Saturday, June 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ያስገኘው ፋይዳ ምንድነው?

በሒሩት ደበበ

ኢትዮጵያዊያን እንደ ልማድ ሆኖብን ደግ ነገርን ከማውሳት ይልቅ መጥፎንና ደካማውን መጠቃቀስ ይቀናናል፡፡ ከድልና ከብሥራት ወሬ ይልቅ “የመክሸፍ ዜና” ይበልጥ ድንኳኑን ሲጥል የምንመለከተውም ለዚህ ነው፡፡ በግሌ ያልተሠራንና የሌለን ታሪክ በሐሰት እየሞላን እንቆልል፣ እናወድስ የሚል ፍላጎት የለኝም፡፡ መሬት ላይ ካለው እውነታ ጋር የሚጋጭ መቀባጠርም ትዝብት ላይ እንደሚጥል አውቃለሁ፡፡

ዛሬ ላወድሰውና ልመሰክርለት የተነሳሁት ጉዳይ ግን እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለም አድናቆት የቸረውን ጉዳይ ነው፡፡ በግሌ ያነጋገርኳቸው በተለያየ የፋይናንስና የውጭ ግንኙነት ዲፕሎማሲ ሥራ ላይ የተሰማሩ የውጭ አገር ዜጎች በአንደበታቸው ያረጋጡትም ነው፡፡

አገራችን ከሐምሌ 6 እስከ 9 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) አዳራሽ በአዲስ አበባ እንዲካሄድ ሁኔታዎችን ያመቻቸው ዓለም አቀፍ የፋይናንስና ልማት ጉባዔ በወዲያኛው ሳምንት በስኬት ተጠናቋል፡፡ በስብሰባው ላይ የተገኙ ተሳታፊዎች (በአብዛኛው የአገሮች የመሪዎች ተወካዮች፣ ሚኒስትሮች፣ የፋይናንስና ገቢዎች ሴክተር መሪዎችና ከፍተኛ ሙያተኞች ናቸው) ታዛቢዎች፣ የአገሮች መሪዎችና የክብር እንግዶች እንዲሁም የአኅጉራትና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኃላፊዎች ሲሆኑ፣ የተለያዩ ዕውቅና ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ወኪሎችም ተሳትፈዋል፡፡ ከአምስት ሺሕ እስከ ሰባት ሺሕ እንግዶች የጠበቀችው አዲስ አበባ የየአገሮቹን ኮር ዲፕሎማቶች ጨምሮ አሥር ሺሕ የሚደርሱ እንግዶችን በኩራትና ፍፁም አስተማማኝ በሆነ ደኅንነት አስተናግዳለች፡፡

ከእንግዶቹ መካከል የንግዱ ማኅበረሰብ መሪዎች፣ ታዋቂ ባለሀብቶችና የበርካታ ኩባንያ ወኪሎችም ተገኝተዋል፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች መሪዎችና የበጎ አድራጎትና የድኅነት ቅነሳ ስትራቴጂ ዓለም አቀፍ ተቋማት ወኪሎችም ነበሩ፡፡   

ይህ ሁሉ የውጭ ዜጋ ከአፍሪካ፣ ከላቲን አሜሪካና ከእስያ ከሚገኙ ታዳጊ አገሮች ብቻ አልነበረም የተገኘው፡፡ ይልቁንም ከበለፀጉት አውሮፓና አሜሪካ አገሮችም የተገኙት ቁጥራቸው ከፍተኛ ነበር፡፡

የዚህ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ውሳኔ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ውሳኔ ቁጥር 68/204ና ውሳኔ ቁጥር 68/279 መሠረት ሲፀድቅ፣ ኢትዮጵያ የተመረጠችበት ምክንያት አለ፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፣ “ዋነኛው የአገራችን መመረጥ መንስዔ ፈጣኑ ዕድገታችን፣ በምዕተ ዓመቱ ግቦች ላይ ያስመዘግብናቸው ስኬቶችና ሕዝብና መንግሥት የጀመሯቸው ሥራዎች ናቸው፤” ይላሉ፡፡

