Friday, March 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ያልተፈቱት የግብር ሥርዓቱ ውስብስብ ችግሮቹና መፍትሔዎቹ በረዳት ፕሮፌሰሩ ዕይታ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ አንድ ሲምፖዚየም አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ ሲምፖዚየም ላይ የአሠሪው (የነጋዴው) አብይ ጥያቄዎች ናቸው ባሉዋቸው ሦስት ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን በማቅረብ አወያይቷል፡፡ ከቀረቡት ጥናታዊ ጽሑፎች ውጭ አንዱ የሲምፖዚየሙን ተሳታፊዎች ትኩረት የሳበው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ ጴጥሮስ ‹‹በታክስ አስተዳደር ላይ የሚታዩ ዋና ዋና ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው›› በሚል ርዕስ ያቀረቡት ጽሑፍ ነበር፡፡ በፕሮፌሰሩ ጥናትና ጽሑፍ ከአገሪቱ ታክስ አሠራሮች ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች ያሉ ቢሆኑም፣ ዋና ዋና ባሉዋቸው ችግሮች ዙሪያ ላይ በማተኮር ማብራሪያ እንደሚሰጡ በመግለጽ ነበር ጽሑፋቸውን ያቀረቡት፡፡

በጽሑፋቸው መነሻ ላይም እንደጠቆሙት የአገሪቱ የታክስ ሕግ ውስብስብ ከመሆን አልፎ ከሌሎች ዘርፎች በተለየ ወደ ሰባት አዋጆችና በመቶዎች የሚቀጠሩ የተለያዩ መመርያዎች ያሉት መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ውስጥ የትኛውንም አዋጅ ወይም ፕሮግራም ለማስፈጸም በመቶ የሚቆጠር መመርያ የወጣበት የግብር ሕግ ብቻ ነውም ብለዋል፡፡ ይህ የሚያሳየው ሰፊ ችግሮች በመኖራቸው፣ እነዚህ ችግሮች ለመፍታት ተብሎ በየጊዜው መመርያዎች እንደሚወጡ ነው ብለዋል፡፡ በጥናታዊ ጽሑፋቸው ላይ ያነሱዋቸውን የታክስ ችግሮችና የመፍትሔ ሐሳቦችን የዳሰሰውን ጽሑፋቸው እንደሚከተለው ተሰናድቶ ቀርቧል፡፡ 

የግብር ድርሻ በኢትዮጵያ

የኢትዮጵያ መንግሥት ከግብር የሚያገኘው ገቢ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት (ጂዲፒ) 13 በመቶ ብቻ መሆኑን ጥናት አቅራቢው ገልጸዋል፡፡ 87 በመቶውን ከሌላ የሚያገኝ ነው ማለት ነው፡፡ ይህም መንግሥት ከግብር የሚሰበስበው ገንዘብ ምን ያህል አነስተኛ እንደሆነ የሚያመለክት ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ፣ ይህም መንግሥት ከግብር በቂ ገንዘብ ያለመሰብሰቡ ደግሞ መንግሥት ሊሰጥ የሚገባውን አገልግሎት በበቂ ሁኔታ እንዳይሰጥ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከግብር የሚገኘው ገንዘብ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ከሚያገኙት ዓመታዊ የግብር መጠን ጋር ሲነፃፀር ተቀራራቢ ቢሆንም፣ አደጉ ከሚባሉ የምዕራብ አገሮች መንግሥት ከሚያገኙት ጋር ሲመዘን እንደረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ ገለጻ ምዕራብያውያን እስከ 55 በመቶ የሚሆነውን የመንግሥት ወጪ የሚሸፍኑት ከግብር መሆኑ ሲታሰብ የኢትዮጵያ እጅግ አነስተኛ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ የሚሰበሰበው ዓመታዊ ግብር አነስተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን የግብር አሰባሰቡ ብክነት ያለበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ ገለጻ መንግሥት በግብር ከሚሰበስበው ውስጥ ስድስት በመቶው ታክስን ለማስከፈል የሚወጣውን ወጪ ይሸፍናል፡፡ ግብር ለመክፈል የሚያስወጣው ወጪ ከሚሰበሰበው ግብር ውስጥ ስድስት በመቶውን እንደሚወስድ በ2015 የዓለም ባንክ ጥናት ማመላከቱንም በአስረጅነት አቅርበዋል፡፡

ይህ ወጪ ደግሞ ከጠቅላላው ዓመታዊ ምርት (ጂዲፒ) አንድ በመቶ የሚሆነው ሲሆን፣ ይህንን ያህል ገንዘብ መንግሥት የሚያጣ ስለመሆኑም ገልጸዋል፡፡ ከዚህ አንፃር መንግሥት ከግብር የሚያገኘውን ገቢ ከፍ ማድረግ እንደሚኖርበት አመላካች ነውም ብለዋል፡፡

ከግብር የሚሰበስበው ገቢን ከፍ ለማድረግ ደግሞ ግብር ለመክፈል እያስወጣ ያለውን ወጪ (ታክስ ኮምፕልየንስ በርደን) ማቅለል አንዱ መፍትሔ መሆኑንም ጽሑፍ አቅራቢው ጠቁመዋል፡፡ ግብር ለመክፈል የሚያስወጣው ወጪ ከባድና ውስብስብ በመሆኑ ምክንያት፣ ከፍተኛ ነው ሲባል ከገንዘብና ከሳይኮሎጂ አንፃር የሚታይ ነው ብለዋል፡፡ ከገንዘብ አንፃር ወጪው ብዙ መሆን ደግሞ አንዳንዴ የወንጀል ተጠያቂነትን ያስከትላል ብለው፣ በጣም በትንሽ ጉዳዮች የወንጀል ተጠያቂነት ይመጣል በማለት ተናግረዋል፡፡ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ደግሞ ዜጐች ወደ ንግድ ሥራ ውስጥ እንዳይገቡ እያደረጉ መሆኑንና የገቡትም ሕጋዊ በሆነ መንገድ ከመሥራት ይልቅ ግብር ወደማይከፈልበት ሕገወጥ ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ የሚገፋፋ በመሆኑ፣ መንግሥት መሰብሰብ የነበረበትን ገቢ እያሳጣው እንደሚሄድ አስረድተዋል፡፡

‹‹ስለዚህ የታክስ ኮምፕልየንስ በርደኑ መቀነስ አለበት፤›› የሚሉት ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ፣ ሰዎች ግብር ለመክፈል የሚሄዱበት አድካሚው አሠራር መሻሻል አለበት ብለዋል፡፡ ‹‹ይህ ሲደረግ ነው ብዙ ሰዎች ወደ ንግድ የሚገቡትና ከንግድ ሳይወጡ ሥራቸውን እንዲሠሩ የሚያደርገው፤›› በማለት አድካሚ ያሉትን አሠራር እንዲሻሻል ጠይቀዋል፡፡

የታክስ ኮምልያንስ በርደኑን ለማቅለል ምን መደረግ አለበት የሚለውን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ደግሞ፣ መፍትሔዎቹ በርካታ ቢሆኑም ዋና ዋና ብለው ያስቀመጡት ግን ሁለቱን ብቻ ነው፡፡

‹‹አንዱ መፍትሔ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መጠቀም ነው፤›› ይላሉ ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ፡፡ በርካታ አገሮች ግብር አሰባሰብ ሥርዓታቸውን በማዘመን  በኦንላይን በመሰብሰብ ውጣ ውረዶችን መቀነስ በመቻላቸው፣ ይህንን ልምድ ይዞ በኢትዮጵያም ኤሌክትሮኒክ የክፍያ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ ጥሩ መፍትሔ ነው ብለዋል፡፡

ሁለተኛው የመፍትሔ ሐሳብ ደግሞ አሁን ያለውን በግብር አስከፋይ አስተዳደር ውስጥ የሚታየውን አስተሳሰብ መቀየር መሆኑን ያሰምሩበታል፡፡ የኢትዮጵያ የግብር ሥርዓት ‹‹ሠልፍ ዲክላሪዬሽን›› ወይም ግብር ከፋዩ በሚሰጠው መረጃ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ግብር አስከፋዩ ደግሞ ጥርጣሬ ላይ የተመሠረተ አሠራር ስላለው እያንዳንዱን መረጃ መረጋገጥ ላይ እንዲሆን አድርጐታል፡፡ ይህም አድካሚ አሠራር በመሆኑ ይህንን አሠራር ማቃለል ያስፈልጋል ይላሉ፡፡

 

