Monday, March 4, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹ፕሬዚዳንት ኦባማ በአካል መምጣታቸው ብቻ በቂ ነው›› አምባሳደር ግርማ ብሩ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በታሪካዊነቱ የተመዘገበው የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት እንደምታ በተለያየ መንገድ እየተገለጹ ነው፡፡ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ የባራክ ኦባማን ጉብኝት እንዴት እንደሚገልጹት ዳዊት ታዬ ላቀረበላቸው ጥያቄ ይህን አጭር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የፕሬዚዳንት ኦባማ ኢትዮጵያን መጎብኘት ምን አንደምታ አለው

አቶ ግርማ፡- የፕሬዚዳንት ኦባማ ጉብኝት በራሱ ሌላ ድርድር ባይካሄድበት እንኳ ብዙ ነገሮችን ያሳያል፡፡ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር ዓለም ነው የሚዞረው፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ብቻቸውን የሚንቀሳቀሱ አይደሉም፡፡ ዓለምን የሚዘግቡ ጋዜጠኞች በሙሉ አብረው ነው የመጡት፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያ ዛሬ ያላትን ገጽታ ለማሳወቅ የእርሳቸው በአካል መምጣት ብቻውን በቂ ነው፡፡ ከዚህ አልፎ ግን በሁለቱም አገሮች መካከል ባለ ግንኙነት አንድ መሪ ከአገር ወጥቶ ወደ ሌላ አገር በመሄድ ከአንድ መሪ ጋር በሚወያዩበት ጊዜ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የደረሰ መሆኑ መገለጫ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያና የአሜሪካ የንግድ ግንኙነት ሲታሰብ የቀረጥና የኰታ ነፃ ገበያ ዕድል ወይም አገዋ ይጠቀሳል፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ በአገዋ ምን ያህል ትጠቀማለች? ለዚህስ ምን ያህል ዝግጅት ተደርጓል?

አቶ ግርማ፡- የአገዋ ዕድል ከዚህ ቀደም ባልተደረገ ደረጃ እንዲራዘም ተደርጓል፡፡ በቅርቡ በተወሰነ ውሳኔ አገዋ ለአሥር ዓመት ነው የተራዘመው፡፡ ከዚህ ቀደም ለአምስት ዓመት ነበር ሲራዘም የቆየው፡፡ ኢንቨስት ለሚያደርጉ ሁሉ በአሥር ዓመት መራዘሙ ትልቅ ነገር ነው፡፡ በአገር ደረጃ ደግሞ ኢትዮጵያ በአሥር ዓመት ውስጥ ከዚህ ዕድል ምን ያህል ጥቅም ልታገኝ እንደምትችል የአገር ስትራቴጂ አዘጋጅታ ወደ ተግባር ለመግባት እየተዘጋጀች ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ወደዚህ ከመምጣታቸው በፊት የአገዋ ዕድል ለአሥር ዓመት እንዲራዘም ፈርመው ነው የመጡት፡፡ የኢትዮጵያን ተጠቃሚነት ስናይ ካለፉት ዘመናት ጋር ሲመዛዘን አሁን የተሻለ አቅም ገንብታለች፡፡ በጨርቃ ጨርቅ፣ በአልባሳትና በሌሎች ዘርፎች በብዙ ጥቅም የሚያስገኙላትን አቅም ስለ ያዘች የበለጠ ትጠቀማለች፡፡

ሪፖርተር፡- የኦባማ ጉብኝት ቻይናና አሜሪካ በአፍሪካ ያላቸውን ጥቅም በማስመልከት የሁለቱን ግጭት ያጎላል የሚሉ አሉ፤

አቶ ግርማ፡- አሜሪካና ቻይና በአፍሪካ ባላቸው ጥቅም ሳቢያ አይጋጩም፡፡ እርስ በርስ የሚነግዱት እኮ ይበልጣል፡፡ በአፍሪካ ከሚነግዱበት በላይ እርስ በእርስ ያላቸው የንግድ ልውውጥ ከፍተኛ ነው፡፡ በአፍሪካ ያላቸው ገበያ ግጭት ይፈጥራል የሚለው የሰዎች የተሳሳተ አመለካከት ነው፡፡ ሁለቱም የዓለም ትልልቅ ኢኮኖሚዎች ናቸውና የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ የግጭት አድርገን መቁጠር የለብንም፡፡ የየራሳቸውን ጥቅም ለማራመድ አፍሪካ ውስጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ግሎባላይዜሽን (ሉላዊነት) የፈጠረው ነው፡፡ ስለዚህ አሁን ባለው መረጃ ሒደቱ የውድድር እንጂ የፀብ አይደለም፡፡ በእኛ በኩል ባለው ላይ ግን ችግር የለም፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች