Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅማነው ተጠያቂ?

ማነው ተጠያቂ?

ቀን:

አምቦሳ ጥጃ ከጋጣ ወይም ከበረት ወደ ሜዳ ባንድ ጊዜ አይለቀቅም፡፡ ሜዳ መስሎት ገደል ገብቶ ተሰባብሮ ይሞታልና ነው፡፡ ሕፃናት ስለሚሰሙና ስለሚያዩ ብቻ እሳት ዳር አይለቀቁም፤ ነበልባሉ እንደሚያቃጥል ለመገንዘብ የበሰለ ወይም የማስተዋል አዕምሮ ላይ አልደረሱምና፡፡ በራሱ ሊደርስበት የማይወደውን ነገር ሁሉ በሌላውም ላይ እንዳይደርስ ማሰብ፤ የኔ መብት ነው የሚለውን የሌላውም መብት መሆኑን መገንዘብ ሲቻል ነው፤ መብቴን አስከብራለሁ ለማለት የሚቻለው፡፡ ግዴታን ሳያውቁ መብትን መጠበቅ ባንድ እጅ እንደማጨብጨብ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን፡፡ ዋናው ዛሬ የተነሳቡበት ጉዳይ የኢትዮጵያ ወይም የአፍሪካ ዋና ከተማ እያልን በምንኮራባት በውድ ከተማችንም ሆነ በጠቅላላው አገራችን ላይ በሚታየው ፈር የለቀቀ አነዳድ በፎቶግራፍ በተደገፈ ማስረጃ ጭምር የሚወድመውን ንብረትና የሚጠፋውን ሕይወት በመመልከት የዜግነት ግዴታዬን ለመወጣት ነው፡፡ መጀመሪያ ስለትራፊክ አደጋ፣ ጭንቅንቅና የንብረት መውደም በየዕለቱ ሲነገር ይሰማል፡፡ ይህም ማለት ለወሬ ያህል ካልሆነ በቀር ፍሬ ሲሰጥ አይታይም፡፡ ለምን? ለአፍ ጉቦና ሰሚውን ለማስደሰት ብሎም ያውቃሉ ለመባል ካልሆነ በቀር ፋይዳ የሚሰጥ ሆኖ አልተገኘም፡፡ ለዚህ ጉዳይ ማነው ተጠያቂ? ኅብረተሰቡ፣ የመንጃ ፈቃድ ሰጪው ወይስ የትራፊክ ሕግ አስከባሪው? ዘንድሮ (2007 ዓ.ም.) በአዲስ አበባና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች ስዘዋወር የተመለከትኳቸው የትራፊክ አደጋዎችን በፎቶግራፍ ይዤያቸዋለሁ፡፡ ፎቶዎቹ የተነሱበት አካባቢ እንደ ቅደም ተከተላቸው በሞጆና ደብረ ዘይት መካከል፣ ሱሉልታ፣ ቃሊቲ፣ ጎጃም መውጫ (ድል በር)፣ መተሐራና ቃሊቲ ነው፡፡ (በአሰፋ አደፍርስ)

*******

የሥጋ ገበታ

ቀርቦልኝ ገበታ

ቁርጥ በሚጥሚጣ

ክትፎ ተከታትፎ፣ አሮስቶና ቋንጣ፡-

አይ! በሬ ብኩኑ፡-

ትላንት እንዳልነበር –  እንዲህ መኳኳኑ

ቁመናው ሊረግፍ – መኖር መኳተኑ፣

አኘኩት፣ ፈጨሁት – በዝንጠላ ስቀት

በመላመጥ ሕመም – በሽርከታ ጭንቀት፡፡

      ያን መሳይ ዓይነ – ግብ፡-

      ደሙ ካፈር ሊውል – በሰይፍ ግብግብ

      ቆዳው ለመርገጫ – ሥጋውም ለምግብ

      ወደ’ዚያው እኮ ነው – የኛም የመኖር ግብ፡፡

ካሳሁን ወልደ ጊዮርጊስ ‹‹ማርገጃ›› (2006)

*******

አደንዛዥ ዕፅ በትዊተር

በፍሎሪዳ ነዋሪ የሆነች ሴት በትዊተር ገጿ ላይ ‹‹ዕፅ አቅርቡልኝ፣ ዋጋውን እከፍላለሁ፤›› ስትል ታሰፍራለች፡፡

አደንዛዥ ዕፅ ለመግዛት እፈልጋለሁ የሚለውን መልዕክት ተከትሎ የፍሎሪዳ ፖሊስ አፋጣኝ መልስ ይሰጣል፡፡ አደንዛዥ ዕፁ አንዲደርሳትም የምትኖርበትን ሥፍራ እንድታሳውቅ ትጠየቃለች፡፡ እሷም ‹‹መልዕክቴን ተከታተል፣ መኖሪያዬን አሳውቅሃለሁ፤›› የሚል መልዕክት ትተዋለች፡፡

ዩፒአይ እንደዘገበው፣ ሮዝ በሚል መጠሪያ በትዊተር መልዕክት ያስቀመጠችው ሴት ድርጊቱን የፈጸመችው በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ዝናን ለማትረፍ ብቻ ብላ ነበር፡፡ ሮዝ በሚል የተጠቀመችው ስምም የእውነት ስሟ አልነበረም፡፡ ፖሊስ የሴትዮዋን ማንነት አልደረሰበትም፡፡ እሷም ለዲፕ ኮምሽን ብሎግ ‹‹ምንም ቢመጣ አልጸጸትም፡፡ ትዊት በማድረጌ ለአምስት ደቂቃ የዘለቀ የኢንተርኔት ዝናን አትርፌያለሁ፤›› ብላለች፡፡

********

የፓንቴ ቬክሆ ድልድይ በጣልያን

የፓንቴ ቬክሆ ድልድይ በፍሎረንስ ከተማ የሚገኝና አርኖ የተባለውን ወንዝ የሚያቋርጥ ነው፡፡ የድልድዩ ግንባታ ሥረ መሠረት ከሮማ ገናናነት ዘመን ይመዘዛል፡፡ ጥንታዊው የፖንቴ ቬክሆ ድልድይ እ.ኤ.አ. በ1333 በጎርፍ ቢወድምም በ1345 ዳግም ተገንብቶ አገልግሎት ይሰጥ ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. 1565 ጆርጂዮ ቫዛር ተተባለ መሐንዲስ ደረጃውን እንዲያሳድገው ኃላፊነት ተሰጥቶት በድልድዩ አናት ላይ ሌላ አዲስ ድልድይ እንዲገነባበት አድርጓል፡፡ ይህንን ድልድይ ለየት ከሚያርጉት ነገሮች መካከል በጥንታዊው (በታችኛው) አካሉ ላይ በርከት ያሉ ገፀ በረከት መሸጫ ሱቆች መኖራቸውና አሁንም ለጎብኚዎች አገልግሎት መስጠታቸው ነው፡፡

  • ‹‹ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ›› (2006)
  •  

አርባ ልጆች – ‹‹የግርማዊ ንጉሥ ተፈሪ የሙዚቃ ነፊዎች››

ከአንድ መቶ ዓመት በፊት የኦትማን ቱርክ መንግሥት ሕዳጣን (ማይኖሪቲ) አርመናውያንን በታሪካዊው መኖሪያ መሬታቸው በጅምላ የፈጀበትን ዕለት አርመናውያን እያሰቡ ነው፡፡ ከሚያዝያ 1907 ዓ.ም. ጀምሮ በጅምላ በግፍ የተገደሉት (ጄኖሳይድ የተፈጸመባቸው) ከ800,000 አስከ 1.5 ሚሊዮን እንደሚደርሱ በ‹‹አርሜንያን ጄኖሳይድ›› ድረ ገጽ ተመልክቷል፡፡ በዘመኑ ከጅምላ ፍጅቱ ተርፈውና አምልጠው በኢየሩሳሌም በእጓለ ማውታን (የሙታን ልጆች) ከተጠለሉት መካከል አርባ ልጆችን በማደጎ ልጅነት በ1916 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ያመጧቸው ሐምሌ 16 ቀን 2007 ዓ.ም. 123ኛ ልደታቸው የታሰበው የያኔው አልጋ ወራሽ ግርማዊ ንጉሥ ተፈሪ መኰንን (በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ) ነበሩ፡፡ እነዚህ አርባ ልጆች የመጀመርያው የኢትዮጵያ ዘውድ ኦርኬስትራ በመሆን የሙዚቃ መሣርያ ሲጫወቱ መጠርያቸው ‹‹የግርማዊ ንጉሥ ተፈሪ የሙዚቃ ነፊዎች ልጆች›› (የተፈሪ ማርሽ) ነበር፡፡ በቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ የተደረሰውና በናልባዲያን የተቀመረውን ከ1923 እስከ 1967 ዓ.ም.  በአገልግሎት ላይ የነበረው ‹‹ኢትዮጵያ ሆይ ደስ ይበልሽ›› ብሔራዊ መዝሙር በማርሽ ባንድ ለመጀመርያ ጊዜ የተጫወቱት በፎቶግራፉ የሚታዩት አርባ ልጆች ናቸው፡፡ (ሔኖክ መደብር)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...