236

የትርፍ ክፍፍል ታክስና ያልተፈቱት ጥያቄዎች

 

ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ በጥናታቸው ክፍተት የታየበት ብለው ያነሡት ሌላው ጉዳይ በተከፈለ ትርፍ ላይ የሚጣለውን ታክስ (ዲቪደንድን) የሚመለከት ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ዲቪደንድ ታክስ ጉዳይ ላይ በርካታ ቅሬታዎች ተነስተው እንደነበር በማስታወስ ቅሬታው ከብዙ ክርክር በኋላ መፍትሔ መገኘቱ ይፋ መደረጉንም ገልጸዋል፡፡ የተገኘው መፍትሔ ግን አሁንም ያልፈታቸው ችግሮች አሉት ይላሉ፡፡

ባልተከፋፈለ ትርፍ ላይ የተጣለው የዲቪደንድ ታክስ ጉዳይ 2005 ዓ.ም. ነው የተነሳው፡፡ ሕጉ ግን የወጣው በ1994 ዓ.ም. ነው፡፡ ከዚያ ጀምሮ የዲቪደንድ ታክስ ይጣል የነበረው በኃላፊነቱ የተወሰነና በአክሲዮን ኩባንያዎች ውስጥ ትርፍ ለባለአክሲዮኖች ሲከፈል ኩባንያው ከሚከፈለው ትርፍ ላይ አሥር በመቶውን ቀንሶ እንዲያስገባ ነው፡፡

ትርፍ ለባለአክሲዮኖች ሲከፍል ኩባንያው ደግሞ ከሚከፍለው ትርፍ ላይ አሥር በመቶ ቀንሶ እንዲያስገባ ነው፡፡ 2005 ዓ.ም. ግን ግብር አስከፋዩ መሥሪያ ቤት (በጥናት ላይ የተመሠረተ ነው ብለን እናምናለን) ነገሩን ሲመለከት በርካታ ኩባንያዎች ትርፍ አያከፋፍሉም፡፡ ስለዚህ ትርፍ ባያከፋፍሉም ትርፍ ቢያከፋፍሉ ኖሮ ለገቢዎች ማስገባት የነበረባቸውን አሥር በመቶ የትርፍ ታክስ መክፈል አለባቸው በሚል የመጣ ነው፡፡

ይህ መከፈል አለበት የለበትም የሚለው ካከራከረ በኋላ መጨረሻ ላይ የተገኘው መፍትሔ ኩባንያዎች ባለፉት አሥር ዓመታት ያላከፋፈሉትን ትርፍ ለካፒታል ማሳደጊያነት ካዋሉና ለዚህም በቂ መረጃ ካቀረቡ ነፃ ይደረጋሉ የሚል ሆነ፡፡ ይህም እስከ 2005 ዓ.ም. ድረስ ያለውን የሚመለከት ነው፡፡

ከዚህ በኋላ የሚያገኙትን ትርፍ በተመለከተ ግን የኩባንያው የበጀት ዓመት ካለቀ በኋላ 12 ወራት ውስጥ ወደ ካፒታል ማሳደጊያ ሊያውሉት ይገባል፤ ሳያውሉና ሳያከፋፍሉ ቢቀሩ ግን አሥር በመቶውን ዲቪደንድ ታክስ መክፈል አለባቸው የሚል ውሳኔም መተላለፉን ገልጸዋል፡፡

ኩባንያዎቹ ይህንንም ሲያደርጉ ሕጋዊ መጠባበቂያ ብቻ ቀንሰው የቀረውን ካፒታል እንደሚያሳድጉበት ወይም የዲቪደንድ ታክስ እንዲከፍሉ የሚያዝ ነው፡፡ ያለፉትን አሥር ዓመታት ያለውንም የዲቪደንድ ታክስ የግብር ዕዳ በሦስት ዓመት ውስጥ ከፍለው እንዲጨርሱ ተደርጓል ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፣ ይህ ውሳኔ በጊዜው መፍትሔ ቢሆንም አንዳንድ ይዟቸው የመጡ ጥያቄዎች አሉ ይላሉ፡፡ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከልም የትርፍ ክፍፍል ታክስ ክፈሉ ሲባሉ የተገኘውን ትርፍ ካፒታል አሳድገውበት የነበሩ ኩባንያዎች ሳይቀሩ ካፒታል ማሳደጊያ ያደረጉትን የአሥሩንም ዓመት ትርፍ 2005ም የዲቪደንድ ታክስ አምጡ ሲባሉ፣ መንግሥት አይሳሳትም እኛ ነን የተሳሳትነው ብለው ደንግጠው የከፈሉ መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ኩባንያዎች ግን ቢዘገዩ በተሻሻለው ሕግ ይጠቀሙ የነበሩ ናቸው ይላሉ፡፡ አሁንም ቢሆን ግን በድንጋጤ የከፈሉ ኩባንያዎች በተሻሻለው አሠራር መሠረት ገንዘቡ ሊመለስላቸው እንደሚገባም አስረድተዋል፡፡ ወይም ወደፊት ከሚከፍሉት ታክስ ላይ ሊታሰብላቸው ይገባል፡፡ ይህ ርእታዊነት ጥያቄ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ፣ በተመሳሳይ መስፈርት አንዱ ከፍሎ ሌላው ደግሞ መክፈል ያልነበረበትን የከፈለ ሊመለስለት ይገባል፤ ገንዘቡ መንግሥት እጅ የገባና ልማት ላይ የዋለ ነው ከተባለ ደግሞ ወደፊት ከሚከፈል ታክስ ላይ ሊታሰብላቸው ይገባል የሚለው ጉዳይ ጊዜያዊ መፍትሔውን ተከትሎ የመጣ ጥያቄ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በዲቪደንድ ዙሪያ የተቀመጠው መፍትሔ ሐሳብና አሠራር ኩባንያዎች በቂ መጠባበቂያ ገንዘብ እንዳይዙ በማድረግም ክፍተት መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ ምክንያቱም በ12 ወራት ውስጥ ሕጋዊ መጠባበቂያ ብቻ ቀንሳችሁ ዲቪደንድ ትከፍላላችሁ፤ ያለዛ ካፒታል አሳደጉ የሚለው አሠራር በንግድ ሕጉ ከሕጋዊ መጠባበቂያ በተጨማሪ ሌሎች ብዙ ዓይነት መጠባበቂያዎች መያዝ እንደሚችሉ ስለተቀመጠ አሠራሩ ከንግድ ሕጉ ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ነው ይላሉ፡፡

ይህ ተቃርኖ ደግሞ እንደ አዋጅ የሚታየውን የንግድ ሕግ በመመርያ እንደማሻሻል የሚቆጠር መሆኑ እንደ ችግር ይታያል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የገንዘብ ችግር ባለበት የባንክ ብድር ማግኘት ከባድ በሆነበት አገር የምታገኙትን ገንዘብ አከፋፍሉ ወይም ካፒታል አሳድጉበት ማለት ተገቢ አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የተገኘውን ትርፍ ወደ ካፒታል ማሳደጊያ ሳያደርጉ፤ ወደ ራሳቸውም ሳያስገቡ ለአሠራር በሚመች መንገድ እየተጠቀሙ መቆየት በየትም ያለ አሠራር ሆኖ ሳለ ይህንን አሠራር እንዲጣበብ ማድረጉ ተገቢ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ ይህ ዲቪደንድን የተለከተው አሠራር ድጋሚ ፈተሽ እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ከንግድ ሕጉ ጋር በተጣጣመ መልክ መመርያው ሊሻሻል ይገባልም በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በዚሁ ጉዳይ አጽንኦት የሰጡትና ሊሻሻል ይገባል ያሉት ሌላው ነጥብ ደግሞ ትርፍ ከተገኘ በኋላ በ12 ወራት ውስጥ ለካፒታል መዋል አለመዋሉን መወሰን አለበት የሚለው የመመርያው አንቀጽ ነው፡፡ 12 ወራት በቂ አይደለም፡፡ በርካታ የአክሲዮን ማኅበራት በ12 ወራት ውስጥ ካፒታል ማሳደግን ላያስወስኑ ወይም ሊያረጋግጡ አይችልምና ይህ መራዘም አለበት ብለዋል፡፡

የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያና ችግር

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር ገለጻ የሽያጭ መመዝገቢያ መሣሪያ መጠቀም የግብር አሰባሰቡን ዘመናዊ የሚያደርግ ብዙ ነገር የሚያቀል ቢሆንም፣ በርካታ ችግሮች ያሉበት ነው ብለውታል፡፡ ከችግሮቹ አንዱ መብራት ኃይል ሲቋረጥ የሚፈጠር መረበሽ ነው፡፡ በተለይ እንደ ሆቴል፣ ሬስቶራንትና የመሳሰሉ ድርጅቶች መብራት ሲጠፋ በማሽን የታተመ ደረሰኝ መስጠት ስለማይችሉ ችግር ውስጥ ይገባሉ፡፡ የወረቀት ደረሰኝ ለመጠቀም ለገቢዎች አሳውቆ መጠቀም ግድ ስለሚል ይህንን ለማድረግ ስልክም ስለሚቋረጥ አስቸጋሪ የሚሆንበት አጋጣሚዎች የሚፈጠሩ በመሆኑ፣ ይህ በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ጫና ይፈጥራል ይላሉ፡፡

በዚህ መሃል አንድ ሠራተኛ ደረሰኝ ሳይሰጥ ሒሳብ ቢቀበል የሚያመጣው መዘዝ ከፍተኛ በመሆኑ፣ በዚህ አካባቢ ያለውን አሠራር ማሻሻል ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ ለምሳሌ ሠራተኛው ላጠፋው ጥፋት ባለቤቱና ሥራ አስኪያጁ ለወንጀል እስከመጠየቅ ይደርሳል፡፡ እንዲህ ያሉ አካሄዶች በጣም አደገኛ አካሄዶች ናቸው፡፡ ግብር ከፋዩን እያሸማቀቁ ያሉ በመሆኑ እንደገና መፈተሽ ያለባቸውና ማስተካከል የሚገባቸው ናቸው ይላሉ፡፡

ከአስተዳደር ችግር ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይም ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ከአስተዳደራዊ ችግሮች አንዱ የሠራተኞች የትራንስፖርት አባል ነው፡፡ የገቢ ግብር አዋጁን ለማስፈጸም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው ደንብ ውስጥ ለሠራተኞች ከግብር ነፃ የሆነ የትራንስፖርት አበል መክፈል እንደሚችል ይደነግግና የግብር ባለሥልጣኑ መጠኑን በተመለከተ መመርያ ያወጣል ይላል፡፡

ስለዚህ በመርህ ደረጃ ለሠራተኞች ከገቢ ግብር ነፃ የሆነ የትራንስፖርት አባል መክፈል በሕጉ ተከልክሏል፤ መጠኑን በተመለከተ ግን ግብር አስከፋይ መሥሪያ ቤት ይወሰናል ይላል፡፡ ነገር ግን ግብር አስከፋዩ ያወጣቸው ደንቦች ግን በ25 ኪሎ ሜትር ውስጥ ካለ አይከፈልም፤ ከዚያ ውጭ ላለ ይከፈላል ይላል፡፡ ይህም መመርያ ከሕጉ ውጭ የመጣ ነው ይላሉ፡፡ መመርያው የሕጉን መንፈስ ተከትሎ የወጣ ባለመሆኑ ሊሻሻል ይገባል ብለዋል፡፡

የከብትና ሥጋ ነጋዴዎች የሒሳብ አያያዝና ያለመተማመን

የከብት ሥጋ ነጋዴዎችን የሒሳብ አያያዝ በተመለከተ አንድ መመርያ ተግባራዊ ሆኗል፡፡ ነገር ግን መመርያው ሥራ ላይ ሲውል ችግሮች እንደታዩበት በጽሑፍ አቅራቢው ማብራሪያ ያስረዳል፡፡ ‹‹ቀደም ብሎ የከብትና የሥጋ ነጋዴዎች ከገበሬ ከብት በሚገዙበት ጊዜ ደረሰኝ ካላቀረቡ ወጪያቸው አይወራረድም ነበር፤›› ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ፣ አሁን ግን በአዲሱ መመርያ መሠረት የግዥ ደረሰኝ አሳትመው እንደሚጠቀሙ ተፈቅዷል፡፡ በተጨማሪም መመርያው ሰንጠረዥ በማዘጋጀት የከብት ከፍተኛ ዋጋ ምን መሆን እንዳልበትም አስቀምጧል፡፡ ነገር ግን ገበያው በየጊዜው የሚጨምር በመሆኑ ከብት ሲገዙ የገዛነው በዚህ ዋጋ ነው ብለው ሪፖርት ሲያቀርቡ ተቀባይነት አለማግኘቱ፣ በመመርያው አተገባበር ላይ ችግር ያለበት መሆኑን ያሳያል ይላሉ፡፡

