Thursday, February 22, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት የእንፋሎት ኃይል ከግል ኩባንያ ለመግዛት ስምምነት ፈረመ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚደረግበትን የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ለመገንባት የመግባቢያ ሰነድ የፈረመው ሬይክቪክ ኩባንያ እዚህ የሚያመርተውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለኢትዮጵያ መንግሥት ለመሸጥ የሚያስችለውን ስምምነት ፈረመ፡፡

ፓወር አፍሪካ በሚሰኘው የኦባማ ኢንሽዬቲቭ ድጋፍ ይገነባል የተባለው ይህ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ በግሉ ዘርፍ የሚገነባ የመጀመርያው የኃይል ማመንጫ ይሆናል፡፡ የሚያመርተውንም ኃይል ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሽያጭ የሚቀርብበት ዋጋ ላይ ስምምነት በመድረስ ሰኞ ሐምሌ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ተፈራርሟል፡፡

በደቡብ ክልላዊ መንግሥት ቆርቤቲ በተባለ አካባቢ የሚገነባውና ቆርቤቲ ጂኦተርማል ተብሎ የተሰየመውን ፕሮጀክት ለመገንባት የመግባቢያ ስምምነት ላይ ተደርሶ የነበረው ባለፈው ዓመት ቢሆንም፣ እስካሁን ዝርዝር ጉዳዮችን የተመለከቱ ስምምነቶች ሳይካሄዱ ቆይቶ ነበር፡፡

የመጀመርያው መግባቢያ ሰነድ ከተፈረመ በኋላም ኩባንያው ለእንፋሎት ማመንጫ ፕሮጀክቱ በተከለለ ቦታ ቅድመ ግንባታዎች ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ የኢትዮጵያን መንግሥት በመወከል ከኩባንያው ጋር የኃይል ግዥ ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር አዜብ አስናቀ እንደገለጹት፣ አሁን ዋጋን የተመለከተ ስምምነት ተፈረመ እንጂ ኩባንያው ወደ ተግባራዊ ሥራ ገብቷል፡፡

የዚህ ፕሮጀክት ዋነኛ ስምምነት ግን ከትናንት በስቲያ ሐምሌ 20 ቀን 2007 ዓ.ም. የተካሄደው ነው ማለት እንደሚቻል ጉዳዩን በቅርበት ሲከታተሉ የነበሩ ወገኖች ይገልጻሉ፡፡ ምክንያቱም ፕሮጀክቱ ከኢትዮጵያ መንግሥት ፋይናንስ ውጭ በግል ኩባንያ በኩል የሚገነባና የሚያመነጨውንም ኃይል ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸጥ በመሆኑ የሽያጭ ዋጋው ላይ መስማማት ግድ ስለነበር ነው ይላሉ፡፡

እዚህ ስምምነት ላይ ከመደረሱ በፊት ግን እጅግ ፈታኝ ሒደቶች እንደታለፉ ይነገራል፡፡ የፕሮጀክቱ ዋና የገንዘብ ምንጭ ፓወር አፍሪካ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ በመሆኑ፣ ይህ ስምምነት ከፕሬዚዳንት ኦባማ የኢትዮጵያ ጉብኝት ጋር እንዲገናኝ በመፈለጉ ከፕሬዚዳንቱ መግባት ጎን ለጎን ስምምነቱ ሊደረስ ችሏል፡፡

ስምምነቱን ማድረግ ፈታኝ ነበር የተባለለት ዋነኛ ምክንያት ኩባንያው ኃይል ማምረት ሲጀመር ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በምን ያህል ዋጋ ይሸጣል የሚለው ነበር፡፡

የሬክቪክ ኩባንያ የቆርቤቲ ፕሮጀክት ሊቀመንበር ኬንያዊው አንዲ አራጉጂ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት፣ እንደተናገሩት፣ ድርድሩ እ.ኤ.አ. ከኖቬምበር 2014 ጀምሮ ሲካሄድ እንደነበር አስታውሰው በኩባንያውና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ልዩነቶች ቢኖሩም፣ አንዴ በረድ ሌላ ጊዜ ሞቅ እያለ ተጉዞ መጨረሻ ስምምነቱ  ሊደርስ ችሏል፡፡

በኩባንያውያና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል ያለው ድርድር ረዥም ጊዜ የወሰደበት ሌላው ምክንያት ደግሞ እንዲህ ያለው ስምምነት የፖሊሲ ጉዳዮችን የሚመለከት ጭምር በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ ጉዳዩን ለመቋጨት የከፍተኛ ባለሥልጣናትን ይሁንታ ማግኘት ስለነበረበት ድርድሩ መርዘሙንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ በድርድሩ ላይ የነበሩ ወገኖች እንደገለጹት ደግሞ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ከየትኛውም ኩባንያ ጋር እንዲህ ያለ ስምምነት አድርጋ ስለማታውቅ ድርድሩ ጊዜ መውሰዱ ግድ ነበር፡፡ መንግሥት ከግል ኩባንያዎች ጋር በጋራ ኢንቨስት ለማድረግ የሚያስችለው የሕግ ማዕቀፍ ገና እንዳላወጣ ይታወቃል፡፡

ኢንጂነር አዜብ እንደገለጹትም፣ ‹‹ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነቱን ውል ስትዋዋል የመጀመርያዋ ነው፡፡ በኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ዙሪያ እስካሁን ያለው አሠራር የኃይል ማመንጫው ከተገነባ በኋላ ኮንትራክተሩ ፕሮጀክቱን ለመንግሥት ያስረክባል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል መሥሪያ ቤቱ ደግሞ ኃይል ማመንጫውን ተረክቦ ያስተዳድራል፡፡ በዚያ ፕሮጀክት የሚመረተውንም ኃይል ይሸጣል፤›› ብለዋል፡፡

አሁን ግን የእንፋሎት ኃይል ማመንጫውን ከሚገነባው ኩባንያ ጋር የተደረሰው ስምምነት ኩባንያው በራሱ ወጪ ኃይል ማመንጫውውን የሚገነባና የሚያመርተውንም ኃይል በሁለቱ ወገኖች መካከል በተደረሰ የመሸጫ ዋጋ መሠረት ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸጥ በመሆኑ፣ የተለየ ስምምነት ነው በማለት ገልጸዋል፡፡ የትናንት በስቲያው ስምምነትም ኢትዮጵያ ከአንድ የግል ኩባንያ ኃይል የምትገዛበት የመጀመርያው ስምምነት እንደሆነ የተገለጸውም ለዚህ ነው ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥትና በኩባንያው መካከል በተደረሰው ስምምነት፣ ሬክቪክ  ያመረተውን ኃይል በምን ያህል ዋጋ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደሚሸጥ ግን ሁለቱም ወገኖች ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ኢንጂነር አዜብ በተለይ በምን ያህል ዋጋ እንደምንገዛ መግለጹ ከዚህ በኋላ ለምናደርገው ተመሳሳይ ሥራ እንቅፋት ስለሚሆንብን ዋጋውን አንገልጽም ብለዋል፡፡

ይህ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በሁለት ምዕራፍ ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን፣ ቆርቤቲ አካባቢ የተጀመረው የመጀመርያው ምዕራፍ ፕሮጀክት 500 ሜጋዋት የሚያመነጭ ይሆናል፡፡ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ ሥራ የሚጠናቀቀውና ኃይል ማቅረብ የሚጀምረው በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሸን የዕቅድ ዘመን ውስጥ እንደሚሆን ኢንጂነር አዜብ ገልጸዋል፡፡

ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ ደግሞ ቱሉቦዬ በተባለ አካባቢ የሚገነባ ሲሆን፣ በሦስተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የሚከናወን ስለመሆኑም ኢንጂነር አዜብ ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ በሁለቱ ምዕራፎች አንድ ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ከእንፋሎት ይመነጫል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የግንባታው ጊዜ ረዥም ነው፤ ለምን? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ፣ የፕሮጀክቱ ጊዜ መራዘም የፕሮጀክቱ ባህሪ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ እንደ ምሳሌ የሚጠቀሱትም በአንዱ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ላይ ብቻ ከ1800 እስከ 2000 ሜትር ርዝማኔ ያላቸው ከ200 በላይ ጉድጓዶች እንደሚቆፈሩ በመግለጽ ነው፡፡ ሌሎች ተያያዥ ሥራዎች ጊዜ የሚወስዱ በመሆኑ ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ረዥም ጊዜ ሊወስድ ይችላል ብለዋል፡፡

የእንፋሎት ማመንጫው ፕሮጀክት ያስፈልገዋል የተባለው ወጪ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገው አራት ቢሊዮን ዶላር ወጪ በአሁኑ ወቅት በግንባታ ላይ ያለው የህዳሴ ግድብ ከሚጠይቀው ወጪ ጋር የተቀራረበ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ለምን ተመራጭ ሆነ የሚለው ጥያቄ ይነሳል፡፡

ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልገው ገንዘብ በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሸፈን ባለመሆኑ እንደሆነ በአንድ በኩል ሲገለጽ፣ የፕሮጀክቱ ግንባታ ወጪ ላይ የመንግሥት እጅ የማይኖርበት መሆኑም የግንባታው ጊዜ መወሰድ ብዙም ትኩረት እንዳልተሰጠው ይነገራል፡፡ እንደ ኢንጂነር አዜብ ገለጻ ግን ይህ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የኃይል አቅርቦትን ከማሳደግ ባሻገር በተለይ የኢነርጂ ስብጥሩ ላይ የራሱ ሚና ይኖረዋል፡፡

‹‹እስካሁን የኤሌክትሪክ ኃይል በብዛት የምናመነጨው ከውኃ ነው፤›› ያሉት ኢንጂነር አዜብ፣ የኃይል ምንጫችን ውኃ ብቻ መሆን ስለሌለበትና መቀላቀል ስላለበት ከአየር ንብረት ለውጥና ከተለያዩ ምክንያቶች የውኃ ሀብት ላይ ችግር ቢመጣ  የጂኦተርማል፣  የነፋስ ወይም የፀሐይ ኢነርጂ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡ የኃይል ምንጩ በተለያየ መንገድ በሚመነጭ ኃይል ተቀላቅሎ ሲስተሙ ውስጥ መግባቱም የአገሪቱን የኃይል አቅርቦት መጠን እንዲጨምር ያደርጋል፡፡

የፓወር አፍሪካ ኢንሼቲቭ ባሰራጨው መረጃ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በእንፋሎት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት የተደረሰው ስምምነት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የታዳሽ ኃይል ባለቤት እንድትሆን ያደርጋታል፡፡

ይሁን እንጂ በዘርፉ የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ ዝቅተኛ ነው፡፡ በኢትዮጵያ 45 ሺሕ ሜጋዋት የኃይድሮ ኤሌክትሪክ የማመንጨት አቅም  በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ብቻ ከአሥር ሺሕ ሜጋ ዋት በላይ የጂኦተርማል ኃይል ማመንጨት ይቻላል ተብሎ ይታሰባል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2035 ዓ.ም. እስከ 37 ሺሕ ሜጋ ዋት የማመንጨት ውጥን እንደተያዘ የሚያመላክተው የፓወር አፍሪካ መረጃ በዚህም ውስጥ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ትልቋ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅራቢ (ላኪ) አገር ትሆናለች ይላል፡፡ 

የኢትዮጵያ መንግሥት በኢነርጂ ዘርፍ የግሉ ክፍል ኢኮኖሚ ተሳትፎ እንዲኖር መጣር ይኖርበታል የሚለው የፓወር አፍሪካ ኢኒሼዬቲቭ፣ በተለይ የግሉ ዘርፍ በኢነርጂ ማሰራጨትና ማከፋፈል ብሎም የአገሪቱ የኢነርጂ ደንበኞች ዘመናዊ አገልግሎት እንዲያገኙ በማስቻሉ ረገድ ትልቅ ሚና ይኖረዋል ተብሏል፡፡

ፓወር አፍሪካ የኢትዮጵያን የኢነርጂ ልማት ስትራቴጂ የሚደግፈው በቴክኒክ  ጭምር ሲሆን፣ ከዚህ በተጨማሪ የአገሪቱን የግሉ ዘርፍ በጂኦተርማል፣ በፀሐይና በነፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች እንዲሳተፉና የፋይናንስ አቅርቦት እንዲያገኙ ማድረግ ስለመሆኑም ገልጿል፡፡ የቆርቤቲ ጂኦተርማል ፕሮጀክትም የዚሁ አካል ነው፡፡

በሌላ በኩል በፓወር አፍሪካ የሚደገፍ፣ የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን የሚያመርት  ሌላ ኩባንያንም ሥራ ጀምሯል፡፡ ድቬንተስ የተባለው ኩባንያ በኢትዮጵያ 2,000 ዘመናዊ (ስማርት) የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎችን ለአዲስ አበባ ደንበኞች አምርቶ ለማቅረብ የሚያስችል ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ ሁለት ሚሊዮን ስማርት ቆጣሪዎች በኢትዮጵያ እንዲመረቱ ፓወር አፍሪካ ድጋፍ ያደርጋል ተብሏል፡፡

እነዚህ ስማርት የኤሌክትሪክ ቆጣሪዎች በኢትዮጵያ ግልጋሎት ላይ ሲውሉ፣ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች የሚሰጡ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ የኤሌክትሪክ መጥፋትና መቆራረጥን በመቀነስ ጉልህ ድርሻ እንደሚኖራቸው ይታሰባል፡፡

ፓወር አፍሪካ በሌላ በኩል ተቀማጭነቱ በአዲስ አበባ ላደረገው የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል (Easter Africa Power Pool-EAPP) ድጋፍ ይሰጣል፡፡ ይህ ተቋም ድንበር ተሻጋሪ ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭን በአነስተኛ ዋጋ ተግባራዊ እንዲሆን የሚንቀሳቀስ ሲሆን፣ በመንግሥትና በግሉ ዘርፍ ስምምነት መሠረት ተፈጻሚ የሚሆነው በኢትዮጵያ መንግሥት፣ በሬክቪክና በአጋሮቹ መካከል ነው፡፡

ፓወር አፍሪካ በአሜሪካ መንግሥት አመንጪነት የተጠነሰሰና በባራክ ኦባማ አማካይነት እ.ኤ.አ. በ2013 ወደ ተግባር የገባ ነው፡፡ ዋና ዓላማውም ከሰሃራ በታች በሚገኙ አገሮች የኤሌክትሪክ ኃይልን ማስፋፋት ሲሆን፣ ከመንግሥትና ከግሉ ዘርፍ ጋር በትብብር የሚሠራ ነው፡፡

ፓወር አፍሪካ ከ20 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ የሚጠይቁ ፕሮጀክቶችን ለመደገፍ የሚንቀሳቀስ ነው፡፡ የአሜሪካ መንግሥት ለፓወር አፍሪካ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ሰባት ቢሊዮን ዶላር መድቧል፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የዓለም ባንክና የስዊድን መንግሥት በድምሩ ዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ አድርገዋል፡፡

እንደ ኢንጂነር አዜብ ገለጻ፣ በኢትዮጵያ የእንፋሎት ኃይል ፕሮጀክቱን የሚያካሂደው ኩባንያ አብረውት እንደባለአክሲዮን የሚታዩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎችን በጥምረት የያዘ ሲሆን፣ በእንፋሎት ኃይል ላይ የካበተ ልምድ አለው ብለዋል፡፡

የዚህ ፕሮጀክት መሥራች የአላና ፖታሽ ኩባንያ መሥራች የሆኑት አቶ ነጅብ አባቢያ ሲሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት ግን የአሜሪካና ሌሎች አገሮች ትልልቅ ኩባንያዎችም በአክሲዮን ባለቤትነት ተቀላቅለውታል፡፡ እስካሁን በቆርቤቲ ፕሮጀክት ላይ እየወጣ ያለውን ወጪ የሸፈኑት ባለአክሲዮኖቹ ናቸው ተብሏል፡፡

ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደርና ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሴናተሮች ተገኝተዋል፡፡ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ግርማ ብሩን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትም በስምምነቱ ታድመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች