Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየእኛ ነፍስ የዶሮ ነፍስ ነው?

የእኛ ነፍስ የዶሮ ነፍስ ነው?

ቀን:

 በይነጋል በላቸው

 ‹‹ፍርድ እንደ ራስ ነው›› በየአጋጣሚው የምንሰማው አነጋገር ነው፡፡ ተራ አነጋገር አይደለም፡፡ ብዙ ትንተና ሊሰጥበት የሚችል ጥልቅ ሐሳብ ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር፣ የንግድና የወንጀል ሕጎች ከመደንገጋቸው በፈት ነበር፡፡ ከኑሮ ልምድ የተገኘ የሕዝብ ዕውቀት በመሆኑ ከቤተ መንግሥት ያልወጣውን  ፍትሐ ነገሥትንም ሊቀድመው ይችል ይሆናል፡፡ ፍርድ እንደ ራስ ነው፡፡ ፍርድ እንደ ራስ ነው ማለት፣ ከሳሽም ሆነ ተከሳሽ ዳኝነት ተቀምጦ ነገሩን ቢያየው የሚፈርደው ፍርድ እንዲህ እንደተፈረደው ነው የሚሆነው ብሎ ማመን ነው፡፡ እጅ የቆረጠ ሰው እጅ በመቆረጥ አይቀጣም ብሎ  የፈረደ ሰው፣ የእሱን እጅ አንዱ ቢቆርጠው፣ በእሱ ላይ ጉዳት ስላደረሰ እጁን በመቁረጥ እንዲቀጣ ሊፈርድ ወይም እንዲፈረድለት ሊጠይቅ አይችልም ማለት ነው፡፡ አቶ አያሌው አስረስ ሐምሌ 12 ቀን 2007 ዓ.ም. በታተመው ሪፖርተር  ጋዜጣ፣ ‹‹የካሳ ክፍያ ጥያቄው የፍትሕና የክብር ጥያቄ ነው›› ሲሉ ያነሱት ጉዳይ ዋጋ የሚያገኘው ፍርድ እንደ ራስ ብሎ ነገሩን የሚገነዘብና ስለአውነት የሚቆረቆር ሰው ሲኖር ነው፡፡ ጥያቄው ጊዜ እንዳለፈበት ወይም ተገቢ እንዳልሆነ የሚያስቡ ካሉ ተሳስተዋል፡፡ ከሁሉ በፊት ለምን ተገቢና ተመጣጣኝ ከሳ እንደተነፈግን ቢጠይቁ መልካም ይሆናል፡፡

በ1917 ዓ.ም.  የንግሥት ዘውዲቱ ምኒልክ እንደራሴና አልጋ  ወራሽ የሆኑት ራስ ተፈሪ መኮንን አወሮፓን ጎበኙ፡፡ በዚህ ጉዟቸው ከጎበኟቸው አገሮች አንዷ ኢጣሊያ ነበረች፡፡  በጉበኝቱ ጊዜ ሙሶለኒ ኢትዮጵያን ለመውረር መነሻ ዕቅዱን መጨረሱን፣ ጦርነቱን ከአስመራና ከሞቃዲሾ በመነሳት ለማካሄድ መታስቡ እንደተነገራቸው ለአንጀሎ ዶል ቦኮ ገልጸውለታል፡፡ ኢጣሊያዊው ዶል ቦኮ የኢትዮጵያ ጦርነት የተባለ የታሪክ መጽሐፍ አለው፡፡

ጣሊያኖች ድንበር ጥሰው ወለወልን የያዙት ‹‹የጣሊያን ወታደር የረገጠው መሬት የጣሊያን ግዛት ነው›› ብላ እንዳወጁ ነው፡፡ ኅዳር 14 ቀን 1927 ዓ.ም.  የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ወሰን ተካላይ ባለሥልጣናት ከቦታው ሲደርሱ የጠበቃቸው፣ በኢጣሊያ ወታደር የተያዘ መሬትና ከዚህ አታልፉም የሚል ኃይል ነው፡፡ ኅዳር 26 ቀን 1927 ዓ.ም. ጣሊያኖች በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ደንገት ጥቃት ከፈቱ፤ ጦርነቱ በዚህ ተጀመረ፡፡ ይህ የሆነው ንጉሡ ስለወረራው ከሰሙ ከአሥር ዓመታት በኋላ ነው፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ ጦርነቱ በሚጠይቀውና በሚፈለገው መጠን ተዘገጅተውበታል፣ ሕዝቡንም አዘጋጅተውታል ተብሎ አይታመንም፡፡ ያለመቻላቸው ዋናው ምክንያት ንጉሡ በመንግሥታቱ ማኅበር ላይ ያሳደሩት እምነት፣ የውስጥና የውጭ ችግሩ ከፍተኛ መሆን  እንደነበር ይጠቀሳል፡፡ ኢትዮጵያ የገዛችው የጦር መሣሪያ ጂቡቲ ወደብ ደርሶ ወደ አገር ቤት እንዳይገባ በፈረንሣዮች መደረጉ፣ ታግቶ ቀይቶ በኋላ ለጣሊያኖች መሰጠቱ  ከተፅዕኖው አንዱ መሆኑ አይዘነጋም፡፡ በአንፃሩ በተከፈቱት የወታደር ማሠልጠኛዎች እየሠለጠኑ የወጡ ኢትዮጵያዊያን ጦራቸውን በመምራትና በማዋጋት ብቃታቸው ጠላት ሳይቀር ያደነቃቸው መሆናቸውም ሳይነገር አይታለፍም፡፡

አልሞ ከመተኮስ ልምምድ በስተቀር የተለየ የውጊያ ሥልጠና የኢትዮጵያ ሠራዊት የለውም፡፡ ወደ ኋላ ከጠላት እየማረከ ከታጠቀው መሣሪያ በስተቀር መጀመርያ  ላይ ምንም አልነበረውም፡፡ ጦርነቱን የተዋጋው ሕይወቱን  መሣሪያ አድርጎ መሆኑም ተደጋግሞ የተነገረ ነው፡፡ በእጁ በነበረው መሣሪያ የሠራው ሥራ ግን አጀብ የሚያሰኝ ነው፡፡ እንደ ውጂግራና ናስማሰር ያሉ ጠበንጃዎችን የአየር መቃወሚያ አደርጎ  በመጠቀም የኢጣሊያ ጦር አይሮፕላኖች ከ7,000 ጫማ በታች እንዳይበሩ በማድረግ ተፈታትኗቸዋል፡፡ ጣሊያኖች ነገሩ እየከበደቸው በመሄዱ የመረጡት በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ ቦምብና የመርዝ ጋዝ ማዝነብ ነው፡፡ በዚህም ለጊዜው አሸናፊ ሆኑ፡፡ ‹‹ጣሊያኖች ጦርነቱን ያሸነፉት በጦር ኃይላቸው ሳይሆን በጦር አይሮፕላናቸው ነው፡፡ እሱ ባይሆን ኑሮ ለእነሱ ድል ቀላል ባልሆነም ነብር፤›› በማለት ዊሕብ ፓሻ ይመሰክራል፡፡

አርባ ዓመት ቂም ቋጥረው፣ ከአሥር ዓመታት በላይ ተዘጋጅተው በኢትዮጵያ ላይ ወረራ የጀመሩት ጣሊያኖች የሚፈልጉት ምን እንደነበር  ፍርጥ አድርጎ የሚነግረን አምባላጌ ላይ የተማረከው የጣሊያኑ መስፍን  ዑል ዱካ ዲ ኣኦስታ  ነው፡፡ ‹‹ከተቻለ ኢትዮጵያን ከኢትዮጵያዊያን ጋር ካልተቻለ ኢትዮጵያን ብቻዋን ሙሶሎኒ ይፈለጋል፤››  በማለት፡፡ ለዚህም ነው ሕዝቡን ያለ ርኅራሔ የፈጁት፡፡