ይህ ማለት ደግሞ የግዥ ደረሰኙ ተቀባይነት እያገኘ አለመሆኑን የሚያመለክት በመሆኑ አሠራሩ መስተካከል እንዳለበት የረዳት ፕሮፌሰሩ ጥናት ያመለክታል፡፡ አለበለዚያ መመርያው በየጊዜው ከሚጨምረው ዋጋ ጋር መሄድ እንደሚኖርበት አስገንዝበዋል፡፡ በሆቴሎች አካባቢም ተመሳሳይ ችግር እንዳለ ያብራሩት ረዳት ፕሮፌሰር፣ በሆቴሎች አካባቢ የሚታይ ችግር ነው ብለው ያከሉት ነጥብ ሆቴሎች ለሠራተኞቻቸው ምግብ የሚያቀርቡ መሆኑን እየታወቀ፤ ይህ ለሠራተኛው የሚያቀርቡት የምግብ ወጪ ተቀናሽ አለመደረጉ ነው ብለዋል፡፡

ከአገሪቱ የዜጐች ገቢ አንፃር በእነዚህ ሆቴሎች የሚሠሩ ሠራተኞች ውስጥ በሚያገኘው ገቢ ቤተሰቡን አስተዳድሮ በቂ ምግብ የማያገኝበት አጋጣሚዎች በመኖራቸው፣ አብዛኛዎቹ አሠሪዎች ለሠራተኞቻቸው ምግብ ማቅረብ እየለመዱ መጥተዋል ይላሉ፡፡ በተለይ በአምራች ኢንዱስትሪዎች ውስጥ የተለመደ ቢሆንም መንግሥትም አምራች ኢንዱስትሪዎች ለሠራተኞቻቸው ለሚያቀርቡት የምግብ ወጪ ግብር ከማይጣልበት ገቢያቸው ላይ ተቀናሽ ይሆናል መባሉ በጣም የሚያስመሰግን ቢሆንም፣ እንዲህ ያለው መመርያ ለሆቴሎችም ሊሠራ ሲገባ እየተሠራበት አይደለም ብለዋል፡፡

ተመላሽ ቫትና አከፋፈል

በአሁኑ ወቅት ከግብር ሥርዓቱ ጋር ተያይዞ የጐላ ችግር ሆኖ እየታየ ነው የተባለው ሌላው ጉዳይ የተመላሽ የተጨማሪ እሴት ታክስ (ቫት) ጉዳይን የተመለከተ ነው፡፡ ረዳት ፕሮፌሰሩ የተመላሽ ቫት አከፋፈል ላይ በርካታ ችግሮች ያሉ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ አንድ ተመላሽ ቫት ያለው ኩባንያ ገንዘቡን ለማግኘት አታካች ቢሮክራሲዎችን ማለፍ አለበት፡፡ አገልግሎቱን ለማግኘት ረዥም ጊዜ የሚወስድ ነው፡፡ አሠራሩ እያንዳንዱን ደረሰኝ በመመርመርና በመፈተሽ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ደግሞ አሰልቺ አድርጐታልም ይላሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የተንዛዛ አሠራር ፈጽሞ የማይደገፍ እንደሆነ በመጥቀስ፣ በተንዛዛው አሠራር ምክንያትም ብዙ ተመላሽ ያላቸው ነጋዴዎች በጊዜው ገንዘባቸውን እንዳያገኙ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

