Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

‘ኤር ፎርስ ዋን’ ያልሰማው ጉድ?

እነሆ ከአቦ ሳሪስ ወደ ቦሌ ድልድይ ልንጓዝ ነው። “ዱብ ዱብ በሉዋ! ቀይ ምንጣፍ አማራችሁ? እንኳን እኛ መንግሥትም ኦባማን ቤተ መንግሥት ሲቀበላቸው ቀይ ምንጣፍ አላነጠፈላቸውም፤” ወያላው ያመጣቸውን አራግፎ ተረኞቹን ሊያስገባ ይቁነጠነጣል። “በቀይ ሆነ በጥቁር ደግሞ አፍሪካ ውስጥ ከወንበሩ በክብር የወረደ አይተሃል? የማን ነው እባካችሁ!” ብላ አንዷ እየተመናቀረች ጥላው ስትሄድ፣ ሌላ ወራጅ ቀበል አድርጎ “አይገርምሽም ‘የአገሩን ሰርዶ በአገሩ በሬ’ እንደማስበላት ከሰው አገር ሰው ጋር ያነካካናል፤” ይላታል። “ያውም አትላንቲክን አቋርጦ ከመጣ እንግዳ ጋር ነዋ!” ይላል ደግሞ መጨረሻ ወንበር ላይ ተቀምጦ የነበረ ተሳፋሪ። እንደ ወለላ የማር ዘለላ በረጂም ቁመቱ እየተዝለገለገ ሲወርድ። “ኧረ አፍጡኑት ወሬውን ተውና። ዝናብ አስደበደባችሁን እኮ። ምንድነው ሰውም በኔትወርክ መተንፈስ ጀመረ እንዴ? መንቀራፈፍ በዛሳ?” ካፊያው እያረጠባት ከፊት ለፊቴ የቆመች ተሳፋሪ አልጎመጎመች።

“ጭራሽ በኔትወርክ መንቀሳቀስ ጀምረንማ ፈጣኑ የኢኮኖሚ ዕድገት አለቀለት በይኛ፡፡ እኮ በእኛ ኔትወርክ?” ይላታል ደግሞ ከእሷ ፊት የተገተረ ጎልማሳ። “ምን ኔትወርክ አለን ደግሞ እኛ? አንድ ነው ያለን እሱም የሐሜትና የቧልት ነው። ምንድነው የምታወሩት?” ተራውን ከጀርባዬ የቆመ፣ ባለመነጽር ወጣት ተብሰልስሎ ይናገራል። “እህህ እህህ ይላል ሞኝ ሰው የፈሰሰን ውኃ ደርሶ ላያፍሰው’ አለ ያገሬ አዝማሪ። እንዲያው ነው የእኛ ነገር፤” ለተለኮሰው ጨዋታ ራቅ ብለው የቆሙ የሚመስሉ አዛውንት እንደ መብረቅ በሚያጉረመርም ድምፃቸው ይደርሱብናል። ወራጁ ወያላውን እየተራገመና እየሰደበ ሲወርድ ወጪው ደግሞ ነገሩን አስፍቶ አላሰማ ያለውን የኑሮውን ምጣድ በምፀት ያሟሸው ይዟል። ቀጣናው በከፍተኛ ጥበቃና ፍተሻ ተተራምሶ ሰው እርስ በርሱ እየተገለማመጠ ሲታይ የ‘አክሽን’ ፊልም ቀረፃ ላይ ያለ ይመስላል። “ሳያደናብሩን ተደናብረናል ለራሳችን፤” እያለ መንገደኛው አንገቱን ደፍቶ ቁም ስቅሉን ያያል። በአገሩ የተከበረ ነብይ ያለ ይመስል ብዙ ከማለት ተቆጥበናል። ኧረ የ“መ” ሕጎች የት ደረሱ ይሆን? አንስተን የምንጥለው መፈክር ብዛቱ እኮ!

መንቀሳቀስ ጀምረናል። “ተመችቷችኋል?” ወያላው ሳያስባት ከአፉ ያመለጠች ቃል ናት። “እሰይ ዛሬስ ምቾታችንን የሚጠይቅ ወያላ ተገኘ። እውነትም አገራችን በፈጣን ዕድገት ላይ ነች፤” ይላሉ ከሾፌሩ ጀርባ የተቀመጡ ወይዘሮ እየሳቁ። “የኦባማን ቲሸርት ስላደረገ ምናልባት የኋይት ሃውስ ሰብዓዊ መብት አከባበርና አያያዝ በመንፈስ ተጋብቶበት ይሆናላ!” ይላቸዋል አጠገባቸው የተቀመጠ ወጣት። “እንዲያ ከሆነስ ሁላችንም እንልበሰዋ፤” መሀል መቀመጫ ላይ የተሰየመው ጎልማሳ ያፌዛል። “ግዙ እንዳይሉን እንጂ የዴሞክራሲና የሰብዓዊ መብቶች አያያዝና አከባበር ኦባማ በታተሙበት ቲሸርት ብቻ ‘አፕግሬድ’ የሚሆን ከሆነ ምን ገዶን?” ትለዋለች አጠገቡ የተቀመጠች ደርባባ። “እና በነፃ ነበር ያማረሽ? የትኛው የሠለጠነ አገር ነው በነፃ ዋጋ ሳይከፍል በኢኮኖሚያዊ፣ በፖለቲካዊና በማኅበራዊ ጉዳዮች መጥቆ የሄደው?” ይላታል ያ ባለመነጽር ወጣት አጠገቤ ተንሸራቶ እየተቀመጠ። “ኧረ ስለፈጠራችሁ ተው። ስደት ይቁም እያልን የኦባማ ምሥል የታተመበት ቲሸርት ተባዝቶ ይሰጠንና እንልበስ ትላላችሁ? እንዲያ ተማምለን እንዲያ ተገዛዝተን?” መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ተሳፋሪዎች ዘለግ ያለ ቁመት ያለው ተሳፋሪ ጣልቃ ገባ። “ምንድነው የሚያወራው? እኛ የምናወራው ስለዴሞክራሲ። ስደትን ምን ዶለው?” ስትል ደርባባዋ ሰማትና መልሶ፣ “እስኪ አስቢው። ሚስተር ኦባማ ራስ ዳሸን የሚያክል አውሮፕላን ለብቻቸው ይዘው፣ መኪናቸውን፣ ብስክሌታቸውን፣ ኩሽኔታቸውን ሳይቀር በሁለት የዕቃ መጫኛ አውሮፕላኖች አሸክመው መጥተው፣ በመሀል ይኼ ሁሉ ሰው ቲሸርታቸው በነፃ ታትሞ ቢሰጠው፣ መሄጃቸው ደርሶ ‘በሉ ደህና ሁኑ’ ሲሉ ‘ደህና ሁኑ’ ብሎ አዳሜ የሚሸኛቸው ይመስልሻል?” አላት። “ምን ሊለን ነው ይኼ ሰው እባካችሁ?” ይባባላል ተሳፋሪው። ነገርና ዕዳ መምጫው አልታወቅ አለ ጎበዝ!

ደርባቢት ቀጠለች። “ለምን ባጭሩ አታስረዳንም? ኢቢሲን ይመስል ዙሪያ ጥምጥም አትዙር፤” አለችው ከአፉ ነጥቃ። ጨዋታው እየተሟሟቀ ሄደ። “ይኼ የ‘ፌስቡክ’ ጀኔሬሽን እኮ አንድ ገጽ ላይ ብቻ አፍጥጦ እየዋለ በሦስት ‘ዳይሜንሽን’ ማሰብ፣ ነገር መተንተን ተሳነው እኮ፤” ብሎ ቀውላላው ጥቂት ከቆዘመ በኋላ፣ “ባይሆን እስከ ሊቢያ ሸኝተነው እንመለስ ብሎ ግልብጥ ብሎ ኤርፖርት ቢገባስ?” ሲል ተሳፋሪዎች ተደናገጡ። ማ? ሲሉት ባንድ ድምፅ፣ “ስለማን ነው የምናወራው? የኦባማ ምሥል ያለበት ቲሸርት በነፃ ይታደለው የምትሉት ነዋ! ይኼ ሁሉ ለስደት የቋመጠ ዜጋ ያውም አሜሪካ ይታያችሁ እስኪ …  ሆሆ! … ያውም ዲሲ …  ‘ዳይሬክት ፍላይት’ አግኝቶ እጁን አውለብልቦ ኦባማን ሸኝቶ ሊመለስ? ምነው የመሪያቸው ምሥል ያለበትን ቲሸርት ለብሰን ይቅርና  በዕለት ተዕለት ኑሯቸው ምሳሌ መሆን የማይችሉ ተዋናዮቻቸውና ዘፋኞቻቸው የሚለብሱትንና የሚጫሙት እያየን አይደል እንዴ ‘አሜሪካን ያረገጠ ገነት አይገባም’ የተባልን የመሰልነው። ትቀልጃለሽ መሰለኝ፤” ብሎ ቀውላላው ጋብ አለ። ስንናገር ባይደክመን እኮ ዘንድሮ ገፊ አልቆለት ነበር፡፡

ወዲያው ከወይዘሮዋ አጠገብ የተቀመጠው ተሳፋሪ አንገቱን መለስ አድርጎ፣ “ፓ ይኼን ድርሰት አድርገህ ብትጽፈው በተለይ ወግ ብቻ በሚታተምበት በዚህ ጊዜ ጥሩ ያዋጣህ ነበር። በተረፈ ግን እውነት ሊሆን ይችላል እያልክ  ጆሯችንን አታደንቁረው። ባዳመጥን፣ በታገስን፣ ቀን ያልፋል ባልን ስንቱ ‘ሳይንስ ፊክሽን’ እላያችን ላይ ጻፈብን እኮ ጎበዝ፤” ብሎ የምሩን ተቆጣ። ከቀውላላው በስተቀኝ መስኮቱ አጠገብ የተቀመጠች ወጣት በበኩሏ፣ “እንኳን የኃያሏ አሜሪካ መሪ አውሮፕላን ውስጥ፣ ኮተት ተሸካሚውንም ጨምሮ ዘው ብሎ መግባት ይቅርና ታክሲ መሳፈርም በሠልፍና በሥርዓት ሆኗል። ሥርዓት ያለው ሠልፍ አይወድልንም እንጂ። ከግል ጠባቂ አልፎ ጦራቸው በአገራችን ሰማይ ላይ ሲያንዣብብ እያየህ ማን አስጠግቶን?” ብላ አንሾኻሾከች። ቀውላላው  ‘ያንቺ ይባስ’ ዓይነት አየት አድርጓት፣ “ምነው አውሬ ይብላኝ ብለን ከአንበሳና ከዘንዶ ጋር እየታገልን በረሃ የምናቋርጠው እኛ አይደለንም እንዴ? ምነው ከአውሬ የባሰ የሰው አውሬ አጉሮ ሰብስቦ እያረደን ዓለም ያየን እኛን አይደለም እንዴ? ቦሌን መዝለል ሊከብደን ነው?” እያላት ብዙ ተጓዝን። ወይ ‘ኤር ፎርስ ዋን’ ያልሰማው ጉድ!

ወያላው ሒሳብ እየተቀበለ ነው። ከቀውላላው ተሳፈሪ በስተግራ ጥጋቸውን ይዘው የተቀመጡት አዛውንት ኦባማንና አውሮፕላናቸውን አያይዞ የተነሳው ጨዋታ አንገሽግሿቸዋል። “ገና ለገና ‘ተንጠላጥለን ቢሆን አትላንቲክ ካልበላን’ ባይ ይኖራል ብላችሁ የሰው አገር በስቅታ ልትገሉ ነው? ምነው ቢበቃችሁ?” ብለው ድምፃቸውን አሰሙ። ይኼን ጊዜ አርፎ መቀመጥ የማይወድ የሚመስለው ለነገሮች ቅፅበታዊ ምላሽ በመስጠት ‘ታለንት ሾው’ ኖሮ ቢወዳደር አንደኝነቱን ማንም ሊነጥቀው የሚችል ያለ የማይመስለው ከጎኔ ያለው ወጣት፣ “እማማ እነሱማ ከስቅታ አልፈው ስቀውብናል እኮ!” አላቸው። “ምን?  ሳቁብን? እንወዳችኋለን፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገታችሁ በሚቀጥልበት ጎዳና ሁሉ አብረናችሁ ነን እያሉን? ቤታችን ሰንብተው፣ ቡና ጠጥተው፣ እስክስታ ጨፍረው? ሳቁብን?” ይሉታል። “የለም እዚህ አይደለም የሳቁት። አገራቸው ላይ ነው የሳቁት፤” ይላል ወጣቱ ወይ አያብራራ ወይ አይተወው የአዛውንቷን ልብ ያንጠለጥላል። “ ‘ገጣጣ ሲሞት የሳቀ ይመስላል’ ይባላል። ምናልባት በፊልማቸው አንድ የሞተ ገጣጣ አይተህ በእኛ የሳቀ መስሎህ እንዳይሆን ልጄ? ወዳጅ ነን ብለው ተንጋግተው መጥተው ሳቁብን ትለኝ?” አዛውንቷ አጥብቀው እየጠየቁ ነው። “አዎ እማማ። ኦባማ እዚህ ቡና እየጠጡ በእርግጥ በሳቁ ተባባሪ አልነበሩም። የእሳቸው አንዲት ሹም፣ ‘የኢትዮጵያ መንግሥት መቶ በመቶ አሸነፍኩበት ያለው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ ነው ብለው ያምናሉ?’ ተብለው ሲጠየቁ ጥርሳቸውን ሦስት ዙር እስክንቆጥረውና ዓይናቸው እስኪጠፋ ድረስ የሳቅ ጎሞራ ትን አላቸው ተብሎ ተወራ፤” ቢላቸው ወጣቱ ሳቅ ሳቅ እያለው፣ “ታዲያ መቼ በእኛ ሳቁ? ይኼን ወሬ ብለህ ነው አሁን። ኤድያ!” ብለው አዛውንቷ ችላ እንደማለት ቃጣቸው። ቀውላላው፣ “እና በማን ነው የተሳቀው የሚሉት እርስዎ?” አላቸው። “ምን አልኩህ አንተ? እንዴት እንዲህ ዓይነት አሉባልታ ትጠይቀኛለህ?” ብለው ሲመልሱለት ተሳፋሪዎች በሳቅ ፈረሱ። እንዲህ ሲስቁ እያየን እየሳቅን፣ ሳቃቸው አስቆን እየተንከተከትን፣ ምክንያቱ ሲገባን ደግሞ በገነተረ ነገርና ሳቅ እየተጃጃልን የምንጓዘው መንገድ የሚያልቅ አይመስልም። መጥኔ!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ወያላው መልስ እየመለሰ ነው። ድንገት የትራፊክ ፖሊስ ፊሽካ ሰማን። ታክሲያችን ቀጥ ብላ ቆመች። ትራፊክ ፖሊሱ እየተንደረደረ መጣ። ሾፌሩ፣ “ምን አጠፋሁ ጌታዬ?” አለ እየተሽቆጠቆጠ። “መንጃ ፈቃድ አምጣ!” መፈጠሩን እስኪረግም ገላመጠው። ያለማንገራገር መንጃ ፈቃዱን አወጣና ሰጠ። ሾፌሩ  ቃል አይናገርም። “አውርዳቸው!” ከትራፊክ ፖሊሱ ቀጭን ትዕዛዝ እንሰማለን። “ሲሆን ጥፋቱን በነገረው። ካልሆነ የቅጣት ወረቀት ጽፎ መሸኘት እንጂ ለምን እኛ እንወርዳለን?” ጎልማሳው ግራ ተጋብቶ የብዙዎቻችን ጥያቄ ይፋ አወጣው። “እንጃ!” አለ ወያላው ኩምሽሽ ብሎ። “ዳይ ውረዱ ሌላ ታክሲ ያዙ!” ትራፊክ ፖሊሱ እንኳን ከሰው ከነፍሳት የቆጠረንም ያልመሰለው አንዱ ተሳፋሪ፣ “ተደምረንም የአንድ ሰው ያህል አንመዝንም?” እያለ ቀዳሚ ወራጅ ሆነ። ጋቢና ከተቆመጡት ተሳፋሪዎች አንደኛው ግን ወርዶ ትራፊኩን ለማነጋገር ይሞክራል። ትራፊኩ ይሳደባል። ሾፌሩ ወጣቱን ተሳፋሪ ዝም እንዲል ይማጠነዋል። “ለምንድነው ዝም የምለው? ሲሆን የተቀጣህበት ምክንያት ግልጽ በሆነ። ሲቀጥል እንደ ዕቃ ያለበቂ ምክንያት ተሽቀንጥረን የምንወርድበት ምክንያት ምን እንደሆነ ያስረዳን፤” እያለ ፀንቶ ሙግት ያዘ። “ይኼ ልጅ ዛሬ አለቀለት፤” ሲል ካልወረድነው መሀል አንዱ ደርባቢት ቀበል አድርጋ፣ “‘ሎካል’ ባይሆን ነው። እንደ አውሮፓ መስሎታል እዚህ፤” ትላለች። “ግን መብት ለማስከበር የግድ ባህር መሻገር አለብን? በገዛ አገራችን?” ሲል ቀውላላው እጓዛለሁ ብሎ ተስፋ ያደርግ የነበረው ተሳፋሪ በጠቅላላ “አንተም ዳያስፖራ ነህ መሰል። እንደ እኛ እስኪሰለችህ ተዳረቅ፤” እያለው ትቶት ወረደ። የቀናው ሌላ ታክሲ ያዘ። ያልቀናው ሲቃ እየተያያዘ በእግሩ ተጓዘ። በዝም ዝም እንደተሸፋፈነ ይኼም መንገድ እንደ ወትሮው እያረረ ሳቀ። በቃ፣ እያረሩ መሳቅ ብቻ? “የእኛስ ዕዳው ገብስ ነው፤” አለች ድምጿን አጥፍታ የነበረች ቆንጅዬ፡፡ “አሁን የፌስቡክ ገጼ ላይ ምን እንዳየሁ ታውቃላችሁ?” አለችን በፈገግታ ታጅባ፡፡ ጎልማሳው፤ “ምን ይሆን?” በማለት ለወሬ ሰፍ አለ፡፡ “‘ለሥራ ጉብኝት ኢትዮጵያ የሄዱት ፕሬዚዳንት ኦባማ ወደ አሜሪካ የሚያደርጉትን በረራ ለመቃወም ፊርማዎትን ያኑሩ፤” ይላል ብላ ሆዷን ይዛ ስትስቅ እኛም በሳቅ አጀብናት፡፡ ‘ኤር ፎርስ ዋን ያልሰማው ጉድ!’ ማለትስ አሁን አይደል? መልካም ጉዞ!     

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት