Sunday, September 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጉብኝት ኢትዮጵያን ተጠቃሚ ያድርግ!

የኢትዮጵያና የአሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከ112 ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ዓመታት አንድም በሥልጣን ላይ ያለ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን ጎብኝቶ አያውቅም፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ሪቻርድ ኒክሰን ኢትዮጵያን ሲጎበኙ በወቅቱ ምክትል ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ቢል ክሊንተን፣ ጆርጅ ቡሽና ጂሚ ካርተር ኢትዮጵያ የመጡት ከሥልጣናቸው ከወረዱ በኋላ ነው፡፡ በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ ኢትዮጵያን በይፋ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚጎበኙት፣ ከሥልጣናቸው በቅርቡ የሚሰናበቱት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ናቸው፡፡ በሥልጣን ላይ ያለ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ጊዜ ለመጎብኘት የሚያነሳሱት በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም፣ አገሪቱ እያሳየችው ያለው ለውጥና በአፍሪካም ሆነ በዓለም ደረጃ ያላት ተሰሚነት ትልቅ ድርሻ አላቸው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ከፍታዋን በመጨመሯ ከዚህ ጉብኝት ተጠቃሚ መሆን አለባት፡፡

በኢትዮጵያና በአሜሪካ መካከል የነበረው ግንኙነት በአመዛኙ ዕርዳታ በመቀበልና በመስጠት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የአፄ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓት ተወግዶ የደርግ መንግሥት ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በጣም የቀዘቀዘ ነበር፡፡ በንጉሡ ዘመን ኢትዮጵያና አሜሪካ ግንኙነታቸው ጥሩ ነበር ቢባልም፣ ኢትዮጵያ የአሜሪካ ጥገኛ ነበረች፡፡ በደርግ ዘመን ደግሞ አሜሪካ ከመንግሥት ጋር የነበራት ግንኙነት የተበላሸ ሲሆን፣ በድርቅና በጦርነት ምክንያት ችግር ለሚያጋጥማቸው ወገኖች ሰብዓዊ ዕርዳታ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ዕርዳታ መቀበልና መስጠት የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ዋና መገለጫ ነበር፡፡ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ ገጽታ እየተለወጠ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ በኢኮኖሚው መስክ እያስመዘገበችው ያለው ዕድገት፣ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለዓመታት የነበረውን የደፈረሰ ሰላም በማረጋጋትና ሽብርተኝነትን ለመከላከል ጠንካራ ኃይል ሆና በመገኘቷ ለአሜሪካ በጣም አስፈላጊ አገር ሆናለች፡፡ የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት በትብብርና በመጠቃቀም መርህ ላይ እንዲመሠረት አሁን ያለው ወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ ሁነኛ ማረጋገጫ ነው፡፡ በሥልጣን ላይ ያሉት የፕሬዚዳንት ኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝትም ይህንን መሠረት ያደረገ መሆኑን በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ታዋቂ የዓለም የፖለቲካ ተንታኞችም ተግባብተውበታል፡፡

ኢትዮጵያና አሜሪካ በአሁኑ ጊዜ ያላቸው ግንኙነት በአፍሪካ ቀንድ በተለይም ሶማሊያ ውስጥ የመሸገውን አልሸባብ መነሻ በማድረግ በሽብርተኝነት ላይ ብቻ ያተኮረ ትብብር እንዳላቸው ይነገራል፡፡ በተለይ አሜሪካ ከዚህ ቀደም ቻይና በኢትዮጵያ እንዳደረገችው በቀጥታ ኢንቨስትመንት አለመሳተፏ ይወሳል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያና የሌሎች የአፍሪካ አገሮች ከኮታና ከቀረጥ ነፃ በሆነው ‘የአፍሪካን ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት’ (AGOA) በሺዎች የሚቆጠሩ ምርቶችን ወደ አገሯ በማስገባት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ታዋቂ ኩባንያዎቿ በቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲሳተፉ ጥረት እያደረገች መሆኗ ይታወቃል፡፡ ኢትዮጵያ ምንም እንኳ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ተጠቃሚነቷ በጣም ውስን የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን ይህንን ዕድል በሚገባ በመጠቀም በቁርጠኝነት መነሳት አለባት፡፡ በተለይ ይህ ጉብኝት የኢትዮጵያ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ መሆን አለበት ሲባል፣ ከዘጠና ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት አገር የአሜሪካ ገበያ መሆን እንደምትችል ጭምር ማሳየት ያስፈልጋል፡፡

የፕሬዚዳንት ኦባማ ጉብኝነት ከሁለቱ አገሮች የፀጥታና የኢኮኖሚ ግንኙነት በተጨማሪ፣ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ላይም መሠረት መጣል አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያ ለገዛ ሕዝቧ የምትመች አገር እንድትሆን፣ በአሜሪካም ሆነ በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልድ ኢትዮጵያዊያን በነፃነት በኢንቨስትመንትም ሆነ በተለያዩ መስኮች የሚሳተፉበት፣ አሜሪካውያን ቱሪስቶች በዓለም በመወደስ ላይ ያሉትን የአገሪቱን ተፈጥሯዊ፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ መስህቦችን እንዲጎበኙ፣ ወዘተ ይህ ታሪካዊ ጉብኝት ፈር መቅደድ ይኖርበታል፡፡ ኢትዮጵያ ከፍታዋ በመጨመሩ የአሜሪካ ፕሬዚዳንትን ትኩረት መሳብ ችላለች ሲባል እየታየ ያለው ዕድገት ውስንነት ሳይኖረው መጠነ ሰፊ መሆን አለበት፡፡ ይህም የኢትዮጵያን የተጠቃሚነት ደረጃ ያሳድገዋል፡፡