ለምሳሌ የማይነበብ ደረሰኝ በሚያጋጥምበት ጊዜ ‹‹አንድ ፊደል እንኳን በደንብ ካልታየ›› ደረሰኙ ውድቅ ይደረጋል፡፡ ይህ ከሕጉ መንፈስ ውጭ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የታየውን ችግር መፍትሔ ለመስጠት ደግሞ የሌሎች አገሮችን ልምድ ጠቅሰዋል፡፡ ለምሳሌ አሁንም አደጋ ላይ የተመሠረተ አገልግሎት መከተል ይገባል በማለት ከዚህ በፊት ሐሰተኛ ደረሰኝ ያቀረቡ ነጋዴዎች ወይም አታለውና ተከሰው የሚያውቁ ነጋዴዎች ካሉ እነሱን በመለየት እያንዳንዱን ደረሰኞቻቸውን መመርመር (እሱም ቢሆን አታካች ነው) ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ሁሉም ላይ ተፈጻሚ አለማድረግ ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ግን ሥራውን ለማቀላጠፍ ከተፈለገ ተመላሽ ቫት ያላቸው ጥያቄ አቅራቢዎች ለሚቀበሉት ገንዘብ ከባንክ ዋስትና እንዲያቀርቡና በዚያ መሠረት መተማመኛ ይዞ መክፈል ጥሩ መፍትሔ ሊሆን ይችላል እንጂ፣ በጥርጣሬ ጊዜን መግደል አያስፈልግም ባይ ናቸው፡፡

ታክስና ኦዲት

በጽሑፍ አቅራቢው ጥናት መሠረት ከኦዲት ጋር በተያያዘ የሚታው ችግርም በግብር ሥርዓቱ ውስጥ ጐልተው ከሚታዩ ክፍተቶች መካከል አንዱ ሆኖ ቀርቧል፡፡ አብዛኛው የግብር ቅሬታ መንስዔ የሚሆነው ከኦዲት ጋር ያለው ያለመተማመን መሆኑም ተገልጿል፡፡ የግብር ሰብሳቢው ኦዲተሮችም ሆኑ የግብር ከፋዩ ኦዲተሮች ሁለቱም ጋር ችግር እንዳለ ይጠቁማሉ፡፡ የችግሮቹ መገለጫዎች ደግሞ በርካታ ናቸው ተብሏል፡፡ ጐልቶ የሚታየው ችግር የኦዲቲንግ ሒደቱ ላይ ያለመስማማት ነው፡፡ ለተጠቆመው ችግር ግን መፍትሔ የሚሆነው በቅርቡ የወጣው ‹‹የሒሳብ አያያዝና ሪፖርት አቀራረብ አዋጅ››ን ተግባራዊ ማድረግ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አዋጁን ሁሉም እንዲያውቀው መደረግና አዋጁን ተመሥርቶ ቢሠራ ለችግሩ አንድ መፍትሔ ይሆናል የሚለውን እምነታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ በሁለቱም ወገኖች ያሉ ኦዲተሮች አንድ ዓይነት ቋንቋ እንዲናገሩ ለማድረግ ደግሞ ሥልጠና በመስጠት ክፍተቱን ማጥበብ የሚቻል ስለመሆኑም እምነት አላቸው፡፡

የታክስ ቅሬታና አፈታት

 በታክስ ጉዳዮች የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ያለው አሠራር በርካታ ችግሮች ያለበት እንደሆነ ጥናት አቅራቢው ይገልጻሉ፡፡ ከችግሮቹ መካከልም የፌዴራል ይግባኝ ሰሚ ጉባዔ ያለው በአዲስ አበባ ብቻ መሆኑና በክልል ዋና ከተሞች ያላመሩ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በዚህም ምክንያት በክልል የሚገኙ ግብር ከፋዮች ይገባኝ የሚያቀርቡበት አዲስ አበባ መጥተው ነው፡፡ በክልል ከተሞች የግብር ይግባኝ ሰሚ አካል እንዲኖር ግን ከዚህ በፊት በተደረጉ ውይይቶች ላይ በተደረገ መግባት ይግባኝ ሰሚዎችን በክልል ለማቋቋም በመርህ ደረጃ ተቀባይነት ቢያገኝም፣ እስካሁን ተግባራዊ አለመሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

በግብር ይግባኝ ሥርዓት ውስጥ እንደ ከፍተኛ ችግር እየታየ ያለው የግብር ይግባኝ አቤቱታ ለማቅረብ፣ ቅሬታ አቅራቢው እንዲከፍል ከተነገረው ግብር ውስጥ 50 በመቶውን በቅድሚያ ማስያዝ አለበት የሚለው አሠራር ነው፡፡ ይህ ከኦዲት ችግር ጋር የተያያዘም ነው ይላሉ፡፡ አንድ የግብር ሰብሳቢው ኦዲተር አንድ ግብር ከፋይ ላይ 50 ሚሊዮን ብር መክፈል አለብህ ሲለው፣ ይህ ነጋዴ 50 ሚሊዮን ብር መክፈል የለብኝም ወደ ግብር ይግባኝ ለመቅረብና ጉዳዩን ለማስመርመር መጀመሪያ 25 ሚሊዮን ብር ማስያዝ አለበት ማለቱ ነው፡፡ ይህንን ካላደረገ ፍትሕ የማግኘት መብቱን የሚነግፍ በመሆኑ እንዲህ ዓይነቱ አሠራር አደገኛ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

በዚህ ችግር ምክንያት በርካታ ግብር ከፋዮች ሳያምኑ የተጠየቁትን ግብር እንዲከፍሉና እንዲደራደሩ የሚገደዱበት አንዱ ምክንያት ፍትሕ ለማግኘት ከተጠየቁት ግብር 50 በመቶ በቅድሚያ አሲይዙና ጉዳያችሁ ይታይላቸዋል የሚለው አሠራር ነው፡፡

እንደ ጽሑፍ አቅራቢው እምነት በዚህ አሠራር በመቶኛ ተሰልቶ የተቀመጠው፤ 50 በመቶ ወይም 70 በመቶ መባሉ ሳይሆን ይህ እንዳለ ሆኖ ለግብር ከፋዩ ፍትሕ የማግኘት መብቱን በማያጣብብበት መንገድ ሌሎች አማራጮች የሉም ወይ የሚለው ጥያቄ መታየት እንደሚኖርበት ይገልጻሉ፡፡

50 በመቶውን አስይዝ የሚለው እንዳለ ሆኖ ግብር ከፋዩን ሳያጨናንቅ ሊሠራባቸው የሚችሉ በርካታ አማራጮች እንዳሉ የሚጠቁሙት ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ፣ አንዱና ቀላሉ አማራጭ 50 በመቶውን ማስያዣ በባንክ ማስቀመጥ ነው፡፡ እንዲህ ተደርጐ ቅሬታውን አቅርቦ የተሸነፈ ከሆነ ባንኩ በገባው ዋስትና መሠረት 50 በመቶውን ይከፍላል፡፡ ይህ በሌሎች አገሮች የሚሠራበትና ውጤት ያገኘ በመሆኑ እዚህም መተግበር ይኖርበታል ብለዋል፡፡ ይህ አሠራር ለግብር አስከፋዩ ጭምር የሚጠቅም ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

በባንክ በሚሰጥ ዋስትና መሥራቱ እጅግ ጠቃሚ ስለመሆኑም በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያ፣ የትኛውም ነጋዴ በሥራ ላይ ስለሚያውለው ጥሬ ገንዘብ አይኖረውምና የባንክ ዋስትናውን መጠቀሙ ሥራውን ሳያስተጓጉል እንዲሠራ ያደርገዋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ያሉ ሌሎች ችግሮችም ድጋሚ መታየት እንደለባቸው አመልክተው፣ መታለፍ የሌለበት ሌላው ጉዳይ ግን ከዚህ በፊት ለግብር ሰሚው አካል ጉዳዩን ለማሳየት የሚቀርበው 50 በመቶ ገንዘብ ቅጣት ጭምር ይጣልበት የነበረው አሠራር ፍሬ ግብሩን ብቻ እንዲመለከትና ወለድና መቀጫው እንዲቀር መንግሥት መወሰኑ ትልቅ እመርታ ነው ብለውታል፡፡

በዚህ ጥናት ላይ ተመሥርቶ በዕለቱ ውይይት ተደርጓል፡፡ በተለይ የግብር አስከፋይ መሥሪያ ቤት ተወካዮች በረዳት ፕሮፌሰሩ ላቀረቡዋቸው አንዳንድ ሐሳቦች ላይ የማይስማሙ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ አንዳንድ ያነሱዋቸውን የመፍትሔ ሐሳቦች ደግሞ ግብር አከፋዩ መሥሪያ ቤት ተግባራዊ እያደረጋቸውም መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በተለይ ዘመናዊ አሠራሮች እየተተገበሩ ነው፡፡ ከአሠራር አንፃር አሁን ባለው አካሄድ መቀጠል ያለባቸው ጉዳዮች ያሉ መሆኑንም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡ ጠቃሚ ናቸው ባሉዋቸው ላይም አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች