Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊስብሰባና የመዲናችን መንገዶች

ስብሰባና የመዲናችን መንገዶች

ቀን:

ዋናው ቦሌ መንገድ ተዘግቷል፡፡ እዚህም እዚያም በርከት ያሉ ሰዎች ሰብሰብ ብለው ቆመዋል፡፡ በመንገዱ ላይ የተወሰነ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ትራፊክና ፌደራል ፖሊሶች ናቸው፡፡ ቦሌ ጫፍ ከዋናው መንገድ በኖክ ነዳጅ ማደያ በኩል በሚወስደው አቋራጭ ላይ ባለበት እንዲረጋጋ የተደረገው ሰው ቁጥር በዛ ያለ ነበር፡፡ ሳይፈልግና ሳያስበው አንድ ላይ ተሰብስቦ ከቆየው ሰው አንዳንዱ በየጊዜው በሚደረጉ ስብሰባዎች ምክንያት መንገድ ስለመዘጋቱ እያወራ ሲያማርር፣ ሌላው ነገሩን በመረዳት በሚመስል መልኩ በትዕግሥት ይጠባበቃል፡፡ አንድ ወጣት ‹‹በዚህ አጋጣሚ ነበር ሰላማዊ ሠልፍ መውጣት›› በማለት አጠገቡ የነበሩ ብዙዎችን አሳቀ፡፡

በተለያዩ አጋጣሚዎች መንገዶች ሲዘጉ መንገድ ላይ የሚታየው ሁኔታ ከሞላ ጐደል ይህን ሲመስል ታክሲዎች ውስጥ የሚፈጠረው ትዕይንት ደግሞ በተወሰነ መልኩ ለየት ይላል፡፡ አንዳንዱ የታክሲ ሾፌር መንገድ ሲዘጋ ማውረድ የሚፈቀድለት ቦታ ላይ የጫነውን ተሳፋሪ አውርዶ መስመሩ ክፍት እስኪሆን ሥራ ማቆምን ሲመርጥ፣
ሌላው ደግሞ አማራጭ የውስጥ ለውስጥ መስመሮችን በመጠቀም ሥራውን ይቀጥላል፡፡

መንገዶች ሲዘጉ የሚፈጠረው ሁኔታ አስቸጋሪና ለተሳፋሪ ለአሽከርካሪም የማይመች ቢሆንም ነገሩ ከአገር ፖለቲካና ኢኮኖሚ ጋር የተገናኘ በመሆኑ ሁሉም ነገሮችን መረዳትና በትዕግሥት ማሳለፍ አለበት የሚል አስተያየቱን የሰጠው የታክሲ ሾፌር አቶ በሻው ጋረደው ነው፡፡

እሱ እንደገለጸው፣ አብዛኛውን ጊዜ ትራፊክ ፖሊስና ፌደራሎች መኪኖች ያለምንም ማቆም ቀጥታ እንዲያልፉ እያዘዙ ተሳፋሪዎች እዚህ ጋር ወይም እዚያ ጋር እንውረድ በማለት ያስቸግራሉ፡፡ ለምሳሌ የቦሌ ዋናው መንገድ ሊዘጋ ሲል ተሽከርካሪዎች ሳይቆሙ እንዲያልፉ ይታዘዛሉ፡፡ ማቆም የሚቻለው ስታዲየም ላይ ብቻ ሆኖ ሳለ ተሳፋሪዎች ወሎ ሰፈር፣ ሩዋንዳ አልያም ደንበል ላይ መውረድ አለብን ይላሉ፡፡ ለመውረዱ ካሰቡበት ቦታ በጣም በመራቃቸው ግብግብ የሚገጥሙ ተሳፋሪዎች መኖራቸውን ጭምር አቶ በሻው ይናገራል፡፡ ‹‹ግማሹ ይጮሃል፣ መኪና የሚደበድብም አለ፡፡ ከእረዳቱ ጋር የሚተናነቅም ያጋጥማል›› የሚለው አቶ በሻው፣ የተሳፋሪም ሆነ የአሽከርካሪ አጠቃላይ ሁኔታውን አለመረዳት ችግር እንደሚፈጥር ያስረዳል፡፡

መንገዶች በሚዘጉበት አጋጣሚ እሱ የሚያደርገው የያዘውን ተሳፋሪ አውርዶ ሁኔታዎች ተረጋግተው መስመሩ ሙሉ ለሙሉ ክፍት እስኪሆን መጠበቅ ነው፡፡ እንደ ሌሎቹ የታክሲ አሽከርካሪዎች የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ተጠቅሞ ሥራውን መቀጠል የማይፈልገው፣ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ስለማይመቹና ከነዳጅና ከሰዓትም አንፃር አዋጭ ባለመሆኑ ነው፡፡ መንገዱ ረዥም መሆኑን ታሳቢ በማድረግ የተወሰነ ሳንቲም መጨመርም በተሳፋሪና በረዳት መካከል ጭቅጭቅ ያስነሳል፡፡ በእንደዚህ ያለው አጋጣሚ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች መሔጃም መመለሻም መንገድ ስለሚሆኑ መጨናነቅ መፈጠሩንም እንደ ችግር የሚያነሳው ነው፡፡

የመንገዶች መዘጋት በሰዎች ላይ በተለያየ መንገድ የሚፈጥረው ችግር ቢኖርም በተለይም በዓለም አቀፍ ጉባዔዎች ወይም በባለሥልጣናትና ዲፕሎማቶች ምክንያት መንገዶች ሲዘጉ ጉዳዩን ከአገር ጥቅም አንፃር ሰፋ አድርጐ ማየት እንደሚያስፈልግ አቶ በሻው ያምናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በትራፊክና በፌዴራሎች በኩል መስተካከል አለባቸው የሚላቸውን ነገሮች ያነሳል፡፡ ‹‹መንገድ ሊዘጋ ነው ተብሎ ጐማ ከጥቅም ውጭ ሆኖ በቸርኬ ሒድ ይባላል፡፡ ዝም ብሎ ሒድ ነው፡፡ ከአቅም በላይ የሆኑ ችግሮችን ያለመረዳት፣ ለመረዳትም ያለመፈለግ ሁኔታ ያለ ይመስለኛል›› ይላል፡፡ የአማራጭ መንገዶች አለመኖር፤ ያሉትም ፓርክ በሚያደርጉ መኪናዎች የተጨናነቁ መሆን እንደ ችግር የጠቀሳቸው ናቸው፡፡

አቶ በኃይሉ ሞገስ አብዛኛውን ጊዜ እግረኛ ነው፡፡ አልፎ አልፎ ግን መኪና ይይዛል፡፡ የአፍሪካ ኅብረትህም ሆነ ሌሎች ስብሰባዎች ሲኖሩ በመገናኛ ብዙኃን ስለሚነገር አሽከርካሪዎች የትኞቹ መንገዶች ዝግ እንደሚሆኑ የውቃሉ ይላል፡፡ የስብሰባዎቹ ተሳታፊዎች ሊያርፉባቸው ከሚችሉ ሆቴሎችና የስብሰባ ቦታዎች አንፃርም ዝግ ሊሆኑ የሚችሉ መንገዶችን መገመት ከባድ አይሆንም የሚል እምነት አለው፡፡ እሱ እንደ ችግር የሚያነሳው ቀደም ሲል በመገናኛ ብዙኃን ሳይነገርም ከተጠቀሱት ቦታዎች ጋር ግንኙነት ሳይኖራቸው ድንገት የሚዘጉ መንገዶች መኖርን ነው፡፡

እንደ ተሳፋሪ ረዥም ደቂቃዎችን መንገድ ላይ ወይም ታክሲ ውስጥ ማሳለፍ፣ ተጨማሪ ክፍያ መጠየቅ አስቸጋሪ ቢሆንም ይህ የሆነበትን ምክንያት በማሰብ በሚደርስበት ነገር ብዙም እንደማይማረር ይናገራል፡፡

አቶ ቢላል አንበሴ የአዲስ አበባ ታክሲ አሽከርካሪዎች ማኅበር ሰብሳቢ ነው፡፡ በከተማዋ በሚካሔዱ ትልልቅ ስብሰባዎች በግንባታ ምክንያትም የመንገዶች መዘጋትም በተሳፋሪው በአሽከርካሪውም ላይ የሚያሳድረው ጫና መኖሩን ይናገራል፡፡ ነገር ግን ሁኔታውን በመረዳት አማራጮችን በመጠቀምና በመግባባት ነገሩን ቀለል ለማድረግ ሲሞክሩ፣ በትራፊክ ፖሊሶች በኩል ክፍተት መኖሩን ይጠቁማል፡፡

የአቋራጭ መንገዶችን ረዥምና አስቸጋሪ መሆን ከግምት በማስገባት ከመደበኛው ታሪፍ የተወሰነ ጭማሪ ሲያደርጉ አብዛኛው ተሳፋሪ እንደሚቀበል ይገልጻል፡፡ አልፎ አልፎ ግን ሁኔታውን መረዳት ያልቻሉ ተሳፋሪዎች ሲያጋጥሙና ንትርኩ ትራፊክ ፖሊስ ዘንድ ሲደርስ ሁሌም ጥፋተኛ የሚደረጉት ታክሲዎች መሆናቸው አግባብ አይደለም ይላል፡፡ እንደነዚህ ዓይነት አጋጣሚዎችን ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባትና በመረዳት እንጂ ወረቀት ላይ በተቀመጠ ነገር ብቻ ለመፍታት መሞከር ትክክለኛ አካሔድ አይደለም የሚል አቋም አለው፡፡

በቅርቡ የተከበረውን የኦሕዴድ የምሥረታ በዓል በምሳሌነት በመጥቀስ ዋናው ቦሌ መንገድ ዝግ በመሆኑ አቋራጮችን በመጠቀም ለሚያደርጉት ጉዞ ከሜክሲኮ ቦሌ መደበኛ የሆነው የሦስት ብር ከሃምሳ ታሪፍ ላይ አንድ ብር በመጨመራቸው ለምን ትጨምራላችሁ መባላቸውን ያስታውሳል፡፡ እንደ አቶ በሻው ሁሉ ከአቅም በላይ የሆኑ የታክሲዎችን ሁኔታ ያለመረዳት ነገር በሕግ አስከባሪዎች በኩል መኖሩን አቶ ቢላልም ይጠቅሳል፡፡

መንገዶች በስብሰባ ምክንያት ሲዘጉ እንደ አቶ በሻው ሥራ አቁሞ መንገድ እስኪከፈት ከመጠበቅ ይልቅ አቋራጮችን እየተጠቀመ ሥራውን እንደሚቀጥል አቶ ቢላል ይናገራል፡፡ ‹‹በመደበኛ ታሪፍ ጨምሬም አቋራጮችን መጠቀምን አይቼዋለሁ፡፡ ዋናው ነገር መጀመሪያ ለተሳፋሪው ታክሲው የሚሔደው በየት በየት እንደሆነ ማስረዳት፣ ጭማሬ ሒሳቡንም አውቆት እንዲገባ ማድረግ ነው›› በማለት በእንደዚህ ያለው አጋጣሚ ምክንያታዊ የሆነ ጭማሪ አድርገው ተሳፋሪውን የሚያገለግሉ አሽከርካሪና ረዳትም እንደማይጠፉ ያምናል፡፡

የመንገዶች መዘጋትና እንደ አማራጭ ሊሆኑ የሚችሉ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን በሚመለከት በመገናኛ ብዙኃን የሚነገር ቢሆንም፣ አብዛኛው የታክሲ አሽከርካሪ የሚመርጠው ራሱ የሚያውቀውንና ይበልጥ አቋራጭ ነው የሚለውን መንገድ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ነገር ግን ታክሲዎች ሲጀምሩ የቤት መኪኖችም ስለሚከተሉ እነዚህም መንገዶች በመጨረሻ እንደሚጨናነቁ ያስረዳል፡፡

መንገዶች በስብሰባ፣ በግንባታም ይሁን ታላቁ ሩጫን በመሰሉ አጋጣሚዎች ሲዘጉ ከጋዜጣ በስተቀር በቴሌቪዥንና በሬዲዮ በተደጋጋሚ እንደሚነገር፤ አማራጭ መንገዶች፣ መኪና ማቆምና ተሳፋሪ ማውረድ መጫን የሚቻልበትና  የማይቻለበት ቦታም እንደሚጠቆም የአዲስ አበባ ትራፊክ ፖሊስ የሕዝብ ግንኙነት ምክትል ኢንስፔክተር አሰፋ መዝገቡ ይገልጻሉ፡፡ ምን ያህሉ አሽከርካሪ ተሳፋሪስ መረጃውን ሰምቶ አካሄዱን ያሳምራል? የሚለው ግን ጥያቄ እንደሆነ የሚቀር ይሆናል፡፡ መረጃውን ሰምተው እንቅስቃሴአቸውን በዚያ መልክ የሚያደርጉ መኖር ግን አከራካሪ አይሆንም፡፡ በሌላ በኩል መረጃ ካለመኖር ሳይሆን መንገዶቹ ሙሉ ለሙሉ ስለማይዘጉ የሚዘጋበትን አጋጣሚ አመልጣለሁ በሚል ብዙ ታክሲዎች እንደሚንቀሳቀሱ ኢንስፔክተሩ ይገልጻሉ፡፡ በዚህ ደግሞ አሽከርካሪውም ተሳፋሪውም አጣብቂኝ ውስጥ ሊገባ ይችላል፡፡

የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ተሽከርካሪዎች ሲጠቀሙ መጨናነቅ ይኖራል፡፡ ኗሪዎችም ተሽከርካሪዎች ይኖራሉ ብለው ስለማይገምቱ ባለመጠንቀቅ ለአደጋ ሊጋለጡ ይችላሉ፡፡ ኢንስፔክተሩ እንደሚሉት ግን፣ በእንደዚህ ያሉ አጋጣሚዎች በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ጭምር ሕግ አስከባሪ በብዛት እንዲሰማራ ስለሚደረግ በውስጥ ለውስጥ መንገዶች የሚኖረውንም እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ይቻላል፡፡ ‹‹ነገር ግን በተለይም ግንባታ ተጠናቅቆ መንገዶች ክፍት ሆነው እያለ ታክሲዎች ይጠቀሙ በነበሩበት አቋራጭ ከፍ ባለ ሒሳብ መጫንን እንደ ምርጫ ይቀጥሉበታል›› ብለዋል፡፡

እሳቸው እንደሚሉት፣ በተለይም ከስብሰባዎች ጋር በተያያዘ በመንገዶች መዘጋት ኅብረተሰቡ ላይ የሚፈጠር ችግር አለ፡፡ ነገር ግን መንገዶች የሚዘጉት ለተወሰኑ ደቂቃዎች ብቻ በመሆኑ፤ ስብሰባዎቹም ረዘሙ ቢባል ከሳምንት የሚበልጡ ባለመሆናቸው ሁሉም ሁኔታዎችን በመረዳት ሰው እንደ ግለሰብ ከሚቸገረው እንደ ሕዝብና አገር የምንጠቀመው ከፍተኛ በመሆኑ ይህንን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

ስብሰባዎች ከሚካሔዱባቸው ወይም ተሳታፊዎች ከሚያርፉበት ሆቴል ጋር የማይገናኙ መንገዶች ዝግ የሚሆኑበት አጋጣሚ ለፀጥታ ሲባል እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ይህን ምን አልባትም ተገልጋዩ በቀላሉ ላይቀበለው ቢችልም ከፀጥታ አንፃር አግባብ ነው ይላሉ፡፡ 

የፀጥታው፣ የትራፊኩ ፍሰትና የኅብረቱ ትብብር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መሆኑንና በመንግሥትም በኩል ሁኔታዎች በየጊዜው እየተሻሻሉ መምጣታቸውን ከጥቂት ቀናት በፊት የተደረገውን ሦስተኛው ዓለም አቀፍ የልማት ጉባኤን በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡

    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...