ለ112 ዓመታት የቆየውን የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት ወደ ቀጣዩ ደረጃ ያሻግረዋል የተባለው የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጉብኝት እሑድ ምሽት ተጀምሮ ሰኞ ሐምሌ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ተጠናቋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ሐምሌ 19 ምሽት ላይ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ ማኒስትር ኃይለ ማርያምና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ተገኝተው ተቀብለዋቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱም ስድስት ኪሎ የሚገኘው ኤምባሲ ትንሽ ቆይታ ካደረጉ በኋላ አዳራቸውን በሸራተን አዲስ አድርገዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በነጋታው ሐምሌ 20 በብሔራዊ ቤተ መንግሥት አቀባበል ከተደረገላቸው በኋላ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር ለሰዓታት የቆየ ዝግ ውይይት አድርገዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩና ፕሬዚዳንቱ የጋራ ውይይታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ በቤተ መንግሥት ለተገኙት የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሥልጣን ላይ ያለን የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ተቀብለው በማስተናገዳቸው የተሰማቸውን ክብር ገልጸው ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ፣ የአፍሪካ የነፃነት ብርሃን ፈንጣቂና የአፍሪካ የፖለቲካ መቀመጫ እንደመሆኗ መጠን የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት አፍሪካና ኢትዮጵያ አስደናቂ የኢኮኖሚ ዕድገት እያስመዘገቡ ባሉበት ወቅት በተለይም ደግሞ ኢትዮጵያ የሁለት አኃዝ ዕድገት እያስመዘገበች ባለችበት ወቅት በመሆኑ፣ የኦባማ ጉብኝት ወሳኝ ነው ማለት እንችላለን ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሬዚዳንቱ ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ መነጋገራቸውን ገልጸው፣ ከንግድና ኢንቨስትመንት አንስቶ እስከ የአየር ንብረት ለውጥ ድረስ ባሉ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ተናግረዋል፡፡ የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ያለውን የዴሞክራሲ ሒደት ሊያግዝ የሚችልበትን መንገድ መወያየታቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ያለውን የዴሞክራሲ ሒደት ለማጐልበትና የመልካም አስተዳደርና የሰብዓዊ መብት ችግሮችን ለመፍታት ቆርጦ መነሳቱን ለፕሬዚዳንቱ ማስታወቃቸውን ገልጸዋል፡፡
በተኮላተፈ አማርኛ ‹‹ደህና ዋላችሁ!›› በማለት ንግግራቸውን የጀመሩት ፕሬዚዳንት ኦባማ፣ ውይይታቸው ፍሬያማ መሆኑን ገልጸው በቤተ መንግሥቱ የጐበኟቸው አንበሶች ወደ ዋይት ሃውስ ለመውሰድ እንዳሰቡ ተናግረው ታዳሚዎችን አስፈግገዋል፡፡ ኢትዮጵያን የጐበኙት የመጀመሪያው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት በመሆናቸው የተሰማቸውን ኩራት ገልጸው፣ ጉብኝታቸው የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት ያጠናክረዋል ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ በዓለማችን ካሉ አገሮች በተሻለ እያስመዘገበች ያለውን የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስቀጠል እንደሚፈልጉና ሁሉን ያሳተፈ ዕድገት መኖሩ ለኢትዮጵያዊያን ጠቃሚ ከመሆኑም ባሻገር ለአሜሪካም የንግድና የኢንቨስትመንት ዕድል እንደሚከፍት ተናግረዋል፡፡
‘የአፍሪካ ግሮውዝ ኤንድ ኦፖርቹኒቲ አክት’ (አጎዋ) ስምምነት በማደስ የኢትዮጵያ ምርቶች በአሜሪካ ገቢዎች እንዲሸጡ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ፓወር አፍሪካ በተባለው የፕሬዚዳንቱ ኢንሺዬቲቭ ኢትዮጵያ ተጠቃሚ የምትሆንበትን መንገድ እንደሚያመቻቹ ተናግረዋል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ኢትዮጵያ በዓለም ደረጃ መሪነቱን በወሰደችበት የልማት ትብብር ላይ እንደሚሠሩ ገልጸው፣ ኢትዮጵያ የቀድሞውን ገጽታ በመቀየር በርካቶችን ከድህነት ማላቀቋን መስክረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በድህነት ውስጥ ያሉ ዜጐችን ከድህነታቸው ለማላቀቅ እንደሚሠሩ ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል ብለዋል፡፡ በተለይም በቅርቡ በአዲስ አበባ በተካሄደው የፋይናንስ ለልማት ጉባዔ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል፡፡
በሦስተኛም ደረጃ ሽብርተኝነት ለማስወገድ በደኅንነት ላይ እንደሚሠሩ የተናገሩት ፕሬዚዳንቱ፣ ኢትዮጵያ አልሸባብን በመዋጋቱ ረገድ ያላትን ሚናም አድንቀዋል፡፡ ከዚህም ባለፈ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰላም ተልዕኮዎች ወታደሮቿን በማዋጣት ግንባር ቀደም በመሆኗ ምሥጋናቸውን ቸረዋል፡፡ በተመሳሳይም በደቡብ ሱዳን ሰላም ለማውረድ የኢትዮጵያ ሚና ወሳኝ መሆኑን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በማጠቃላያቸውም ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ጋር በሰብዓዊ መብት፣ በፖለቲካ ምኅዳሩና ሐሳብን በነፃነት በመግለጽ ጉዳዮች ዙሪያ ግልጽ ውይይት ማካሄዳቸውን ፕሬዚዳንት ኦባማ ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ መልካም አስተዳደርን በማስፈን፣ የሰብዓዊ መብትን በማስጠበቅና ዴሞክራሲን በማጠናከሩ ረገድ የገባችውን ቃል ታከብራለች ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአሜሪካ ጠንካራ አጋርና በቀጣናውም በተለያዩ ጉዳዮች መሪ የሆነች አገር ነች ብለው፣ ይህ የመሪነት ሚናዋ ዜጐቿን ተጠቃሚ ከማድረግም ባለፈ በአካባቢው ምሳሌ የምትሆን አገር እንድትሆን ያስችላታል ብለዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ ንግግራቸውን ሲያበቁ በአማርኛ ‹‹አመሰግናለሁ›› ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ ንግግራቸውን ካበቁ በኋላ በመንግሥትና በዋይት ሃውስ ለተመረጡ አራት ጋዜጠኞች የመጠየቅ ዕድል ተሰጥቷቸዋል፡፡ ምንም እንኳን በርካታ የአገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞች ጋዜጣዊ መግለጫውን ቢታደሙም፣ ቀድመው የተመረጡት እነዚሁ አራት ጋዜጠኞች ከጠየቁዋቸው ጥያቄዎች የተወሰኑት እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡
ጥያቄ– ኢትዮጵያና አሜሪካ ሽብርተኝነትን በመዋጋት በጋራ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን በአሜሪካና በኤርትራ ያሉ ቡድኖች የኢትዮጵያን ሰላም ያውካሉ፡፡ የእርስዎ መንግሥት ኢትዮጵያን በዚህ ጉዳይ ላይ እንዴት ሊረዳት ይችላል?
ፕሬዚዳንት ኦባማ፡– ይህ ጉዳይ በደኅንነት አንፃር ብቻ ሳይሆን በመልካም አስተዳደርና በሰብዓዊ መብት ጉዳዮችም በኩል በውይይታችን ተነስቷል፡፡ በፖሊሲያችን መሠረት ሽብርተኝነትን እንቃወማለን፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠን መንግሥት በኃይል ለመገልበጥ የሚንቀሳቀሱ ቡድኖችን እንቃወማለን፡፡
በደኅንነት ትብብር ዙሪያ ያለንን ግንኙነት ለማጐልበት ያለንን ፍላጐት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጫለሁ፡፡ ሽብርተኝነትን ለመደገፍ የሚንቀሳቀስ የውጭ ፋይናንስንም ለማቆም ፍሬያማ ውይይት አካሂደናል፡፡ በቀጣናው ያለን ትብብር አመርቂ ነው፡፡ ከኢትዮጵያ መንግሥት አንፃር አንዳንድ ቡድኖች ሥጋት መሆናቸውን አውቃለሁ፡፡ የእኛ የደኅንነት መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ እነዚህ ቡድኖች የሽብርተኝነት ጐራ ውስጥ አለመግባታቸውን ነው፡፡ ይህንንም ለማረጋገጥ የራሳችን መለኪያ አለን፡፡
ነገር ግን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳስታወቅኳቸው፣ በውይይታችንና የደኅንነት ትብብራችንን በማጠናከሩ ሒደት ትክክለኛ የሽብርተኝነት ሥጋት መኖሩን የምንመለከትና የምናጣራ ይሆናል፡፡ ስለዚህ የአንድ ቡድን ድርጊትን የምንተረጉምበት አካሄድ ሊተኮርበት ይገባል፡፡ እነዚህ ቡድኖች መንግሥትን የሚቃወሙ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሆኑ፣ ምንም እንኳን ከእነሱ ጋር ባንስማማም ለእነሱ ከለላ መስጠታችንን ግን አናቋርጥም፡፡ ይህ በአሜሪካ እውነት ነው፡፡ በሌላውም ቦታ እንደዚሁ ነው፡፡ ይህም ለዴሞክራሲ አስፈላጊ ነው፡፡ ነገር ግን መንግሥትን በኃይል ለመገልበጥ ከተንቀሳቀሱ፣ ያኔ ለእኛም ሥጋት ይሆናሉ፡፡
ጥያቄ፡- ስለሚዛናዊነት ልጠይቅዎት፡፡ በተደጋጋሚ መልካም አስተዳደር መሞገስ እንዳለበት ይናገራሉ፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ላይ የሚነሱ የሰብዓዊ መብት ችግሮችንና ከኢትዮጵያ ጋር በኢኮኖሚና በደኅንነት ዙሪያ ያላችሁን ትብብር ሚዛኑን እንዴት ያስጠብቁታል?
ፕሬዚዳንት ኦባማ፡- በመክፈቻ ንግግሬ እንደተናገርኩት፣ ይኼ ወሳኝ የውይይታችን ርዕስ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ በምን ዓይነት አስቸጋሪ ታሪክ እንዳለፈች እናውቃለን፡፡ በቅርቡ ነው ሕገ መንግሥቷ የወጣውና በዴሞክራሲያዊ መንገድ መንግሥት የተመረጠው፡፡ በኬንያም እንደገለጽኩት፣ ተጨማሪ ሥራዎች አሉ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በርካታ ሥራዎች እንደሚቀሩ የገለጹት የመጀመሪያው ሰው ናቸው፡፡
በዚህ ረገድ የምናስበው ከመንግሥታት ጋር መወያየት ነው፡፡ በቻይናና በሌሎች ሐሳብነት የመግለጽ መብት፣ የመሰብሰብ መብትና ሌሎች የዴሞክራሲ ሒደቶች ላይ ያሉንን ሥጋቶች በየጊዜው በመወያየት ለመፍታት እንጥራለን፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለኝን ምልከታ እንዳስታወቅኩት፣ ገዥው ፓርቲ ታዋቂ ነው፡፡ ነገር ግን የጋዜጠኞች፣ የሚዲያውና የተቃዋሚዎች ድምፅ እንዲሰማ ምኅዳሩን ማስፋት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ገዥው ፓርቲን ያጠናክራል እንጂ አይጐዳቸውም፡፡
ጥያቄ፡- ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በኢኮኖሚና በኢንቨስትመንት አመርቂ ውጤት ብታስመዘግብም፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በአገሪቱ መኖራቸው ይታወቃል፡፡ ይህ ደግሞ የዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ የምታደርጉትን ጥረት ሊያደናቅፍ ይችላል፡፡ ይህ ጉዳይ ያሳስብዎታልን? የሚያሳስብዎት ከሆነ ይህን ለመቀየር ምን እያደረጋችሁ ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፡- በአገራችን ያለው እውነታና በውጭ ያለው ግንዛቤ እንደማይጣጣም እናውቃለን፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድ መሥራት እንፈልጋለን፡፡ የእኛም ሥጋት ነው፡፡ አንድ ነገር ግን መረሳት የለበትም፡፡ ገና ታዳጊ ዴሞክራሲ ነው ያለን፡፡ ለምዕተ ዓመታት ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ሒደትንና ባህልን ያሳለፍን ነን፡፡ ስለዚህ በሁለት አሥርት ዓመታት ባለ የዴሞክራሲ ልምድ ይህን ችግር መቅረፍ ቀላል አይደለም፡፡
ነገር ግን በትክክለኛው መስመር ላይ ነን ብለን እናምናለን፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድ መሥራት አለብን፡፡ በመክፈቻ ንግግሬም እንደገለጽኩት፣ ከአሜሪካ የምንማራቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ እርግጥ ነው ድክመቶች እንዳሉብን እናውቃለን፡፡ አነዚህንም ድክመቶች ለመቅረፍ የበለጠ መሥራት አለብን፡፡
ጥያቄ፡- ሲፒጄ የተባለው ተቋም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጋዜጠኞችን በማሰር ሁለተኛ ደረጃ ላይ አስቀምጧታል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ እዚህ ከመምጣታቸው አስቀድሞ ታስረው ከነበሩ ጋዜጠኞች የተወሰኑትን ተለቀዋል፡፡ አሁንም ግን በርካታ የታሰሩ አሉ፡፡ ነፃ ፕሬስን አስመልክቶ ያለዎትን ተቃውሞ ሊያስረዱኝ ይችላሉን?
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም፡- ጋዜጠኞችን እንፈልጋለን፡፡ ምክንያቱም መጥፎ ታሪኮች ብቻ ሳይሆን ሊነገሩ የሚገባቸው ስኬታማ ታሪኮችም አሉን፡፡ ስለዚህ እንፈልጋችኋለን፡፡ ይህ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ነገር ግን ሥነ ምግባሩን ተከትለው የሚሠሩ ጋዜጠኞችን ነው በዚህ አገር እንዲኖሩ የምንፈልገው፡፡ በሁሉም ሥራዎቻችን የአቅም ማነስ እንዳለ እናውቃለን፡፡ በጋዜጠኝነት ዘርፍም ይህ ውሱንነት አለብን፡፡ በአደጉ አገሮች ያላችሁ እናንተ ጋዜጠኞች፣ የእኛን አገር ጋዜጠኞች ያላቸውን የሙያ ሥነ ምግባር ለማሳደግ ሥልጠና በመስጠት ልትረዱን ትችላላችሁ፡፡ እንደዚህች አገር መሪ ግን ጋዜጠኝነት መስመሩን ሲያልፍ ማየት አልፈልግም፡፡ ጋዜጠኞች ከአሸባሪዎች ጋር እንዲሠሩ በአሜሪካም ቢሆን እንኳን አይፈቀድም፡፡ ስለዚህ የዘመነ ጋዜጠኝነትን እንደ ባህልና ሙያ እንዲኖረን እንፈልጋለን፡፡