በደቡብ አፍሪካዊው የመገናኛ ብዙኃን ወኪል ጀምስ በርናርድ እምነት ደግሞ፣ የኢትዮጵያ መመረጥ ዋነኛ ምክንያት ሌላ ነው፡፡ “ኢትዮጵያ የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሕፈት ቤት ማዕከል በመሆኗ ነው” ይላል፡፡ እርግጥ በርናርድም ቢሆን በኢትዮጵያ ገጽታ መቀየርና እያደገች መሆን ላይ ጥርጣሬ የለውም፡፡ ይሁንና በአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ፣ ጋና፣ ሞዛምቢክ፣ ታንዛኒያ፣ ቦትስዋና፣ ሩዋንዳ፣ ወዘተ እያሳዩ የመጡት ዕድገትም ቀላል አይደለም ባይ ነው፡፡ “ኢትዮጵያ በሰላምና ደኅንነት (ከፀረ ሽብር ትግል አኳያ) ኮሽ የሚልባት አገር አትመስለኝም፤” የሚለው ገለጻውም ትኩረቴን ስቦታል፡፡

የአዲስ አበባው ታሪካዊው ጉባዔ ከዋና ዋና መድረኮች ባሻገር በተለያዩ የጎንዮሽ ውይይቶች የአገሮች መሪዎችና ሚኒስትሮች ምክክሮች የተካሄዱ ሲሆን፣ በድምሩ እስከ 180 የሚደርሱ ስብሰባዎችን ያቀፈ ነበር፡፡ በውይይቶቹ ማጠናቀቂያ መግባባት ላይ ለመድረስ በተካሄደ ጥረትም እስከ ሌሊቱ ስድስት ሰዓት መምከር ግድ እንደነበር፣ የጉባዔው አስተባባሪ ኮሚቴ አባልና የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር አቶ ሱፊያን አህመድ በማጠቃለያው ላይ ሲገልጹ ተደምጧል፡፡

እዚህ ላይ ለአንባቢያን የስብሰባው ዋነኛ ትኩረት ምን ላይ እንደነበር ማውሳት ተገቢ ይመስለኛል፡፡ አንደኛው በድኅነት ቅነሳና በዘላቂ ልማት ጉዳይ ላይ በሜክሲኮ ሞንቴሮ ስምምነትና በኳታር ዶሃ ውሳኔ መሠረት፣ በአፈጻጸም ረገድ የታዩ ዕርምጃዎችን መገምገም ነው፡፡ በነገራችን ላይ ለሦስተኛ ጊዜ በተካሄደው በዚህ ጉባዔ የእኛዋ አዲስ አበባ ከአፍሪካ ቀዳሚ አስተናጋጅ አገር መሆኗ  ብቻ ሳይሆን፣ የስምምነት ጭብጦቹ ጥንካሬና ተደራዳሪዎች ለተግባር ቅርበት ባለው ውሳኔ ላይ ለመድረስ ያሳዩት መቀራረብ ከሁለቱ ቀዳሚዎቹም እጅግ የተሻለ የሚባል ነበር፡፡

ዓለም አቀፍ የልማት ትብብርን ለማሳደግ ከሚደረገው ዘርፈ ብዙ ትኩረት አንፃር የታዩ አዲስና ድንገት ብቅ ያሉ ጉዳዮችን መገምገም ነው፡፡ በተለይ አሁን እየተፈጠረ ያለውን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር ማየት፣ የልማት ፋይናንስ ሁሉንም መስተጋብር (የብድር፣ የዕርዳታ፣ የአገሮች የውስጥ ገቢ አቅም፣ የመልካም አስተዳደርና የፀረ ሙስና ሥራዎችን) ማየት፣ እንዲሁም እ.ኤ.አ. ከ2015 በኋላ የተመድ የልማት አጀንዳን በመደገፍ አስፈላጊነት ላይ መነጋገርና ውሳኔ ማሳለፍ ነበር፡፡ የፋይናንስ ልማት አፈጻጸም የመከታተያ ሒደትን ማጠናከርና ማበረታታት ላይም በተለይ ታዳጊው ዓለም ራሱን ከፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም መፈላቀቅ ሳጥን አውጥቶ ለሕዝቦች ጥቅምና ዘላቂ ልማት ምን መሠራት እንዳለበት ጥልቅ ምክክር ተካሂዷል (ምንም እንኳን እዚህ ነጥብ ላይ ልዩነቶች ጎልተው መስተዋላቸው ባይቀርም)፡፡

ጉባዔው ከገጽታ ግንባታ አኳያ

የአንድ አገር ገጽታ ሊገነባ የሚችለው ከውስጥም ከውጭም በሚፈጠር እውነተኛ ዕድገትና መሻሻል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ የመቀየር አቅጣጫ (በተለይ በኢኮኖሚና በልማት መስክ) እየታየ የመጣው በተለይ ባለፉት 13 ዓመታት ነው፡፡ (ከሻዕቢያ ወረራና ከኢሕአዴግ ተሃድሶ ወዲህ) ለዚህ ተከታታይና ባለሁለት አኃዝ ዕድገት የመንግሥት ፖሊሲና ስትራቴጂ፣ እንዲሁም የማስፈጸም ቁርጠኝነት ከነጉድለቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ኢኮኖሚና በመሠረተ ልማት ግንባታው ሕዝቡም ለሥራ መነሳሳትና ወደ ልማት ገብቷል፡፡

ከዚህ አንፃር አንዳንዴ “ለፕሮፓጋንዳ ፍጆታ” እየመሰለ እንጂ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት በነፍስ ወከፍ ገቢ፣ በዜጎች የኑሮ መሻሻልም እንበለው፣ ከዕርዳታና ከልመና መውጣት ጋር ተያይዞ መነገሩ ገጽታችን ቀይሮታል፡፡ መነገሩ ብቻ ሳይሆን በተግባርም ልማቱ በሕዝብ ተጠቃሚነት ላይ አሻራውን እያሳረፈ በመምጣቱ ኢትዮጵያ የምትለወጥ አገር መሆኗን አሳይታለች፡፡ ዕድገቱ በዓለም አቀፍ ምዘና ሲታይ ዋጋ እያገኘ የመጣው በአንድ በኩል የምዕተ ዓመቱ ግብ ተነድፎ ወደ ተግባር ከገባ በኋላ፣ ኢትዮጵያ ያስመዘገበችው ተከታታይ ዕድገት “ነጋዴና ገበያ” ዓይነት ሥምሪትን ፈጥሮላታል፡፡ በሌላ በኩል ግሎባላይዜሽን አንድ መንደር ያደረጋት ዓለም በገበያና በቴክኖሎጂ ሽግግር የፈጠረችውን ምቹ ሁኔታ እንደ ልብ ለመጠቀም ተችሏል፡፡

በዚህ ወሳኝ ወቅት ኢትዮጵያ ይህን የ198 አገሮች ጥቅም የተመለከተ በፋይናንስና በልማት መርሐ ግብር የዓለምን ውሳኔ ሰጪዎች አሰባስባ እንዲመክሩ ማድረጓ፣ በገጽታ ግንባታ ረገድ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስኩት የሚዲያ አማካሪውን ጀምስ በርናርድ፣ “ኮንረፈረንሱ መካሄድ ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ዓለም የኢትዮጵያን ወቅታዊ ምሥል በድጋሚ እንዲመለከት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል፤” ይላል፡፡ በግሉ አዲስ አበባ ሲመጣ ለሦስተኛ ጊዜ ቢሆንም የከተማዋ የ“ኮንስትራክሽን አብዮት” አስደናቂ ግርምትን ፈጥሮበታል፡፡ “በየቦታው ይቆፈራል፣ ይገነባል፡፡ በተለይ እንደ ባቡር መስመር ዝርጋታ ያለው ውድ የመሠረተ ልማት ግንባታ በአጭር ጊዜ ዕውን ሲሆን ማየት ትልቅ የመነቃቃት ውጤት ነው፤” ብሏል፡፡

በግሌ የኮራሁበት መልካም ነገር “ኢትዮጵያዊያን እንግዳ ተቀባይ ናቸው” የሚለውን አገላለጽ ዕውን ለማድረግ የሚሠሩ ሰዎችን በማየቴ ነው፡፡ በመሠረቱ ዓለም አቀፍ እንግዶች ጎጃም ዓባይ ዳር፣ ትግራይ ተራራ ላይ ወይም አፋር በረሃ የሚገኘውን አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች አግኝተው ከጎጇቸው ገብተው ሊስተናገዱ አይችሉም፡፡ “እንግዳ ተቀባይ ሕዝብ” ሲሉም ከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል አንፃር ያለውን የእጁን አካፋይነት ቢያንስ የቱሪስቶችን ያህል አይረዱም፡፡

ዞሮ ዞሮ እንግዳ ተቀባይነታችን ሊንፀባረቅ የሚችለው በአውሮፕላኖቻችን ውስጥ ካሉት “ሆስቶሶቻችን” (አስተናጋጆች) ጀምሮ ነው፡፡ በአውሮፕላን ማረፊያ ያሉ የፍተሻና የመስተንግዶ ሠራተኞች፣ የአገራችን የፀጥታና የደኅንነት ባለሙያዎች ከአቀራረባቸውና ከትህትናቸው ይጀምራል፡፡ አልፎም ኢሲኤን ጨምሮ በየመሰብሰቢያ አዳራሹ ያሉ ሠራተኞች፣ አሽከርካሪዎች (መቼም እንግዶች በአውሮፕላን መኪና ጭነው አይመጡ የሚንቀሳቀሱት በእኛው ተሽከርካሪዎችና ሾፌሮች እንጂ)፣ እንዲሁም የሆቴል መስተንግዶ ሠራተኞችና ቆነጃጅቶቻችን ናቸው፡፡

ብዙዎቹ ወደ አገራችን የመጡ እንግዶች ከዚህ ቀደም እንደ አጋጠሙኝ ቱሪስቶችና ፖለቲከኞች ሁሉ በኢትዮጵያዊያን ቆነጃጅት ሴቶች ይደመማሉ፡፡ በአየር መንገዳችን፣ በአትሌቶቻችን፣ በባንዲራችን ቀለማት ለሌላው አፍሪካ ባንዲራ መነሻ በመሆኑ እንደሚያውቁን ያስረዳሉ፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህም የመከላከያ ኃይላችን በሰላም ማስከበር በሚያደርገው ጥረትና ሽብርተኝነት በቀላሉ “የሚበረግደን” እንዳልሆነ መነገር ተጀምሯል፡፡

የገጽታ ግንባታ ከልማትና ከሰላም ጉዳይ ጋር ብቻ ሳይሆን ከዴሞክራሲም ጋር ስለሚገናኝ፣ በዚህ ረገድ የጋዜጠኞች መታሰር (አንዳንዴ በድንገት መፈታት)፣ የፖለቲካ  ፓርቲዎች አለመጠናከርና ፓርላማው በአውራ ፓርቲ ብቻ መያዝ፣ እንዲሁም የፕሬሱና የመገናኛ ብዙኃንን መዳከም የተረዱ ወደነ ቻይና ተርታ እንድንወርድ ያደርጉናል፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ ልማት እንጂ ዲሞክራሲ የሌለባት ግራ ዘመም ርዕዮተ አራማጅ ነች ብለው ሊነግሩኝ ያማራቸው እንግዶች ነበሩ፡፡ ስለዚህ የገጽታ ግንባታ ምልዑነትንም ሆነ የተጀመረውን አገር አቀፍ ሁለንተናዊ መሻሻል አጠናክሮ ለማስቀጠል፣ ዲሞክራሲና መልካም አስተዳደር ላይ ሥራ ማዋል እንደሚያስፈልግ መዘንጋት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ በተለይ በሰብዓዊ መብት አከባበር ረገድ ይህ መንግሥት በእጅጉ እየተኮነነ ስለሆነ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በኢኮኖሚ ዕድገትና በመሠረተ ልማት ግንባታ ብቻ የአገር ገጽታ ይለወጣል የሚሉ ካሉ ስህተተኛ ናቸው፡፡

የኮንፈረንሱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ

የኮንፈረንስ ቱሪዝም ዋነኛው የአገልግሎት ዘርፍ ስኬትና የአገሮች ጥቅም እየሆነ ከመጣ ሰነባብቷል፡፡ ከዚህ አንፃር አፍሪካዊቷ አዲስ አበባ እንደ ኒውዮርክ፣ ዶሃም ሆነ ሌሎች የመሰብሰቢያ ማዕከላት ከፍተኛ የተጠቃሚነት ዕድል አላት፡፡ በሦስተኛው ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ በአማካይ ከስምንት እስከ አሥር ሺሕ የውጭ አገር እንግዶች ወደ አገራችን ገብተዋል፡፡ ከሦስት እስከ ስድስት ቀናት ለሚሆን ጊዜም በአዲስ አበባና ዙትዋ ታድመዋል፡፡ እነዚህ እንግዶች ለሆቴል፣ ለመስተንግዶ፣ ለትራንስፖርት፣ ለጉብኝትና ለሌሎች ዕለታዊ ወጪ (የተለያዩ ዕቃዎችን ግዥን ጨምሮ) የሚያወጡት ገንዘብ በዘርፉ ሙያተኞች ግርድፍ ግምት ሲሰላ ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው፡፡ በሙያተኞች ግምት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አገሮች ሳይገኙ አይቀርም፡፡

በእርግጥ እንዲህ ዓይነት መስተንግዶ የኢትዮጵያ መንግሥትንም ቢሆን ወጪ የሚያስወጣ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ነገር ግን ጉባዔው ከሚገኝበት ፖለቲካዊና ኢኮኖሚ ፋይዳ አንፃር የሚኖረው ወጪ የሚጋነን ሊሆን አይችልም፡፡ ሰሞኑን በአዲስ አበባ በተካሄደው ጉባዔ የአንድ ወር ገበያቸውን በአራት ቀናት ውስጥ እንዳስገቡ ከሚናገሩ ባለሆቴሎች አንፃር ግን ያለጥርጥር ከፍተኛ የሆነ የገቢ ጥቅም አስገኝቷል ማለት ስህተት ሊሆን አይችልም፡፡

ሌላው የጉባዔው ኢኮኖሚያዊ ፋይዳና ከፍ ያለው ጥቅም ግን እንደ አገር መንግሥት ለነደፈው የድህነት ቅነሳም ሆነ ዘላቂ ልማት የኢትዮጵያ ተሞክሮዎች ተደጋግመው መወሳታቸው ነው፡፡ “ይህ ሁኔታ ለአበዳሪዎች፣ ለዕርዳታ ሰጪዎችም ሆነ ከኢትዮጵያ ጋር አጋርነት መፍጠር ለሚሹ ወገኖች መለሳለስና መቀራረብ ትልቅ ጥቅም ሊሰጥ የሚችል ነው፤” ይላሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር የሆኑ አንድ አስተያየት ሰጪ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጉባዔው ሊቀመንበርነታቸው ባደረጉት ንግግር የኢትዮጵያን የዕድገት ተሞክሮ ለተሳታፊዎች ለመግለጽ ችለዋል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በጎንዮሽ ምክክሮች በስፋት ተሞክሮዎችን ለማስገንዘብ ችለዋል፡፡ በተለይ ከአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ግንባታ አንፃር (በኃይል ማመንጫ፣ በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ፣ በኤሌክትሪክ የሚሠራ የባቡር መስመር ዝርጋታ) ትልቅ አብነት መሆን ችላለች፡፡

በእናቶችና ሕፃናት ሞት፣ በትምህርት ሽፋንና ተደራሽነት፣ በፈጣን የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ያስመዘገበችውን ውጤት በብድርና በዕርዳታ ባለፉት ዓመታት ካገኘችው ሀብት አንፃር የመዘኑትም አልታጡም፡፡ በዚህም አንፃራዊ የሀብት አጠቃቀሞችና የአገር ውስጥ ገቢ አሰባሰብ መሻሻል እንዳለ ተመዝግቧል፡፡ የእነዚህና ሌሎች በጎ ገጽታዎች መጠናከር ደግሞ ተጨማሪ የፋይናንስ ዕድል እንደሚፈጥር መገመት አያዳግትም፡፡

በአጠቃላይ ዓለም አቀፍ ፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ከተገመተው በላይ እንግዶች የተሳተፉበት፣ እምብዛም የትራፊክ መጨናነቅ ያልታየበት፣ ምንም ዓይነት የፀጥታም ሆነ የሰላም ሥጋታ ያልተስተዋለባት፣ ከሁሉም በላይ የተነደፉትን ግቦች ለማሳካት የላቀ ደረጃ ላይ የደረሰ ምክክር ሆኖ አልፏል፡፡ ይህ ጉባዔ በእርግጥም የአገራችንን ገጽታ አንድ ዕርምጃ ወደፊት እንደሚወስድ ይታመናል፡፡ ለዚህም መንግሥት (የውጭ ጉዳይ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትሮችና የሚመለከታቸው ኮሚቴዎች) ራሱ ሕዝቡ፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት መመስገን አለባቸው፡፡ ሌት ከቀን ዝናብና ፀሐይ ሳይሉ በሚያኮራ ቅንጅት የተንቀሳቀሰው የፖሊስና የፀጥታ ኃይልም ሊከበርና ሊወደስ የግድ ነው፡፡

በቀጣይም ቢሆን እንግዳ አክባሪነታችንና ለቱሪዝም ኮንፈረንስ ያለን አመቺነት እንዲሻሻል መትጋት ይኖርብናል፡፡ በተለይ ከፅዳትና ከመንገድ አጠቃቀም ጋር ያሉ ችግሮችን በመፍታት፣ የአገርን ገጽታ በትክክል ለመሸጥ በማስተዋወቅ፣ ደኅንነታችንን ከዚህም በላይ ሁሌም ነቅቶ በመጠበቅ ተጨማሪ ትጋት ይጠብቀናል፡፡ ዓለም በአንድ መንደር ልጅነት እየተሰባሰበ ለአንድ ጉዳይ ሲመክር እኛ በጎጥና በመንደር አልፎም በብሔርና በቋንቋ መገፋፋቱን ማክሰም አለብን፡፡ ይልቅ እንደ አገር በማንነቱ የሚኮራ ትጉ ሕዝብ መሆን ነው መፍትሔው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles