Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርስለመልካም አስተዳደር ሀቁን እንነጋገር!

ስለመልካም አስተዳደር ሀቁን እንነጋገር!

ቀን:

በኢዮብ አሰለፈች ባልቻ

ከሁለት ሳምንት በፊት እሑድ ሐምሌ 5 እና ረቡዕ ሐምሌ 8 ቀን 2007 ዓ.ም. የወጡት የከተማችን ተነባቢ ጋዜጦች በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚታተመው አዲስ ፎርቹንና ሪፖርተር በርዕሰ አንቀጾቻቸው ላይ ተመሳሳይ አቋም አንፀበርቀዋል፡፡ ሁለቱም ጋዜጦች የመልካም አስተዳደር እጦት በአገሪቱ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ መንሰራፋቱን ገልጸው፣ መፍትሔ ያሉትን ሐሳብ ጠቁመዋል፡፡ በመፍትሔ ሐሳባቸው ላይም ለዚህ ለመልካም አስተዳደር እጦት ዋነኛ ተዋናይ የሆነውን ኢሕአዴግን የመፍትሔው ቁልፍ ባለቤት አድርገው ገልጸውታል፡፡ በእኔ አተያይ ኢሕአዴግን ለመልካም አስተዳደር መስፈን እንደ አጋፋሪ ለመውሰድ የሚያበቃ አንዳችም አሳማኝ ምክንያት ይኖራል ብዬ አላስብም፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ጋዜጦቹ የመልካም አስተዳደርን ችግር ሲተነትኑ፣ መፍትሔ ሲያስቀምጡና ለተግባራዊነቱ ኢሕአዴግን እንደ መሪ ተዋናይ ያስቀመጡበትን አቋም መሞገትና መተቸት ነው፡፡ ለሙግቴ እንዲረዳኝ ሦስት መከራከሪያ ሐሳቦችን አነሳለሁ፡፡

የመጀመሪያው መከራከሪያዬ መልካም አስተዳደርን በአሁኑ ጊዜ አገራችን ውስጥ ላለው ውስብስብ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች ወደር የሌለው ፍቱን መድኃኒት አድርጐ ማቅረብ ስህተት ነው የሚል ነው፡፡ መልካም አስተዳደርን ከልክ በላይ አግንኖ የማየት አባዜ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በብዙ አገሮች፣ የልማት ተራድኦ ድርጅቶችና ተመራማሪዎች ዘንድ የነበረ ቀስ በቀስ ግን እየተቀረፈ የመጣ አስተሳሰብ ነው፡፡ ስለዚህ መልካም አስተዳደርን የችግሮቻችን ሁሉ መፍቻ ወርቃማ ቁልፍ አድርገን ከመውሰዳችን በፊት አስፈላጊነቱን በደንብ ልናጤነው ይገባል፡፡

ሁለተኛው መከራከሪያ ሐሳቤ የኢሕአዴግ ርዕዮተ ዓለማዊ ዝንባሌ፣ ድርጅታዊ መዋቅርና አገራዊው የፖለቲካ ኢኮኖሚ ዓውድ ኢሕአዴግን ለፖለቲካዊ ሙስና የሚያጋልጥ፣ የጥቅመኝነት ትስስርና አድርባይነትን እንደ ውስጣዊ ባህሪያት እንዲይዘው የሚያመቻች ነው፡፡ ስለዚህም ከእነዚህ ሁለት መከራከሪያ ሐሳቦች በመነሳት በሦስተኛው ሐሳቤ ኢሕአዴግ የሥልጣኑን መደላድል ሳያስነካ ሙሰኝነትንና ሌሎች የአስተዳደሩን ችግሮች ይፈታል ማለት ዘበት ነው ብዬ እከራከራለሁ። ስለዚህም ተጠያቂነትና ፈጣን የሆነ ምላሽን ለሕዝብ መስጠትን ዋነኛ መገለጫው ያደረገ ሥርዓት በዘመነ ኢሕአዴግ አይሳካም ብዬ እሞግታለሁ።

የተጋነነው ዲስኩር

የመልካም አስተዳደር ዲስኩር መሠረታዊ ውስንነት የሚጀመረው ልማት የሚመጣው ሥልጡን ባለሙያዎች በሚከውኑት ሥራ መሆኑን በማጉላት ለፖለቲካዊ ሒደቶችና ክንውኖች ጆሮ ዳባ ልበስ ከማለቱ ነው። ከጥንስሱ ጀምሮ መልካም አስተዳደር አክብዶ የሚያያቸው ጉዳዮች መደበኛ የሆኑ ሥራን የመከወኛ ሒደቶችን፣ የተቀመሩ ልምዶችንና ለሠራተኛው በአቅም ግንባታ ስም የሚሰጡ ሥልጠናዎችን ነው። እነዚህና መሰል ሥራዎች ተሠርተው የሚፈለገው ለውጥ ሳይመጣ ሲቀር የፖለቲካ ተነሳሽነት ወይም ቁርጠኝነት አለመኖር ሁልጊዜ እንደ ሰበብ ይወሰዳል። ይህን የፖለቲካ ተነሳሽነት ወይም ቁርጠኝነት እንዴት እናምጣው ለሚለው አንኳር ጥያቄ ግን መልስ አይሰጥም። ጉዳዮች የሚከናወኑባቸው ሒደቶች በሙሉ በመደበኛ ግንኙነቶች ተቀምረው በተለኩና ሁሉም ቦታ ላይ ይሠራሉ ተብለው በሚታመንባቸው መንገዶች ለመሥራት መሞከር ለፖለቲካና ለኢኮኖሚ ልሂቃኑ ብዙም የሚመች አሠራር አይደለም።

አለማዳላት፣ የሕግ የበላይነት፣ ተጠያቂነትና መሰል መርሆዎች በሁሉም ቦታ ቢሰፍኑ ለፖለቲካ ካድሬው ከተጠያቂነት ውጪ ከሚከውነው ሥራና ከሚያገኘው ጥቅም የበለጠ ፋይዳ አይኖረውም። ስለዚህም ምንም ማበረታቻ  የለውም። በግልም ሆነ በቡድን የሚገኙ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅሞች በከፍተኛ ደረጃ ይሸረሸራሉ። ስለዚህ የፖለቲካ ጨዋታው የሚሆነው ስለመልካም አስተዳደር መርሆዎች የከንፈር ሽንገላን በመለገስ በተግባር ግን በጥቅመኝነትና በሙስና የተሞላ ሥራን መከወን ይሆናል።

ሌላው የመልካም አስተዳደር ዲስኩር መሠረታዊ ውስንነት የሚመነጨው በኅብረተሰብ ውስጥ ላሉ ኢመደበኛ (መደበኛ ላልሆኑ) ግንኙነቶች ዕውቅና አለመስጠቱ ነው። በመልካም አስተዳደር ዲስኩርና ተግባራት ውስጥ በትውውቅ፣ በትብብርና በማመቻመች የሚከወኑ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሒደቶች ቦታ የላቸውም። በእውነታው ዓለም ግን ይህን መሰል መደበኛ ያልሆኑ ግንኙነቶች የግልም ሆነ የመንግሥት ሥራን ለመከወን፣ ከዚያም ባለፈ የፖሊሲ አፈጻጸሞች ላይ ተፅዕኖ ማሳረፍ የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው።

ማኅበረሰባዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን ቢያንስ ቢያንስ በግማሽ የሚወክሉትን እነዚህን መደበኛ ያልሆኑ ግንኙነቶችን ችላ ማለቱ የመልካም አስተዳደርን ዲስኩር ገና ከመነሻው የጨነገፈ ያደርገዋል። የኢመደበኛ ግንኙነቶችን መሠረታዊ ሚና በተገቢው መልኩ መረዳትና ማጤን አሉታዊ ተፅዕኖአቸውን ለመቀነስና ለመቆጣጠር፣ አዎንታዊ ጎናቸውን ደግሞ ለማበረታታትና ለማጠንከር ይረዳል። ምክንያቱም ኢመደበኛ ግንኙነቶች በቀበሌ ወይም በወረዳ ደረጃ ያለን ጉዳይ ከማስፈጸም እስከ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በመሰሉ ዓለም ዓቀፍ ተቋማት ውስጥ ያሉ ውሳኔዎች ላይ ተፅዕኖ ማሳረፊያ መንገዶች ናቸውና። እዚህ ላይ በተለምዶ የኮሪደር ዲፕሎማሲና በከፍተኛ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ወቅት የሻይ ቡና ሰዓት ወጎችን ሚና መመልከት ለዚህ ይረዳል።

ኢሕአዴግና መልካም አስተዳደር

አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ርዕዮተ ዓለሙን ወደ ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመር እንደቀየረ ኢሕአዴግ ገሀድ ባልሆነ መንገድ አስቀምጧል። ይህም ማለት ኢሕአዴግ አሁን ያለበት ከፍተኛ ሥራ መሠረታዊ የሆነ ተቃርኖ ያላቸውን ልማትንና ዴሞክራሲን በተመሳሳይ ደረጃ የማስፈን ተልዕኮ ነው። ይህ ተልዕኮ ግን በጣም ብዙ ተግዳሮቶችና ጋሬጣዎች የበዙበት ነው። ከልማቱም ከዴሞክራሲም ብዙም ሥር የሰደደ ቁርኝት የሌለው የአገራችን ታሪክ መዋቅራዊና ሥርዓታዊ ለውጥን በማምጣት ሁለቱንም የማሳካትን ተልዕኮ እጅግ ፈታኝና ረጅም ያደርገዋል። ይህን ማለት ግን ኢሕአዴግን ከተጠያቂነት ማግለል አይደለም። የዚህ ታሪክ አንዱ ተዋናይ የሆነው ኢሕአዴግ መንግሥታዊ በትረ ሥልጣኑን ለማስጠበቅ አፈናን፣ የይስሙላ ምርጫንና ፖለቲካዊ መሣሪያ የሆኑ ሕጎችን ያወጣል። በዚህም ተግባሩ ከእሱ የቀደሙ ገዢዎች   እንዳደረጉት አገራዊ በትረ ሥልጣንን መያዝ ማለት ከሕግ በላይ መሆንን ማረጋገጫና የተለየ አመለካከትና አቋም ያላቸውን ማጥፊያ መሣሪያ የማድረግ ልምድን አፅንቶበታል።

ኢሕአዴግ መልካም አስተዳደርን ለማስፈን ትክክለኛ ያልሆነ ዕጩ መሆኑን ለማሳየት ብዙ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ አገራዊና የመንግሥት ተቋማትን ከፓርቲው (ከድርጅቱ) መዋቅር ጋር አዋህዶ በዚህም መንግሥታዊ ሥራን ለፓርቲ ሥራና ሥርዓት ተገዢ ከሚያደርግ ፓርቲ መልካም አስተዳደርን መጠበቅ የማይጨበጥ ህልም ነው። በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ለተቋቋሙለት ዓላማና መርህ በግልጽ የቆሙ በፓርቲው አሠራር ቁጥጥር ሥር ያልዋሉ አገራዊ ወይም ሕዝባዊ ተቋማትን ማግኘት ከባድ ነው። ይልቁንም አብዛኞቹ በገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ሥር ሆነው ለስኬቱ እልልታን ለውድቀቱ ደግሞ ወዮታን ያስተጋባሉ። የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን፣ የሃይማኖት፣ የትምህርትና የፍትሕ ተቋማት ጥሩ ምሳሌዎች ናቸው።

በተጨማሪም በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የተዋቀረው አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ርዕዮተ ዓለም የኢሕአዴግ ባለሥልጣናትን ከያዙት ሥልጣንና የሕዝብ ውክልና ይልቅ፣ ለውስጠ ፓርቲ ሽኩቻዎችና ውጣ ውረዶች የበለጠ ተጠያቂና መልስ ሰጪ እንዲሆኑ ያስገድዳቸዋል። ይህ ፖለቲካዊ ቅኝት ሕጋዊም ሆነ ሕጋዊ ያልሆነ የፖለቲካ ታማኝነትን ከሕዝብ አገልጋይነትና ተጠያቂነት በላይ የተሻለ ዋጋ እንዲኖረው ያደርጋል። ስለዚህም አሁን ያለው ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ አስተዳደር ሥረ መሠረቱና አወቃቀሩ በራሱ ለሙስና ምቹ የሆነ ነው።

ከድርጅታዊ መዋቅር አንፃር በተለይ ከ97 ምርጫ ወዲህ ከ6.5 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ “አባላትን” ያፈራው ኢሕአዴግ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንዱን ከአንዱ ለመለየት የሚከብዱ በኢሕአዴግ አጠራር “አደረጃጀቶችንና መዋቅሮችን” አቋቁሟል። በከተማና በገጠር በመላ አገሪቱ ያሉ እነዚህ አደረጃጀቶች ለፖለቲካዊ ቁጥጥር፣ ለሕዝባዊ ንቅናቄና ለመሰል ዓላማዎች ዋነኛ ተዋናዮች ናቸው። አንድ ማስተዋል ያለብን ነገር በእነዚህ አደረጃጀቶችና መዋቅሮች ውስጥ በስውር የተዋሀዱት የጥቅመኝነትና የሙስና ትስስሮች (Clientelistic Networks) የዕለት ከዕለት የመንግሥት ሥራና የፓርቲ ሹመኞች እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ የሆነ አዎንታዊም አሉታዊም ተፅዕኖ ይፈጥራሉ።

የእነኚህ ግንኙነቶች ተፅዕኖ በየትኛውም የመንግሥትና የሕዝብ ግንኙነት ምኅዳሮች ላይ ይንፀባረቃል። ለምሳሌም ማዳበሪና ምርጥ ዘር ከማግኘት እስከ የሥራና የትምህርት ዕድል ወይም የብድር አገልግሎትን ማግኘትን ያካትታል። እነዚህ የጥቅመኝነት ትስስሮች የሚመሠረቱት ከበድ ያለ ጥቅምን መሠረት አድርገው ለምሳሌ የመሬት ጥያቄን፣ ከፍተኛ መጠን ያለው የባንክ ብድርን፣ ከፍተኛ ወጪ ያለው የመንግሥት ግዢ አስተዳደርንና ከፍተኛ ንግድን ሲያካትቱ የበለጠ የተወሳሰቡና ከአብዛኛው ሕዝብ ዕይታ የተሰወሩ ይሆናሉ። ኢሕአዴግ ራሱ በግልጽ እንዳስቀመጠው “ኪራይ ሰብሳቢነትና አድርባይነት” የፓርቲው ብቻ ሳይሆን የአጠቃላይ ሥርዓቱ ዋነኛ ተግዳሮት ነው። የእነዚህ ተግባራት ዋነኛ ምንጭና ምሽግ ደግሞ ማንም ሳይሆን ኢሕአዴግ ራሱ ነው።

አንኳር ጥያቄዎች

ኢሕአዴግ የመልካም አስተዳደር መርሆዎችን እንዲያሰፍን የሚያበረታቱ ፖለቲካዊ ማበረታቻዎች አሉት? ተጠያቂነትን፣ የሕግ የበላይነትንና አለማዳላትን ማኅበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ሒደቶችን ለመፈጸም እንደ ገዢ መርህ መጠቀም በእርግጥ ለኢሕአዴግ ምን ዓይነት ሥጋትን ይዟል?

አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ኢሕአዴግ የፖሊሲ ሰነዶችንና የመንግሥት ቢሮ ግድግዳዎችን ያጨናነቁት የመልካም አስተዳደር መርሆዎችን እንዲፈጽም የሚያነሳሳውም ሆነ የሚያበረታታው (የሚገፋው) ነገር የለም የሚባል ደረጃ ላይ ተደርሷል።  መቶ በመቶ የፓርላማ መቀመጫዎችን በማሸነፍ ሒደት ውስጥ ፈጣን ምላሽ ሰጪ፣ ተጠያቂነት ያለበትና ሙስናን የሚፀየፍ የመንግሥት ባህሪያት አንዳችም ሚዛን የሚደፋ ሚና አልነበራቸውም። ይልቁን ፖለቲካዊ አፈና፣ መንግሥታዊና ተቋሟዊ ሙስና ተገቢውን ሥልጣንን የማስጠበቅ ተግባርን በስኬት ተወጥተዋል። በእርግጥ ይህ አካሄድ አሁን ለሚታየው የኢኮኖሚ ዕድገት የራሱ የሆነ በጎ ሚና በተወሰነ መልኩ ተጫውቷል።

ስለዚህ ኢሕአዴግ አሁን ያለውን ፍፁም የሆነ የበላይነትና ብቸኛ የፖለቲካም ሆነ የኢኮኖሚ ኃይል ባለቤትነት ሳያስነካ የሚታሰበውን ተጠያቂነትና የሕግ የበላይነት ያለበት አስተዳደር መመሥረት አይችልም።

ሐሳቤን ለመደምደም ያህል የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ በጋዜጦቹ ርዕሰ አንቀጽ የተያዙትን መንታ አቋሞች መተቸትና መሞገት ነበር። እነዚህ መንታ አቋሞች ደግሞ  ለመልካም አስተዳደር የተሰጠው የተጋነነው ዋጋና አሁን በሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ መልካም አስተዳደርን እንዲያሰፍን ያስተላለፉት ጥሪ ናቸው። በእኔ አተያይ መልካም አስተዳደር የሚባለው ዲስኩር አሁን ላለንበት ውስብስብ ችግር የሚሰጠን መፍትሔ በጣም ውስን ነው።

በይበልጥ ደግሞ አሁን ባለው ሁኔታ ውስጥ መልካም አስተዳደር የሚባሉት መርሆዎች አለመተግበር በይበልጥ የሚጠቅመው ገዢው ፓርቲን ነው። ምክንያቱም አሁን ያለው ሁኔታ ሥልጣኑን የበለጠ እንዲያደላድል ተቀናቃኞቹንም ፖለቲካዊ ቅኝት ባላቸው የሕግ ማዕቀፎችና ሒደቶች ጭምር እየታገዘ እንዲያንበረክክ ምቹ ሁኔታን ስለሚፈጥርለት። “ሥልጣን ሙሰኛ ያደርጋል፣ ፍፁም ሥልጣን ደግሞ ፍፁም ሙሰኛ!” የሚባለውን ብሂል በተግባር እያየነው ያለንበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።

በዚህ ጽሑፍ መፍትሔ የምለውን ሐሳብ ከማሳየት ይልቅ የጋዜጦቹን አቋም መተቸት ላይ አተኩሪያለሁ። ምናልባትም በሌላ ጽሑፍ መፍትሔ የምለውን ለማቅረብ እሞክራለሁ።

ማስታወሻ:- የዚህ ጽሑፍ እንግሊዝኛ ቅጂ ሐምሌ 19 ቀን 2007 ዓ.ም. ዕትም በአዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ላይ ወጥቷል::

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በማንቸስተር ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ ተመራማሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...