Monday, October 2, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአየር መንገድ ሠራተኞች ቤቶች ግንባታ ከቻይናው ኮንትራክተር ተነጠቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ኩባንያ በ760 ሚሊዮን ብር ለመገንባት ተዋዋለ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሠራተኞች የቤቶች ግንባታ ፕሮጀክት ሥራ ዤጂያንግ ዬቴንግ ከተባለው የቻይና ኮንትራክተር ተነጥቆ፣ በአዲስ ኮንትራክተር ለማስገንባት በተካሄደ ጨረታ አገር በቀሉ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ኩባንያ አሸናፊ ሆኖ የኮንትራት ውል መፈጸሙ ተገለጸ፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ፣ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን አሸናፊ የሆነው በጨረታው የቴክኒካል ምዘናውን ካለፉ ስድስት የአገር ውስጥና የውጭ ኮንትራክተሮች ጋር ተወዳድሮ ዝቅተኛ ዋጋ ማቅረብ በመቻሉ ነው፡፡ አፍሮ ጽዮን በቻይና ኩባንያ ተጀምረው የተቋረጡትን ቀሪ ግንባታዎች ለማጠናቀቅ በጨረታ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ 760 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

በዚህ ጨረታ ላይ ከአገር ውስጥ ተክለብርሃን አምባዬ፣ ፍሊንስቶንና ዮቴክ ኮንስትራክሽን ኩባንያዎች ተወዳዳሪ የነበሩ ሲሆን፣ ሁለቱ የቻይና ኮንትራክተሮች ኤቪኢሲና ሲኤምኢሲ የተባሉ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኤቪኢሲ የተባለው የቻይና ኮንትራክተር በአሁኑ ወቅት በአየር መንገዱ ተርሚናል የማስፋፊያ ሥራ ላይ በማከናወን ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት መጠናቀቅ የነበረበት ይህ ፕሮጀክት የዘገየው፣ ግንባታውን ሲያካሂድ የቆየው የቻይናው ዤጂያንግ ዬቴንግ ከአቅም ማነስ ጋር በተያያዘ ማጠናቀቅ ባለመቻሉ  እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህንንም በማየት የፕሮጀክቱ ኃላፊዎች ከኩባንያው ጋር  የነበራቸውን ውል ሊያቋርጡ እንደቻሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ይህ የመኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክት ቦሌ በሻሌ አካባቢ ከ300 ሺሕ ካሬ ሜትር በላይ እየተገነባ የነበረ ሲሆን፣ የቻይናው ኩባንያ ውሉ እስኪቋረጥ ድረስ ያከናወነው ግንባታ ከ25 እስከ 30 በመቶ የሚገመት ነው ተብሏል፡፡

የአየር መንገዱ የሠራተኞች ቤቶች ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ከአፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ጋር ባደረገው አዲስ ውል መሠረት 1,192 ቤቶች ይገነባሉ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 43 ታውን ሃውስ የሚል ስያሜ ያላቸው ቪላዎች፣ 20 ብሎክ ያላቸው አፓርትመንቶች፣ አምስት መልቲ ፋሚሊ አፓርትመንቶች ይገኙባቸዋል፡፡ በጠቅላላው 68 ብሎኮችን ይገነባል፡፡ እነዚህ የተለያዩ ደረጃና ይዘት ያላቸውን ቤቶች ለመገንባት ቀደም ብሎ ተሠርቶ በነበረ ዋጋ አነስተኛው ቤት 327,800 ብር አካባቢ ሲሆን፣ ከፍተኛው ደግሞ ከ1.05 ሚሊዮን ብር በላይ የሚፈጁ ናቸው፡፡ በዚህ ዋጋ መሠረት ሠራተኞች ቅድሚያ ክፍያ ፈጽመው የቤቶቹን መጠናቀቅ ሲጠብቁ ነበር፡፡

ቀደም ብሎ በተሠራው ዋጋ መሠረት አጠቃላይ ፕሮጀክቱ ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ይጠይቃል ተብሎ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ የቻይናው ኩባንያ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የሠራተኞች ቤቶች ሥራ ፕሮጀክት ማኅበር ጋር ውል ፈጽሞ ሥራ የጀመረው ከአራት ዓመት በፊት እንደነበር ይታወሳል፡፡ ግንባታውንም አጠናቅቆ ማስረከብ የነበረበት ባለፈው ዓመት ነበር፡፡  

ከኩባንያው ጋር ገብቶ የነበረው ውል ከቤቶቹ ግንባታ ውጪ በመንደሩ የመሠረተ ልማቶችንም ለመገንባት ጭምር ሲሆን፣ ኩባንያው እነዚህንም ሥራዎች ባለመሥራቱ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን ኩባንያ ተረክቧቸዋል፡፡ አጠቃላይ ግንባታውን በ15 ወራት ለማጠናቀቅ ተዋውሏል፡፡ ለዚህ ፕሮጀክት ግንባታ አየር መንገዱ ከሁለት ዓመትም በፊት ከፒቲኤ ባንክ 40 ሚሊዮን ብር ዶላር ብድር ማግኘቱ አይዘነጋም፡፡

አፍሮ ጽዮን በደረጃ አንድ ኮንትራክትነት የተመዘገበ ሲሆን፣ በተለያዩ ግንባታዎች ላይ በመሳተፍ ይታወቃል፡፡ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ፣ የሐሮማያ ዩኒቨርሲቲ፣ የኦሮሚያ ባህል ማዕከል፣ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ፣ የጂማ ዩኒቨርሲቲ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንና የጎንደር ብቅል ፋብሪካ ግንባታዎች ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅትም እየገነባቸው ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል የጂንካ አውሮፕላን ማረፊያና የጋምቤላ ስቴዲዮም ይገኙበታል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች