኝም ገልጸዋል፡፡ ስለዚህም መንግሥት እንዲያስብበት ጠይቀዋል፡፡ ‹‹ያለ ነዳጅ ማጣሪያ ነዳጅ ማስተላለፊያ መገንባት አርቆ አለማሰብ ነው፤›› ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በአዲስ አበባ በሚያደርጉት ጉብኝት ውስጥ አንዱ አጀንዳ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ፕሮጀክት 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚጠይቅ እንደሆነ ይገመታል፡፡
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አህመድ ሺዴ በበኩላቸው የአቶ ታደሰን ሥጋት እንደሚገነዘቡ፣ ሆኖም መንግሥት ከአሜሪካው ኩባንያ ጋር ገና በድርድር ላይ መሆኑን፣ በአገሪቱ ላይ የሚያስከትለው አሉታዊ ተፅዕኖም እንደሚገመገም ተስፋ ሰጥተዋል፡፡ መንግሥት በነዳጅ ማስተላለፊያ ግንባታ ላይ እንደማይሳተፍ፣ ይልቁንም የአሜሪካው ኩባንያ ከመንግሥት ጋር በአጋርነት የሚገነባው መሆኑን አቶ አህመድ ገልጸዋል፡፡ ይዘረጋል የተባለው የነዳጅ ማስተላለፊያ ከጂቡቲ ተነስቶ ወደ አዋሽ እስከ 550 ኪሎ ሜትር እንዲዘረጋ መታሰቡን ያብራሩት አቶ አህመድ ፕሮጀክቱ ከኢኮኖሚ፣ ከአካባቢና ከማኅበራዊ ጉዳዮች አኳያ ብዙ ጥናትና ድርድር የሚደረግበት በመሆኑ ፋይዳው ተፈትሾ መረጋገጥ እንደሚኖርበት አስታውቀዋል፡፡ ይህም ሆኖ መንግሥት ፕሮጀክቱን በከፍተኛ ጉጉት የሚመለከተው መሆኑን አቶ አህመድ አልሸሸጉም፡፡
የአሜሪካው ብላክ ስቶን ኩባንያ ብላክ ሬይኖ በሚባለው እህት ኩባንያው በኩል የነዳጅ ማስተላፊያ መስመር ለመገንባት ድርድር ከጀመረ መቆየቱን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ የመጀመሪያውን የነዳጅ ማስተላለፊያ ግንባታ ለማካሄድ ታስቦ የነበረው በደቡብ ሱዳን በኩል እንደነበር የሪፖርተር ምንጮች ያረጋግጣሉ፡፡ ከደቡብ ሱዳን መንግሥት ጋር ሲካሄድ የነበረው ድርድር ድንገት በተፈጠረው የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ ሊደናቀፍ ችሏል፡፡ ፕሮጀክቱ በርካታ ቢሊዮን ዶላሮች የሚጠይቅ እንደነበርም ታውቋል፡፡