Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየአውታር ፊልም ቢዝነስ

የአውታር ፊልም ቢዝነስ

ቀን:

ውብሸት ሙሉጌታ ባለ ሰባት አውታር (ሰቨን ዳይሜንሽናል) ፊልም ለመጀመርያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበትን ወቅት አይዘነጋውም፡፡ ብዙዎችን ያነጋገረ ነበርና እሱም የማየት ጉጉት እንዳደረበት ይናገራል፡፡ ከመመልከቱ አስቀድሞ በሰቨን ዳይሜንሽናል (ሰቨንዲ)  ፊልም ያዩ ጓደኞቹን ተሞክሮ ጠይቆ ነበር፡፡ ያገኘው ምላሽ ፈጽሞ የተለያየ ሆነበት፡፡ አንዳንዶች እንደፈሩ፣ ሌሎች በቴክኖሎጂው እንደተደነቁና የተቀሩት ግራ መጋባታቸውን ገልፀውለታል፡፡ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት እንደ አማራጭ የወሰደው ድረገጾችን መመልከት ነበር፡፡

ስለ ሰቨንዲ የሰማውና ያነበበው በመጠኑ ቢያሸብረውም ተመልክቶ ለመፍረድ ይወስናል፡፡ በአንድ የሕዝብ በዓል ምክንያት መሥሪያ ቤቱ ሲዘጋ ጥሩ አጋጣሚ ተፈጥሮለት ወደ ኤድና ሞል አቀና፡፡ እሱ እንደሚለው፣ በቦታው ሲደርስ የተመለከተውን ያህል ሰልፍ ይኖራል ብሎ አልጠበቀም፡፡ አብራው የነበረችው ጓደኛው በሰቨንዲ ፊልም አይተው የሚወጡ ሰዎች ፊት ላይ የሚነበበውን ስሜት እያየች ፈርታ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

ተራ ደርሷቸው ወደ ሲኒማ ቤቱ ገቡና ፊልሙ ተጀመረ፡፡ የፊልሙን ርዕስ ባያስታውሰውም ብዙ ዳይኖሰሮች እንደነበሩ ይናገራል፡፡ ‹‹ከተመልካቹ መካከል የሚጮሁ ነበሩ፤ አጠገቤ ተቀምጣ የነበረችው ጓደኛዬ ከሚጮሁት አንዷ ነበረች፤›› ይላል፡፡ እሱም ለጥቂት ደቂቃዎች ተጨንቆ ነበር፡፡ በተለይ ፊልሙ ላይ በሳር ውስጥ የሚጥመዘመዘው እባብ እግሩን የነካው ሲመስለው የሚገባበት ጠፍቶት ነበር፡፡ ፊልሙን መጨረስ ተስኗቸው መነፅራቸውን ያወለቁ ሰዎች መመልከቱንም ይናገራል፡፡

‹‹በቴክኖሎጂው መራቀቅ ተገርሜ ነበር የወጣሁት፤ ከዛ በኋላ ግን ሰቨንዲ ደግሜ አልተመለከትኩም፤›› ይላል፡፡ ከስድስት ወር በፊት ግን ብስራተ ገብርኤል አካባቢ በፋይቭዲ ፊልም ለማየት ሄዶ እንደነበር ያስታውሳል፡፡

ውብሸት እንደሚለው፣ ቴክኖሎጂውን ተከትሎ መሣሪያዎቹን ወደ አገር ውስጥ ማስገባት መልካም ቢሆንም ሲኒማው ደረጃውን የጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ስሪዲ ከተጀመረበት ዓመት አንስቶ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻሻለውን ቴክኖሎጂ የሚያስመጡ ሰዎች ቁጥር መጨመሩ ከቢዝነስና ለተመልካች አማራጭ ከማስቀመጥ ረገድ ይበረታታል ይላል፡፡ በየወቅቱ አዳዲስ ኢፌክት ቢታከል የበለጠ ትኩረት ሳቢ እንደሚሆንም እምነቱ ነው፡፡

ባደጉት አገሮች ለበርካታ ዓመታት የዘለቀው ይህ የሲኒማ ጥበብ በየጊዜው አዳዲስ ኢፌክቶች እየታከሉበት ነው፡፡ እያንዳንዱ ፊልም ላይ ያሉ ግብዓቶችን መነሻ በማድረግ ተመልካቾች ልዩ ልዩ ስሜቶች ያድሩባቸዋል፡፡ ፊልም ከዓይንና ከጆሮ ባለፈ በሌሎች የስሜት ህዋሳትም እንዲገባ ያደርጋል በሚል ጥበቡን የሚገልጹት ባለሙያዎች አሉ፡፡

ተመልካቾች ዝናብ፣ ንፋስ፣ በረዶ፣ ጭስ፣ መብረቅ እንዲሁም በአንድ ፊልም ያሉ ግብዓቶች ዕውን እንደተፈፀሙ ያህል ይሰማቸዋል፡፡ ተመልካቾች የሚያደርጉት መነጽርና የፊልሞቹ አሠራር ዋነኛ መሠረቱ ነው፡፡ የሲኒማ ቤቶች ወንበር እንዲሁም በየማዕዘኑ ያሉ መሣሪያዎች ስሜትን ይፈጥራሉ፡፡ በተለይ አስፈሪ ፊልሞች በዚህ መንገድ ሲታዩ፣ ገፀባህሪያቱ ከእስክሪኑ ወጥተው በተመልካቹ የሚዳሰሱ ስለሚመስሉ የሚሸበሩ ሰዎች ጥቂት አይደሉም፡፡

የኤድና ሞል ከስተመር ሰርቪስ ኦፊሰር አቶ ዓለምሰገድ ጌታቸው ሰቨንዲ ሲመጣ ለአገሪቱ አዲስ ስለነበረ ሕዝቡ ለመመልከት ከፍተኛ ጉጉት እንደነበረው ይገልጻል፡፡ ‹‹ስሪዲ በመጣበት ወቅት የማየት ጉጉት ቢኖርም፣ ሰቨንዲ ሕዝቡን ለማስተናገድ እስኪያዳግት ድረስ ተመልካች ነበረው፤›› ይላል፡፡ አሁንም ድረስ በርካታ ተመልካቾች በተለይ በበዓላትና በሣምንቱ መጨረሻ ቀናት እንደሚመጡ ይናገራል፡፡ ተመልካቾችን ለመሳብ በየጊዜው አዳዲስ ኢፌክቶች እንደሚጨመሩም ያክላል፡፡

አዳዲስ ነገሮች መጨመራቸው የተመልካቹ ቁጥር እንዳይቀንስ ለማድረግ እንደሚረዳቸው ያምናል፡፡ ተመልካቾችን ከማዝናናት ባሻገር ከቢዝነስ አንጻርም አዋጭ መሆኑን ያስርዳል፡፡ ሰቨንዲ ከሰኞ እስከ ሐሙስ በፊልም 40 ብር፤ ከዓርብ እስከ ቅዳሜ በፊልም 50 ብር ያስከፍላል፡፡ ስድስት ፊልሞች ለምርጫ የሚቀርቡ ሲሆን እያንዳንዱ እስከ 15 ደቂቃ ይወስዳሉ፡፡

ሰቨንዲ ሲያሳዩ ከገጠማቸው መካከል በፍርሃት ሽንታቸውን የለቀቁ ሰዎችን ያስታውሳል፡፡ ‹‹ለምን ገንዘቤን ከፍዬ እሳቀቃለሁ›› የሚሉም አሉ፡፡ ፊልሙ ለእርጉዞች እንዲሁም ከአጥንት ጋር የተያያዘ በሽታ ላለባቸው ባይፈቀድም፣ እንይ የሚል ጥያቄ የሚያቀርቡ አሉ፡፡

ተመልካቾች ፊልሞችን ሲያዩ በፊልሙ ውስጥ ያሉ እስከሚመስላቸው ድረስ የፊልሙ ግብዓቶች እንዲሰሟቸው የማድረግ ጥበብ ወደ ሲኒማው ጎራ ካለ ሰነባብቷል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመጣም ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ በዘርፉ ለሚገኙ ድርጅቶችም ሁነኛ የገቢ ምንጭ የፈጠረ ይመስላል፡፡

በቦራ አሚውዝመንት ፓርክ ኤይትዲ መታየት ከጀመረ ሁለት ዓመት ሊሞላው ነው፡፡ 120 ፊልሞች ያሏቸው ሲሆን፣ ሳምንቱን በሙሉ ለአንድ ፊልም 40 ብር በመክፈል መመልከት ይቻላል፡፡ ፓርኩ በዋነኛነት የሕፃናት መዝናኛ ቢሆንም፣ ፊልሞቹ በተለያየ ዕድሜ ደረጃ የተከፋፈሉ መሆናቸውን ማርኬቲንግ ማናጀሩ አቶ ሰለሞን አብርሃ ያስረዳል፡፡

ኤይትዲ ለማስመጣት የወሰኑት ፓርኩ ለሕፃናትና አዋቂዎች ሙሉ አገልግሎት እንዲሰጥ ነው፡፡ ‹‹በግቢው ያሉ መጫወቻዎች ለልጆች ናቸው፤ ኤይትዲ ግን ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ሊዝናኑበት ይችላሉ፤›› የሚለው ሰለሞን፣ ኤይትዲ ከቢዝነስ አንፃር የሚጠበቀውን ያህል አዋጭ እንዳልሆነ ይናገራል፡፡

ልጆች በትምህርት ቤት የሚያሳልፉትን ሰፊ ጊዜና ልጆቹን በየጊዜው የሚያዝናና ቤተሰብ ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ከግምት በማስገባት ገቢው አንድ ወቅት የሚጨምር ከዛም የሚቀንስ መሆኑን ይናገራል፡፡ ‹‹ወጪው ከገቢው ጋር ባይመጣጠንም ለኅብረተሰቡ አዲስ ነገር ማምጣትና ልጆችን ማዝናናትን ከፍተኛ ቦታ እንሰጠዋለን፤›› ይላል፡፡

ልጆች በሚያዩአቸው ፊልሞች እንዳይረበሹ ጥንቃቄ እንደሚወስዱና ፊልሞቹን ለልጆች ከማሳየታቸው በፊት ቤተሰቦች አይተው እንዲመርጡም ያደርጋሉ፡፡ ፊልሞች በሲኒማው በሚታዩበት ወቅትም ቤተሰቦች ከሲኒማው ውጪ ሆነው በስክሪን ይከታተላሉ፡፡ በእሱ እምነት፣ ሕፃናቱ ከመዝናናታቸው ባለፈ ጊዜው የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ማየታቸው አዕምሮአቸውን ያጎለብተዋል፡፡

የመብራት መቆራረጥ በሥራቸው ላይ ያሳደረባቸውን ተፅዕኖ ሳይጠቅስ አላለፈም፡፡ መብራት ጠፍቶ ተመልሶ የሚለቀቅበት ኃይል ከፍተኛ መሆኑ እንደሚያስቸግራቸው ይናገራል፡፡

የዘመኑ ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ከሰባት ወር በፊት ናይንዲን ይዞ ገበያውን የተቀላቀለው ሻካይና ጄኔራል ቢዝነስ ነው፡፡ ናይንዲው የሚገኘው መኪና ውስጥ ሲሆን፣ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በአንድ ጊዜ ስድስት ሰዎችን የሚያስተናግደው ሲኒማው ከ10 እስከ 15 ደቂቃ ለሚወስዱ ፊልሞች 55 ብር ያስከፍላል፡፡

ሥራ አስኪያጁ አቶ በሱፍቃድ ንጉሤ ከአዲስ አበባ ውጪ ላሉ ተመልካቾች ማሳየት እንዲቻል መኪና ማዘጋጀታቸውን ይናገራል፡፡ ሥራ ከጀመሩ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ በጥቂት ፌስቲቫሎችና ባዛሮች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ አሁን ከዓለም ሲኒማ ጀርባ የሚገኙ ሲሆን፣ ፊልም ለመመልከት ወደ ሲኒማ ቤቱ የሚሄዱ ተመልካቾች ተራ እስኪደርሳቸው ናይንዲ እንዲመለከቱ ይጋብዛሉ፡፡ በሱፍቃድ በቅርቡ ከአዲስ አበባ ውጪ የሚያደርጉትን ጉዞ እንደሚጀምሩ ይናገራል፡፡ ‹‹የማየት ዕድሉን ላላገኙ ሰዎች የማዳረስ ዕቅድ አለን፤ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ፋይቭዲ፣ ሰቨንዲና ኤይትዲ የመመልከት አጋጣሚ አግኝተዋል፤›› ይላል፡፡

እያንዳንዱ ሰው እንደፍላጎቱ የሚያየውን ፊልም እንዲመርጥ ስለየፊልሞቹ መረጃ እንደሚሰጡ፣ ከዚህ ቀደም ተሞክሮ ያላቸው ሰዎች ብዙም እንደማይደናገሩ ሆኖም በፍርሃት የሚንቀጠቀጡ አንዳንዴም ራሳቸውን የሚስቱ ተመልካቾች እንደገጠሙት ያስታውሳል፡፡

‹‹አንድ ቦታ ሆኖ ቢዝነስ ከመጠበቅ እየተንቀሳቀሱ መሥራት አዋጭ ነው፤›› የሚለው በሱፍቃድ፣ ወደተለያዩ ከተሞች የሚያደርጉት ጉዞ ጠቀም ያለ ገቢ እንደሚያስገኝላቸው ተስፋ በማድረግ ነው፡፡ ሰው የመዝናኛ አማራጭ እንዲያገኝ አስበን አስመጥተነዋል የሚለውን ናይንዲ ወደ ክፍለ አገር በሚያጓጉዙበት ወቅት የሚገጥሟቸውን ችግሮችም ይጠቅሳል፡፡

ዋነኛው የመንገድ አለመመቻቸት ሲሆን፣ የመብራት መቆራረጥም ይጠቀሳል፡፡ ምንም እንኳን በመኪናው ላይ የተገጠሙት መሣሪያዎች ለተንቀሳቃሽ ሲኒማ የተሠሩ ቢሆንም፣ እንዳይበላሹ መኪናው የሚሄድበት መንገድ የተመቸ መሆን አለበት፡፡ አባጣ ጎርባጣ የበዛባቸው መንገዶችን አልፎ ወደገጠር ለመግባት ያላቸው ዕቅድም አስጊ መሆኑን ይናገራል፡፡ ከሌሎቹ አስተያየት ሰጪዎች ጋር የሚስማማው መሰል የሲኒማ አማራጮች መበራከት እንዳለባቸው ነው፡፡

ሦስቱንም ድርጅቶች ወክለው አስተያየት የሰጡን ኃላፊዎች አማራጭ በበዛ ቁጥር ተመልካች የተሻለውን የመምረጥ ዕድል እንደሚኖረው ይናገራሉ፡፡ ቢዝነሱ ወቅት ተኮር መሆኑንና ክረምት፣ ሥራ የማይሠራባቸው ቀናትና በዓላት የተሻለ ገቢ የሚያገኙበት እንደሆነም ገልፀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...