ጣሊያኖች ኢትዮጵያን መያዛቸውን ለዓለም ቢያውጁም በተለይም ወደ ኋላ ከዋና ዋና ከተሞችና  ከጦር ካምፖች  ውጪ  የመንቀሳቀስ ዕድላቸው ጠባብ ነበር፡፡ ይህ ማለት ግን በደረሱበት ሁሉ የጥፋት አጃቸውን አልዘረጉም ማለት አይደለም፡፡ ምን ያህል ንብረት ዘረፉ? እጅግም የተያዘ መረጃ የለም፡፡ እንኳን በዘያን ጊዜ ዛሬም ቢሆን የመረጃ አየያዛችንና ስለመረጃ ያለን ግንዛቤ ዝቅ ያለ ነው፡፡

ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት 125,000 ጣሊያናዊያንና 200,000 አፍሪካዊያን ወታደሮች፣ እንዲሁም  50,000 መንገድ ሠሪዎችና  12,000 መምህራን ጣሊያኖች እንደነበራቸው እንግሊዞች ጽፈዋል፡፡ ከወታደሩ ውስጥ 7,000 የሚሆኑት መኮንኖች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ በአምስቱ ዓመት የወረራ ጊዜ ምን ያህል ጣሊያኖች  ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንደወጡ አይታወቅም፡፡ አልበርት ሰባኪ የተባለ ጸሐፊ ጄኔራል  ቦዶሊዮ ቤቱን ያስጌጠው ከኢትዮጵያ  በተወሰዱ 300 ልዩ  ልዩ ዕቃዎች መሆኑን ገልጿል፡፡ ጄኔራል ግራዚያኒ  ሰባ ዘጠኝ ሳጥን፣ ተሩዚ አራት መኪና ሙሉ ዕቃ መጫናቸውን ይኼው ጸሐፊ ማስፈሩን በላይ ግደይ ‹‹ኢትዮጵያ አገሬና ትዘታዬ›› በተባለው መጽሐፋቸው ላይ ከትበዋል፡፡

ከምሳሌያዊ አነጋገሮቻችን አንዱ ‹‹አካሄዱን አይተው ስንቁን ይቀሙታል››  ይላል፡፡ ይህ በአጭሩ የምታየው ሁኔታ ወይም ምልክት አንድ ነገር እንድትረዳ ያደርገሃል ማለት ነው፡፡ ከአክሱም ሃያ ስምንት ቶን ከብደት ያለው ሐውልት ነቅሎ ያጋዘ፣ ከአዲስ አበባ የይሁዳ አንበሳን ሐውልት የወሰደ፣ የአፄ ምንሊክን መታሰቢያ ሐውልት የቀበረ የኢጣሊያ መንግሥት፣ በሰው ሸክም የሚንቀሳቀስ ነገር ይተርፈዋል ተበሎ አይጠበቅም፡፡ ከዘረፋ ተርፈው ለዛሬ የደረሱ ቅርሶቻችን ለዚህ የበቁት በቦታ ርቀት ወይም በአርበኞች መንገድ መዘጋት ሊሆን ይችላል፡፡ ክብር ለእነሱ ይሁንና በደሉ ግን የሕግ ያለህ የፍትሕ ያለህ የሚያሰኝ ነው፡፡

የኢትዮጵያና የኢጣሊያ ጦርነት ከተጀመረበት ከኅዳር 1927 ዓ.ም. እስከ አለቀበት ግንቦት 1934 ዓ.ም. ያለውን ጉዞ ‹‹ኢጣሊያ በኢትዮጵያ›› መጽሐፋቸው ተድላ ዘዮሐንስ እጥር ምጥን አድርገው አቀርበውታል፡፡ እሳቸው በኢጣሊያ ተወስዶ የተቀበረ አርባ ኩንታል ወርቅ ደብዛው እንደጠፋ መቅረቱን ይነግሩናል፡፡ ይህ  ብቻ በዛሬ ገበያ 67.47 ሚሊዮን ፓውንድ ያወጣል፡፡ እነሱ ለኢትዮጵያ የከፈሉት ደገሞ 6.25 ሚሊዮን ፓውንድ ነው፡፡ ይህ ያላሳዘን ምን የሚያሳዝን ይኖራል? ወደ ኢትዮጵያ ከገቡት አውሮፕላኖች አንዷ (የልዕልት ፀሐይ መማሪያ ነበረች ይባላል) ሮም ተወስዳ ስለመቀረቷ ስንቶቻችን እናውቃለን?

ኢጣሊያ በኢትዮጵያ ላይ ለፈጸመቸው ወረራ፣ ላደረሰችው ሰብዓዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳት የከፈለችው ካሳ ከተጠየቀው አንፃር የተከፈለው ከመቶ  አራት እንኳ አይሞላም፡፡ ‹‹እሱን አታንሳብኝ›› የሚባል ሊናገሩት የሚከብድ ነው፡፡ ለአንድ ሰው የሕይወት ዋጋ 271 ብር፤ የአበሻ ነፍስ የዶሮ ነፍስ ነው? ብለን በንጠይቅ ምን ይገርማል?

ፍርድ እንደ ራስ ነው፡፡ የትናንቱ ዓለም በትክክል አልፈረደልንም፡፡ እያንዳንዱ አገር ራሷ ኢጣሊያ ጭምር ጉዳቱ እንደደረሰባት አስባ ከነሕይወታቸው ገድጓድ ወስጥ ለተቀበሩ፣ እንደ ሰለስቱ ደቂቅ ከነነፍሳቸው እሳት ውስጥ ለተወረወሩ፣ እንደ ከብት ቆዳቸው ለተገፈፈ ወገኖቻችን ተገቢ ካሳ ልትክሰን ይገባል፡፡ ዓለምም ጥያቄያችንን እኛ በቆምንበት ቦታ ቁሞ እውነቱን መለስ ብሎ  እንዲያይልን እንፈልጋለን፡፡ ዓለም ምን እየጠየቅን አንደሆነ ማወቅ አለበት፡፡ የጠየቅነው ፍትሕ ነው፡፡ የጠየቀነው በሰውነታችን የሰው የመሆንን  ክብር ማግኘት ነው፡፡

      ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊያን ዛሬ በህዳሴ ዘመን ውስጥ ነን፡፡ ‹ትልቅ ነበርን ትልቅም እንሆናለን› ብለን ተነስተናል፡፡ የህዳሴ አንዱ ገጽ የነበረ ክብርን መመለስ ነው፡፡ የእኛ ነፍስ የሰው እንጂ የዶሮ ነፍስ አለመሆኑን ዓለም ያውቅ ዘንድ ጠንክረን መሥራት አለብን፡፡ ዓለም ለራሱ የሚፈልገውን መከበር ለእኛ ሊያጎልብን አይገባም፡፡ መጽሐፍ ለአንተ የምትፈልገውን ለሌላው አድርግ ይላል፡፡ ለእኛ ሕግ አይከበርም? በሕግ አምላክ ማለት አሁን ነው፡፡

      በጦርነቱ ጊዜ መጠኑ ያልታወቀ የጦር መሣሪያ በተለይም የእጅ ቦምብ በብዛት በመላ አገሪቱ ተበትኗል፡፡ በአገራችን የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ተስፋፍቶ ችግሩን እስከ ሸፈነው ድረስ የራዲዮና የጋዜጣ ወሬ  የወደቀ ቦምብ አግኝተው ሲቀጠቅጡ የሞት ወይም የአካል ጉዳት ስለደረሰባቸው ሕፃናትና አዋቂዎች ነበር፡፡ ይህስ የካሳ ጥያቄ አያስነሳም? ሁሉም ሰው  እሪ በይ አገሬ ማለት ያለበት በዚህ ጊዜ ነው፡፡

       ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...