Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የምግብ ዘይት እንዲያስመጡ ከተፈቀላቸው ኩባንያዎች መካከል ሁለቱ ግዥ ፈጽመው እያስገቡ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ውሳኔ ለአገሪቱ ፍጆታ የሚውለውን የፓልም ዘይት ከውጭ እንዲያስገቡ ከተፈቀላቸው ዘጠኝ ኩባንያዎች ውስጥ፣ እስካሁን ሁለቱ ብቻ ግዢውን ፈጽመው በማስገባት ላይ መሆናቸው ተጠቆመ፡፡ ሌሎቹም እየተጠበቁ ነው፡፡

እንደ ምንጮች ገለጻ፣ ዘጠኙ ኩባንያዎች ማስገባት ያለባቸውን የምግብ ዘይት ከሐምሌ 1 ቀን 2ዐዐ7 ዓ.ም. ጀምሮ ማስገባት የነበረባቸው ቢሆንም፣ ሳያስገቡ ቆይተዋል፡፡ ኩባንያዎቹ ዘይቱን የሚያስገቡት ጊዜ ሊራዘም የቻለው ከምግብ ዘይት ግብይት እንዲወጣ የተደረገው ጅንአድ ለሐምሌ 2007 ዓ.ም. ዘይት ገዝቶ ስለበር፣ እሱን እንዲያስገባ በመፈቀዱ እንደሆነ ተጠቁሟል፡፡ ይሁን እንጂ በቀጣዩ ወር ሁሉም ኩባንያዎች በተደለደለላቸው ኮታ መሠረት ዘይቱን ገዝተው ማስጫን ነበረባቸው ተብሏል፡፡ በአሁኑ ወቅት የምግብ ዘይት እንዲያስመጡ ከተፈቀደላቸው ዘጠኙ ኩባንያዎች ውስጥ ግዥ ፈጽመው በማስገባት ላይ ናቸው የተባሉት አለ በጅምላና ሐዋዝ የተባሉት ኩባንያዎች ናቸው፡፡ በሌላ በኩል ግን ቀሪዎቹም ኩባንያዎች ዘይቱን አያስጭኑ እንጂ የግዥ ትዕዛዝ መስጠታቸው እየተነገረ ነው፡፡

በመንግሥት የምግብ ዘይት እንዲያስገቡ የተፈቀደላቸው ኩባንያዎች ቢፍቱ፣ አልሳም፣ ሐዋዝ፣ በላይነህ ክንዴ፣ አማሬሳ፣ ወንዶ፣ አምባሰልና አለ በጅምላ ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ኩባንያ በወር ማስገባት ያለበት የዘይት መጠን የተደለደለ ሲሆን፣ በአንድ ወር ውስጥ ያስፈልጋል ተብሎ የሚገመተውን 40 ሚሊዮን ሊትር ዘጠኙ ኩባንያዎች ከ3.2 ሚሊዮን እስከ 5.2 ሚሊዮን ሊትር የፓልም እንዲያስገቡ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ መሠረት በማስገባት በተመደቡበት ክልል ማሠራጨት ይጀምራሉ ተብሎ እየተጠበቀ ነው፡፡ በሥርጭት ድልድሉ መሠረት ከፍተኛ መጠን ያለውን የምግብ ዘይት እንዲያስገባ የተፈቀደለት ቢፍቱ የተባለው የኢንዶውመንት ኩባንያ ሲሆን፣ በወር ከ5.2 ሚሊዮን ሊትር በላይ በማስገባት በአብዛኛው በኦሮሚያ ክልል ያከፋፍላል፡፡

በኩባንያዎቹ የሥርጭት ድልድል መሠረት አለ በጅምላ አዲስ አበባ ውስጥ ለቂርቆስ፣ ለአዲስ ከተማና ለቦሌ ክፍለ ከተሞች እንዲሁም በሁለት የተለያዩ የክልል ከተሞች እንዲያሠራጭ ተመድቧል፡፡

እንደ ደብረ ማርቆስ ባህር ዳርና የመሳሰሉ ከተሞች ደግሞ በላይነህ ክንዴ እንዲያሠራጭ የሚደረግ ሲሆን፣ ቀሪውን የአማራ ክልል አምባሰል ይዞታል ተብሏል፡፡ ሌሎቹም ኩባንያዎች በተመሳሳይ መንገድ ዘይቱን የሚያከፋፍሉበት ቦታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ላለፉት አምስት ዓመታት የፓልም ዘይትን በብቸኝነት በማስመጣት ሲያከፋፍል የቆየው ጅንአድ ብቻ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አሁን ግን ይህንን ሥራ ዘጠኙ ኩብንያዎች እንዲይዙ ተደርጓል፡፡ የዘይት ማስመጣትና የማከፋፈሉ ሥራ ለጥቂት ኩባንያዎች ብቻ መፈቀዱ ተቃውሞ ያስነሳ ሲሆን፣ ይህም ተቃውሞ ለንግድ ሚኒስቴር ቢቀርብም እስካሁን ምንም ዓይነት ምላሽ አልተሰጠም፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ዓመታዊ የምግብ ዘይት ፍጆታ ከ480 ሚሊዮን በላይ ሊትር ወይም በወር 40 ሚሊዮን ሊትር እንደሚሆን ይገመታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች