Friday, December 9, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊ‹‹ውበትን ፍለጋ››

  ‹‹ውበትን ፍለጋ››

  ቀን:

  ቀዶ ሕክምና ወደሚደረግበት ክፍል የሚወሰደው ኮሪደር ላይ ሁለት ሴቶች ቆመዋል፡፡ ግንባራቸው ድረስ በሻሽ ተሸፍኗል፡፡ አንደኛዋ የሕክምና ካርድዋን በፌስታል አንጠልጥላ ይዛለች፡፡ የፊቷ ቆዳ ላይ ጥቁረት ይታያል፡፡ ወደ ሕክምና ክፍሉ ለመግባት መቸኮሏ ገጽታዋ ላይ ይነበባል፡፡ ከኮሪደሩ ትይዩ የሚገኘው ክፍል ታካሚዎች ቁጭ ብለው ተራቸውን የሚጠበቁበት ነው፡፡ በዚህኛው ክፍል አምስት የሚሆኑ ሴቶች ፈንጠር ፈንጠር ብለው ተቀምጠዋል፡፡ በሃያዎቹ የዕድሜ ክልል የምትገኝ ወፈር ያለች ወጣት ተራዋ በመድረሱ ወደበሩ ተጠግታ ተቀምጣለች፡፡

  ተወልዳ ያደገችው እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች እናት ነች፡፡ ሁለቱም ልጆቿን የተገላገለችው በቀዶ ሕክምና ነበር፡፡ ውፍረቷም ከወሊድ በኋላ የመጣ መሆኑን ትናገራለች፡፡ ክብደቷ 89 ኪሎ ግራም ሲሆን እሷ ግን ከ60 ኪግ በላይ መሆን አትፈልግም፡፡

  ይህንን ለማሳካትም ውፍረት ያጠፋሉ የተባሉ ነገሮችን ሞክራለች፡፡ በየስፖርት ቤቱ በመዘዋወር ስፖርት ሠርታለች፡፡ ውፍረት ይቀንሳሉ የተባሉ የተለያዩ ሻይ ቅጠሎችን ከባህርማዶ እያስመጣች ተጠቅማለች፡፡ ነገር ግን አልተሳካላትም፡፡ ክትትሏን ለተወሰኑ ቀናት ካቋረጠች ክብደቷ ይብሱን ይጨምራል፡፡ መላ ስታጣለት አሜን ብለ ተቀብላ ነበር፡፡ ነገር ግን ክብደቷ የሰውነት ቅርጿን ከማበላሸት ባለፈ ሌላ መዘዝ አስከተለ፡፡ ውፍረቷ የሚበዛው ሆዷ አካባቢ ነው፡፡

  ስትወልድ ቀዶ ሕክምና ተደርጎ የተሰፋበት ላይ ቦርጯ ይተኛል፡፡ ይህም ከጊዜ ወደ ጊዜ ሕመም ይፈጥርባት ጀመረ፡፡ ሐኪሟን ስታማክርም ቦርጯ የሚተኛበት ቦታ ኢንፌክሽን እየፈጠረ መሆኑና ይህም ለከፋ አደጋ እንደሚዳርጋት በማስረዳት በተቻላት ሁሉ ክብደቷን እንድትቀነስ አስጠነቀቃት፡፡ በመሆኑም ከዚህ ቀደም ሲወራለት ወደ ሰማችው ልዩ ልዩ የፕላስቲክ ሰርጀሪ ወደሚሠራው ‹‹አይኮን ልዩ ክሊኒክ›› ለመሄድ ወሰነች፡፡

  በክሊኒኩ ቁጭ ብላ ተራዋን ስትጠባበቅ ሰዓታት አልፈዋታል፡፡ እንደሷ ያሉ ጥቂት የማይባሉ ሴቶች ቀዶ ሕክምናቸውን ጨርሰው ሲወጡ ምን ዓይነት ስሜት እንደሚፈጥር ትጠይቃቸዋለች፡፡ ተራ እስኪደርሳትም በተስፋ ትጠባበቃለች፡፡ በክሊኒኩ ማክሰኞ እና ሐሙስ ቀን በርካታ ታካሚዎች የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ያገኛሉ፡፡ ሥራ የሚበዛበትና ከወትሮው በላይ ቁጥር ያላቸው ሰዎች የሚገኙበት ቀን ነው፡፡ ግልጋሎቱን ለማግኘት ረዘም ያለ ቀጠሮ መጠበቅ ግድ ይላል፡፡

  እንደ ወይዘሮዋ አገላለጽ የቀዶ ሕክምና የሚሠራውን ዶክተር ለመግኘት አንድ ወር ይፈጃል፡፡ በቀጠሮ በወሩ ከተገኙ በኋላ የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠንና የቀዶ ሕክምና ሁኔታ ይገለጽላቸዋል፡፡ በዚህ ሥርዓት ለማለፍ 200 ብር የሚያስከፍል ሲሆን፣ ወር ሙሉ አልጠብቅም ላለ ግን ሌላ አማራጭ አለ፡፡  ተጨማሪ 200 ብር በመክፈል የአንድ ወር ጊዜውን ማሳጠር ይቻላል፡፡ እሷም ካለባት አስቸኳይ ጉዳይ አንፃር ተጨማሪ 200 ብር በመክፈል ዶክተሩን ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ ነበረች፡፡

   ምንም እንኳን የሕክምናውን መደበኛ ወጪ ከዶክተሩ ባትሰማም ከ20 እስከ 30,000 ብር እንደሚያስፈልጋት ከዚህ ቀደም ከታከሙ ሰዎች ሰምታለች፡፡ ይሁን እንጂ በሕክምና ክፍሉ ካሉ ታካሚዎች ጋር ስትወያይ ባገኘችው መረጃ ከ30,000 ብር በላይ ሊያስወጣት እንደሚችል ተነግሯታል፡፡ ‹‹በዚህም አቅሙ ካላቸው በስተቀር ሌሎች ሕክምናውን ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡ በጣም ውድ ነው፤›› ትላለች

  ክሊኒኩ በተፈጥሮ አልያም በአደጋ ፊት ላይ የተፈጠረ ችግርን ማስተካከል፣ የዕርጅና ምልክቶችን ማስገወድ፣ የዓይን እብጠትን፣ አፍንጫ የአገጭና የቆዳ ችግሮችን ማስተካከል፣ ጡት ማቃናት እና መጠኑን መቀነስ መጨመር ንቅሳት ማጥፋት ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል ናቸው፡፡ በርካታ ሰዎች አገግሎቱን ለመግኘት ወደ ክሊኒኩ ብቅ ይላሉ፡፡

  አብዛኛዎቹ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች  ሴቶች ቢሆኑም አልፎ አልፎ ወንዶችም ብቅ ይላሉ፡፡ የ19 ዓመቱ መርዋን አህመድም አንዱ ነው፡፡ መርዋን የሁለት ዓመት ልጅ ሳለ ነበር ከብስክሌት ላይ ወድቆ ከንፈሩ ላይ የመሰንጠቅ አደጋ የደረሰበት፡፡ አደጋው እምብዛም የከፋ አልነበረም፡፡ እሱም ቢሆን ብዙ ትኩረት አይሰጠውም ነበር፡፡ ነገር ግን ዕድሜው ከፍ እያለ ሲመጣ ገጹ ላይ የፈጠረው መጠነኛ ልዩነት ያስከፋው ጀመር፡፡   ፈገግ በሚል ጊዜ ጐልቶ ይታይ ስለነበር በመሳቀቅ ከንፈሩን ይሸፍናል፡፡

  ወላጅ እናቱንም መላ እንድትፈልግለት ዘወተር ይጎተጉታት ነበር፡፡ ስለ ክሊኒኩ እንደሰሙም ሕክምናውን በአፋጣኝ ለማግኘት ወሰኑ፡፡ ከሦስት ሳምንታት በፊትም ከቦታው ደርሰው ሕክምናውን ማግኘት ችለዋል፡፡ ለአጠቃላይ ሕክምናው 9,500 ብር የከፈሉ ሲሆን፣ ቀዶ ሕክምናው 50 ደቂቃዎች ያህል ፈጅቷል፡፡ እንደወጣም ቁስሉ እስኪድንለት መናገርም ሆነ  መመገብ አይችልም ነበር፡፡ የሚያስፈልገውን ሁሉ ለእናቱ በምልክት ማስረዳት የግድ ሆኖበት ነበር፡፡

  በአንድ ጊዜ የቀዶ ሕክምና ሥራ የሚያልቅ እንዳለ ሁሉ ተደጋጋሚ ሥራዎች የሚጠይቁ የሕክምና ዓይነቶችም አሉ፡፡ ንቅሳት የማጥፋት ሥራ ረዘም ያለ ክትትል ከሚያስፈልጉት አንዱ ነው፡፡ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች እንደሚሉት ከሆነ ክሊኒኩ አገልግሎት መስጠት ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን የሚመላለሱ ታካሚዎች አሉ፡፡ ይህም ተሰፋ የሚያስቆርጥ ሲሆን በየሕክምናው የሚደረግ ክፍያም ከአቅማቸው በላይ እንደሆነ ቅሬታቸውን ያሰማሉ፡፡ ጥቂት የማይባሉ ታካሚዎች በአቅም ማነስ አኳያ ሕክምናውን ጀምረው ከዳር ሳይደርሱ ይተውታል፡፡

  ተወልዳ ያደገችው ጎንደር አካባቢ ነው፡፡ እንደ አካባቢው ባህልም ውበቷን ቤተሰቦቿ በመስቀል ንቅሳት ለማጉላት ሞክረዋል፡፡ አዲስ አበባ ከመጣች ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ከተሜነት ከገባት በኋላ የንቅሳቷ ውበት አልታያትም፡፡ ይልቁንስ የምታጠፋበትን መንገድ ማፈላለግ ጀመረች፡፡ አንድ ቀን የቴሌቪዥን ፕሮግራም በመከታተል ላይ ሳለችም የአይኮን ክሊኒክ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል ንቅሳት ማጥፋት እንደሆነ ተመለከተች፡፡

  ወዲያውም 500 ብር ከፍላ የመጀመሪያውን ሕክምና አገኘች፤ በቀጣይ ወር ቀጠሮም የ100 ብር ቅናሽ ተደርጎላት በ400 ብር ቀጣዩ ሕክምና ተደረገላት፡፡ አሁንም ሕክምናዋን በመከታተል ላይ ትገኛለች፡፡ ሱቅ ጠብቃ የምታገኘው የወር ገቢ 1,500 ብር ነው፡፡ እስከ አንድ ዓመት ከሰባት ወር ያህል በቀጠሮ ተመላልሳለች፡፡ እስካሁን ከ8,000 ብር በላይ ለሕክምናው አውጥታለች፡፡ የሕክምናው ዋጋ ውድ ነው የምትለው ታካሚዋ አንዳንዴ በአቅም ማነስ ቀጠሮዋን እንደምታሳልፍ ትናገራለች፡፡

  ‹‹የኔ ንቅሳት ትንሽ ናት፡፡ ነገር ግን ከኔ በላይ ሰፊ ንቅሳት ያለባቸው ሰዎች ይመጣሉ፡፡ አንዷ ጓደኛዬ ንቅሳቷ ሰፊ በመሆኑ የመጀመሪያ ሕክምና የተደረገላት በ1,500 ብር ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙ ተመላልሳ እስከ 30,000 ብር ድረስ አውጥታለች፡፡ አሁንም እየተመላለሰች ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ በኋላ ብዙም አትገፋበትም፡፡ ከአቅሟ በላይ ሆኗል›› በማለት በመመላለስ የሚወጣው ወጪ ከአቅም በላይ መሆኑን ትናገራለች፡፡

  የአይካ ልዩ ክሊኒክ መሥራች ዶ/ር ቴዎድሮስ መሰለ በአገር ውስጥ መሥራት ከመጀመራቸው በፊት አሜሪካ በሚገኘው ሲደርሳንጎ ሆስፒታል  ዳይሬክተር ሆነው አገልግለዋል፡፡ እንደሳቸው ገለፃ ክሊኒኩ የፕላስቲክ እና የቫስኩላር (የደም ሥር) ቀዶ ሕክምናዎችን ይሠራል፡፡

   የደም ሥር ቀዶ ሕክምና ለኩላሊት ዲያሊስስ (ደም ለማጥራት) የሚውል የፌስቱላ ቀዶ ሕክምና ዓይነቶች ይሠራል፡፡ ምንም እንኳን ዕቃዎችን ወደ አገር ለማስገባት የሚገጥማቸው ውጣ ውረድና ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር ለመሥራት አስቸጋሪ ቢሆንባቸውም በአገር ውስጥ ከገመቱት በላይ መሥራት መቻላቸውን ይናገራሉ፡፡

  በሳምንት ከ15 እስከ 25 የሚደርሱ ቀዶ ሕክምናዎችን ይሠራሉ፡፡ ለደም ሥር ቀዶ ሕክምና፣ ጠባሳ ለማጥፋት፣ ከንፈር ለመቀነስ ወደ ማዕከሉ የሚመጡ ሰዎች አብላጫውን ቁጥር ይይዛሉ፡፡ አልፎ አልፎም ምንም ዓይነት ችግር የሌለባቸው ሰዎች ወደ ክሊኒኩ የሚመጡ ቢሆንም ‹‹ችግሩ ያለው ጭንቅላታቸው ውስጥ በመሆኑ አላስተናግዳቸውም›› ይላሉ፡፡ ለተጨማሪ ቀዶ ሕክምና የሚመለሱም አሉ፡፡ ‹‹እነዚህን ደግሞ እንደ አስፈላጊነቱ እናስተናግዳቸዋለን፤›› ብለዋል፡፡

  እንደ እሳቸው ገለጻ፣ አብዛኛው ሥራ የሚሠራው ለውበት በመሆኑ ውድ አይደለም፡፡ በሌላው ዓለም ታካሚዎች እዚህ ከሚከፈለው በብዙ እጥፍ ይከፍላሉ፡፡ በሌላ በኩልም ተደጋጋሚ ሕክምና የሚያስፈልጋቸው ታካሚዎች ተጨማሪ ገንዘብ ለመክፈል ይገደዳሉ፡፡ ይህ የሕክምናው ባህሪም ነው፡፡ አንዳንድ የሕክምና ግብዓቶችም በውድ ዋጋ የሚገቡ በመሆኑ የሕክምናው ዋጋም ከዚያ አንፃር ሊጨምር ይችላል፡፡

  ቴክኖሎጂው በአገር ውስጥ መተግበር ከጀመረ ጥቂት ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ተደራሽነቱን ለማስፋትም ዶ/ር ቴዎድሮስ የተለየዩ እንቅስቃሴዎችን ጀምረዋል፡፡ ‹‹በርካታ ሰርጂኖችን ማፍራት እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህም አንድ ሆስፒታል እየገነባሁኝ ነው፡፡ በዚህ ሁለት ዓመት ውስጥ ሥራ የሚጀምር ሲሆን፣ በሙያው ብቃት ያላቸው ዶክተሮችን ከውጭ በማምጣት እንዲያስተምሩ አደርጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋና ሥጋቱ

  ኦሮሚያ ክልል ከቀውስ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው ይመስላል፡፡ ከ200 በላይ...

  እናት ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

  መጠባበቂያን ሳይጨምር የባንኩ የተጣራ ትረፍ 182 ሚሊዮን ብር ሆኗል እናት...

  ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

  ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...