Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የሠራተኛ ማኅበራት አመራሮች የሕግ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል›› አቶ ዳዊት ሳሙኤል፣

የቀድሞ የሸራተን አዲስ ሌግዠሪ ኮሌክሺን ሆቴል ሠራተኛ ማኅበር ሊቀመንበር

የዛሬው ምን እየሠሩ ነው ዓምድ እንግዳችን አቶ ዳዊት ሳሙኤል ይባላሉ፡፡ አቶ ዳዊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሶሽዮሎጂና ሶሻል አንትሮፖሎጂ እንዲሁም በዲዛስተር ሪስክ ማኔጅመንትና ሰስተነብል ዴቨሎፕመንት ሁለት ዲግሪዎችን አግኝተዋል፡፡ በሶሻል ወርክ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም ሠርተዋል፡፡ አቶ ዳዊት ከሆቴልና ቱሪዝም ሥራ ማሰልጠኛ ተቋም ዲፕሎማም አግኝተዋል፡፡ ለ14 ዓመታት በሸራተን አዲስ ሌግዠሪ ኮሌክሺን ሆቴል በተለያዩ ዲፓርትመንቶች ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜም በአንድ ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ውስጥ የምግብና መጠጥ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆነው እየሰሩ ነው፡፡ አቶ ዳዊት ቀደም ብለው ከ14 ዓመታት በላይ ይሠሩበት ከነበረው ሸራተን አዲስ ሌግዠሪ ኮሌክሺን ሆቴል የለቀቁት፣ ባላሰቡትና ባላወቁት ጉዳይ ሕገወጥ በሆነ መንገድ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ እሳቸው ብቻ ሳይሆኑ በተመሳሳይ ሁኔታ ከሥራ የተሰናበቱ ሌሎች 64 ሠራተኞችም እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ በሕገወጥ መንገድ ሥራ እንዲለቁ የተደረገበትን ሁኔታ በመቃወም ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ በክርክር ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል፡፡ አብረዋቸው የተሰናበቱ ሠራተኞች አንድ ላይ በመሆን አክሲዮን ማኅበር በማቋቋም፣ የራሳቸውን ቢዝነስ በመሥራት ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ አቶ ዳዊትን ታምሩ ጽጌ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ሥራ መቼና እንዴት እንደጀመሩ ቢነግሩን?

አቶ ዳዊት፡- የሆቴል ሥራ የጀመርኩት በሸራተን አዲስ ሌግዠሪ ኮሌክሺን ሆቴል ነው፡፡ በሰዓት አራት ብር እየተከፈለኝ ጊዜያዊ ሠራተኛ ሆኜ ነው ሥራ የጀመርኩት፡፡ ግብዣ በሚኖርበት ጊዜ (የባንኩዌት  ሥራ) እየተጠሩ በሰዓት አራት ብር ከሚከፈላቸው ሠራተኞች አንዱ ነበርኩ፡፡

ሪፖርተር፡- የሆቴልና ቱሪዝም ሥልጠና ወስደው ነበር?

አቶ ዳዊት፡- አዎ በሆቴልና ቱሪዝም ተመርቄ እንደጨረስኩ ነው ሸራተን እየተጠራሁ መሥራት የጀመርኩት፡፡ ሥራ የጀመርኩት እ.ኤ.አ. 1999 ሲሆን በጊዜያዊነት ለአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ከሠራሁ በኋላ ቋሚ ተቀጣሪ ሆንኩኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ቋሚ ሠራተኛ የሆኑት በምን የሥራ ዘርፍ?

አቶ ዳዊት፡- ቋሚ ሠራተኛ ሆኜ የተቀጠርኩት በተመሳሳይ የሥራ ዘርፍ ሳይሆን ሴኩዩሪቲ ሆኜ ነው፡፡ በሴኩዩሪቲ ዲፓርትመንት ለአምስት ዓመታት ሠርቻለሁ፡፡ ከዛ በመቀጠል በትለር (ሆቴሉ ውስጥ ያለውን አጠቃላይ ሁኔታ ለእንግዶች ማሳየትና፣ እንግዶቹ በሆቴሉ ውስጥ ሲቆዩ፣ ቆይታቸውን አስደሳች ማድረግ፣ ችግር ካጋጠማቸውም አነጋግሮ ችግሩን መፍታትና እንደ ቤታቸው ሆነው ምንም ሳይሰማቸው በደስታ እንዲያሳልፉ ማድረግ) በሚባል የሥራ ዘርፍ ዕድገት አግኝቼ ተቀየርኩኝ፡፡ በትለርነት ለሰባት ዓመታት ከሠራሁ በኋላ፣ አሁንም ዕድገት አግኝቼ ቪአይፒዎች ብቻ ወደሚስተናገዱበት ክፍል ተዛወርኩኝ፡፡ ኤክስኪዩቲቭ ላውንጅ ይባላል፡፡ ይኸ የሥራ ቦታ ማንኛውም እንግዳ የሚስተናገድበት ሳይሆን የአገር መሪዎችና ከፍተኛ ባለሥልጣናት ብቻ የሚስተናገዱበት ዝግና በሆቴሉ የተወሰኑ ክፍሎች የሚሠራ ነው፡፡ በዚህ የሆቴል ክፍል የሚስተናገዱ ቪአይፒዎች የሚከፍሉት ገንዘብ በጣም ብዙ በመሆኑ፣ ከምሽቱ አሥራ አንድ ሰዓት በኋላ የሚስተናገዱት ያለ ክፍያ ነው፡፡ በአጠቃላይ በሸራተን አዲስ ሌግዢሪ ኮሌክሽን ሆቴል ውስጥ ከ14 ዓመታት በላይ ሠርቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ትልቅ ልምድ ካገኙበትና ከ14 ዓመታት በላይ ከሠሩበት የአገሪቱ ትልቅ ሆቴል ለምንና እንዴት ለቀቁ?

አቶ ዳዊት፡- ከሸራተን ሆቴል የለቀቅሁት ራሴ ፈልጌ ወይም የሆቴሉ ባለቤት እንድለቅ ፈልገው አይደለም፡፡ ከሥራ በሕገወጥ መንገድ እንድለቅ የተደረግኩት የሠራተኞች ማኅበር መሪ በመሆኔ ነው፡፡ 650 አባላት የነበሩበትን የሠራተኛ ማኅበር ለአራት ዓመታት መርቻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- የሠራተኞች ማኅበር መሪ በመሆንዎ ከሥራ የተባረሩበት ምክንያት ምንድነው?

አቶ ዳዊት፡- ነገሩ በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ በሆቴሉ ውስጥ የሠራተኛ ማኅበር አልነበረም፡፡ ማኅበር ባለመኖሩ ሠራተኞች መብታቸውን ለማስከበርና ግዴታቸውንም ለመወጣት ሲቸገሩ ቆይተዋል፡፡ ስለመብታቸው መጠየቅ አይችሉም፡፡ የሆቴሉ አስተዳደር እንደፈለገ እንጅ፣ እነሱ የሚያነሱት ማንኛውም የመብት ጥያቄ አይደመጥም ነበር፡፡ ይኸ በመሆኑ ሕግ በፈቀደው መንገድ መሠረት ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የሠራተኛ ማኅበር አቋቋምን፡፡ ማኅበሩን ካቋቋምን በኋላ፣ በሕግ የተፈቀዱት የመብት ጥያቄዎች እንዲሟሉልን ጠየቅን፡፡ ማኅበሩም ሆነ ሠራተኛው ይኸንን ሲያደርግ ምንም ዓይነት እኩይ ተግባር ለመፈፀም ሳይሆን፣ ሆቴሉን ይበልጥ ተጠያቂነት በተመላበት ሁኔታ ለማገልገል ነበር፡፡ ነገር ግን የማኅበሩን መቋቋም የሆቴሉ ማኔጅመንት በጥሩ መንፈስ አልተቀበለውም፡፡

ሪፖርተር፡- በሆቴሉ ውስጥ ሠራተኞች ይበደላሉ የሚሉበት አሠራር ምን ነበር?

አቶ ዳዊት፡- ለምሳሌ በሕግ ከተመደበው ውጪ በቀን ከስምንት ሰዓት በላይ መሥራት፣ የሴቶች በወሊድ ጊዜ ተጨማሪ ዕረፍት አለማግኘት፣ ሠራተኞች በታመሙ ጊዜ የተሻለ ሕክምና አለማግኘት፣ ሠራተኞች በሥራ ላይ በሚሆኑበት ወቅት የሥራ ላይ አደጋ መከላከያ አለማግኘት፣ ለሠራተኛ ማኅበር መቋቋም ምክንያት ከሆኑት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ እነዚህንና ሌሎች በሕግ የተፈቀዱ መብቶችን ለማረጋገጥ የሠራተኛ ማኅበር አቋቁሞ በሠራተኛ ማኅበሩ መሪዎች አማካይነት እንዲሟሉ ማድረግ፣ በዓለም አቀፍም ሆነ በእኛ አገር ሕግ ላይ ተደንግጎ የሚገኝ ነው፡፡ በአሜሪካና በአውሮፓ ከ200 ዓመታት በላይ ተረጋግጦ የሚገኝን መብት፣ እኛም በአገሪቱ ቁጥር አንድ ነው በሚባለው ሸራተን አዲስ ሌግዠሪ ኮሌክሺን ሆቴል ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ በመንቀሳቀሳችን ሥራችንን አጣን፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ የመብት ጥያቄ ስታነሱ የሆቴሉ አስተዳደር ምላሽ ምን ነበር?

አቶ ዳዊት፡- የሆቴሉ አስተዳደር ምላሽ ‹‹አይሆንም›› ነው፡፡ ማኅበሩ በሆቴሉ የመጀመሪያ ነው፡፡ በማኅበሩ ውስጥ የተመረጡ አመራሮች ከሆቴሉ አስተዳደር አባላት የተሻለ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው ናቸው፡፡ ከማኅበሩ አሥር አመራሮች ውስጥ አንድ ሰው ብቻ ዲፕሎማ ያለው ሲሆን ቀሪዎቹ የመጀመሪያ ዲግሪና ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- የሠራተኛ ማኅበሩ መሪዎች በቂ የትምህርት ዝግጅት ያላቸው መሆን ባለፈ ሥጋት የሆነው ለምን ነበር?

አቶ ዳዊት፡- በእኛ አገር ሁኔታ የሠራተኛ ማኅበር መሪ ስትሆን ሁለት ነገር መሆን አለብህ፡፡ አንደኛ ከአስተዳደር ጋር ተለጣፊ ሆነህ፣ አስተዳደሩ ያለህን እያደረግክና የተሾምክበትን የሠራተኛ መብት ማረጋገጥ ትተህ የራስህን ጥቅም ማጋበስ አለብህ፡፡ ይኸ ካልሆነ በሁለተኛ ደረጃ ሕጉ የሚያረጋግጥለትንና ሠራተኛው ማግኘት ያለበትን የመብት ጥያቄ እንዲያገኝ እስከ መስዋዕትነት ድረስ መጋፈጥ አለብህ፡፡ ወደ ሥራችን ጉዳይ ስንመጣ፣ የማኅበሩ መሪዎች ጠንካሮችና በትክክለኛ መንገድ የሠራተኛውን መብት ለማስከበር ጠንክረው የሚሠሩ ነበሩ፡፡ ለድርጅቱ ህልውናና ለሠራተኛው ጥቅም ብቻ የቆሙ ናቸው፡፡ ማንኛውንም ነገር ማለትም በሕግ የተፈቀደን ነገር በማድረግ የሚመጣውን ሁሉ ለመቀበል የተዘጋጁ እውነተኛ የማኅበር መሪዎች ነበሩ፡፡ እነዚህ የማኅበር መሪዎች ከሥራቸው መፈናቀል ሳይሆን፣ በአገር ደረጃ የተሻለ ነገር ሊሰጣቸው የሚገቡ ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- የሆቴሉ ባለቤት ሼክ መሐመድ ዓሊ አልአሙዲ በእናንተና በሆቴሉ ማኔጅመንት መካከል ስለተፈጠረው ሁኔታ ያውቃሉ?

አቶ ዳዊት፡- ይኸ ጥያቄ ለኔ ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ ምክንያቱም ሆቴሉ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በሰዓት አራት ብር ከመከፈል ጀምሮ ለ24 ሰዓታትና አንዳንድ ጊዜ እስከ 33 ሰዓታት እንሠራ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ እኛ እንዴት እንደምንሠራ እንጂ በኛ ላይ የሚደርሰውን በደል እሳቸው የሚያውቁ አይመስለኝም፡፡ ሁሉም ሠራተኛ ግን ለሳቸው ያለው ክብር የተለየ ነው፡፡ እኛ እሳቸው ጋ ለመድረስ ስለማንችልና እሳቸውም አብዛኛውን ጊዜያቸውን በሥራ ላይ ስለሚያሳልፉ፣ ችግራችንንም ሆነ በማኔጅመንቱና በኛ መካከል ያለውን ጉዳይ አያውቁትም፡፡  

ሪፖርተር፡- ሥራ አላሠራ የሚለው አካል በትክክል ተለይቶ ይታወቅ ነበር?

አቶ ዳዊት፡- በሆቴሉ ውስጥ ምንም ሥራ የሌላቸው፣ ነገር ግን የሠሩ በማስመሰል የራሳቸው የተለየ ፍላጎት ያላቸው የተለያዩ ቡድኖች አሉ፡፡ ማኔጅመንቱ የራሱ ፍላጎት አለው፡፡ በማኔጅመንቱ ዙሪያና በአካባቢው ያለው ቡድን የራሱ ፍላጎት አለው፡፡ የኛ ፍላጎት በግልጽ ተዘርዝሮ ቢቀርብ፣ በዚህ ቡድን ላይ ሊነሱ የሚችሉና ሊደረሱበት የሚችሉ ነገሮች ስላሉ፣ ነገሩን ማድበስበስና ማስመሰል እንጅ ግልጽ እንዲሆን አይፈለግም፡፡ ለሆቴሉ ባለቤት ለሼክ መሐመድ እኛ የምንሠራውም ሆነ የሚደርስብን በደል በትክክል አይነገራቸውም፡፡ ተገልብጦ ነው የሚነገራቸው፡፡ ለምሳሌ በአንድ ወቅት ስድስት ሚሊዮን የተገዛ ማሽን በአስር ሺሕ ብር ተሸጦ ሊወጣ ሲል ሠራተኛው ያዘው፡፡ ለባለቤቱ ግን ሠራተኛ ሊሸጠው ሲል እንደተያዘ ተደርጎ ተነገራቸው፡፡ የሚቆጨን ነገር ቢኖር ባለቤቱ እውነተኛውንና ትክክለኛውን ነገር ለአንድ ቀን እንኳን ሳያውቁት ሳያናግሩን በስማ በለው ብቻ እዚህ ደረጃ ላይ መድረሳችን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማኔጅመንቱ ባለቤቱን ሊያገናኛችሁ ፈቃደኛ ባይሆንም በራሳችሁ ጥረት ለማግኘት አልሞከራችሁም?

አቶ ዳዊት፡- ሼክ መሐመድን ሁላችንም የምናያቸው እንደ አባት ነው፡፡ እሳቸው ለማረፍም ሆነ ለመዝናናት በሚመጡበት ጊዜ ለማናገር ዕድሉ አለን፡፡ ነገር ግን ብዙ መንገዶችን ዘሎ እሳቸውን ማናገር እንደ ነውር ይቆጠራል፡፡ ባህላችንም አይፈቅድም፡፡ መሆንም ያለበት ደረጃውን ጠብቆ እሳቸው ጋ መድረስ እንጅ በተገኙበት ቦታ ማናገር ክብርን መንካት ነው፡፡ የሚገርመው ነገር ግን እኛ በማፈርና በመሽኮርመም ይሉኝታ ይዞን ያለፍነውን፣ በሆቴሉ ተቀጥረው የሚሠሩ የውጭ ዜጎች ተጠቅመውበታል፡፡ ሰውዬው ካላቸው ክብርና ለአገሪቱም ካደረጉት አንጻር እኛ እናከብራቸዋለን፡፡ ምንም ብንደረግም ለእሳቸው ሄደን መናገር ይከብደናል፡፡ ይኸንን አጋጣሚ ግን የውጭ ዜጎቹ በመጠቀም ስማችንን ጥላሸት ለመቀባት ተጠቀሙበት፡፡ እሳቸውን በቀጥታ ማናገር ባለመቻላችን መጨረሻ አካባቢ በመንግሥት ባለሥልጣናት በኩል እንዲነገርልን  ሞክረናል፡፡ ነገር ግን ያንንም ቢሆን እኛ የምንለውን ለመስማት እንጂ እሳቸው ጋ ያደረሰልን የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን በመንግሥት ባለሥልጣናት በኩል ለማነጋገር ፈለጋችሁ? ባለሥልጣናቱ  በዚህ ጉዳይ መሳተፍን እንዴት መረጡ?

አቶ ዳዊት፡- እኛ እሳቸውን በማክበር እንዲያነጋግሩን የተወሰኑ ደብዳቤዎችን ጻፍን፡፡ ደብዳቤው ግን ይድረስ አይድረስ እርግጠኛ መሆን አልቻልንም፡፡ እሳቸውም ምንም ያሉን ነገር የለም፡፡ በዚህ ጊዜ ትላልቅ ሰዎችን ለመላክ ተገደድን፡፡ አሁን የተረዳሁት ነገር ቢኖር ለሰውዬው የሆነ ያልሆነ ነገር ስለኛ በመንገር በኛ ላይ ጥሩ አመለካከትና አስተሳሰብ እንዳይኖራቸው አድርገዋቸዋል፡፡ ይኸንን ለመረዳት ያስቻለኝ ግንኙነታችን ተቋርጦ ወደ ፍርድ ቤት ስንሄድ አንዱ ለመከራከሪያነት ያነሱት ነጥብ ‹‹የባለቤቱን ስም በማጥፋት›› የሚል ነው፡፡ የሴት ሠራተኞች የወሊድ ጊዜ ዕረፍት እንዲጨመር፣ ሠራተኛ ከስምንት ሰዓት በላይ መሥራት እንዲቀነስና ከሆቴሉ የሚገኘው ሰርቪስ ቻርጅ በአግባቡ እንዲከፈል ሲጠየቅ፣ “ሰርቪስ ቻርጅ ተሰረቀ አሉ…” በማለትና የሆነው እንዳልሆነ፣ የተደረገውን እንዳልተደረገና ያልተባለውን ተባለ እያሉ እንደሚያቀርቡላቸው በፍርድ ቤት በክርክር ወቅት ተረድተናል፡፡ እኛ እሳቸው ጋ እንዳንደርስ ድልድዩን ሰባብረው ስማችንን ስላጠለሹት፣ ምንም መልካም ነገር ብንሠራ እንዳንደመጥ ተደርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- መሠረታዊ የሠራተኛ ማኅበር ስትመሠርቱ ማኔጅመንቱ ተቃውሞ ነበረው?

አቶ ዳዊት፡- ከባድ ተቃውሞ ነበረው፡፡ ምክንያቱም የሠራተኛን መብት በመጨፍለቅ እንደፈለጉ ማባረር አይችሉማ፡፡ በከባድ ትግል ማኅበሩ ከተመሠረተ በኋላ፣ ለዘጠኝ ወራት ተከራክረን ደግሞ የኅብረት ስምምነት ተፈራረምን፡፡ በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ትዕዛዝ ማኔጅመንቱ ተደራድሯል፡፡ ፌዴሬሽን፣ ኮንፌዴሬሽን፣ የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮና ሌሎች አካሎች ገብተውበት ስምምነቱ እንዲፈረም ቢደረግም፣ ወደ መሬት ወርዶ ሥራ ላይ እንዲውል ለማድረግ ለሁለት ዓመታት ትግል ፈልጓል፡፡ የሠራተኛው አስተሳሰብ በአሠሪና ሠራተኛ መንፈስ ሳይሆን በአባትና በልጅ መካከል ያለ ግንኙነት ነው የሚል አስተሳሰብ ነበረን፡፡ አንድም ቀን ስለመጥፎ ነገር አስበን አናውቅም፡፡ ስለሥራችንና የሆቴሉ ዕድገት እንጂ፤ ማኔጅመንቱ በሠራው ሴራ እንደዚህ እንሆናለን ብለን አስበን አናውቅም ነበር፡፡ ይኸ በመሆኑም በጣም አዝነናል፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ፣ ባለቤቱ የሚረዱበትና እያንዳንዱም የሴራ ቡድን የሚጋለጥበትና የሥራውን የሚያገኝበት የፍርድ ቀን እሩቅ አይሆንም፡፡

ሪፖርተር፡- ከሥራ የተሰናበታችሁት ሠራተኞች ስንት ናችሁ? እንዴትስ ነው የተሰናበታችሁት?

አቶ ዳዊት፡- በአንድ ጊዜ የተሰናበትነው 65 ሠራተኞች ነን፡፡ ከሥራ የተባረርነው በሕገወጥ መንገድና ለአገርም በሚያሳፍር ሁኔታ ነው፡፡ ምክንያቱም ሕግና መንግሥት ባለበት አገር የሆቴሉ ሠራተኞች ባልሆኑ ጉልበተኞች (ባውንሰሮች) አንገታችንን እየተያዝን እንድንባረር ተደርገናል፡፡

ሪፖርተር፡- እንዴት?

አቶ ዳዊት፡- በምስጢር የማባረሪያ ወረቀት አዘጋጁ፡፡ ጉልበተኞችን (ባውንሰሮች) ከተለያዩ የሴኩሪቲ ማሠልጠኛና ከተለያዩ ቦታዎች በማዘጋጀት ሠራተኛውን አዳር ከሚሠራበት ዲፓርትመንት አንድ በአንድ እየተጠሩ፣ ወረቀት ይሰጣቸውና በጉልበተኞቹ ተይዘው ዩኒፎርማቸውን የሚቀይሩበት ቦታ ተወስደው፣ ልብሳቸውን እንዲቀይሩ ከተደረጉ በኋላ ዕቃቸውን በፌስታል ይዘው እንዲወጡ ተደረጉ፡፡ ጠዋት የገባውም በተመሳሳይ ሁኔታ ተባረረ፡፡ 80 ጉልበተኞች ከየሴኪዩሪቲ ማሠልጠኛ ተሰብስበው ከ14 ዓመታት በላይ ካለገለገልንበት መሥሪያ ቤት አንገታችንን ተይዘን ተባረርን፡፡

ሪፖርተር፡- ይኸ ከሆነ በኋላ ምን አደረጋችሁ?

አቶ ዳዊት፡- እኔ የማኅበሩ ሊቀመንበር እንደመሆኔ ሁኔታውን ሁሉ ካየሁ በኋላ፣ ወደ ፌዴሬሽንና ኮንፌዴሬሽን በመሄድ የሆነውን ሁሉ አስረዳሁ፡፡ ከነሱ ጋር በመሆንም ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጠን፡፡ የተፈፀመው ድርጊት በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ በመታወቁ፣ ሊያባርሩ ካሰቡት ከ400 በላይ ሠራተኞች 65ችንን አባረው አቆሙ፡፡ እኛ ላይ የተደረገው ድርጊት የመጀመሪያዎች የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎች፣ አቶ አበራ ገሙ ላይ ከተደረገው የበለጠ ነገር ነው፡፡ አቶ አበራ ገሙ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ሠራተኞች አንድነት (ኢሠአማ) ማኅበር ሊቀመንበር ነበሩ፡፡ በወቅቱ በነበረው የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የሥራ ሚኒስትር ባደረሱባቸው ግፍ የተመላበት ድርጊት፣ ተበሳጭተው ራሳቸውን ያጠፉ የማኅበር መሪ ነበሩ፡፡ የሚገርመው ነገር ግን የሠራተኛ ማኅበሩ ፕሬዚዳንት ራሳቸውን እንዲያጠፉ ያደረጉትም ሚኒስትር በደርግ ተረሸኑ፡፡ ይኸ የሚያሳየው የግፍ ቀንበር በንጹሀን ላይ መጫን ለጊዜው ቢያስደስትም፣ መልሶ በጫኝው ላይ መጫኑ የማይቀር መሆኑን ነው፡፡ እኛም ላይ የተደረገው በተለይ ዓለም በሠለጠነችበት፣ ሕግና መንግሥት ባለበት አገር በኛ ላይ የተደረገው ከዚያ የሚበልጥ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ ሕግ ይውጣ ባሉ ነው ራሳቸውን እስከማጥፋት የደረሱት፡፡ አሁን ግን ሕግ ባለበት፣ ሕገ መንግሥት ባለበት አገር፣ ሕግና ሥርዓቱን ጠብቆ ሠራተኛው ያልተፈለገበትን ሁኔታ ነግሮ የሥራ ውል ማቋረጥ ሲቻል፣ በጉልበተኛ አንገት እያስያዙ ማባረር እጅግ ነውርና የአገርንም ክብር የሚነካ ነው፡፡ በሕግ ላይ ያለን መብት መጠየቅ ነውሩ ባይገባንም፣ የገባን ነገር ግን በአገሪቱ በ1950ዎቹ በሠራተኛ ላይ ይደረግ የነበረው ተግባር አሁንም ከ50 ዓመታት ወዲህም ያው መሆኑ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እናንተ እንዳላችሁት በሕገወጥ መንገድ ከሥራ ተባረራችሁ፡፡ ከዛ ምን አደረጋችሁ?

አቶ ዳዊት፡- ብዙ ጊዜ ሠራተኞች በሕገወጥም ይሁን ሕግን ተከትሎ ከሥራ ሲሰናበቱ ተበታትነው ይቀራሉ፡፡ እኛ ግን እንደዛ አልሆንንም፡፡ ሁላችንም አንድ ዓይነት አቋምና የተለያየ ሙያ ስለነበረን፣ በራሳችን ተደራጅተን የተሻለ ሥራ ለመሥራት እንደምንችል ስለምናውቅ ተሰባስበን መመካከር ጀመርን፡፡ ለአንድ ወር ያህል እየተገናኘን ከተመካከርን በኋላ፣ አክሲዮን ማኅበር አቋቋምን፡፡ ያለንን ገንዘብ በማሰባሰብ የሆቴልና ሬስቶራንት አገልግሎት ፈቃድ አወጣን፡፡ የአክሲዮኑ ፈቃድ ብዙ ሥራዎችን የያዘ ነው፡፡ ሆቴል ማደራጀት፣ ምግብ ማቅረብ፣ የጽዳት፣ የሴኩዩሪቲ ሥራ፣ የሆቴል ዕቃዎችን ማምረትና ማቅረብ፣ የተዘጋጁ ምግቦችን ማቅረብ ወዘተ ነው፡፡ በዚህ አጋጣሚ የተለያዩ የፌዴሬሽን መሪዎች አቅማቸው የሚችለውን የገንዘብ ዕርዳታ አድርገውልናል፡፡ በጣም እናመሰግናለን፡፡ አንደኛው ወገናችን በደል ቢፈጽምብንም ሌላኛው ወገናችን ደግሞ ረድቶናል፡፡ ይኸ ለኛ ትልቅ ብርታት ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- የሬስቶራንታችሁ መጠሪያ ምንድነው?

አቶ ዳዊት፡- ሳብሉ ሬስቶራንት ይባላል፡፡ የምግብ ማቅረቡ ደግሞ ማሚቴ የምግብ አቅርቦት ይባላል፡፡ ማሚቴ የሚል ስያሜ የሰጠነው፣ ማሚቴ የሚለው ስም በኢትዮጵያ ውስጥ የኩሽና ሥራ የምትሠራ ሴት መጠሪያ ስም በመሆኑ ነው፡፡ ነገሥታቱንና መኳንንቱን ክሽን ያለ ምግብ በመሥራት ታበላ የነበረች የባለሙያ ስም ነው፡፡ ይኸ ስም ግን ከጊዜ በኋላ እየተረሳ መጥቷል፡፡ ያንን ለማስታወስና አገራዊ ስምም ስለሆነ ደስም ይላል፡፡ ከመካከላችን አንዱ ጓደኛችን ስያሜውን አመጣና ሁላችንም ተስማምተን አፀደቅነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ በመልሶ ማልማት በሚፈርሱ ቤቶችና ግንባታ እየተካሄደባቸው ባሉ አካባቢዎች ምግብ በማቅረብ ጥሩ እየሠራን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሁላችሁም አንድ ላይ ሆናችሁ እየሠራችሁ ነው?

አቶ ዳዊት፡- አይደለም፡፡ አክሲዮን ማኅበሩን ካቋቋምን በኋላ ከውስጣችን አሥር የሚሆኑት ሬስቶራንቱ ላይ እንዲሠሩ በማድረግ፣ የተቀረነው እንደየሙያችን በተለያዩ ቦታዎች በመቀጠር እየሠራን ነው፡፡ በዚሁ በአዲስ አበባ ከተማና የክልል ከተሞች በመሄድ በጥሩ ደመወዝ ተቀጥረን እየሠራን ነው፡፡ አዳዲስ ሆቴሎች ሲከፈቱ ይደወልልንና የማደራጀት ሥራ እንሠራለን፡፡ ሬስቶራንታችን በጥሩ ሁኔታ እየሠራ ነው፡፡ በኅዳር ወር 2007 ዓ.ም. የተከፈተና ብዙ ደንበኞችን ያገኘ ሬስቶራንት ሆኗል፡፡

ከሸራተን አዲስ ሌግዠሪ ኮሌክሺን ሆቴል በሕገወጥ መንገድ የተባረርነው ሐምሌ 23 ቀን 2006 ዓ.ም. በአሳፋሪና አሳዛኝ ድርጊት ነው፡፡ ይኸ በኛ ላይ የተፈፀመው ድርጊት በሌሎች ሠራተኞች ላይ እንዳይደገም ትግል ያስፈልጋል፡፡ የሠራተኛ ማኅበር ማቋቋም ሕጋዊ ቢሆንም፣ የማኅበር መሪ ግን ጥበቃ የለውም፡፡ በመሆኑም መንግሥትም ትኩረት ሰጥቶ ሠራተኛና የሠራተኛ ማኅበራት መሪዎች ጥበቃ እንዲያገኙ እንዲያደርግ፣ መልዕክታችንን በዓመታዊ በዓላችን ላይ ለማስተላለፍ እንሞክራለን፡፡

ሪፖርተር፡-  ከሸራተን አዲስ የተባረራችሁበትን ቀን በምን መልኩ ለማክበር ነው ያሰባችሁት?

አቶ ዳዊት፡- የማኅበር መሪዎች ዋስትናና ትኩረት እንዲሰጣቸው፣ በሕጉም ውስጥ ተካቶ  ጥበቃ እንዲደረግላቸው በማሳሰብና የረዱንን የተባበሩንን ሰዎች ለማመስገንም ቀኑን እናከብረዋለን፡፡ ተመሳሳይ ችግር ያለባቸውም ጠንክረው ከሠሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ ለማሳየትና በእኛ ላይ በደል የፈፀሙ ሰዎችም እኛ እነሱ ያሰቡን ዓይነት ሰዎች እንዳልሆንም በማሳየት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ከሥራ ከተባረራችሁ በኋላ መብታችሁን በሕግ ለማስከበር ያደረጋችሁት ነገር አለ?

አቶ ዳዊት፡- ወደ ሕግ ሄደናል፡፡ ከሰንም ድርጊቱ ሕገወጥ መሆኑን ፍርድ ቤት ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ ነገር ግን በኛ ላይ የተፈፀመው ድርጊት ሕገወጥ መሆኑ በፍርድ ቤት የተረጋገጠ ቢሆንም፣ ድርጊቱን የፈጸሙት አካሎች ግን ምንም አልተባሉም፡፡ እኛም ሕገወጥ መባሉን ከመስማት ባለፈ ምንም ያገኘነው ነገር የለም፡፡ ነገር ግን ይኸንን ድርጊት የፈጸሙት ሰዎች መቼም ቢሆን በታሪክ ተጠያቂዎች ናቸው፡፡ የሠራተኛ ትግል በተነሳ ቁጥር እነዚህ ሰዎች በመጥፎ ተምሳሌት ሲነሱ ይኖራሉ፡፡ ሲሆን ሲሆን ሕግ ሕገወጥ ያላቸው እነዚህ ሰዎች ሊጠየቁ ይገባል፡፡ ለሌሎች ማስተማሪያ እርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ እኛም የሞራል ካሳ ያስፈልገናል፡፡ ስማቸው በግልጽ የሚታወቁ የራሳቸውን ቡድን አደራጅተው ሠራተኞችን በገዛ አገራቸው ቅኝ ግዛት ውስጥ ያስገቡ አካሎች በሕግ ተጠያቂ ሊደረጉ ይገባል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥትም ሆነ የድርጅት ባለቤቶች ምን ማድረግ አለባቸው ይላሉ?

አቶ ዳዊት፡- እኛ ሼኽ መሐመድ ዓሊ አልአሙዲንን የምናስባቸው እንደ አባት ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ስለሳቸው ምንም ዓይነት ክፉ ነገር ተናግረን አናውቅም፡፡ እሳቸው አሁን ለደረስንበት ደረጃና ዕውቀት ምክንያት ናቸው፡፡ በሳቸው ድርጅት ውስጥ ሆነን ተምረናል፡፡ ዕውቀት አግኝተናል፡፡ ይኸ በመሆኑም ዕድሜ ይስጣቸው ማለት እንወዳለን፡፡ በኛና በሳቸው መካከል ክፍተት በመፍጠር ያተረፉና የሚያተርፉ ነጋዴዎች አሉ፡፡ እኛን እንደ መስዋዕት በግ ቢሸጡንም፣ ለፍርድ የሚቀርቡበት ቀን ግን ይኖራል፡፡ ሼክ መሐመድ አንድ ቀን እውነቱ ይገባቸዋል፡፡ የዛን ጊዜ በዙሪያቸው ያሉ አስመሳዮችና እሳቸውን ብለው ሳይሆን ገንዘባቸውን ብለው የተጠጉ ሁሉ እነማን እንደሆኑና ለምን እንደቀረቧቸው ማወቃቸው አይቀርም፡፡ የዚያን ጊዜ እኛን ያስቡናል፡፡ ይኸ የማይቀር እውነታ ነው፡፡ ለእሳቸውም ዕድሜና ጤና ይስጣቸው፣ እኛም ለከርሞው የምናየው ይሆናል፡፡ ሌላው እኛ መጥፎ ነገር እንደፈጸምን በማስመሰል የራሱን ቢዝነስ ለመሥራት ባለሀብቱን ከቦ የሚገኘው የተለያየ ቡድን፣ በራሱ መንገድ ማስፈራራቱ ሳያንስ፣ የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች እየተከታተሉን እንደሆነና የጊዜ ጉዳይ እንጂ እንደሚያጠፉን ያስወሩ ቢሆንም፣ እስካሁን በእኔም ላይ ሆነ በጓደኞቼ ላይ አንድም የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችም ሆኑ ሌላ አካል ያደረሰብን ጫናም ሆነ ሥጋት የለም፡፡ እነሱ ይመስላቸዋል እንጂ መንግሥት ዜጎቹን የመጠበቅ ኃላፊነቱን በሚገባ ለመወጣት ባለፈ ስለግለሰቦችና ድርጅቶች አግዞ ርካሽ ነገር ውስጥ አይገባም፡፡ ገብቶም አያውቅም፡፡ ንፁህ በመሆናችን ያለምንም መሳቀቅና ፍርሀት ሠርተንና ውለን እንገባለን፡፡ በዚህም መንግሥትን ለማመስገን እንወዳለን፡፡ በሁሉም መስክ የተባበሩንና ወገኖቻችንን በዚህ አጋጣሚ እናመሰግናለን፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች