Friday, June 9, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየሲዳማ ሴቶች ባህላዊ አለባበስ

የሲዳማ ሴቶች ባህላዊ አለባበስ

ቀን:

መሰንበቻውን በባህላዊ የቀን አቆጣጠሩ መሠረት አዲስ ዓመቱን የጀመረው የሲዳማ ብሔር ነው፡፡ በደቡብ ክልል የሚገኘው የሲዳማ ብሔር ከሐምሌ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ያህል ‹‹ፊቼ ጫምባላላ›› ተበሎ የሚታወቀውን የአዲስ ዓመት ክብረ በዓል በክልሉ መዲና ሐዋሳ በጉዱማሌ ባህላዊ አደባባይ አክብሯል፡፡ በጨረቃና በከዋክብት ዑደት ላይ በተመሠረተው የፊቼ ጫምባላላ ክብረ በዓል አጋጣሚ የሲዳማ ብሔር ባህላዊ እሴቶችና ትሩፋቶች በኅትመት ለዕይታ በቅተዋል፡፡ ዩኒክ ኢትዮጵያ ባዘጋጀውና በአማርኛ፣ በሲዳምኛና እንግሊዝኛ የቀረበው ሐተታ ከተመለከታቸው አንዱ በምልኪስ ሳሙኤል የዳሌ ወረዳ ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ባለሙያ የተዘጋጀው የሲዳማ ባህላዊ አለባበስ ሲሆን፣ በተለይ ስለሴቶች አለባበስ የሚያወሳው ቀጥሎ ቀርቧል፡፡

ሕፃናት የሆኑ ሴት ልጆች የሚለብሱት ከበግ ቆዳ ተለፍቶ የሚዘጋጅ ለምድ  (Lande) ነው፡፡ ወጣት ልጃገረዶች ከውስጥ ቆሎ (Qolo) የሚባል ልብስ የሚለብሱ ሲሆን ከላይ ከጥጃ ቆዳ ተለፍቶ የሚዘጋጅ ለምድ (Qonxolo) ይደርባሉ፡፡ የልጃገረዶች ቆሎ ከጥጥ የሚሠራ ሆኖ ከላይ እስከ ታች ተደርጎ የሚሰፋ ሲሆን እንደ ልብ ለመራመድ እንዲያስችል ዳርና ዳሩ ክፍት ይተዋል፡፡ ወጣት ልጃገረዶች የሚለብሱት ቆሎ የተለያዩ ቀለማት ባላቸው አዝራሮች፣ ጨሌዎችና ፈትሎች እንዲያሸበርቅ ይደረጋል፡፡

እንደ ዕድሜያቸው ለትዳር የደረሱ ዱቤ (Dubbe) የሚባል ከቆዳ የሚሠራ ልብስ ይለብሳሉ፡፡ ላገባች ሴት ባሏ ዎዳሬ (Woodare) ይገዛላታል፡፡ ዎዳሬ ከበሬ ቆዳ የሚሠራ ሲሆን እጅግ ለስለስ ያለም ነው፡፡ አለባበሱም በሁለት በማጠፍና በወገብ ላይ በቆዳ የሚሠራ መቀነት በቁኔ (Qu’ne) በማሰር እጥፋቱ ወደ ታች በመልቀቅ ነው፡፡ ለጋብቻ የደረሰች ልጃገረድ ስታገባ ከእናቷ በስጦታ መልክ የሚሰጣትን ዎዳሬ ታጥቃ በልዩ ጌጣ ጌጦች ያሽቆጠቆጠ ለምድ ደርባና ተሞሽራ ስትወጣ በተለየ ሁኔታ የተጌጠ ቆሎና ቆንጦሎ ደርባ ነው፡፡

የሲዳማ ሴቶች ጎፋ (Gorfa)፣ ቱባ (Tuba)፣ ዱዳ (Dudda)፣ ቦኬ (Boke) የሚባሉ ከቆዳ የሚሠሩ አልባሳትን ይለብሳሉ፡፡ ቦኬ፣ ወዳሬ የክት ልብሶች ሲሆኑ ቱባና ዲዳ በአዘቦት ቀናትና በሥራ ቀናት ጊዜ የሚለበሱ አልባሳት ናቸው፡፡ ከጎርፉ በስተቀር ከላይ የተጠቀሱ አልባሳት ከወገብ በታች የሚታጠቋቸው ሲሆን ጎርፉ በተለያየ ጨሌዎች ያጌጠና ሴቶች ወደ አደባባይ ሲወጡ ከላይ የሚደርቡት ካባ ነው፡፡

በማንኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ ያሉ ሴቶች በተለያዩ ጌጣ ጌጦች ያሸበረቁ ቆሎና የተጌጠ ቆንጦሎ ይለብሳሉ፡፡ ሁለት ቆንጦሎ ከፊትና ከኋላ በማጠፍ መልበስ በሲዳማ ሴቶች ዘንድ የድሎት ወይም የቅንጦት ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በዚህ አለባበስ የሚታወቁ አበዛኞቹ ሴቶች ‹‹La’ma Lamu Landite›› ተብለው ይወደሳሉ ትርጉሙ ባለ ሁለት ለምድ ቅምጥል ወይም የተቀማጠለች መሆኗን የሚገልጽ ነው፡፡

ለሴት ልጅ ውበቷ ጌጧ እንደሚባለው ሴቶች ለአጋጌጥና ለፀጉር አሠራር ልዩ ሥፍራ ይሰጣሉ፡፡ በልጅነት ዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሴት ልጆች ፀጉራቸው ዙሪያ ተላጭተው መሀል ላይ ቁንጮ (Guuto) በማሳደግ የተለያየ መልክ ያላቸውን ጨሌዎች ዶቃዎና ለውበት ድምቀት የሚሰጡት የተለያዩ ጌጣጌጦች ይደረግላቸዋል፡፡ ፀጉራቸው ቶሎ እንዲያድግና አናታቸው እንዳይደርቅ ቁቶአቸው (Qutto) ላይ ቅቤ እየተቀቡ እርስ በርስ እንዲያያዝ በማድረግ ጉዱሮ (Guduro) ወደሚባል ፀጉር አሠራር ዓይነት ይቀየራል፡፡ ጉዱሮ የተደረገላቸው ሕፃናት እየተሯሯጡ በሚጫወቱበት ወቅት ወዲህና ወዲያ እየተወዛወዙ ለሕፃናቱ ውበትን ለጫዋታቸው ድምቀትን በተጨማሪም የፀጉራቸው ርዝመትና የመልካቸው ውበት ምን ያህል እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡

ለጋብቻ የደረሱ ልጃገረዶች ከፊት ያለውን ፀጉራቸውን እየተላጩ ቀሪውን ወደ ኋላ ይሠራሉ፡፡ ለማግባት ሲቃረቡ ከፊት ያለውን ፀጉር በማሳደግ የሚያጎፍሩ ሲሆን ቀሪውን ወደ ኋላ ተሠርተው ዙሪያውን በክር (Heqo) ተሰፍቶላቸው ያሳምራሉ፡፡ ይህም የፀጉር አሠራር ጎዳያ (Goodayya) በመባል ይታወቃል፡፡ ጎዳያ አንዲት ልጃገረድ ለጋብቻ የደረሰች ወይም የታጨች መሆን ከሚገጹ ምልክቶችና መንገዶች አንዱ ነው፡፡  ለጎዳያዋም ትልቅ ሥፍራ በመስጠት እንክብካቤ ታደርጋለች፡፡ ተቀብታ ጎዳያዋን የንጋት ጤዛ አስመስላ ስትወጣ ብዙ አደናቂዎች አድናቆታቸውን ይገልጹላታል፡፡

ወጣት ልጃገረዶች ፊታቸውን አድምቀውና ለመታየት ጉንጫቸው ላይ ጭረት ቁራ (Qurra) ይነቀሳሉ፡፡ አንዳንዶቹ ቁራ በእግራቸው ባት ላይም የሚነቀሱ ሲሆን በዘመን መለወጫ ፊቼ በዓል ወቅት እጃቸውንና እግራቸውን እንሶስላ (Hanshuluulle) በማሞቅ ይበልጥ ደምቀውና ተውበው ለመታየት ይጥራሉ፡፡ ያገባች ሴት በሙሽርነቷ ወቀት ፀጉሯን ቦንኮዬ (Bonkooyye) የሚባል አሠራር ተሠርታ የበለጠ አምራና ደምቃ ትታያለች በቅርብ ያገባች ሴት ለመጀመርያ ጊዜ በዘመን መለወጫ ፊቼ ማግሥት በልጁ (በባሏ) እናት አማቷ ታጅባ ወደ አደባባይ ጉዱማሌ (Gudumale) ትወጣለች፡፡ ስትወጣም ጎምብሳ (Gombisa) ወይም ሹራ (Shura) በሚባል ፀጉር አሠራር አምራ ተውባና ደምቃ ነው፡፡ በሌላ መልኩ ወጣት ሴቶች ሾዶሌ (Shodolo)፣ ታዪሻ (Tayisha)፣ ጎምቢሳ (Gombisa) እና ናኖ (Naano) የሚባሉ የፀጉር አሠራር ዓይነቶችን በመሠራት ይዋባሉ፡፡ ቦንኮዬ (Bonkoye) የተባለውን የፀጉር አሠራር ከአራስ ቤት የምትወጣ ሴት የምትሠራው የፀጉር አሠራር ነው፡፡ ለጋብቻ ለእናቶች የሚሠሩት የፀጉር ዓይነት ቦፌ (Boffe) በመባል ይጠራል፡፡ ልጆቻቸውን ወልደው የዳሩ ሴት እናቶች ፀጉራቸውን ቆርጠው በማሳጠር ጎፈሬ ፀጉራቸውን ቆርጠው በማሳጠር ጎፈሬ በኪቻ (Bukkicha) ያበጥራሉ፡፡ በልዩ አጠራር ፀጉራቸውን የቆረጡ እናቶች ኡሞቂዲኖቴ (Umoqeedinote) በመባል ይታወቃሉ፡፡

የሲዳማ ሴቶች ባህላዊ አለባበሳቸውንና ጌጣ ጌጦቻቸውን በጥንቃቄ የመያዝ ልምድ አላቸው፡፡ ልብሶቻቸውና ጌጣ ጌጦቻቸው ጥሩ መዓዛ ሽታ አንዲኖራቸው የተለያዩ አትክልት፣ የዛፍ ሥራ ሥሮች፣ ቅጠላ ቅጠሎችና ቅርፊቶችን በማደባለቅ የተቀመመ ንጥረ ነገር ያዘጋጃሉ፡፡ በባህላዊው መንገድ ተጠቅምሞ የተዘጋጀው ንጥረ ነገር በስያሜ ቁኔ (Qu’ne) ይባላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