ከእሑድ ሐምሌ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ምሽት ጀምሮ አዲስ አበባ እንደሚገቡ የሚጠበቁት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከኢትዮጵያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በሁለቱ አገሮች የጋራ ጉዳዮችና የአካባቢው አገሮች የፀጥታ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ እንዲሁም ከአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች መሪዎች ጋር የሚወያዩ ሲሆን፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ አባላት ጋርም ይነጋገራሉ፡፡ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ጉዳዮች ላይ ከመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ጊዜ ተሰጥቶ ውይይት እንደሚደረግ እየተጠበቀ ነው፡፡ የኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት ከተሰማ ጊዜ ጀምሮ በአገር ውስጥና በውጭ ባሉ ኢትዮጵያዊያን ዘንድ የተደበላለቁ ስሜቶች ቢንፀባረቁም፣ ኦባማ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋርም ሆነ ከተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በሚያደርጉት ውይይት የሰብዓዊ መብት ጉዳይን እንዲያነሱ ግፊት እየተደረገባቸው ነው፡፡ በአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች ታሪክ በሥልጣን ላይ እያሉ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን የሚጎበኙት ፕሬዚዳንት ኦባማ፣ በኬንያና በኢትዮጵያ በሚያደርጉት ጉብኝት አሜሪካ በምሥራቅ አፍሪካ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ያላትን ቁርጠኝነተ የምታሳይበት እንደሆነም እየተነገረ ነው፡፡ የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማን ጉብኝት አስመልክቶ በየማነ ናግሽ የተጠናቀረው ዘገባ ለመመልከት እዚህ ላይ ይጫኑ፡፡