Tuesday, February 27, 2024

ፖለቲካዊ ትኩረት የሚሻው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ልማት

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በአሥረኛው ዙር የኮንዶሚኒየም ቤቶች ዕጣ ዕድል ከደረሳቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች መካከል አቶ ፈጠነ ዋቅጅራ ይገኝበታል፡፡ በዚህ ዕጣ ባለ ሦስት መኝታ ቤት መኖሪያ የደረሰው አቶ ፈጠነ በቅርቡ ወደ ደረሰው መኖሪያ ቤቱ እንደሚገባ በደስታ ቢናገርም፣ ደስታው በሥጋትና በሐሳብ የታጠረ ነው፡፡

‹‹የመኖሪያ ቤት ባለ ዕድል መሆኔን በሰማሁ ጊዜ በተመዘገብኩበት የ20/80 ቁጠባ ደብተር መቆጠብ የቻልኩት 14,000 ብር ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም ለደረሰኝ ባለሦስት መኝታ ቤት መኖሪያ የሚያስፈልገውን 109,000 ብር ቅድመ ክፍያ ለመክፈል ከጓደኞቼና ከዘመዶቼ መበደር ነበረብኝ፤›› በማለት ያለፈበትን ሁኔታ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር በ1996 ዓ.ም. አስተዳደር የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ቤት ፈላጊዎችን ተጠቃሚ ለማድረግ ባካሄደው ምዝገባ ወቅት ነው አቶ ፈጠነ የቤት ባለቤት ለመሆን የተመዘገበው፡፡ ይሁን እንጂ የአዲስ አበባ አስተዳደር ከሁለት ዓመት በፊት ቁጠባ ላይ የተመሠረተ የቤት ባለቤት መሆን የሚቻልበትን አሠራር ተግባራዊ ለማድረግ ዳግም ምዝገባ በጀመረበት ወቅት፣ አቶ ፈጠነ በዳግም ምዝገባው በመጠቀም ቀደም ሲል የመረጠውን ባለሦስት መኝታ ክፍል መኖሪያ ቤት ለማግኘት ተመዝግቧል፡፡

አስተዳደሩ በዳግም ምዝገባው ይፋ ካደረጋቸው ቁጠባን መሠረት ያደረጉ የቤት ዓይነቶች ሦስት ዓይነት መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ለመጥቀስ ያህልም 10/90፣ 20/80 እና 40/60 ሲሆኑ ይህም ማለት በፕሮግራሞቹ መታቀፍ የሚፈልጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በቅድሚያ አሥር በመቶ ወይም 20 በመቶ ወይም 40 በመቶ እንደየመረጡት የፕሮግራም ዓይነት በባንክ መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በመረጡት የቤት ዓይነት የሚቀረውን መቶኛ ከባንክ በብድር እንዲዋዋሉ በማድረግ በ15 ዓመት ከነወለዱ የሚከፈልበት አሠራር ነው፡፡

‹‹አሁን እያስጨነቀኝ የሚገኘው ያለብኝን የገንዘብ ዕዳ እንዴት ነው የምወጣው? የሚለው ነው፤›› በማለት አቶ ፈጠነ ጭንቀቱን ይናገራል፡፡

ከሁለት ዓመት በፊት ማለትም በዳግም ምዝገባ ወቅት ለባለ ሦስት መኝታ ቤት መኖሪያ ይፋ የነበረው ዋጋ 304,000 ብር እንደነበር የሚያስታውሰው አቶ ፈጠነ፣ አሁን በዕጣ የደረሰው ተመሳሳይ መኖሪያ ቤት 512,000 ብር እንዲከፍል ይጠበቅበታል፡፡

ይኼንን ለማድረግ አቅም የሌለው በመሆኑ ግን 20 በመቶውን ቅድመ ክፍያ ከፍሎ ቀሪውን በ15 ዓመት የባንክ ብድር ጋር ተዋውሏል፡፡

ይህ አሠራር አቶ ፈጠነን ብቻ የሚመለከት አይደለም፡፡ በአሥረኛው የኮንዶሚኒየም ዕጣ ዕድለኛ የሆኑ 35,000 አዲስ አበባውያንም ሆኑ ቀደም ሲል የደረሳቸው ያለፉበት አሠራር ነው፡፡ በመሆኑም ከአንድ ዓመት የዕፎይታ ጊዜ በኋላ በአሥረኛው ዙር የኮንዶሚኒየም ዕጣ የደረሳቸው ነዋሪዎች፣ ያለባቸውን የቤት ዕዳ በየወሩ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መክፈል ይጠበቅባቸዋል፡፡ አቶ ፈጠነ በደረሰው የቤት ዕድል ያለበትን ዕዳ ከዓመት በኋላ በየወሩ ከ4,000 ብር በላይ በመክፈል መወጣት ይጠበቅበታል፡፡

‹‹በየወሩ መክፈል ያለብኝን የቤት ዕዳ እንዲሁም ቅደመ ክፍያውን ለመክፈል ከወዳጆቼ የተበደርኩትን ሳስበው በእርግጥ ይህ ቤት የኔ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ያስጨንቀኛል፤›› በማለት አቶ ፈጠነ ሥጋቱን ይገልጻል፡፡

ይህ ዓይነቱ ጭንቀት በአሁኑ ወቅት የበርካታ የቤት ዕጣ ዕድለኞች ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም የቤት ባለቤት ለመሆን ተመዝግበው እየቆጠቡ ያሉ አዲስ አበባውያን ጭንቀት ነው፡፡

የአዲስ አበባን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ ከተቀረፁ የቤት ፕሮጀክቶች በአጠቃላይ አንድ ሚሊዮን ነዋሪዎች ተመዝግበዋል፡፡ በመሆኑም የሚጠበቅባቸውን ወርኃዊ ቁጠባና አሁን ለሚኖሩበት የመኖሪያ ቤት የኪራይ ክፍያ ይገደዳሉ፡፡

የቤቶች ግንባታና የቤት ፈላጊዎች ቁጠባ

የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የተመሠረተው በ1996 ዓ.ም. ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው የከተማዋ አስተዳደር የቤት ችግርን ለመቅረፍ በመወሰን ባካሄደው ጥናት፣ ከ446 ሺሕ በላይ የቤት ፍላጎት በወቅቱ እንደነበር አረጋግጧል፡፡ ይህንንም መነሻ በማድረግ በተቀረፀው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተጠቃሚ ለመሆን 453,287 የከተማዋ ነዋሪዎች በ18 ቀናት ውስጥ መመዝገባቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

አስተዳደሩ በየዓመቱ 50,000 ቤቶችን የመገንባት ዕቅድ ሰንቆ ቢነሳም፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከ30,000 በላይ መኖሪያ ቤት የመገንባት አቅም አልፈጠረም ነበር፡፡ በመሆኑም በመጀመርያው ዙር የቤቶች ማስተላለፍ ሒደት (በሁለት ዙር) 18,988 ቤቶች ሲተላለፉ በሁለተኛው ዙር ወደ 15,000 ዝቅ ብሏል፡፡ በሦስተኛው ዙር 10,735፣ በአራተኛው ዙር 15,032፣ በሰባተኛው ዙር 7,300 መኖሪያ ቤቶች ሲተላለፉ በተቀሩት ባልተጠቀሱት ዙሮች በ10,000 እና በ11,000 መካከል ተላልፈዋል፡፡

በመገባደድ ላይ ባለው 2007 ዓ.ም. ሚያዘያ ወር ላይ የተካሄደው አሥረኛው ዙር የቤቶች ዕጣ 35,000 ቤቶችን በማስተናገድ ትልቁ መሆኑ ይጠቀሳል፡፡

በመሆኑም በእስካሁኑ ሒደት ማለትም የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ከተጀመረ ከ11 ዓመታት በኋላ ወደ ተጠቃሚዎች የተላለፉ ቤቶች ቁጥር 140,000 ገደማ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በዚህም ወደ 550,000 የሚሆኑ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የቤት ተጠቃሚ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡

ይሁን እንጂ አስተዳደሩ የከተማዋን ነዋሪዎች የቤት ችግር በተሻለ ለመቅረፍና የተጨማሪ ነዋሪዎችን ፍላጎት ለማሟላት፣ የዛሬ ሁለት ዓመት ገደማ ባካሄደው የቤት ፈላጊዎች ዳግም ምዝገባ በጥቅሉ 950 ሺሕ ነዋሪዎች ነባሮችንም ጨምሮ በመመዝገባቸው የአስተዳደሩን ኃላፊነት አክብደውታል፡፡

በዳግም ምዝገባው በተቀረፀው አዲስ አሠራር ነዋሪዎች የቤት ፍላጎታቸውንና አቅማቸውን አገናዝበው በመረጧቸው የቤት ዓይነቶች የሚያስፈልገውን ቅድመ ክፍያ መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በተገለጹት የቤት ፕሮግራሞች ተጠቃሚ ለመሆን የተመዘገቡ ነዋሪዎችም፣ የመኖሪያ ቤት ፍላጎታቸውንና ቤቱን ለማግኘትም መክፈል የሚችሉትን መስዋዕትነት አስፈላጊውን ቅድመ ክፍያ ለማሟላት በየወሩ በሚያደርጉት ቁጠባ እየገለጹ ይገኛሉ፡፡

ቁጠባው የሚካሄደው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፎች መሆኑ ይታወቃል፡፡ የባንኩ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም መኩሪያ በተካሄደው ምዝገባ መሠረት፣ አብዛኞቹ ቤት ፈላጊዎች ወርኃዊ ቁጠባቸውን እየፈጸሙ እንደሚገኙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በጣም ውስን ቢሆኑም በየወሩ ከሚጠበቅባቸው በላይ የቆጠቡ የመገኘታቸውን ያህል ቀላል ቁጥር የሌላቸው ደግሞ ዕጣ መውጣት ሲጀምር ወይም ሊወጣ መሆኑ ሲገለጽ ከፍተኛ ቁጠባ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡

በ10/90 የቤቶች ፕሮግራም ከተመዘገቡ ነዋሪዎች መካከል እስከ ሰኔ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ድረስ 106 ሚሊዮን ብር መቆጠባቸውን የገለጹት አቶ ኤፍሬም፣ በ20/80 ፕሮግራም የተመዘገቡ 860 ነዋሪዎች እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ አምስት ቢሊዮን ብር መቆጠባቸውን ገልጸዋል፡፡

ትልቁ ቁጠባ እየተደረገ ያለው በ40/60 የመኖሪያ ቤቶች ፕሮግራም ነው፡፡ በዚህ ፕሮግራም 164 ሺሕ ነዋሪዎች የተመዘገቡ ሲሆን፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን ድረስ ከአሥር ቢሊዮን ብር በላይ መቆጠቡን አቶ ኤፍሬም ተናግረዋል፡፡

‹‹በዚህ የቤቶች ፕሮግራም ከተመዘገቡት ጥቂት ነዋሪዎች የተቆጠበው ገንዘብ ግዙፍ የሆነበት ምክንያት አንደኛ የቤቶቹ ዋጋ ከሌላው ጋር ሲነፃፀር ውድ በመሆኑ፣ ሁለተኛ በዚህ ፕሮግራም ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያን መሳተፍ የሚችሉ በመሆኑና አቅም ስላላቸው አጠቃላይ የቤቱን ዋጋ በመክፈላቸው እንደ ምክንያትነት ይጠቀሳሉ፤›› በማለት አቶ ኤፍሬም ገልጸዋል፡፡

በ40/60 የቤቶች ፕሮግራም ከ15,000 በላይ ተመዝጋቢዎች ሙሉ በሙሉ የቤቱን ክፍያ ገቢ አድርገዋል፡፡

የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በከተማዋ ከተጀመረ አንስቶ ተገንብተው ለተጠናቀቁ ቤቶች 17 ቢሊዮን ብር በ11 ዓመት ውስጥ ወጪ ሲደረግ በዳግም፣ ምዝገባው ቤት ፈላጊዎች ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከ15 ቢሊዮን ብር በላይ በመቆጠብ የቤት ባለቤት ለመሆን ያላቸውን ጽኑ ፍላጎት እየገለጹ ነው፡፡

የግንባታው ፍጥነት የፈጠረው ሥጋት

አቶ ፈጠነ ዋቅጅራ የመኖሪያ ቤት ፍላጎቱን ለመመለስ የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጅክት ጽሕፈት ቤት በ1996 ዓ.ም. ተመሥርቶ ምዝገባ ሲጀምር ነው በቀዳሚነት የተመዘገበው፡፡

በወቅቱ የነበረው የዋጋ ሁኔታ አሁን በእጥፍ ቢጨምርም የቤት ፈላጊዎች ቁጥር የዚያኑ ያህል ጨመረ እንጂ ሊቀንስ አልቻለም፡፡ አቶ ፈጠነም የቤት ፍላጎቱን ዕውን ለማድረግ 11 ዓመታትን መታገስ ጠይቆታል፡፡ የግንባታ ግብዓቶች የዋጋ ጭማሪ እጅግ ፈጣን እየሆነ መምጣቱ፣ እንዲሁም የቤት ግንባታ ማኔጅመንትና ቁጥጥር ከቀድሞው የተሻለ ቢሆንም በቂ ደረጃ ላይ ባለመድረሱ ፈጣን የዋጋ ጭማሪ በቤቶች ላይ እየታየ ነው፡፡ ለግብዓትነት ያህል 304 ሺሕ ብር በመክፈል የቤት ባለቤት እንሆናለን ብለው ያሰቡ ባለሦስት መኝታ ቤት ተመዝጋቢዎች፣ ሁለት ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የመረጡት የቤት ዓይነት 512 ሺሕ ብር ለመክፈል ተገደዋል፡፡ ይህ በሌሎቹም የቤት ዓይነቶች የሚገለጽ ነው፡፡

በ20/80 የቤት ፕሮግራም ሥር ከሚገኙ 860 ሺሕ መካከል 132 ሺሕ የሚሆኑት በ1996 ዓ.ም. የተመዘገቡ ነባር ተመዝጋቢዎች በመሆናቸው ቅድሚያ በዕጣ የመካተት ዕድል ያገኛሉ፡፡ በዚህም መሠረት በሚያዝያ ወር 2007 ዓ.ም. በወጣው ዕጣ 34 ሺሕ ተመዝጋቢዎች የቤት ባለቤት ሆነዋል፡፡ ስለዚህ ወደ 100 ሺሕ የሚጠጉ ተመዝጋቢዎች አሁንም የቅድሚያ ዕድል ይዘው በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

መንግሥት የቤት ግንባታ ፍጥነቱንና የግንባታ ስፋቱን በመጨመር ችግሩን መቅረፍ ካልቻለ፣ በየወሩ እየቆጠቡ በኪራይ መኖሪያ ቤት የሚኖሩ አዲስ አበባውያንን ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዳይከታቸው የሚሰጉ አሉ፡፡

አንዳንድ ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች የከተማ የኑሮ ወጪ በዋጋ ግሽበት ምክንያት እየናረ በመሆኑ፣ ለሚኖሩበት ቤት ኪራይ እየከፈሉ ለሚጠብቁትም ቤት ቁጠባ እያደረጉ መቀጠል ሊቸግራቸው እንደሚችል ይገልጻሉ፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ አቶ ኤፍሬም ግን፣ በሁሉም የቤት ፕሮግራሞች የተመዘገቡ ነዋሪዎች ቁጠባውን አብዛኛዎቹ እየፈጸሙ እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ ቢሆንም በሁሉም የቤቶች ፕሮግራም ከተመዘገቡት ነዋሪዎች መካከል እስከ ሦስት በመቶ የሚሆኑ ተመዝጋቢዎች ቁጠባ ማቋረጠቸውን ገልጸዋል፡፡

ዳግም የቤቶች ምዝገባ ከተደረገ ሁለት ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ ወደ 30 ሺሕ የሚጠጉ ነዋሪዎች ቁጠባ አቋርጠዋል ማለት ነው፡፡ የቤት ማስተላለፍ በሚካሄድባቸው ወቅቶች የቁጠባ ገንዘብ መጠን እንደሚጨምረው ሁሉ፣ የቤት ማስተላለፍ በማይኖርበት ጊዜ ቁጠባቸውን አቋርጠው ከፕሮግራሙ የሚወጡ ነዋሪዎች ቁጥር እንዳያሻቅብ ትልቅ ፖለቲካዊ ትኩረት ከመንግሥት የሚሻ ይመስላል፡፡

የመንግሥት ምላሽ

የአዲስ አበባ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት የሕዝብ ግንኙነት የሥራ ሒደት መሪ የሆኑት አቶ ካሳ ወልደሰንበት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ትልቅ ስኬት በዚህ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት እየተፈጸመ ይገኛል፡፡

የቤቶች ግንባታ በአዲስ አበባ ሲጀመር 100 ተቋራጮችን በዚህ ዘርፍ እንዲሳተፉ ለማድረግ ችግር እንደነበር ይገልጻሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ከ2,600 በላይ ተቋራጮች በዚህ ሥራ ላይ እየተሳተፉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ቤቶቹ ለተጠቃሚዎች እየተላለፉበት ያለው ዋጋም ቢሆን ከገበያው ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ‹‹ለአብነት ያህል በአሁኑ ወቅት በካሬ ሜትር 14,000 ብር የገበያው ዋጋ ሲሆን፣ መንግሥት የሚያስተላልፍበት ትልቁ ዋጋ ግን 4,800 ብር ብቻ ነው፤›› በማለት ይከራከራሉ፡፡

ይህ የሆነበት ምክንያት መንግሥት ወገቡ ጎብጦ ድጎማ በማድረጉ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ድጎማው መሬት በነፃ ከማቅረብ አንስቶ፣ ቫት በመቀነስና እንዲሁም የመሠረተ ልማት ሥራዎችን በነፃ በመገንባት እንደሚገለጽ ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ የቤት ተመዝጋቢዎችን በፍጥነት ቤት የማግኘት ፍላጎት አሁን እየተሄደበት ባለው መልኩ መመለስ እንደማይቻል መንግሥት ከድምዳሜ ላይ መድረሱን ተናግረዋል፡፡

‹‹የከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጋር በመሆን የቤት ፍላጎቱን በፍጥነት መመለስ ስለሚቻልበት መንገድ እያጠኑ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የጥናቱ መነሻ ምክንያት የቤት ባለቤት ለመሆን የተመዘገው ነዋሪ ቁጥር ከፍተኛ መሆንና ይህንን ከፍተኛ ፍላጎት በተያዘው የግንባታ ፍጥነት ማሳካት ይቻላል ተብሎ የሚታመን ባለመሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም መንግሥት ከሚገነባው በተጨማሪ፣ በውጭ ባለሀብቶች፣ በመንግሥትና በውጭ ባለሀብቶች፣ በመንግሥትና በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ትብብር ግንባታዎችን ለማካሄድ ጥናት በመካሄድ ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ከውጭ የሚመጣ ባለሀብትም ይሁን የአገር ውስጥ ባለሀብት የሚሠራው ለትርፍ መሆኑን የተናገሩት አቶ ካሳ፣ የቤቶቹ ዋጋ ኅብረተሰቡ ከሚሸከመው በላይ ከሆነ ደግሞ የባለሀብቶች ተሳትፎ ትርጉም እንደማይኖረው ይገልጻሉ፡፡

‹‹ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ያላቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተጠቃሚ መሆን የሚችሉት ምን ዓይነት ቴክኖሎጂን ብንጠቀም ነው? እንዴት ዋጋውን መቀነስ ይቻላል?›› የሚለው በጥልቀት በመመርመር ላይ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በከተማ ልማት፣ ቤቶችና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የመኖሪያ ቤቶች ልማትና የኮንስትራክሽን ኦፕሬሽን ምክትል ቢሮ ኃላፊ የሆኑት አቶ ታደሰ መኩሪያ በበኩላቸው፣ የቤቶቹን ግንባታ ፍጥነትን ለመጨመር በፕሮጀክት ማኔጅመንት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት የተባለ ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተጠሪ የሆነ ተቋም በመደራጀት ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት በቀጣዩ የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን ዘመን በራሱና በውጭ ባለሀብቶች፣ እንዲሁም በአገር ውስጥ ባለሀብቶች ትብብር ለመገንባት ያቀደው አጠቃላይ የቤቶች መጠን 750 ሺሕ መሆኑን ሪፖርተር ያገኘው ረቂቅ ሰነድ ያስረዳል፡፡

ከዚህ ውስጥ 430 ሺሕ የሚሆኑት ቤቶች በመንግሥት የሚገነቡ መሆናቸውን ይገልጻል፡፡ በውጭ ባለሀብቶች የሚገነቡት ደግሞ 63 ሺሕ ቤቶች ናቸው፡፡ በኅብረት ሥራ ማኅበራት ደግሞ 174 ሺሕ ቤቶችን ለመግንባት በረቂቅ ዕቅዱ ላይ ተገልጿል፡፡ በአጠቃላይ በአምስት ዓመት ውስጥ ለቤቶች ግንባታ 116 ቢሊዮን ብር ለማውጣት በዕቅድ ደረጃ ተቀምጧል፡፡

ይህ ዕቅድ ከእስካሁኑ የግንባታ አካሄድ አንፃር ሲታይ እጅግ ግዙፍ ቢሆንም፣ አሁንም የተመዘገበውን የአዲስ አበባ ነዋሪ የቤት ጥያቄ መመለስ የሚቻለው በሦስተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን መሆኑን መገመት ይቻላል፡፡

(ሚኪያስ ሰብስቤ ለዚህ ዘገባ አስተዋጽኦ አድርጓል)

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -