Friday, April 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተማሪው ጉዞ በአምባሳደር ዘውዴ ረታ እይታ

የተማሪው ጉዞ በአምባሳደር ዘውዴ ረታ እይታ

ቀን:

የዘመናዊ ትምህርት እንደ አሁኑ ባልተስፋፋበት ከአራት አሥርት ዓመታት በፊት የትምህርቱን ዓለም የሚቀላቀሉ በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ነበሩ፡፡ የትምህርት ባህሉን ለማሳደግም ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ልዩ ልዩ የትምህርት ዕድሎችን ከብዙ ማበረታቻዎች ጋር ያመቻቹ ነበር፡፡

የውጭ የትምህርት ዕድል ማመቻቸትም አንዱ ነበር፡፡ በወቅቱ ዕድሉን ካገኙት መካከል የታሪክ ጸሐፊው አምባሳደር ዘውዴ ረታ ይገኛሉ፡፡ ሐምሌ 18 ቀን 2007 ዓ.ም. በኤግዚቢሽን ማዕከል በተዘጋጀው የቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ምረቃ በዓል ላይ ባደረጉት ንግግር የአሁን ጊዜ ተማሪዎች የሚገጥሟቸውን ፈተናዎችና ከዓመታት በፊት የነበረውን የተማሪዎች የተመቻቸ የትምህርት ሒደት በንፅፅር አስቃኝተዋል፡፡

እሳቸው እንዳቀረቡት ከዓመታት በፊት የነበረው የትምህርት አመራር ከዛሬው ጋር ሲነፃፀር ልዩነቱ እጅግ የሰፋ ነው፡፡ ተማሪዎች ፍጻሜአቸውን አሳምረው ለመንግሥት አገልግሎት እንዲደርሱ ከአንደኛ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን እስኪጨርሱ ከፍተኛ እንክብካቤ ይደረግላቸዋል፡፡ ‹‹በዚያን ዘመን ተማሪዎች የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የሚያጠናቅቁት አዳሪ ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ምግብ ልዩ ልዩ አልባሳት ሆነ ሌሎች ለትምህርት የሚያስፈልጋቸው ግብዓቶችን በነፃ ያገኙ ነበር፡፡ ከተማሪዎቹ የሚጠበቀው በርትቶ መማር ብቻ ነበር፤›› ይላሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በዚህ መልኩ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡ ብሔራዊ የመልቀቂያ ፈተና ሲያልፉም ለዩኒቨርሲቲ ትምህርት ወደ ባህር ማዶ ይላካሉ፡፡ ብዙ ጊዜ የሚላኩት አሜሪካና እንግሊዝ ነበር፡፡ ትምህርታቸውን ጨርሰው ወደ አገራቸው እስኪመለሱም አስፈላጊው ድጋፍ ሁሉ ይደረግላቸዋል፡፡ ይህም ለጉዞአቸው የሚያስፈልጉ ወጪዎችን ከማሰናዳት ይጀምራል፡፡

ለወንዶቹ ከሱፍ ጨርቅ የተሰፉ አልባሶች፣ ሸሚዞች፣ ክራቫቶች፣ መጫሚያዎች እንዲሁም ካፖርትና ባርኔጣ በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ይቀርብላቸዋል፡፡ ለሴቶቹም እንዲሁ የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ይዘጋጃል፡፡ ለጉዞአቸው ስንቅ እንዲሆንም 350 የአሜሪካ ዶላር ከነፃና አንደኛ ማዕረግ የአውሮፕላን ትኬት ጋር ይሰጣቸዋል፡፡ ከዚያም ከምክትል የትምህርት ሚኒስትሩ ጋር ወደ ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት በመሄድ ንጉሠ ነገሥቱን ይሰናበታሉ፡፡ ንጉሠ ነገሥቱም በርትተው ትምህርታቸውን እንዲጨርሱና ለአገራቸው እንዲበቁ አደራቸውንና መልካም ምኞታቸውን ይገልጡላቸው ነበር፡፡

በዚህ መልኩ ሽኝት የተደረገለት ወጣት ትምህርቱን ጨርሶ ወደ አገሩ ሲመለስ የሚደረግለት አቀባበልም እንደዚሁ አስደሳች እንደነበር አምባሳደር ዘውዴ ያስታውሳሉ፡፡ ቀደም ብሎ ወደ አገሩ ለመመለስ ያቀደበትን ቀን ለትምህርት ሚኒስትሩ በቴሌግራም ያሳውቃል፡፡ በዚያ ቀን የትምህርት ሚኒስትር ወኪልና የወጣቱ ዘመዶች አቀባበል ያደርጉለታል፡፡ ከዚያም የአገሩን አየር እስኪላመድ በሚል ከሦስት እስከ አራት ቀናት ያህል በእቴጌ ሆቴል እንዲቆይ ይደረጋል፡፡

ከዚያም በምክትል ትምህርት ሚኒስትሩ አማካይነት ወደ ቤተ መንግሥት ይወሰዳል፡፡ ንጉሠ ነገሥቱን እጅ ከነሳ በኋላም ስለተማረው የትምህርት ዓይነት መጠነኛ ማብራሪያ ይሰጣል፡፡ በወቅቱ የትምህርት ሚኒስትሩ ራሳቸው ንጉሠ ነገሥቱ ነበሩ፡፡ ትምህርቱን ጨርሶ አገሩ የመጣው ወጣትም በምን ዓይነት ሥራ መሰማራት እንደሚገባው የሚያጠኑትና የሹመት ሐሳብ የሚያቀርቡት ምክትል ትምህርት ሚኒስትሩ ናቸው፡፡ ሹመቱ የሚፀድቀውም የንጉሠ ነገሥቱን ይሁንታ ሲያገኝና ከጽሕፈት ሚኒስትር ትዕዛዙ ሲሰጥ ነው፡፡

ወጣቱን በተገቢው ሥራ ለመመደብ የሚደረገው እንቅስቃሴ ብዙ ጊዜ የሚሳካ ቢሆንም አልፎ አልፎ ፈገግ የሚያሰኙ ክስተቶች ያጋጥማሉ፡፡ በዚህ ረገድም በአንዱ ተማሪ ላይ የደረሰውን እንደዚህ ያስታውሳሉ፡፡ ወጣቱ በውጭ አገር የከብት ሕክምና ትምህርት ተምሮ ይመጣል፡፡ በወቅቱ የነበሩት የጽሕፈት ሚኒስትሩም ግን የተመደበበትን የሥራ ዘርፍ ሲያሳውቁ ችግር ተፈጠረ፡፡ በወቅቱ በአዲስ አበባ ለከብት የተለየ ሕክምና መስጫ ባለመኖሩ በቀዳማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታል ተመድበው እንዲሠሩ የሚል ማዘዣ ተሰጠ፡፡

በሌላ ጊዜ ደግሞ አንድ ወጣት የሳይኮሎጂ ትምህርቱን በውጭ አገር አጠናቅቆ ይመጣል፡፡ ‹‹ይህ ለሴቶች የተመደበ ሥራ በመሆኑ ወደ ተማርክበት አገር ተመልሰህ በሌላ ሙያ ብታስለውጥ ይሻላል›› በሚል አለመግባባት መፈጠሩን አስታውሰዋል፡፡

ምንም እንኳን መሰል ገጠመኞች አልፎ አልፎ ቢከሰቱም ወጣቱ ሥራ ከያዘ በኋላ በበቂ መቋቋም ካልቻለ መንግሥት የተለያዩ ድጋፎችን ያደርግለታል፡፡ በኑሮውም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ስለማያጋጥሙት ለተደረገለት ሁሉ አመስግኖ ይኖራል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ በዚህኛው ትውልድ የትምህርት ባህሉ ቢያድግም ዘርፈ ብዙ ችግሮች ያጋጥማሉ፡፡ በመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የሚመደቡ ተማሪዎች ምግብ ባይቸገሩም ሌሎች ብዙ ወጪዎች ያጋጥሟቸዋል፡፡ ልዩ ልዩ መጻሕፍቶችን መግዛት ግድ ይላቸዋል፡፡ ችግሩ በግል ኮሌጆች በሚማሩት ላይ ሊበረታ ይችላል፡፡ ወርሃዊ የትምህርት ክፍያ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህም በየጊዜው እየናረ ከሚመጣው የኑሮ ውድነት ጋር ተዳምሮ ተማሪውን ሲፈትን ይታያል፡፡ ‹‹ዛሬ እንደዚህ አሸብርቃችሁ ስናያችሁ ትምህርታችሁን ከዳር ለማድረስ ያደረጋችሁት ተጋድሎ ይታወሰናል›› በማለት ንግግራቸውን ቋጭተዋል፡፡  

ምንም እንኳን በዛኔ የነበረው የትምህርት ሁኔታ ለተማሪዎች በእጅጉ የተመቸ ቢሆንም ዕድሉን ያገኙት በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ የመማር ባህሉም አናሳ ነበር፡፡ በተለይም የሴቶቹ ተሳትፎ እጅግ ያነሰ እንደነበር አያጠያይቅም፡፡ አሁን ላይ በትምህርት ገበታ ለመቆየት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም የተማሪዎች ቁጥር በየዓመቱ እየጨመረ ይገኛል፡፡ በትምህርታቸው ከወንዶቹ እኩል መሳተፍ እንዳልቻሉ የሚነገርላቸው ሴቶችም ትልቅ ውጤት እያስመዘገቡ መሆኑ በብዙ አጋጣሚ እየታየ ነው፡፡

በቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ 1063 ተማሪዎች በድህረ ምረቃ፣ ቅድመ ምረቃ፣ በደረጃ ሦስትና በደረጃ አራት ተመርቀዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል 41 ከመቶ የሚሆኑት ወንዶች ሲሆኑ 59 ከመቶ ያህሉ ሴቶች ናቸው፡፡ ጥሩ ውጤት አስመዝግበው ከተሸለሙት ውስጥም ጥቂት የማይባሉ ሴቶች ነበሩ፡፡

የ23 ዓመቷ አሚራ አክመል አንዷ ተሸላሚ ነች፡፡ አሚራ ከዓመታት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ጀምራ ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙ አልገፋችበትም የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ሳለች ባጋጠማት ሕመም ትምህርቷን አቋርጣለች፡፡ በኋላም በቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ የአካውንቲንግ ትምህርት መማር ጀመረች፡፡ ለሦስት ዓመታት ያህል ስትማርም አጠቃላይ የትምህርት ወጪዋ በወር ከ700 እስከ 800 ይደርስ ነበር፡፡ በዚህ ሦስት ዓመት ውስጥም ቤተሰቦቿ ለትምህርት ክፍያ እስከ 15 ሺሕ ብር ድረስ እንዳወጡ ትናገራለች፡፡ በትምህርት ጠንካራ ስለነበረችም 3.95 ነጥብ በማስመዝገብ ከዲፓርትመንቷ የዋንጫ ተሸላሚ ሆናለች፡፡

ለብዙዎቹ ተመራቂዎች ትልቅ ጥያቄ የሆነው የሥራ ዕድልም አያሳስባትም፡፡ ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀላት የማስተማር ዕድል ለመጠቀም ወስናለች፡፡ ተጨማሪ የትምህርት ዕድል ስለሰጣትም አጋጣሚው አስደስቷታል፡፡

spot_img
Previous article
Next article
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...