ይህ ታሪካዊ ጉብኝት ከተሰማበት ጊዜ ጀምሮ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ መነጋገሪያ ነበር፡፡ የፕሬዚዳንቱን ጉብኝት ከሚቃወሙ ጀምሮ እስከሚደግፉ ድረስ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ብዙ ብለዋል፡፡ ዋናው ቁም ነገር ግን የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ማዕከል አድርጎ በከፍተኛ ደረጃ የተወሰነው የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት የቀናት ዕድሜ ሲቀሩት መታሰብ ያለበት የግለሰቦች ፍላጎት ሳይሆን የአገር ጥቅም ነው፡፡ የአገር ጥቅም ሲባል ደግሞ ከኢኮኖሚና ከፀጥታ ትብብሩ ጋር የሰብዓዊ መብት ጉዳይም ይነሳል፡፡ የሰብዓዊ መብት ጉዳይ ሁሌም የአሜሪካ አጀንዳ በመሆኑ፣ የሁለቱ አገሮች መሪዎች እንደሚነጋገሩበት ይጠበቃል፡፡ ኢትዮጵያ የተለያዩ ሐሳቦች የሚስተናገዱባት አገር እንድትሆን የምትፈልገው አሜሪካ፣ በፕሬዚዳንቷ አማካይነት በርካታ ጥያቄዎችን ማንሳቷ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያ ሉዓላዊት አገር እንደመሆኗ መጠን መንግሥት ሰብዓዊ መብትን፣ የንግግርና የመደራጀት መብትን ማክበር ያለባት ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ በመሆን ነው፡፡ በእርግጥም በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚደረጉ ግንኙነቶች ሰብዓዊ መብትንና የንግግር ነፃነትን አለማክበር ያሳፍራል፣ አንገት ያስደፋል፡፡ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር በሚደረገው ውይይትም ሆነ ምክክር ከፍ ብሎ መታየት የሚቻለው የቤት ሥራን አጠናቆ መገኘት ሲቻል ነው፡፡ መንግሥት አስሮ ክስ የመሠረተባቸውን ሰዎች ሲፈታ ፕሬዚዳንቱ ሊመጡ ሲሉ ወቀሳ ፈርቶ ያደረገው ነው ሲባል በጣም ያሳፍራል፡፡ ከምንም በላይ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሠፈሩ መብቶች ያላንዳች መሸራረፍ ሲከበሩ ያላግባብ ማሰርና መክሰስ ይቆማል፡፡ ሕግና ሥርዓትን ማስከበር የመንግሥት ተግባር ቢሆንም፣ የአገሪቱን አንገት የሚያስደፋ መሆን የለበትም፡፡ አሁንም የሰብዓዊ መብት፣ የንግግርና የመደራጀት ነፃነት በዚህ መንገድ ይታዩ፡፡ አገሪቱም ተጠቃሚ ትሁን፡፡ ሕዝቧም በነፃነት ይኑር፡፡ የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት የሁለት ሉዓላዊ አገሮች መሆኑ ግልጽ ቢሆንም፣ በዚህም መስክ ከፍ ብሎ መገኘት ጠቃሚ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ለአሜሪካ በአካባቢው ያላት ስትራቴጂካዊ ጠቃሚነት፣ የፀጥታ አጋርነት፣ የወደፊት ገበያነትና የመሳሰሉት ጥቅሞች ትኩረት ሲደረግበት፣ ኢትዮጵያም ትርፏን በዚህ ሁኔታ ማስላት ይኖርባታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ሰላማዊና የተረጋጋች ሆና መቀጠል አለባት፡፡ ሰላሟ በአስተማማኝነት የሚቀጥለው ደግሞ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ሲከበሩ፣ የመደራጀት መብት ተረጋግጦ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሲሰፋ፣ ዜጎች ከአገሪቱ ሀብት እኩል ተጠቃሚነታቸው ሲረጋገጥ፣ የሕግ የበላይነት ሲከበር፣ መንግሥት የዜጎቹን ደኅንነት ተጨንቆና ተጠቦ ሲጠብቅና የመሳሰሉት ተግባራዊ ሲደረጉ ነው፡፡ ዘላቂው የአገሪቱ ሰላም፣ ደኅንነትና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እነዚህን ወሳኝ ጉዳዮች ማዕከል ሲያደርግ በዓለም ፊት ያኮራል፡፡ ግርማ ሞገስ ያጎናፅፋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ሲመጡም ደኅንነታቸው፣ ክብራቸውና ምቾታቸው ተጠብቆ መስተንግዶ ሲደረግላቸውና በሁሉም መስክ የምታኮራ አገር መሆኗን ሲረዱ የኢትዮጵያ ጠቃሚነት ጎላ ብሎ ይታያል፡፡ የኢትዮጵያም ተጠቃሚነት የበለጠ ከፍ እንዲል ይደረጋል!    

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...