ክረምት ከትምህርት ወይም ከሥራ ፋታ የሚገኝበት ነውና ብዙዎች ወቅቱን ከሌላ ጊዜ በተሻለ ለንባብ ይመርጡታል፡፡ ይህን ከግምት በማስገባት ይመስላል በዚህ ክረምት ብዙ ንባብ ነክ ክንውኖች ተካሂደዋል፡፡ ከእነዚህ ሊመደብ የሚችለው ከነገ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 26 ቀን 2007 ዓ.ም. በኤግዚቢሽን ማዕከል የሚካሔደው የመጻሕፍት ዐውደ ርዕይና ባዛር ነው፡፡
‹‹ንባብ ለሕይወት›› በሚል መሪ ቃል የሚከናወን ሲሆን፣ የዝግጅቱ ዋና ዳይሬክተር ቢንያም ከበደ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ ዋነኛ ትኩረቱን በወጣቶች ላይ ያደረገ ነው፡፡
‹‹ንባብን የዕድሜ ልክ ወዳጃችን እናድርግ የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ መሪ ቃሉን መርጠናል፣›› የሚለው ቢንያም፣ ተማሪዎች ከመደበኛ ትምህርት አጋዥ መጻሕፍት በተጨማሪ ሌሎች መጻሕፍት እንዲያነቡና ሁለገብ ዕውቀት እንዲጨብጡ ለማሳሰብ እንዳቀዱ ይገልጻል፡፡
የባዛሩ የመክፈቻ ሥነ ሥርዓት ነገ ረፋድ ላይ ይካሔዳል፡፡ ባዛሩን በክብር እንግዳነት የሚከፍቱት ሕፃናት ናቸው፡፡ ከሰዓት አሥራ ሁለቱ የንባብ አምባሳደሮች ይፋ ይደረጋሉ፡፡ ቢንያም እንደሚለው፣ ‹‹የንባብ አምባሳደር›› በሚል የተመረጡት ግለሰቦች በሚወጣው ዓመት በየትምህርት ቤቱ እየተዘዋወሩ ስለንባብ ይቀሰቅሳሉ፡፡ አምባሳደሮቹ ተሞክሮአቸውን በማካፈል የንባብ መነቃቃት እንደሚፈጥሩ ተስፋ ያደርጋል፡፡ ግለሰቦቹ ከተለያየ የሙያ መስክ የተውጣጡ ሲሆን፣ የተመረጡት ድርጅቱ የተነሳለትን ዓላማ ለማሳካትና ስለ ንባብ ለማሳወቅ ይረዳሉ በማለት እንደሆነ ይገልጻል፡፡
በባዛሩ መጽሐፍ አሳታሚዎች፣ አከፋፋዮች፣ የትምህርት እንዲሁም የጥናትና ምርምር ተቋሞች ይሳተፋሉ፡፡ ከበርካታ አከፋፋዮች በተጨማሪ ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ፣ ሊደርሺፕ ኢንስቲትዩትና ማኅበራዊ ጥናት መድረክን የመሰሉ ተቋሞች እንደሚገኙ ቢንያም ይናገራል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ በእነዚህ ተቋሞች የሚዘጋጁ ጥናታዊ ጽሑፎችና ጆርናሎች ለአንባቢ የሚደርሱበት አጋጣሚ አናሳ ነው፡፡ ‹‹ጥናቶችና ጆርናሎች በተቋሞቹ መጻሕፍት መደርደሪያ ነው የሚቀመጡት፤ በባዛሩ እነዚህ ጥራዞች ለኅብረተሰቡ እንዲቀርቡ ይደረጋል፤›› ይላል፡፡
ከአሳታሚዎች መካከል በሕፃናት መጻሕፍት ላይ ትኩረታቸውን ያደረጉ ይገኙበታል፡፡ በተለያዩ ቋንቋዎች የሕፃናት መጻሕፍት የሚያዘጋጁ አከፋፋዮች ተሰባስበው ሥራዎቻቸውን እንደሚያቀርቡ ተናግሯል፡፡ በሕፃናት ዙሪያ የሚሠሩ ድርጅቶች ለሕፃናት እንዲሁም ለቤተሰቦቻቸው መልዕክት የሚያስተላልፉበት መንገድ እንደሚከፈት አክሏል፡፡ ከጠቀሳቸው ድርጅቶች አስቴር ነጋ አሳታሚ ድርጅት፣ ቡክ ወርልድና ስፖት ላይት ይገኙበታል፡፡
በዐውደ ርዕዩ ላይ ከሚቀርቡ መጻሕፍትና ጥናቶች ጐን ለጐን በጥራዝ ያልቀረቡም (በሶፍት ኮፒ የሚገኙም) አሉ፡፡ እንደ ቢኒያም ገለጻ፣ ተማሪዎች ሊገለገሉባቸው የሚችሉ 28 የትምህርት ዘርፎችን ያካተቱ መጻሕፍት በሶፍት ኮፒ ቀርበዋል፡፡ የእነዚህን የተመረጡ መጻሕፍት ቅጂ በፍላሽ፣ በሲዲ ወይም በሌላ መንገድ በነጻ መውሰድ ይቻላል፡፡ ‹‹ቅጂዎችን ለመውሰድ ወደ 20 የሚደርሱ ኮምፒውተሮች ተዘጋጅተዋል፤ ወጣቶች ለቴክኖሎጂ ካላቸው ቅርበት አንፃር ዘመኑ በደረሰበት መንገድ እንዲገለገሉ ያስችላሉ፤›› ሲል ያብራራል፡፡ በባዛሩ ላይ የሚሸጡ መጻሕፍት አሥር በመቶ ቅናሽ ይደረግላቸዋል፡፡
