Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን የግልገል ጊቤ አራት ኃይል ማመንጫን ለመገንባት የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የግልገል ጊቤ አራት ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግንባታ ለማከናወን፣ ከጣሊያኑ ግዙፍ ኩባንያ ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ኩባንያ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራረመ፡፡ የመግባቢያ ስምምነቱ ሐምሌ 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በሁለቱ ተቋማት ኃላፊዎች መፈረሙ ታውቋል፡፡

ይህ ፕሮጀክት በጊቤ ወንዝ ላይ ከተገነቡት ጊቤ አንድና ጊቤ ሁለት፣ በጊቤና በኦሞ ወንዞች ላይ ከተገነባውና በሚቀጥለው ዓመት ኃይል ማመንጨት ይጀምራል ተብሎ የሚጠበቀው ጊቤ ሦስት ቀጣይ ፕሮጀክት ነው፡፡

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ጊቤ አራትን ለመገንባት ያቀደውና በመግባቢያ ሰነዱ ላይም የሰፈረው፣ ፕሮጀክቱን ተረክቦ መገንባት የሚችለው ለግንባታ የሚሆን ገንዘብ ይዞ የሚመጣ ከሆነ ብቻ ነው፡፡

ሳሊኒ ኮንስትራክሽን ለግንባታው የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከአውሮፓ የፋይናንስ ተቋማት ያገኛል የሚል እምነት መኖሩን ምንጮች አመልክተው፣ ሳሊኒ በጊቤና በኦሞ ወንዞች ላይ የተካሄዱትን ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች በስኬት አከናውኗል ስለሚባል፣ የጊቤ አራት ፕሮጀክት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚችል አመልክተዋል፡፡

ነገር ግን ከአምስት የማያንሱ የቻይና ኩባንያዎች የጊቤ አራት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት እንዲሰጣቸው ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጥያቄ አቅርበዋል፡፡ መንግሥት በሳሊኒና በሌሎች ኮንስትራክሽን ኩባንያዎች የሚቀርቡለትን አማራጮች በመተንተን ግንባታውን በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን እንዲጀመር ያደርጋል በማለት ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ጊቤ አራት በደቡብ ክልል በቱርካና ሐይቅ አቅጣጫ የሚገነባ ነው፡፡ ይህ ፕሮጀክት ከተካሄደ ኢትዮጵያ ተጨማሪ 1,450 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማግኘት ያስችላታል፡፡ በጊቤና በኦሞ ወንዞች ላይ የሚካሄደው ፕሮጀክት እስከ አምስተኛ ድረስ እንደሚካሄድ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር ጥናት ያመለክታል፡፡ በጊቤ አምስት ላይ ግንባታ የሚካሄድ ከሆነ ደግሞ ፕሮጀክቱ 600 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንደሚኖረው የተደረገው ቅድመ ጥናት ያመለክታል፡፡

እስካሁን በጊቤና በኦሞ ወንዞች ላይ ከተካሄዱ ፕሮጀክቶች ኃይል በማመንጨት አቅም ጊቤ ሦስትን የሚስተካከለው የለም፡፡ ጊቤ ሦስት በአሁኑ ወቅት ግንባታው ከ90 በመቶ በላይ የደረሰ ሲሆን፣ በሙሉ አቅም ማመንጨት ሲጀመር አገሪቱ 1,870 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ታገኛለች፡፡ ከአዲስ አበባ በ300 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በዳውሮና በወላይታ ድንበር ላይ የሚገነባው ይህ ግዙፍ ግድብ 246 ሜትር ከፍታ አለው፡፡

ይህንን ፕሮጀክት ከአንድ ሳምንት በፊት ሦስተኛውን ፋይናንስ ልማት ጉባዔ ለመሳተፍ አዲስ አበባ የተገኙት የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ማቲዮ ሬንዜ ጎብኝተውታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገራቸው ኩባንያ የሆነው ሳሊኒ ያከናወነውን ግንባታ አድንቀው፣ የሚያመነጨው ኃይል ከሁለት የኑክሌር ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እኩል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ማመንጫና ከጣና በለስ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ግንባታ ጨምሮ፣ አምስት ግዙፍ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ያካሄደውና በማካሄድ ላይ ያለው ሳሊኒ አምስተኛውን ፕሮጀክት ለማግኝት ጥረት እያደረገ መሆኑን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች