[ለክቡር ሚኒስትሩ አንድ ጋዜጠኛ ደወለላቸው]
- ሰላም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ሰላም እንዴት ነህ?
- እግዚአብሔር ይመስገን፡፡
- መቼም ጥሩ አድርጋችሁ ነው የምትዘግቡት?
- ምኑን?
- የኦባማን ጉብኝት ነዋ፡፡
- ለእሱማ እናንተን እየጠበቅናችሁ ነው፡፡
- ደግሞ ከመቼ ጀምሮ ነው ዘገባ ለመዘገብ እኛን የምትጠብቁት?
- ማለቴ ሥልጠናውን እየጠበቅን ነው፡፡
- የምን ሥልጠና?
- የውጭ ሚዲያዎች የሚሰጡንን ሥልጠና ነዋ፡፡
- የምን ሥልጠና ነው የሚሰጧችሁ?
- ዘገባውን እንዴት መዘገብ እንዳለብን ነዋ፡፡
- እናንተ ደግሞ ለሌላው ታስተምራላችሁ እንጂ ትማራላችሁ እንዴ?
- እኛማ እንደዚያ ነበር የሚመስለን እንደዚያ እንዳልሆነ ግን አሁን አወቅን፡፡
- እንዴት?
- ሰደባችሁን እኮ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኛ?
- እህሳ፡፡
- ምን ብለን?
- የኢትዮጵያ ሚዲያ ሥነ ምግባር የለውም ብላችሁ ሞለጫችሁን እኮ፡፡
- ኧረ እኛ እንደሱ አላልንም፡፡
- አላችሁ እንጂ፣ እንዲያውም የውጭ አገር ሚዲያዎች ለእኛ ሥልጠና እንዲሰጡን ተማጸናችሁ፡፡
- እ…
- እኔ የምለው ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምንድነው አንተ የምትለው?
- ማያ ነገር ናችሁ ልበል?
- የምን ማያ ነው የምታወራው?
- ስፔስ 99 የሚለውን ፊልም አያስታውሱትም?
- ኧረ አላስታውሰውም፡፡
- ለነገሩ ያኔ በኢቲቪ ሲተላለፍ እናንተ በረሃ ነበራችሁ፡፡
- ምን ለማለት ፈልገህ ነው?
- ማያ የምትባል አክተር ፊልሙ ላይ ነበረች፡፡
- እሺ፡፡
- እና ማያ ስትፈልግ ጭራቅ፣ ስትፈልግ ቆንጆ ሴት፣ ስትፈልግ ወንድ፣ ኧረ ስንቱን ነበር የምትሆነው፡፡
- ታዲያ እዚህ ምን አመጣት?
- እናንተም ማያ ሆናችሁብን እኮ፡፡
- እንዴት?
- ከዛሬ አራትና አምስት ዓመት በፊት የውጭ ሚዲያውን ኒዮሊብራሊስትና የግል ኩባንያዎች ተቀጣሪዎች ናቸው ትሉን ነበር፡፡
- አዎን ልክ ነው፡፡
- አሁን ደግሞ ተቀይራችሁ ለአገራችን ሚዲያዎች ሥልጠና ስጡልን አላችሁ፡፡
- ታዲያ ምን ችግር አለው?
- እኮ እንደ እስስት እየተቀያየራችሁ የራሳችሁን ጥቅም ለማስከበር ትቆማላችሁ፡፡
- እኛ እኮ እንዲያግዟችሁ ብለን ነው፡፡
- ከእነሱ ይቅል እናንተ ብታግዙን ይጠቅመናል፡፡
- እንዴት እናግዛችሁ?
- ሚዲያውን አበረታች የኢንቨስትመንት ዘርፍ አድርጉት፡፡
- እ…
- ጋዜጠኞች እንደ ልባቸው እንዲጽፉና እንዲናገሩ አድርጉ፡፡
- እንደ ልባቸው ከጻፉና ከተናገሩማ ዕድገት አይኖርም፡፡
- ታዲያ ምንድነው የሚኖረው?
- ውድቀት፡፡
- ይኼ ነው ችግራችሁ፡፡
- እንዴት?
- ሰዎች ሮቦት አይደሉም፡፡
- እሱንማ አትነግረኝም፡፡
- ስለዚህ ሁሉም ሰው የተለያየ አመለካከት አለው፡፡ ከእናንተ ስለተለየ ብቻ ማጥላላት ተገቢ አይደለም፡፡
- ለማንኛውም ሥልጠናው ያስፈልጋችኋል፡፡
- ለመሆኑ እኛን ማን ነው የሚያሠለጥነን፡፡
- አንዳቸው ናቸዋ፡፡
- የአሜሪካው ኒውዮርክ ታይምስ ማለት ነው? ወይስ የእንግሊዙ ዘ ሰን ነው? ወይስ የቻይናው ፒፕልስ ዴይሊ ነው?
- ምን ልዩነት አላቸው?
- ትልቅ ልዩነት አላቸው፡፡ ሁሉም የራሳቸው የሆነ ርዕዮተ ዓለም ያራምዳሉ፡፡
- ለእኛ ርዕዮተ ዓለም የትኛው ይቀርባል፡፡
- የቻይናው ይመስለኛል፡፡
- እንዲያውም እነሱ ናቸው ሥልጠናውን የሚሰጧችሁ፡፡
- የአሜሪካኖቹን እኮ ስጡልን ብላችሁ ተማጽናችሁ ነበር፡፡
- ተሰርዟል እንላቸዋለን፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ቢሯቸው ገባ]
- እንዴት አለፈ እባክህ?
- ስኬት ብቻ ነበር ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አንተስ እንዴት ገመገምከው?
- አስፈነደቅነው አይደል እንዴ?
- እንዴት?
- ቅድመ አያቱን አገናኘነው፡፡
- የኦባማ ቅድመ አያት ኢትዮጵያዊ ናት እንዴ?
- አይ ማለቴ ሉሲን ልልዎት ፈልጌ ነው፡፡
- እኔ ደግሞ ይኼንን እስከዛሬ እንዴት ሳላውቅ ብዬ ልቆጭ ነበር፡፡
- ቡናም አስጠጣነው፡፡
- ልክ ነው፡፡
- ጭፈራም ቢሆን አስጨፈርነው፡፡
- ተጠምቆ ነዋ፡፡
- በምን?
- በአብዮታዊ ዲሞክራሲ፡፡
- ሰው እኮ ገርሞታል፡፡
- ምኑ ነው የገረመው?
- ያው ስለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ምናምን አደገኛ ትችት ይሰጣል ተብሎ ነበራ የሚጠበቀው፡፡
- በመርፌ እኮ ነው የሰጠነው፡፡
- ምኑን?
- አብዮታዊ ዲሞክራሲን፡፡
- አንድ ግን ቅር ያለችኝ ነገር ነበረች፡፡
- ምኑ ነው ቅር ያለህ?
- የእሱ ሴኪዩሪቲዎች ናቸዋ፡፡
- ምን አደረጉ?
- እኛ እኮ ቅኝ ግዛት ያልተገዛን አገር ነን፡፡
- አውቃለሁ፡፡
- የእኛን ጥበቃዎች እኮ አላስጠጋ ብለው እነሱ ነበሩ ሲራወጡብን የነበረው፡፡
- ያው ለደኅንነት ብለው ነዋ፡፡
- እኛ እኮ ክቡር ሚኒስትር፣ አይደለም ኦባማን ዳር ድንበራችንን ከጥንት ጀምሮ ሳናስነካ የቆየን ኩሩ አገር ነን፡፡
- እሱማ ልክ ነው፡፡
- ቅኝ ግዛት የማያውቁት ጠባቂዎቻችን እኮ ቅኝ ተገዙ፡፡
- በማን?
- በኦባማ ሴኪዩሪቲዎች ነዋ፡፡
- እ…
- ከዚህ በኋላ ከመጣ ይኼ መደገም የለበትም፡፡
- እውነትህን ነው፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ወዳጅ የሆኑ ነጋዴ ደወሉላቸው]
- ከአሜሪካ ከመጡት ኩባንያዎች ጋር ተፈራረምክ እንዴ?
- በየትኛው ዕድሌ ክቡር ሚኒስትር?
- ለምን አልተፈራረምክም?
- መንግሥት ሁሉን ነገር ጠራረገው እኮ፡፡
- ምን?
- እንዲያው ለእናንተ ሲዘንብ ለእኛም ቢያካፋ ጥሩ ነው፡፡
- ምን ማለትህ ነው?
- ለመሆኑ የኦባማ መምጣት ጥቅሙ ምንድነው?
- በንግድና ኢንቨስትመንት ልንተሳሰር ነዋ፡፡
- እንዴት ማለት?
- በርካታ የአሜሪካ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ሊጐርፉ ነዋ፡፡
- ምን ሊያደርጉ?
- ሊነግዱ ነዋ፡፡
- እ…
- እንደ ድሮው ለምነን ሳይሆን ሠርተን ማደር ልንጀምር ነው፡፡
- ግን ይታሰብበት፡፡
- ምኑ ነው የሚታሰብበት?
- ዕድገታችን ተቀልብሶ ልመና ውስጥ እንዳይከቱን፡፡
- እንዴት?
- የአሜሪካ ኩባንያዎች እኮ እዚህ መጥተው ቢነግዱ፣ የሚያገኙትን ትርፍ ጠራርገው ነው የሚወስዱት፡፡
- እ…
- እኛ ግን ብናተርፍ እዚሁ ነው ኢንቨስት የምናደርገው፡፡
- ስለዚህ?
- ይህ ጉዳይ በሚገባ ሊታሰብበት ይገባል፡፡
- አሁን ጥቅሜ ይነካል ብለህ ነው አይደል?
- አይደለም ክቡር ሚኒስትር፣ በደንብ አስቡበት ብዬ ነው፡፡
- እንዲያውም ሥልጠና የሚያስፈልጋቸው ጋዜጠኞች ሳይሆኑ እናንተ ናችሁ፡፡
- የምን ሥልጠና?
- የውጭ ኩባንያዎች ለእናንተ ሥልጠና መስጠት አለባቸው፡፡
- በምን ጉዳይ?
- በሁሉም ጉዳይ፡፡
- ብቻ አስቡበት፡፡
[የክቡር ሚኒስትሩ ጓደኛ ሌላ ሚኒስትር ደወሉ]
- እንዴት አየኸው የኦባማን ጉብኝት?
- አጨራረሱ ጥሩ አይደለም ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እንዴት?
- የአፍሪካ ኅብረቱን ንግግር አልሰሙም እንዴ?
- ሰምቼዋለሁ፡፡
- በአሽሙር እኮ ነው የነገረን፡፡
- ምን ብሎ?
- ምርጫ ማድረግ ዴሞክራሲ አለ ማለት አይደለም ብሎ ነዋ፡፡
- እ…
- የአፍሪካ መሪዎች ሥልጣን ለምን አለቅም እንደሚሉ እኮ አይገባኝም ነው ያለው፡፡
- አገርን ማገልገል ስለምንወድ ነዋ፡፡
- ሥልጣን ለቃችሁ አገር ማገልገል ትችላላችሁ ብሎ እኮ ነው ወረፍ ያደረገን፡፡
- እ…
- በዚያ ላይ ደግሞ ያንን ሁላ ገንዘብ ይዘው ለምን ሥልጣን እንደማይለቁ ነው ግራ የሚገባኝ እኮ ነው ያለው፡፡
- አፍሪካዊ መሪ ቢሆን ይገባው ነበር፡፡
- ደግሞ የእኛም ባለሥልጣናት ሲያጨበጭቡለት ነበር፡፡
- አሽሙሩ ስላልገባቸው ይሆናላ፡፡
- ለማንኛውም አጨራረሱን አልወደድኩትም፡፡
- ምን ታደርገዋለህ?
- በአፍሪካ አስመስሎ እኛን በአሽሙር ወግቶን ነው የሄደው፡፡
- የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም አሉ፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ቤት ሲገቡ ሚስታቸውን አገኟቸው]
- ነይ ተመልከቺ ይኼን ፎቶ፡፡
- የምን ፎቶ ነው?
- ከኦባማ ጋር የተነሳሁት፡፡
- ምን ያደርግልሃል?
- ይኼ እኮ ቅርሴ ነው፡፡
- የምን ቅርስ?
- ለልጆቼ አሳልፌ የምሰጣቸው ቅርስ፡፡
- ፎቶ ከምትሰጣቸው መርህ ብትሰጣቸው የበለጠ ይጠቅማቸዋል፡፡
- ለማንኛውም ይህ ታሪክ ነው፡፡
- ለመሆኑ እንዴት አለፈ?
- ስኬት በስኬት ነበር፡፡
- ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ የሰፈር ሴቶችንና ወጣቶችን ቲሸርት አስለብሳችሁ አዘመራችኋቸው አይደል?
- እንግዳ ተቀባይ መሆናችንን አትርሺ፡፡
- ያ ሁሉ የአንድ ወር በሥራ መጠመድ ለዚሁ ነው?
- ምናለ ማመስገን ብትለምጂ?
- ለማንኛውም ይኼ ደብል ዲጂት ዕድገታችሁ ሰለቸኝ፡፡
- ለምንድነው የሚሰለችሽ?
- በየሚዲያው እሱን እኮ ነው የምትለፍፉት፡፡
- አሜሪካ ራሷ በደብል ዲጂት እያደገች አይደለም፡፡
- ሌላው የረሳሁት ደግሞ፡፡
- ደግሞ ምን ረሳሽ?
- ጂምናስቲክ ጀምረሃል እንዴ?
- ጠዋት ጠዋት ስፖርት እሠራለሁ እንጂ የምን ጂምናስቲክ አመጣሽ?
- አይ ፕሬዚዳንቱ ከአውሮፕላን ሲወርድ እንደዚያ ወገባችሁ እስኪሰበር ድረስ ምን ሆናችሁ ነው ብዬ ነዋ፡፡
- እሱ ለየት ያለ አቀባበል ነው፡፡
- ምን የሚሉት አቀባበል?
- ልማታዊ አቀባበል!