Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየሚዲያውን ጉዳይ የረሱትን ሰዎች ሚዲያው አልረሳኋችሁም ይበላቸው

የሚዲያውን ጉዳይ የረሱትን ሰዎች ሚዲያው አልረሳኋችሁም ይበላቸው

ቀን:

በበሪሁን ተሻለ

አዲስ አበባ፣ በየቦታው፣ በየቤቱ፣ በየጓዳው፣ በየአደባባዩ በየሬዲዮው ብዙና ልዩ ልዩ ነገር የተባለውንና የተባለለትን የመንግሥታቱ ድርጅት ድግስና ግብዣ የሆነውን ሦስተኛውን ‘ፋይናንሲንግ ፎር ዲቨሎፕመንት ኮንፈረንስ’ አስተናግዳለች፡፡ ኮንፈረንሱም የአዲስ አበባ የድርጊት አጀንዳ ተብሎ የተሰየመ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ የዚህ ዓለም አቀፋዊ ኮንፈረንስ ‘ሎጎ’ ራሱ ስብሰባው የሚካሄድበትን “አምሳያ የሌለው” ሥፍራ ለማንፀባረቅ የኢትዮጵያን ነባር የክብርና የጌጥ ምልክቶች ተጠቅሟል፡፡ የሎጎው (የብራንዱ) አጠቃቀም የመንግሥታቱ ድርጅት መመሪያ እንደሚያስረዳውና ማንም እንደሚያውቀው የዚህ ኮንፈረንስ ሎጎ ቀለሞች የኢትዮጵያ ናቸው፡፡

አራት ቀናት የፈጀው ስብሰባ ተሳታፊዎች የአገርና የመንግሥት መሪዎች፣ የውጭ ጉዳይ እና/ወይም የገንዘብ ሚኒስትሮች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አግባብ ያላቸው ተቋማዊ ባለድርሻ አካላት/ባለጉዳዮች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የንግድ ሥራና የሲቪል ማኅበረሰብ ተወካዮች፣ ወዘተ ናቸው፡፡ ለዚህ ስብሰባ ለራሱ የተዘጋጀው የ(አስተናጋጅ አገር) መንግሥት የልዑካን የእጅ መጽሐፍ እንደሚገልጸው፣ የአዲስ አበባ 143 ሆቴሎች እና 53 እንግዳ ማረፊያዎች (8,044 + 880)  በድምሩ 8,924 የመኝታ ክፍሎች የተዘጋጁበት ስብሰባ ነው፡፡

እነዚህና ሌሎችም ከስብሰባው ጋር ተያይዘው የሚነሱ የተለያዩ ጉዳዮች በገዛ ራሳቸው ምክንያት የማይናቁ የመነጋገሪያ ጭብጦች ቢሆኑም፣ ዋናው የስብሰባው ዓላማና ግብ ወደ ጎን ተገፍቶ፣ ወይም በአንፃራዊነት በእንጥፍጣፊ ጉዳዮች ተረግጦና ተውጦ የስብሰባውም ሆነ የአገር የልማት የዕድገት ውይይት ይድበሰበስ ዘንድ ረድቷል፡፡

ከሁሉም በላይ የሚያሳዝነው ደግሞ ከዋናው ጉዳይ መድበስበስ በላይ፣ የእንጥፍጣፊ ጉዳዮች አይሎ መውጣትና ከዋናው ጉዳይ የተለየ የገዛ ራሳቸውን የተለየ “ነፃነት” አውጀው ብቻቸውንና እርቃናቸውን የሚወሩ ድሎችና ገድሎች መሆናቸው ነው፡፡ የኦባማን የአዲስ አበባ ጉዞ በምሳሌነት እንውሰድ፡፡ ቀድሞ ነገር የኦባማ ወደ አዲስ አበባ መምጣት ከዚህ ስብሰባ ጋር በጊዜም በምክንያትም አይገናኝም፡፡ ኦባማ ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉት ጉዞ ከዚያ በፊት ረዥም ጊዜ የሚወስድ ቅድመ ዝግጅትና ዝግጅት የተደረገበት ነው፡፡ እንደሚታወቀውና በተቋቋመ አሠራር እንደሚደረገው ስንት የአሜሪካ የስቴት ዲፓርትመንት የፕሮቶኮል ሹማምንትና የ“USSS” (ሴኩዊሪቲ ሰርቪስ) ሠራተኞች አስቀድመው መጥተው፣ መላልሰው መጥተው አስሰው፣ አሳስሰው፣ ሰልለው አሰልለው ጊዜ ወስደው ውሳኔ የሚሰጡበት ይህንን ጉዞ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ የሰማነው የኋይት ሀውስ ፕሬስ ሴክሬተሪ እ.ኤ.አ. ጁን 19 ቀን 2015 በሰጠው መግለጫ ነው፡፡   

በዚህ መሠረት የኦባማ ጉዞ በአገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ጋባዡም የኢትዮጵያ መንግሥት ነው፡፡ የፋይናንስ ለልማት ስብሰባ ባለቤት ተመድ ነው፡፡ ጋባዡም እሱ ነው፡፡ ኦባማ ለዚህ ስብሰባ ቢመጡም ኢትዮጵያ የስብሰባው አስተናጋጅ አገር ብትሆንም እንግድነታቸው ለተመድ ነው፡፡ ኦባማ የሚመጡት ግን ለዚህ ስብሰባ አይደለም፡፡ የሚመጡትም ስብሰባው ከተጠናቀቀ በኋላ በጁላይ ወር መጨረሻ ላይ ነው፡፡

ከሌሎች እንጥፍጣፊ ጉዳዮች ጋር የሚምታታውና የሚድበሰበሰው የፋይናንሲንግ ፎር ዲቨሎፕመንት ኮንፈረንስ ዋናው ዓላማና ግብ በመጠናቀቅና በመዘጋጀት ላይ ከሚገኘው የመጀመሪያውና ሁለተኛው የአገር የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር ግንኙነት ያለው የልማት ጉዳይ ነው፡፡ የሚሊኒየሙን የልማት ዕቅድ ከሚቀበለውና ከሚተካው ከ“SDG” ጋር ጉዳይ ያለው ታላቅ የውይይት መድረክ ነው፡፡ በአገር ደረጃ የምንጠይቀውንና መጠየቅ ያለብንን ጥያቄ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠይቅ ስብሰባ ነው፡፡

ልማት ሊሳካልን ቀርቶ ከረሃብ የማምለጥ ጥያቄ ዋናው ችግራችን እስከመሆን ገዝፎ ብዙ ዘመናት አሳልፈናል፡፡ የአገሪቱን ሶሲዮ ኢኮኖሚያዊ ሕይወት፣ አገራዊ ሀብታችንን (ቁሳቁስ፣ ገንዘብ፣ ጥበብ፣ ዕውቀትና የሥራ ኃይል) ለዘለዓለምና ዛሬም ጭምር ከተጠናወተው፣ ከቡዘና እየቀሰቀሰ፣ ከብክነት እየተከላከለ፣ የውጭ ካፒታልን እየሳበ ልማት የማቀጣጠል እርግብግቢት መፍጠር የቻለ ራዕይ፣ ፖሊሲና ፕላን አለን ወይ? የስብሰባው ዓላማ በአጭሩ ይኼው ነው፡፡

ኢትዮጵያ ያስተናገደችውንና ‘የአዲስ አበባ አክሽን አጀንዳ’ የተባለውን ውሳኔ ያሳለፈውን ስብሰባ ምንነት ለመረዳት ከስብሰባው ባለቤት ከመንግሥታቱ ድርጅት በመነሳት ጉዳዩን በዝርዝር እንመለከታለን፡፡ በ1945 ዓ.ም. የተመሠረተው የመንግሥታቱ ድርጅት እጅግ በጣም አብዛኛው አገሮች በማኅበርተኝነት የሚገኙበት እጅግ በጣም የተለቀው (ትልቁ) ዓለም አቀፋዊ ድርጅት ነው፡፡

በዓለም ላይ ሰላምንና ደኅንነትን (ሴኩውሪቲ) ለማደላደልና ለመጠበቅ፣ ሁላችንንና መላውን ዓለም የሚነኩትን ችግሮች በጋራ እንድናስወግድ ለማገዝ፣ የሁሉንም ሰዎች ሰብዓዊ መብቶች የማክበርና የማስከበር ጉዳይን ለማንገስ፣ እንዲሁም አገሮች ለዚህ ዓላማ አብረውና ተባብረው እንዲሠሩ እገዛ ለመስጠት የተቋቋመና አደራ የተሰጠው ድርጅት ነው፡፡

ኢትዮጵያ የመንግሥታቱ ድርጅት መሥራች አባል መሆኗ፣ የእዚህን ማኅበር “መተዳደሪያ ወደ ሳንፍራንሲስኮ በላክናቸው መላክተኞች አማካይነት አብራ…” የሠራች አገር መሆኗ፣ መተዳደሪያ ደንቡ (ቻርተሩ)ም በ1937 ዓ.ም. በፓርላማ ቀርቦ “እንዲስማሙበት ከተደረገ በኋላ” መፅደቁ ብቻ ላይ ያልተወሰነ ፅኑ እምነት ያላት አገር ናት፡፡ ይህንን ቁም ነገር ከጥንት ከጥዋቱ ጀምሮ በሊግ ኦፍ ኔሽን ዘመን ጄኔቭ ላይ በቀድሞው የዓለም መንግሥታት ማኅበር ፊትም (ሰኔ 30 ቀን 1928 ዓ.ም.) የተናገሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ብቻ አይደለም፡፡ እሳቸውም ቢሆኑ ያኔ ከቁጥር አልገባ ያለውን ከጊዜ በኋላ ግን ታሪካዊ ብቻ ሳይሆን ተዓምራዊ ንግግር ሆኖ የሚከበረውን ዛሬ ለጥቅስ የበቃውን ጉዳይ ተናገሩ፡፡

በሕግ የመገዛት፣ በውል የመተዳደር፣ ለተስማሙበት ቃል ኪዳን የመፈጸም ነገር የኢትዮጵያ የግል ጉዳይ የኢትዮጵያ የራሷ ብቻ ሆኖ የማይቆጠር ስለመሆኑ ጀርመን አውሮፓ ላይ ጦር ስታስነሳ ተጋለጠ፡፡ ኢትዮጵያ ላይ የተጫረው እሳት ለሁሉም ሲዳረስ ታወቀ፡፡

በንጉሠ ነገሥቱ የሥልጣን ዘመን በመጀመሪያ ደረጀ ትምህርት ቤት ውስጥ ገና ጥርሳቸውን ሳይነቅሉ፣ “የዓለም ማኅበር ለዘለዓለም ይኑር ለሰላም ለፍቅር” የሚለውን መዝሙር መዘመር የግድና የትምህርት ግዳጅ ሆኖ ይዘምር ከነበረው የመጨረሻው ትውልድ ሰዎች መካከል አንዱ አቶ መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ በሆነ የታወቀ አጋጣሚ በአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባ ወቅት በአገርና በመንግሥት መሪዎች ፊት የተናገሩት ነገር ለጥቅስ የበቃ ነው፡፡ የብቻ መሆንን፣ የብቸኝነትን ጉዳት ከኢትዮጵያ በላይ አውቃለሁ የሚል ና ወዲህ በለኝ (ዓይነት) ነበር ያሉት፡፡ የኅብረትን የማኅበርን ፋይዳ ሲያስረዱ፡፡

እ.ኤ.አ. በ2000 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (የያኔው የ189) አባል አገሮች የሚሊኒየም ዲክላሬሽን የተባለውን ውሳኔ ለማፅደቅ ተሰባሰቡ፡፡ ይህ ዲክላሬሽን ድህነትን የሚዋጋ ዓለም አቀፋዊ ኅብረትና አንድነት ፈጠረ፡፡ ዛሬ የሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ብለን የምንጠራቸውን ግቦች ያወጣውና ያወጀው በዚህ ስብሰባ ነው፡፡

የሚሊኒየም የልማት ግቦች (ምዕተ ዓመትና ሚሊኒየም እየተምታታብን የምዕተ ዓመቱ የልማት ግቦች የምንላቸው) የሚባሉት ድህነትንና ረሃብን ለመዋጋት፣ እንደ ኤችአይቪ/ኤድስ ያሉ በሽታዎችን ለመግታት፣ የፆታ እኩልነትን ለማራመድና ከትምህርት ቤት የሚወድቁ የተማሪዎችን የምጣኔ ቁጥር ለመቀነስ በመንግሥታትና በዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች መካከል ያለውን የጋራ ትጋትና ጥረት መምራትና ማስተባበር ይችል ዘንድ መንግሥታት አምጠው የወለዱዋቸው ስምንት ግቦች ናቸው፡፡

እነዚህ ስምንት ግቦች እ.ኤ.አ. በ2015 ይደረስባቸዋል ተብለው እምነት የተጣለባቸው ነበሩ፡፡ ዲሴምበር 31 ቀን 2015 ለሚጠናቀቀው የግብና የስኬት ቀን በይፋ የኋሊት መቆጠር የተጀመረው ከአፕሪል 5 ቀን 2013 አንስቶ አንድ ሺሕ ቀን ቀረው ተብሎ ነው፡፡ የዛሬ ዓመት ገደማ ኦገስት 18 ቀን 2014 ላይ 500 ቀን ቀረው ብለን የኋሊት መቁጠራችንን ቀጥለን እነሆ ዛሬ (በያዝነው ሳምንት) 150 ቀናት ቤት ውስጥ ገብተናል፡፡

ከጊዜ ወደ ጊዜ መንግሥታት ለመንግሥታቱ ድርጅት እነዚህ ስምንት ግቦች ላይ ለመድረስ ትጋታቸውንና ጥረታቸውን (ያሉትን) ሪፖርት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ድርጅቱም የመንግሥታቱን አረማመድና ግስጋሴ ሲገመግም ቆይቷል፡፡

ዲሴምበር 31 የሚያልቀው የኋሊት ሲቆጠር ከአምስት ወር በታች የቀረው የግቡ ቀን ሲያበቃ ምን ይሆናል? እ.ኤ.አ. ከ2015 በኋላስ ምን ይደረጋል? የሚሊኒየሙ የልማት ግቦች ላይ ለመድረስ በዓለም ዙሪያ የማይናቅ ግስጋሴና ዕርምጃ የተወሰደ ቢሆንም፣ ከተመዘገበው ድል ይልቅ ያልተነካው ችግር እንዳለ በመሆኑ በግዳጅና በግዴታ ገና ብዙ መሥራት ይጠይቃል፡፡ በዓለም ላይ እጅግ በጣም ብዙ ሕዝብ (ከአንድ ቢሊዮን ሕዝብ በላይ) ገና በድህነት አረንቋ ውስጥ ነው፡፡ ይህን ያህል ግዙፍ ሕዝብ ከእኩልነት መብት ርቆ ይኖራል፡፡

በሚለጥቁት 15 ዓመታት ውስጥ (ከ2016 እስከ 2030) ድረስ ሊደረስባቸው የሚገቡ የልማት ቅደም ተከተሎችን የተመለከተ የመንግሥታቱ ድርጅት አዳዲስ ጅምሮችን ሲያስተዋውቅና ሲያራምድ ቆይቷል፡፡ የድኅረ 2015 አጀንዳ የሚባሉትም እነዚህ ቅደም ተከተሎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ ያህልም የከፋ ድህነትን ጨርሶ ማስወገድና ለሁሉም እኩል ዕድሎችን መፍጠር በእነዚህ ቅደም ተከተሎች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው፡፡

ከአንድ ዓመት በፊት ጁላይ 2014 ውስጥ፣ የሚሊኒየም የልማት ግቦች ዘመን ካበቃ በኋላ፣ እነዚህን የሚተኩ ግቦች የያዘ ረቂቅ ሰነድ ያሰናዳውን ስምምነት ላይ የደረሱት የተመድ አባል አገሮች የሚቀጥሉት 15 ዓመታት ዋናው ዓላማ ፕላኔታችንን ለአደጋ ሳናጋልጥ፣ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ሕዝቦች ሻል ያለ ኑሮ እንዲያገኙ የሁሉንም ትጋትና ጥረት አቅጣጫ ማስያዝና መምራት መቻል ነው አሉ፡፡ የዶኪዮሜንቱ ይዘትና የመነሻ ስምምነታቸው ሁኔታዎችና ውለታዎችም እነዚህ ናቸው፡፡ ይህ ረቂቅ ሰነድ ሲፀድቅና ውስጡ የተካተቱት ግቦችም ልክና መልክ ሲይዙ የመንግሥታቱ ድርጅት አባል አገሮች የሚቀጥሉት 15 ዓመታት ተግባር እነዚህ ግቦች ላይ መድረስና እነዚህን አዳዲስ ግቦች መቀዳጀት ነው፡፡ የሚሊኒየሙን የልማት ግቦች የሚተኩት “SDG” (አዛላቂ የልማት ግቦች) የሚባሉትም እነዚህ ናቸው፡፡  

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ከመንግሥታቱ ድርጅት ስድስት ዋና ዋና አካላት መካከል አንዱ ነው፡፡ እያንዳንዱ አባል አገር አንድ ድምፅ የሚሰጥበት የሁሉም ማኅበርተኞቹ ጠቅላላ ስብሰባ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ መደበኛ የስብሰባ ጊዜ ሁሌም በየዓመቱ በሴፕቴምበር ወር ሦስተኛው ማክሰኞ ላይ ይጀመራል፡፡ የዘንድሮው (2015) የሴፕቴምበር ወር ሦስተኛው ማክሰኞ የሚውለው 15 ሴፕቴምበር ነው፡፡ መስከረም 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ማለት ነው፡፡

መስከረም 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ሥራውን በሚጀምረው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 70ኛው ጠቅላላ ጉባዔ ፕሮግራም መሠረት የሚሊኒየሙን የልማት ግቦችን የሚተካው አዲሱ የአዛላቂ የልማት ግቦች የድኅረ 2015 ዕቅድ የሚፀድቀው በዚሁ ጊዜ ነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ የተሰበሰበውና የአዲስ አበባ የድርጊት አጀንዳን ያፀደቀው ጉባዔ ዓላማም፣ የዚህን የድኅረ 2015 የልማት ዕቅድ የሚያስፈልገውን የፋይናንስ ጉዳይ መወሰን ነው፡፡ የነገሩ አመጣጥና የጉዳዩ ዝርዝር ይህ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የረዥም ጊዜ የዕድገት ፕላኖችን በዘመናዊ መንገድ “የሚያነቃቃ [ማንቃት ማለትም ኢኒሽየት ማድረግ] አዘጋጅቶና አደራጅቶ እንዲፈቀድ” እያደረገ የሚሠራ የፕላንና የልማት ሚኒስቴር አቋቁማ መሥራት የጀመረችው በንጉሠ ነገሥቱ ዘመን ነው፡፡ በየጊዜው አፍስሶ መልቀም፣ “ሀ” ብሎ እንደገና መጀመር ስለለመደብን እንጂ፣ የመጀመሪያው የአምስት ዓመት ፕላን ብለን መቁጠር የጀመርነው በ50ዎቹ ውስጥ በንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ዘመን ውስጥ ነበር፡፡ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በተፋጠነ አኳኋን ለማሳደግና ለማዳበር የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ገንዘብ (ካፒታል) በብዛት በልማት ሥራ ላይ እንዲውል ማድረግ፣ የግል ገንዘብ (ካፒታል) በሥራ ላይ እንዲውል ለማበረታታት የተለየ አስተያየት ማድረግና ከቀረጥ ነፃ የመሆን መብት የሚያስገኝ የሕግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል ብላ አገር ቆርጣ የተነሳችውም፣ ያኔ አንደኛውና ሁለተኛው የአምስት ዓመት የልማት ፕላን ብለን ድክ ድክ ባልንበት ዘመን ነው፡፡

ደርግ ሲመጣ እንደገና አንድ ማለት ተጀመረ፡፡ ኢሕአዴግ በ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ሥልጣን ሲቆጣጠር በ“ሥራ ላይ”  የነበረው የከ1976 እስከ 1986 ዓ.ም. የተዘረጋው የአሥር ዓመት መሪ ዕቅድ ነበር፡፡ ኢሕአዴግም በተራው “የመጀመሪያው የአምስት ዓመት (1998-2002) የልማት ዕቅድ” ያለው ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በፊት ያለውን ዘመን ነው (የዕቅድ ጥራዝ አንድ ዋና ሰነድ መግቢያ ይመለከቷል)፡፡

በዚሁ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሰነድ መግቢያ እንደተገለጸው፣ “የመጀመሪያው የአምስት ዓመት (1997-2002) የልማት ዕቅድ የመካከለኛ ዘመን ዕይታ ያለው ሆኖ ቢያንስ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግቦች ለማሳካት ታስቦ የተዘጋጀ ሲሆን የትግበራ ዘመኑ ተጠናቋል፡፡ በዕቅዱ የአምስት ዓመታት የትግበራ ዘመን ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገትና የማኅበራዊ ልማት ውጤቶች ተመዝግበዋል…” ይልና “የቀጣዩ አምስት ዓመት (2003-2007) የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በመጀመሪያው የአምስት ዓመት የልማት ዕቅድ ቋት የተተካ ሲሆን፣ ባለፉት አምስት ዓመታት የተመዘገበውን የኢኮኖሚ ዕድገት ከማስጠበቅ ባሻገር በሁሉም የልማት ዘርፎች የላቀ ውጤት እንደሚመዘገብባቸው ይጠበቃል፤” ይላል፡፡

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ ኦፊሴላዊ ሰነዶች “የምዕተ ዓመቱ” የልማት ግብ ብለው በሚጠሩት የ“ኤምዲጂ” ፍፃሜ የመጨረሻ ወራት ውስጥ ነች፡፡ ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም. የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመንም እነሆ በመጨረሻው የ2007 የዕቅድ ዓመት ውስጥ ነው፡፡ “የሚያስፈራው” ተከታዩና ሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ወይም ሦስተኛው የአምስት ዓመት የልማት ዕቅድ በዝግታና በጥልቀት ታስቦ፣ በለዘብተኛ ክርክር ተጣርቶ፣ በትዕግሥት እየተመላለሰ ተመክሮ ሳይወሰን 2007 ዓ.ም. እንዳያልቅ ነው፡፡ 2007 ዓ.ም. ራሱ የሚያልቀው መቼ ነው? ራሱ አንድ ችግር ነው፡፡ የኢትዮጵያ የ2007 የበጀት ዓመት ያበቃው ሰኔ 30 ቀን ነው፡፡ የ2008 የበጀት ዓመት ከሐምሌ 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሯል፡፡

የ2007 የካሌንደር ዓመት ከአንድ ወር በላይ ቢቀረውም፣ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱን ፓርላማው “አገሪቱ የምትመራበት ሕጋዊ የዕቅድ ሰነድ አድርጎ” ያፀደቀው ኅዳር 23 ቀን 2003 ዓ.ም. ነው፡፡ በዚህ መካከል አዲሱ ፓርላማ ከመስከረም መጨረሻ በኋላ ሥራውን ጀምሮ የሚያፀድቀው ከ2008 እስከ 2012 የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ገና ዝግጁና ስንዱ ሆኖ የመጀመሪያውን ዕቅድ የተካበትን መልክና ልክ፣ እንዲሁም ይዘት አግኝቶ በቦታውና በሥፍራው እንዲገኝ አልተደረገም፡፡

ከዚህ የባሰ የሚያሳስበው ግን ይህን የመሰለ ሰነድ አሁንም እንደተለመደው የሕዝብ ተሳትፎ የሌለበት መሆኑ ነው፡፡ እንደ መጀመሪያው (2003 እስከ 2007) ዕቅድ እንኳን በኦፊሴል መረጃ መሠረት በቂ ጊዜ አልተሰጠውም፡፡ ከ2003 እስከ 2007 ዓ.ም. ዕቅድ ከመስከረም 2002 ዓ.ም. ጀምሮ ያለውን ጊዜ ወስዶ የፀደቀው 2003 ዓ.ም. ኅዳር ውስጥ ነው፡፡ (ራሱን የዕቅዱን መግቢያ ይመለከቷል)

ምርጫ 2007 በዚህ ረገድ ለምን ከምርጫ 2002 እንደተለየ ባናውቅም 2007 ላይ የሚያበቃውን የአምስት ዓመት ፕላን ስለሚተካው ሌላ ፕላን አገር በወሬና በዜና ደረጃ መስማት የተጀመረው፣ ምርጫውና ውጤቱ አካቶ (ጨርሶ) ከተደመደመ በኋላ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በአገር ደረጃ የሚዘጋጀው ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድም (ወይም ሦስተኛው የአምስት ዓመት ፕላን) ሆነ የድኅረ 2005 የአዛላቂ የልማት ግቦች ዕቅድ ችግሮች ተመሳሳይና አንድ ዓይነት ናቸው፡፡ አገራዊውን ችግር ከዓለም አቀፋዊው ተመሳሳይ ችግር የሚለየው ጉዳይ ቢኖር የኛው ኋላቀርና የማያነጋግር የማያናግር መሆኑ ነው፡፡

ዓለም አቀፋዊው ችግር ከዚህ በተለየ ሁኔታ በሰፊው የሚነገርለትና የሚያነጋግር ነው፡፡ የዓለም አቀፋዊ የሚሌኒየሙ የልማት ግቦች ችግር የሚያነጋግረውና የሚያናግረው ደግሞ በዚያው በመንግሥታቱ ድርጅት ማዕቀፍ ውስጥ ጭምር ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብት ጉባዔ ራሱ የዚህ ዘመቻ ፊጻውራሪ ሆኖ እየሠራ ነው፡፡ ዩኔስኮም ሐሳብን በመግለጽ፣ በኢንፎርሜሽን ነፃነትና በነፃ ሚዲያ መብት ግንባር “የሚዋደቅ” ታጋይ ሆኗል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባለፉት 15 ዓመታት አነጋግሮ መነጋገሪያ ሆኖ ተወቅጦና ተብሎ ተብሎ ገኖ በወጣው ሐሳብ መሠረት፣ የሚሌኒየሙ የልማት ግቦች ዋነኛው ማነቆ መንግሥታዊ ተጠያቂነትን፣ የሰብዓዊና በተለይም ደግሞ ሐሳብን የመግለጽ፣ መረጃ የማግኘት ነፃነትንና የነፃ ሚዲያ መብትን የሚያገልሉ መሆናቸው ነው፡፡

የማሌኒየም የልማት ግቦች ድህነትን ማስወገድ፣ ሁሉን አቀፋዊ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ላይ ማቀዳጀት የመሳሰሉ የተቀደሱ ግቦች ቢያዙም እነዚህን ከሰብዓዊ መብቶች፣ ከመንግሥት የተጠያቂነት ግዴታ፣ የአገር ጉዳይ ከሚያገባው የመናገር፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብና የመቃወም መብት ከተቀናጀ የሲቪል ማኅበረሰብ ግዳጅ ጋር የሚያሠልፍና የሚዮቆላልፍ ግዴታ አላቋቋሙም፡፡ እንዲያውም መንግሥታት በትክክለኛ ስማቸው “Duty Bearer” (የግዴታ ባለዕዳዎች) ሕዝቦች ደግሞ የመብት ባለቤቶች መሆናቸው ይረሳና ብሎም ይረገጥና የመንግሥት ተጠያቂነትና ኃላፊነት ይድበሰበሳል፡፡ ሁሉም ነገር በግዴታ መወጣት ግዳጁ ውስጥ መለካቱ ይቀርና መንግሥት መልካም ፈቃዱ ሆኖ፣ በገዛ ሐሳቡ፣ ማንም ሳይጠይቀው፣ በችሮታው የሰጠው ተደርጎ እስኪታመንበት ድረስ የዘቀጠ ሐሳብና አሠራር ሰፍኗል፡፡

የሚሌኒየሙ የልማት ግቦች ሰብዓዊ መብትን ከግቦች ጋር በጥብቅና በሥርዓት ባለማስተሳሰራቸው፣ ከመንግሥት ግዴታም ጋር ባለማጣመዳቸው፣ እንዴት ያሉ ግቦች የአጋጣሚ መጫወቻና የማንም የፖለቲካ ፈቃድ መፈንጫ ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ ግብ ሁለት ዩኒቨርሳል (የሁሉም) የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ላይ ዓለምን ለማቀዳጀት የታቀደ ግብ ነው፡፡ ይህ ግብ ግን የመጀመርያ ደረጃ ትምህርትን ለሁሉም ነፃ ከማድረግ መብትና ይህንንም ነፃ ትምህርት ከመስጠት የመንግሥት ግዴታ ጋር ይቆራኛል፡፡ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች ሳይቀር በምዝገባ፣ በመጽሐፍ፣ በፎቶ ኮፒ በመዋጮ ስም በሚያስከፍሉት ገንዘብ ምክንያት “ነፃ” መሆኑ የቀረውን የትምህርት ሥርዓት የሚጠይቅ፣ ተጠየቅ የሚል የሕዝብ እንቅስቃሴ ይጠይቃል፡፡ የሚሌኒየሙ የልማት ግቦች መለካት ያለባቸውም በመጨረሻው ውጤት ላይ ብቻም አይደለም፡፡ ይህንን ውጤት ለማስመዝገብ የተደረገውን ተግባራዊ እንቅስቃሴም ከቁጥር ማስገባት፣ በውጤትነት የተመዘገበውን ነገር ያስከተለው ምክንያት የመንግሥት ላይ የተጣለው ግዴታ መሆኑም መመርመርና መጠየቅ አለበት፡፡

የዚህ ምክንያት ውጤቶች በአጋጣሚም በዕቅድም ሊመጡ ስለሚችሉ ነው፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ መንግሥትን የግዴታዎች ባለዕዳ ያደጉት የአገር ቤት የበላይ ሕጎችና ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች የሚያቋቁሙት የመንግሥት ግዴታ የውጤትን ብቻ ሳይሆን የባህርይ አረማመድን ጭምር ነው፡፡ መንግሥታት አስመዘገብነው የሚሉትን ድል የባህርይና የተግባር አረማመዳቸው ውጤት መሆኑን የማስረዳት ግዴታ ጭምር አለባቸው፡፡ ለምሳሌም ያህል በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በየቦታው የተጠቀሰው የ“መንግሥት ለጤና፣ የትምህርትና ሌሎች የማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለሕዝብ ለማቅረብ በየጊዜው እየጨመረ የሚሄድ ሀብት ይመድባል” ግዴታ የመንግሥት ባህርይና የተግባር አረማመድ ግዴታ አንድ ማሳያ ነው፡፡ መንግሥት የሚመድበው ሀብት በየጊዜው እየጨመረ እየሄደ ነው? ይህስ ምን ማለት ነው? ማለት፡፡

ዛሬ በአዛላቂው የልማት ግቦች መፅደቅ ዋዜማ ላይም ሆነ ከዚያም ቀደም ሲል እ.ኤ.አ. ከ2010 ጀምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚነሳው ‘ኤምዲጂን’ የሚመለከተው ነቀፌታና ትግል በ‘ኤስጂጂ’ ዘመን ዕቅድና ሰብዓዊ መብት ዕቅድ፣ የመንግሥት ተጠያቂነት የተነጣጠሉና የተጣሉ አይደሉም፡፡ ያለመንግሥት የተጠያቂነት ግዴታ ያለሰብዓዊ መብት፣ በተለይም ያለሐሳብን የመግለጽና የኢንፎርሜሽን ነፃነት ያለነፃ ሚዲያ መብት የሚሳካ ድኅረ 2015 ግብና አጀንዳ የለም ማለት የዓለም አቀፋዊው ንቅናቄ ድምፅና መታገያ መፈክር ሆኗል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ይህን ጉዳይ በጭራሽ አንሰማውም፡፡ አጀንዳም አላደረግነውም፡፡ በተለይ ሚዲያው የገባበት የዝምታ ሴራ ወይም ሚዲያውን ጭልጥ አድርጎ የወሰደው ከእርሳስ የከበደ እንቅልፍ የሚያስፈራና የሚያሳፍር ነው፡፡

የኢትዮጵያ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለሚዲያው የሰጠውን ቦታ የገመገመ፣ እያንዳንዱን የዕቅድ ዓመት የዕድገትና የትራንስፎርሜሽኑን ዕቅድ ዓመታዊ የአፈጻጸም ሪፖርት በአጠቃላይ የሚዲያውን ቦታ በተለይ መርምሮ ሐሳብና ትኩረት የሰጠ፣ በዚህ ላይ የተመሠረተ እንቅስቃሴ የፈጠረ ሚዲያ ማየት ቀርቶ የዚህን ጉዳይ ራሱ ለዜና ያበቃ አላየንም፡፡

የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ዘመን የመጠናቀቂያ ዓመት ለምርጫ 2007 ሥፍራውን ለቅቆ ስለነበር፣ ኢትዮጵያ በይፋ “ጂቲፒ” ሁለትን አጀንዳ ያደረገችው ከምርጫ ቦርድ ውጤት በኋላ ከዚያም ቆየት ብሎ፣ የዚህ ጉዳይ ገና “ዘንቦ አባርቆ አባርቶ” ከጨረሰ በኋላ ነው፡፡ የኦፊሴል ኢትዮጵያን (መንግሥት፣ የመንግሥት የሥልጣን አካላትና ባለሥልጣኖቻቸው እንዲሁም የመንግሥት ሚዲያዎችን) አጀንዳ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጉብኝት ጋር የተምታታው ዋናው ቁም ነገሩ ተዘንግቶ፣ “የኢትዮጵያ ገጽታ” ዋነኛ ጉዳዩ የሆነው የፋይናንሲንግ ፎር ዴቨሎፕመንት ስብሰባ አጀንዳ እስኪቀማው ድረስ፣ የአገር ዋና ወሬ ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ የሚደረገው “ውይይት”፣ “ምክክር” ነበር፡፡

የታወቀውና ሕዝቡን ያስመረረው ድርጅታዊ አሠራር ውጦት፣ የማስመሰል ወጉን እንኳን የገፈፈው ይህ “ውይይት” ሌላው ቀርቶ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ አረንጓዴ ወይም ነጭ ሰነድ ብሎ የሚያሳየውና በሕዝብ ውስጥ (እጅ) እንዲገቡ ያደረገው ረቂቅ ነገር የለውም፡፡

በዚህ መካከል ነው የፋይናንስ ፎር ዴቨሎፕመንት አጀንዳ “ጨዋታው”ን ያቋረጠው፡፡ የሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሚዲያው አጀንዳና የሦስተኛው የአዲስ አበባ የፋይናንስ ፎር ዴቨሎፕመንት ስብሰባ አጀንዳ ግን አንድ ጊዜ እንደሆነው፣ እንደ አሜሪካ የስፖርት ውድድርና እንደ ሳንፍራንሲስኮ የመሬት መንቀጥቀጥ የየቅልና አንዱ ሌላውን ወግድ የሚል አጀንዳዎች አይደሉም፡፡ (በአንድ ወቅት አሜሪካ ውስጥ የእነሱ የፕሪሚየር ሊግ አቻ የሆነ የስፖርት ውድድር የፍልሚያ ግጥሚያ ይካሄድ በነበረበት፣ የሁሉም ዓይንና አጀንዳ ይኼው ጨዋታ በነበረበት ወቅት ሳንፍራንሲስኮ ውስጥ መሬት ይንቀጠቀጣል፡፡ ወቅቱ የ24 ሰዓት ቴሌቪዥን አፍላ የወረት ወቅት ነው፡፡ ያም ባይሆን ለአሜሪካ ሕዝብ ለስፖርት አፍቃሪውም ቢሆን ከዚህ የበለጠ ጉዳይና የአገር ጉዳይ የለም፡፡ ቴሌቪዥኑ ሥርጭት በአንዴና ሳይታወቅ ተቀየረ)

የኢትዮጵያ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድም ሆነ የአዲስ አበባው ጉባዔ የነዋይን ጉዳይ የተነጋገረበት የድኅረ 2005 የአዘላቂ የልማት ግቦች ጉዳይ፣ በተለይ ሚዲያው ጉዳዬና የአገር ጉዳይ ብሎ አጀንዳ ሊያደርገው የሚገባው ነው፡፡

የሁለቱም ጥያቄ የአገርን ሀብት (ሕዝብን፣ የሥራ ኃይልን፣ ገንዘብን፣ ቁሳቁስን ጥበብን) ከቡዘና እየቀሰቀሰ፣ ከብክነት እየተከላከለ፣ የውጭ ካፒታልን እየሳበ ልማት የማቀጣጠል እርግብግቢት መፍጠር የሚችል ፖሊሲ ለማውጣት የሕዝብ ተሳትፎ የስፈልጋል፡፡ የሕዝብ ተሳትፎ ሲባል ደግሞ በ“ድርጅታዊ አሠራር” ወይም የ“የአደረጃጀቶች” ውሳኔ ማለት አለመሆኑን ምሎና ተገዝቶ ከተቀበለ ከመንግሥት ቁርጠኛነት መጀመር አለበት፡፡ ይህ ቁርጠኝነት ደግሞ ሲፈቀድ እሺ፣ አልፈቀድም ሲል ደግሞ እምቢ ከሚል የፓርቲም ሆነ የመንግሥት ዓይነት ዕጣ ፈንታ ጋር እንዳይቆራኝ፣ በሕግ የበላይነት ላይ የተመሠረተ የመንግሥትን የግዴታ ባለዕዳነት የሚያቋቁም ሥርዓት መመሥረት አለበት፡፡ እንዲህ ያለ ሥርዓት ደግሞ ከላይ “በኔ ይሁንባችሁ” ተብሎ የማረጋገጫ ቃል ስለተሰጠበት ብቻ፣ ከታችም ሕዝቡ “አንተን አምኜ” ብሎ የሚገላገሉት ጉዳይ አይደለም፡፡

በተለይ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባለ አገር፣ መንግሥት ሁልጊዜ በበዳይነትና በጨቋኝነት እንጂ በምንም ቀና ነገር በማይታወቅበት አገር፣ የማረጋገጫው ሥርዓት ይበልጥ ጥበቃና ሕዝብ ቆቅ ሆኖ የሚጠብቀውና የሚቆጣጠረው የሕዝብ ዕለታዊ ተግባር መሆን አለበት፡፡ ለዚህም ሰብዓዊ መብትን፣ ዴሞክራሲያዊነትን፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሐሳብን የመግለጽና መረጃ የማግኘት ነፃነትን፣ የነፃ ሚዲያ መብትን ከስም ጌጡ ይልቅ እስትንፋሱ ያደረገ ሥርዓት መኖር አለበት፡፡

ሕዝብ በዓይን፣ በጆሮ፣ በአንደበትና በብዕር አገዛዙ የሚያንቀባርራቸውን ችግሮች እያሳደደ መድረሻ የሚያሳጣበት እንቅስቃሴ ባልተቀጣጠለበት ሥርዓት ልማትን የሚያሳካ ተጠያቂነት ያለበት መንግሥት ሊኖር አይችልም፡፡ ይህ ጉዳይ ገና ከጅምሩና ከማንም አብልጦ ሊገባው የሚገባው ለኢሕአዴግ ነበር፡፡ ቀም ብሎ እንደተለገጸው መንግሥት ማለት ዋነኛና ቀንደኛ የሰብዓዊ መብቶች ደመኛ ጠላት ተደርጎ በሚታወቅበት አገር፣ ይህንን ለአንዴና ለመጨረሻው ለመለወጥ ቆርጦና ታግሎ ሥልጣን የያዘ መንግሥት አዲስ ምዕራፍ እንከፍታለን፣ የዴሞክራሲ ዘመን ይነግሳል ብሎ መነሳትና የተገባው ቃል ኪዳንና የተሰጠው ተስፋ ብቻ የሕዝቡን ታማኝነት እንደማያስገኝ ከሁሉም በላይ ግልጽ መሆን ያለበት ለኢሕአዴግ ነበር፡፡

መንግሥትና ሚዲያው ሁልጊዜም በተለይም የዕድገትና የልማት ዕቅድ ሲደገስ መጠየቅና መጠያየቅ አለባቸው፡፡ መንግሥት በላዩ ላይ የተቀመጡ ሰዎች የግል መሣሪያ መሆኑ አብቅቷል ወይ? በላዩ ላይ የተቀመጡ ሰዎች (ቡድኖች) ከሕዝቡ ፍላጎት፣ አስተያየትና ኡኡታ ውጪ የሚሠሩበት ሲሻሩ እንዳይቆጫቸው ጠባብ ዕቅዶቻቸውን የሚያራግፉበት አሠራር መጠበቂያና መከላከያ፣ መጠየቂያና መፋረጃ ተበጅቶለታል ወይ?

ሕግና ደንብ እንዳመቸ የሚጣሉና የሚነሱበትን የገዢዎችን ተግባር በፅናት የሚዋጋ፣ የሚዲያና የሕዝብ ባህል የሚያበጅ ግብ የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዳችን አካል ለማድረግ ቆርጠን ተነስተናል ወይ? ለሕዝብ እሪታ ምላሽ የመስጠት አደራና ግዴታ አፍጥጦ የመጣበት፣ መገናኛ ብዙኃን፣ የምርጫ አካላት፣ የመከላከያና የፖሊስ ተቋማት በፓርቲ ተቀፅላነት ውስጥ የማይወድቁበት ሁኔታ ይለማ ዘንድ የሚያግዝ ግቦች ጨምረናል ወይ? ብለው ነው፡፡

የልማት ዕቅዶችና የአምስት ዓመት ፕላኖች የረሱትን የሚዲያውን ዋናው ጉዳይ ሚዲያው ከሕዝብ ጋር ሆኖ አልረሳኋቸውም ማለት አለበት፡፡

 

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...