የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ማክሰኞ ሐምሌ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በ‹‹ፊድ ዘ ፊውቸር›› ኢኒሽዬቲቭ የሚደገፈውን ፋፋ የምግብ ፋብሪካ በጎበኙበት ወቅት፣ የኢኒሽዬቲቩ ዋና ዓላማ የኢትዮጵያ እንዲሁም የአፍሪካ አነስተኛ ገበሬዎችን ምርት ማሳደግ መሆኑን አስታወቁ፡፡
‹‹አመርቂ በሆነ ሥራ ፈጠራ የአፍሪካ አነስተኛ ገበሬዎች በምርታቸው ላይ ከፍተኛ ማሻሻያ ማድረግ ይችላሉ፤›› ሲሉ ለአገር ውስጥና ለውጭ ጋዜጠኞች ገልጸዋል፡፡
‹‹ምንም እንኳን ምግብ የሚመረተው እዚሁ ቢሆንም የምግብ ቅንብሩ ግን የሚካሄደው ሌላ ቦታ መሆኑ ሌላው ተጠቃሽ ችግር ነበር፤›› ያሉት ፕሬዚዳንቱ፣ በዚህም ሳቢያ የምግብ ቅንብር የሚያካሄዱት ኢንዱስትሪዎች አልነበሩም በማለት ገልጸው የፋፋ ዓይነት ፋብሪካዎች መምጣት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማ፣ ‹‹እኛ የምንፈልገው ኢትዮጵያ ራሷን መመገብ ብቻ ሳይሆን ምግብ ላኪ እንድትሆን ነው፤›› ብለዋል፡፡
በጉብኝቱ ወቅት ከጉራጌ ዞን የመጡ አነስተኛ ገበሬ ወ/ሮ ጊፍቲ ጀማል፣ ለፕሬዚዳንት ኦባማ እንደገለጹት፣ በዱፖንት-ፓዮኒር ጥምረት በሚያገኙት እገዛ ምርትና ገቢያቸውን አሳድገዋል፡፡
የዱፖንት-ፓዮኒር የኢትዮጵያ ካንትሪ ማኔጀር አቶ መላኩ አድማሱ በበኩላቸው፣ የወ/ሮ ጊፍቲ እና መሰል አነስተኛ ገበሬዎች የበቆሎ ምርት በ300 ፕርሰንት የጥራት መጠን መጨመሩን ገልጸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ፋብሪካውን በጎበኙበት ወቅት ከፋብሪካው ሠራተኞችና ከከፍተኛ የምርት አማካሪ ገለጻ ተደርጎላቸዋል፡፡
‹‹ፊድ ዘፊውቸር›› የፕሬዚዳንት ኦባማ የዓለም አቀፍ የረሃብና የምግብ ደኅንነት ኢኒሽዬቲቭ ሲሆን፣ አጋር አገሮችን ከድህነት የማላቀቅና በምግብ ራሳቸውን እንዲችሉ የሚረዳ ነው፡፡ የኢኒሽዬቲቩ ልዩ ትኩረት በአነስተኛ ገበሬዎች ላይ በመሆኑ፣ በተለይ ሴት አነስተኛ ገበሬዎችን ለማገዝ ይሠራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ኢኒሽዬቲቩ ለ19 አገሮች ድጋፍ ያደርጋል፡፡
ፋፋ የምግብ ፋብሪካ በዓመት 25,000 ቶን ተጨማሪ ምግቦች አምራች ነው፡፡ ምርቶቹም በንጥረ ነገር የበለፀጉ የወተት ዱቄት፣ የሕፃናት ምግብ፣ የተለያዩ ዱቄቶችና የገብስ ቅልቅል ናቸው፡፡ የፋፋ ምርቶችን የተመድ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገዝቶ ለችግር ለተጋለጡ ለሶማሊያና ለደቡብ ሱዳን ስተደኞች ያከፋፍላል፡፡