በባዛሩ ላይ መጻሕፍት ከሚሸጡባቸው ድንኳኖች በተጨማሪ በንባብ ላይ የሚያጠነጥኑ ውይይቶች የሚካሔዱባቸው ክፍሎችም ይኖራሉ፡፡ አዳዲስ መጻሕፍት የሚመረቁ ሲሆን፣ ደራስያኑ በየመጽሐፋቸው ላይ ፊርማቸውን የሚያኖሩበት ሥነ ሥርዓትም ይኖራል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ደራስያን ከአንባቢዎች ጋር በቀጥታ የሚገናኙበትን መንገድ የሚፈጥር ይሆናል፡፡
በዐውደ ርዕዩ ከሚመረቁ መጻሕፍት መካከል ቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ ያዘጋጃቸው ወደ 200 የሚጠጉ የሕፃናት መጻሕፍት ይጠቀሳሉ፡፡ ከባዛሩ በፊት ሊመረቁ የነበሩና ድርጅቱ ከአሳታሚዎች ጋር በመስማማት ባዛሩ ላይ እንዲመረቁ ያደረጋቸው መጻሕፍትም ይገኙበታል፡፡ የአብነት ስሜ ‹‹የቋንቋ መሠረታውያን››፣ የአፈወርቅ በቀለ የትርጉም መጽሐፍ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የተዘጋጀ መጽሐፍና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው፡፡ መጻሕፍቱ እዚያው ለገበያ ከመቅረባቸው ባሻገር አንባቢዎች ከደራስያኑ ጋር መገናኘት መቻላቸው የተለየ ድባብ እንደሚፈጥር ቢንያም ያምናል፡፡
በጐተ ኢንስቲትዩት በኩል 15 ደራስያን ባዛሩ ላይ ስለ ሥራዎቻቸው የሚወያዩበት መድረክ ይኖራል፡፡ ለደራስያኑ ሰዓት ተመድቦላቸው በየአዳራሹ ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡
የመጻሕፍት ዓውደ ርዕዮች በተለይ በክረምት ወራት እንደሚበራከቱ የሚናገረው ቢንያም፣ ዐውደ ርዕዮቹ ደረጃቸውን ጠብቀው መዘጋጀት እንዳለባቸው ይናገራል፡፡ መርሐ ግብሮቹ ሲዘጋጁ በዘርፉ የሚገኙ ባለድርሻ ተቋሞችን ቢያሳትፉ ውጤታማ ይሆናሉ ይላል፡፡ የመጻሕፍት ዐውደ ርዕዮች መበራከታቸው ብቻውን ለውጥ እንደማያመጣ በአጽንኦት የሚናገረው ዳይሬክተሩ፣ ግባቸውን እንዲመቱ ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ያስረዳል፡፡
‹‹ዐውደ ርዕዮች በተደጋጋሚ መዘጋጀታቸው ብቻውን የንባብ ባህሉን አያሳድገውም፤ የሚሰጣቸው ትኩረትና አዘገጃጀታቸው ይወስነዋል፤›› ይላል፡፡ በቀደሙት ዓመታት የመጻሕፍት ዐውደ ርዕዮች በስፋት ይዘጋጁ እንደነበር በማስታወስ፣ ከጊዜ በኋላ መቀዛቀዙን ይናገራል፡፡ አሁንም በዘርፉ ያሉ ተቋሞች ተባብረው ቢሠሩ ለውጥ እንደሚመጣ ይናገራል፡፡
ከንባብ ዐውደ ርዕዮች ዝግጅት ጋር በተያያዘ ስፖንሰር ማጣትና ተያያዥ ችግሮች በተደጋጋሚ ይነሳሉ፡፡ ባዛሩን ሲያዘጋጁ የጐላ የፋይናንስ ችግር እንዳልገጠማቸው ቢንያም ይገልጻል፡፡ የግል የንግድ ተቋሞች፣ የባዛሩ ተሳታፊዎችና ትምህርት ሚኒስቴር በመርሐ ግብሩ ዝግጅት ተሳትፈዋል፡፡
ሌላው በተደጋጋሚ የሚደመጠው ትችት በሌሎች መርሐ ግብሮች የሚገኘው ያህል ጐብኚ በመጻሕፍት ዓውደ ርዕዮች አለመገኘቱ ነው፡፡ ሐሳቡን የሚስማማበት ቢንያም፣ መገናኛ ብዙኃን ቅስቀሳ ማድረግ እንዳለባቸው ያሳስባል፡፡ ስለዐውደ ርዕዮች ከማስተዋወቅ ባለፈ ኅብረተሰቡ ስለ ንባብ ያለው ግንዛቤ እንዲሻሻል መሠራት አለበት ይላል፡፡
በርካታ ታዳሚዎችን ለመሳብ ከፍተኛ ማስተዋወቂያ እንደሠሩ ይናገራል፡፡ በራሪ ወረቀቶችን በመበተን፣ በማኅበረሰብ ድረ ገጽ በመቀስቀስና ሌሎችም መንገዶች መጠቀማቸውን በመግለጽ በርካታ ታዳሚዎች እንደሚገኙ ተስፋ ያደርጋል፡፡