– በሁለት ክሶች ዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበታል
በወሰን ግጭት ምክንያት የሦስት ሕፃናት ወላጆችን በ20 እና በ11 ጥይቶች ደብድቦ መግደሉ በሰዎችና በሰነድ ማስረጃዎች የተረጋገጠበት የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት ፍርደኛ፣ ከማረሚያ ቤት በማምለጡ ተቋርጦ የነበረው ክስ እንዲቀጥል ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጠ፡፡
ፍርደኛው የመከላከያ ሠራዊት አባል እንደነበር የተገለፀው መቶ አለቃ ጌትዬ አለሜ ከማረሚያ ቤት ያመለጠው ሁለት ጊዜ ነው፡፡ መጀመሪያ ያመለጠው የሦስት ሕፃናት ወላጆች የሆኑትን አቶ ዳንኤል ነጋሽና ወ/ሮ ምስለ ማሞን በጥይት ደብድቦ ከገደላቸው ከሁለት ወራት የማረሚያ ቤት ቆይታ በኋላ ነበር፡፡ ፍርደኛው የካቲት 24 ቀን 2006 ዓ.ም. በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 03 ልዩ ቦታው መካኒሳ ጉልት ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ፣ ሁለቱንም የሕፃናቱን ወላጆች በድንበር ግጭት ምክንያት መግደሉን መዘገባችን ይታወሳል፡፡
በግለሰቡ የግድያ ድርጊት ምክንያት የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ሦስት ክሶችን መሥርቶበታል፡፡ አቶ ዳንኤል ነጋሽን በ20 ጥይቶች ደብድቦ በመግደል፣ ወ/ሮ ምስለ ማሞን በ11 ጥይት ደብድቦ በመግደልና ሕገወጥ የጦር መሣሪያ (አንድ ተሽከርካሪ ኮልት ሽጉጥ፣ የተፈታታ ማካሮቭ ሽጉጥ፣ የጦር ሜዳ መነጽር፣ 46 ጥይቶችና ባዶ የክላሽ ካርታዎች) ይዞ መገኘት ወንጀሎች ክሶች ተመሥርተውበታል፡፡
ከሳሽ ዓቃቤ ሕግ የሰውና የሰነድ ማስረጃዎችን አሰምቶ ፍርደኛው ድርጊቱን መፈጸሙን በማረጋገጡ በከባድ የሰው መግደል ወንጀል (ሁለቱን ግለሰቦች) በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ሚያዝያ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት ፍርድ ሰጥቶ ነበር፡፡ ፍርደኛው በድጋሚ በማምለጡ ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ይዞ በመገኘቱ የተመሠረተበት ክስ ተቋርጦ የነበረ ቢሆንም፣ የተገኘ መሆኑን ጠቅሶ ዓቃቤ ሕግ ክሱ እንዲንቀሳቀስለት ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሦስተኛ ወንጀል ችሎት በማመልከቱ፣ ክሱ እንዲቀጥል ፍርድ ቤቱ አዟል፡፡ ለሐምሌ 24 ቀን 2007 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮም ሰጥቷል፡፡