ሰላም! ሰላም! ‹‹ኧረ እኔስ ፈራሁ›› አለች አሉ ሚስትየው። ባል በጣም ተሰማው። በትንሽ በትልቁ እየተሰማን አንዳንዴ እኮ ባሎች ስንባል እናበዛዋለን። እና፣ ‹‹እንዴት! እንዴት! ምን ለማለት ነው እኔ እዚህ ተቀምጨ ፈራሁ ማለት?›› ይላል። ጀግንነትን የተነተንበት መዝገበ ቃላችን ከተፈጥሮም ከፈጣሪም አናንቆን የለ?! እንዲያው እኮ። ሚስት ነገሩ ወዴት እንደሄደ ገብቷት (መቼም ሴት ልጅ ብልህ ናት። ብልጠት ከሥልጣኔ ጋር አጉል ሰዓት ተገናኝተው አጉል እያረጉዋት ተቸገረች እንጂ) ‹‹እህ ሰው አይፈራም? ይፈራል እኮ!›› ብላ ባልን በሙሉ ዓይኗ ሳታየው መለሰችለት። ባል ቱግ ብሎ በአሽሙር፣ ‹‹ለነገሩ የሴት ወጉ መፍራት ነው›› ብሎ ላይ ታች ሲገላመጥ ሚስት ቀበል አድርጋ፣ ‹‹ታዲያ ወንድነትስ ከየት የመጣ ይመስልሃል?›› አለች አሉ። በአሉ እንጀምረው ብዬ እኮ ነው!
አስኮብላይና ኮብላይ ልብ ለልብ ይተዋወቃል ይባላል። እኛን ያስቸገረን ግን ራስን ማወቅ ሳይሆን አይቀርም። እውነቴን እኮ ነው። ደርሶ ግንፍልተኛው አልበዛባችሁም? በበኩሌ ጦር ጠማኝ ባለፍ ባገደምኩበት እየተከተለ እየለከፈኝ ተቸግሬላችኋለሁ። በተለይ ፈገግ ብላችሁ ተረጋግታችሁ፣ ወንዶች ደረት ነፍተን፣ ሴቶች ቀጭ ቋ እያላችሁ ስትጓዙ የተገኛችሁ እንደሆነ አበቃ። የክፍለ ከተማ ጣጣ፣ የአገር ውስጥ ገቢ እንግልቱ፣ የተበጠበጠ ትዳሩ ብቻ አንዱ ትዝ ብሎት፣ ‹‹ምናባታችሁ አቧራ ታቦናላችሁ? ኦባማ ነህ አንተ? ወይስ ኩዊን ኤልዛቤት ነሽ?›› እያለ ለዱላ የሚጋበዘውን ፌደራል ፖሊስም አልቻለውም አሉ። ‹‹እንዴት ያለ ነገር ነው ጃል? የሚያማርረን ነገር በዛና ለእያንዳንዳችን አንድ አንድ ፕላኔት ሊሰጠን አማረን ይሆን?›› ብዬ ከባሻዬ ልጅ ጋር ሳወራ የባሻዬ ልጅ ከት ብሎ ስቆ፣ ‹‹ኮንዶሚኒየም ሳይዳረሰን ጭራሽ በስማችን አንዳንድ ፕላኔት?›› ብሎ አላገጠብኝ። ቆይ ግን እኔ መቼ ይሰጠን አልኩ? ይኼን እኮ ነው የምላችሁ። ኪሎና መጨመር እንጂ መደማመጥ ቀንሰናል። እህ? ሰውዬው፣ ‹‹እኔ እያለሁ ፈራሁ ምንድነው?›› እንዳለው ሰው እያደር ተፈጥሯዊ የሆነውን ዑደት ሳይቀር በእሱ ዓይን ብቻ አይቶ እየረጎመ መንገዱን ‘ዋን ዌይ’ ብቻ አድርጎ መድረሻ አጣን። እንዲያው እኮ!
ወግ ይዘንም አይደል? ‹‹ወግ ባይን ይገባል›› ይባል ነበር ድሮ። ጠዋት ማታ ይኼን መነጽር ዓይኑ ላይ እየገደገደ ዘንድሮ በየት ይግባ? ከዚህ ብሶ ደግሞ ይኼው የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰው ዓይኔ የሚገባ ነገር አጣሁ ይላል። ‹‹እንግዲህ ምናምን ባይኑ ገብቶ ይሆናላ? ጉድፍ አየሁ ከማለት መጀመሪያ ባልጎደፈ ዓይን ማየትን እርግጠኛ መሆን ያስፈልጋል እኮ፤›› ባዩ ባሻዬ ናቸው። የባሻዬን አባባል እያሰብኩ ከአንድ ደንበኛዬ ጋር ስለያዝኩት ቀጠሮ አስባለሁ። አንድ ሁለት ሰዓት አለኝ። ያለወትሮዬ ማልጄ መነሳቴ ሳያንስ እህል ሳልቀምስ ማንጠግቦሽ ገና ከአልጋ ሳትወርድ ነበር የወጣሁት። ‹‹ማልዶ የተነሳ ሰው ሌላው ቢቀር የወደቀ ዕቃ እንኳ ያገኛል፤›› ትለኝ ነበር ውዷ እናቴ በልጅነቴ። የወደቀ ሰው እንጂ የወደቀ ዕቃ ማግኘት ዘበት ነው ብላችሁ፣ ዛሬን አይታችሁ እንዳትስቁባት። በደጉ ጊዜ በየዋሆች ዘመን ኖራ ያየችውን ነው። ይልቅ ሳያይ ሳይሰማ ዓይቶ እንደሰማ የባጥ የቆጡን እየቀባጠረ ይኼን የመረጃ ዘመን የሚያዛባውን ውቀሱ። አይታ ኖራ የተረችውን እናቴን ግን አድንቁልኝ። ከልቤ ነው።
እናላችሁ እኛ ደላሎች እዛች ለሻይ ቡና ወደምናዘወትራት ካፌ ሄጄ ወተት ለመጠጣት ተቀመጥኩ። ካፌው ገና መከፈቱ ነው። ሰማይ ዓይኑን መግለጡ ነው ብያችኋለሁ። አስተናጋጆቹ በሁለት ግሩፕ ተከፍለው ይሰዳደቡታል። ‹‹ይኼ የኢንፎርሜሽን ዘመን ኑሯችንን አቀለ እኛንም አቃለለ…›› ያለው መምህር ማን ነበር? ‹‹ኧረ እባካችሁ ታዘዙኝ?›› ብዬ ስጮህ አንድ አዲስ ፊት መጣች። ‹‹ወተት አምጭልኝ እስኪ›› ብዬ ሳልጨርስ ‹‹በስመ አብ ወ ወልድ ወ መንፈስ ቅዱስ! (አማትባ) በፆም ቀን እኔ የወተት ብርጭቆ አልነካም ሌላ ሰው ይታዘዝህ፤›› አትለኝ መሰላችሁ? እሷ ምን አለባት በወር መጨረሻ አገር ውስጥ ገቢ ወጥሮ የሚይዘው ባለቤቱን። ‘የፆምና የፍስክ አስተናጋጅ ለመለየት ባጅ ለጥፉና ቁሙ’ ብዬ እንዳልጮህ ምን አስጮኸኝ ብዬ ተውኩት። ለምን ስጮህ እታያለሁ። አይደለም እንዴ?
ነገረ ሥራችን እየገረመኝ ስሬ ተገታትሮ ቁጭ ብዬ ሳስብ አንድ ወዳጄ ስልኩ ውስጥ ሊገባ ምንም ሳይቀረው አቀርቅሮ እየተደናቀፈ መጣና አጠገቤ ተቀመጠ። ‹‹አብረን አድረናል?›› አልኩት። ‘ደህና አደርክ አይባልም ወይ?’ ነው ነገሩ። መቼስ ይጠፋችኋል ብዬ አይደለም የማብራራው። ወዳጄ ምዕራባውያን የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻ ካፀደቁ ጀምሮ ጭንቅላቱ ስለተበረዘ፣ ‹‹ምን ለማለት ፈልገህ ነው?›› ብሎ የጎሪጥ ስላንጓጠጠኝ ነው። ‘ወይ ጊዜ እንግዲህ በእያንዳንዷ ቃልና ዓረፍተ ነገር ቀበቶ እያጠበቅን የጎሪጥ እየተያየን ወንድማማቾች ማዶ ለማዶ መቀመጥ ልንጀምር ነው ማለት ነው?’ እያልኩ በውስጤ ካረጋጋሁት በኋላ ምን እንደሚጎረጉር ጠየቅኩት። የአሳ ጓርጓሪ ዘንዶ ታቃፊ ዘመን!
‹‹አልማዝ ባለጭራን ኢንተርኔት ላይ እየፈለግኳት ነው፤›› አለኝ መረጃ በመጎልጎል ትዕግሥቱ እየተመፃደቀ። ‹‹ድራሿን የሚያጠፋ የሐበሻ መድኃኒት እያለለህ ምን መረብ ለመረብ ያዘልልሃል? ይልቅ አሁን እያባከንከው ያለውን ካርድ ለዓባይ ግድብ ላከው ወይ ቁርስ እንብላበት፤›› ስለው ተስፈንጥሮ ቦታ ቀየረ። በስመ ሥልጣኔ በስመ ድረ ገጽ አሳሽነት የስንቱ ጨዋነትና የስንቱ ቀናነነት ሚዛን አጥቶ ወዳጅነት አፈር ሲበላ አያለሁ መሰላችሁ። ‘እያወቁ አለቁ’ እያሉ የሚጮሁትም ቀስ በቀስ አለቁ። ራሳችንን በመስታወት ማየት እየተፀየፍን ቃሉን ቀድሰን የመረጃ መረብ፣ ማኅበራዊ ድረ ገጽ እያልን አሰስ ገሰሱን ስናጋስስ እንውላለን። የሚመረጥ እንዳለም፣ የሚጣል እንዳለው ጠቋሚ ሳያሻን አይቀርም። የባሻዬ ልጅ በዚህ ሐሳቤ በጣም ይስማማል። አንዴ ‘ቁራሌው’ በአጠገባችን እየጮኸ ሲያልፍ አተኩሮ ካየው በኋላ፣ ‹‹ይኼ ምስኪን ሥራው ‘ዲጂታላይዝድ’ እንደሆነ ሳያውቅ አሁንም መንገድ ለመንገድ ይጮሃል?›› ብሎ አስፈግጎኛል። ስንቱን ‘ዲጂታላይዝድ’ አድርገን እንደምገፋው ግን እንጃ!
የቀጠሮዬ ሰዓት ደረሰ። ደንበኛዬ ከአውሮፓ የመጣች ጠና ያለች ወይዘሮ ነች። አገሩ ስለተቀያየረባት አንድም ከተማውን እያያዟዟርኩ ላሳያት፣ አንድም እጄ ላይ የነበረ ባለሶስት ፎቅ ዘመናዊ መኖርያ ቤት መግዛት ፈልጋለች። ቤቱን ለመግዛት ወስና ስለነበር ብዙ አልተንከራተትኩም። በዕድገት ጎዳና ላይ ያለችውን አገራችንን (አዲስ አበባም ያው አገራችን ውስጥ ያለች አገራችን ናት) ማስቃኘቱ ግን አድካሚ ነበር። ወዲህ ስወዳት ወዲያ ሳመጣት ሲኤምሲ፣ መገናኛ፣ ቦሌ፣ ሜክሲኮ፣ ሳር ቤት፣ ለገጣፎ፣ ሳዞራት ዋልኩ። ‹‹ውጭ አገር ነው ያለሁት ኢትዮጵያ?›› ስትለኝ እኔ ደግሞ ዕድገቱን እያሞካሸች መስሎኝ፣ ‹‹ይኼውልሽ እንግዲህ የሚፈርስበት እየፈረሰበት የሆነለት እያለማበት ያደግንበት ሠፈር ጠፍቶናል፤›› እያልኩ እለፈልፋለሁ። ለካ ሴትዮዋ ባለፍን ባገደምንበት ሁሉ በእንግሊዝኛ ፊደል የተጻፉ ፈረንጅኛ መጠሪያዎችን እያነበበች በሽቃ ነው። ‹‹የት ሄዶ ነው ኢትዮጵያዊው ፊደል?›› ስትለኝ ነው ነገሩ የገባኝ። (ምን አውቃለሁ ቋንቋችንም እንደ ቡናችን ኤክስፖርት መደረግ ጀምሮ ይሆናላ!)
አቤት ቻፓ እና ነገር ቶሎ ቢገቡልኝ። ይኼኔ ልማታዊ ባለሀብት ሆኜ ሕንፃ ገንብቼ በእንግሊዝኛ ሰይሜው ነበር። ግን እንኳንም አንዳንዱ ምኞት በነበር የሚቀር ሆነ። ደንበኛዬ ነገሩን ችላ ብላ ማለፍ አቃታት። ጭራሽ ‘ፍሬንች ኪስ’ የሚል ሕንፃ ስታይማ ራሷን ስታ እጄ ላይ ወደቀች። እኔ የጠየቅኩት ጥያቄ አንድ ነው። እርሱም፣ ‘ከዚህች ሴትዮና ከእኔ ጤነኛው ማን ነው? አጥወልውሏት ራሷን ስታ እስክትወድቅ መያዣ መመለሻ ያጣው የማንነት ቀውስ ለእኔ ምንም ያልመሰለኝ ምን ሆኜ ነው?’ ብዬ ውሎ አድሮ ባሻዬን ስጠይቃቸው፣ ‹‹ዓይን እኮ ራሱን አያይም። ቅርብ ነሃ። ተላምደኸው እየኖርክ ነው። ገና ብዙ ጉድ የሚሠራን ይኼው መላመድ ነው። ጠብቅ ባሻዬ ምን አሉ ትላለህ?›› ብለውኛል። እናም ከመልመድ ለመሸሽ መሰደድ አለብን? ‘ሳይቃጠል በቅጠል’ እያለ? ለስደትስ የሚገፋፋን ይኼ እንደሆን ተጠንቷል? ወይስ ስደትን በተመለከተ ሕገወጥ ደላሎች ብቻ ናቸው ተጠያቂዎቹ? “What is wrong with us?” ካላልኩ ጆሮም አላዘገኝ መሰል!
እንሰነባበት። ከባሻዬ ልጅ ጋር የተለመደችዋ ግሮሰሪ ተሰይመናል። ‹‹ምግብማ ሞልቷል…›› ይላል አንጋፋው ጥላሁን ገሠሠ። ከወደ ጥግ አንዱ ዘፈኑን አብሮ እየዘፈነ ቆይቶ፣ ‹‹እኔ ቤት ግን የለም። ያንተ ቤት ቡፌ ቢሆን የእኔ ቤት አልሞላም ጋሼ…›› ይላል። ‹‹ዝም አትልም አንተ ሰካራም?›› ሲል ሌላው ከወዲያ ማዶ ደግሞ አንዱ፣ ‹‹ለምን ዝም ይላል? አንተ ባፈንከው መንግሥት እየተሰደበ እንዲኖር ነው? ዝም ከምትል ጩህ!›› ይላል። ወዲያው ነገሩ ይረሳና ወከባው፣ ሳቁና ግርግሩ ይቀጥላል። ዘፈኑ ይጮሃል፣ ብርጭቆው ይጋጫል፣ ጠርሙሱ ይንኳኳል። ዕድሜ ይሄዳል፣ ጊዜ ይሮጣል፣ ምሽቱ ይነጉዳል። ያለወትሮዬ ጥጌን ይዤ የግሮሰሪዋን ትዕይንት እያየሁ ስለኖህ መርከብ አስባለሁ። በጥፋት ውኃ በወጀቡና በእንግልቱ መሀል በባህሪ እጅግ የሚቃረኑ አራዊትን አጉራ ከፅንፍ ፅንፍ የሚለያይ ርዕዮተ ዓለም ያላቸውን እንስሳት ተሸክማ፣ 40 ቀናትና 40 ሌሊቶች የተንሳፈፈችበት ሚስጥር ይፈታልኝ ይመስል እቃብዛለሁ። ሲበዛብኝ ለባሻዬ ልጅ የማስበውን እነግረዋለሁ። ‹‹የአንዱን ሕመም አንዱ ያንዱን ሸክም ሌላው መሸከም ነዋ የኖህ መርከብ ሚስጥር ሊሆን የሚችለው። መቻቻል፣ መደማመጥና መከባበር ባይኖር ኖሮ ዘር ይተርፍ ነበር ታዲያ?›› ይለኛል። ታዲያ ዛሬ እኛ ምን ነክቶን ነው ከአውሬ የማይሻል አመል እየተጠናወተን የመጣው? መቻቻል፣ መከባበርና መደማመጥ ምነው አቃተን? ይኼንን እያሰብኩ ቢራዬን ስጨልጥ ምሽቱ ቢገባደድም፣ የማላውቀው ስሜት ተናገር ተናገር ይለኛል፡፡ በእንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ አለመናገርን እመርጣለሁ፡፡ መናገር ከጀመርኩ ማቆሚያ የለኝም፡፡ ወዳጅና ጠላት ሳልለይ ሁሉንም አንድ ላይ በሞቅታ በነገር እዠልጥና መቀያየም ይመጣል፡፡ የባሻዬ ልጅ በመገረም እያየኝ ‹‹ምን ሆንክ?›› አለኝ፡፡ ምን እያሰብኩ እንደሆነ ብነግረው ነገር ሊቀጥል ነው፡፡ ‹‹ምንም›› አልኩት፡፡ ነገር ነገርን እየወለደ ለምን እንቸገር? መልካም ሰንበት!