Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቀድሞ ከፍተኛ አንድ ሊቀመንበር በ‹‹ኢሕአፓ እና ስፖርት›› መጽሐፍ ደራሲ ላይ ክስ መሠረቱ

የቀድሞ ከፍተኛ አንድ ሊቀመንበር በ‹‹ኢሕአፓ እና ስፖርት›› መጽሐፍ ደራሲ ላይ ክስ መሠረቱ

ቀን:

በደርግ ዘመን በቀይ ሽብር ወቅት የከፍተኛ አንድ ሊቀመንበር የነበሩት አቶ እርገጤ መድበው፣ በ‹‹ኢሕአፓ እና ስፖርት›› መጽሐፍ ደራሲ አቶ ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ላይ የስም ማጥፋት ወንጀል ክስ መሠረቱ፡፡ ከሳሽ አቶ እርገጤ በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ አራዳ ምድብ ችሎት በመሠረቱት ክስ ተከሳሽ የመጽሐፉ ደራሲ አቶ ገነነ የሌላ ሰውን ከብር ወይም ስም ለመጉዳት በማሰብ፣ ‹‹ኢሕአፓ እና ስፖርት እውነተኛ ታሪክ›› የተባለ መጽሐፍ በማሳተምና በማሰራጨት፣ የተከሳሽን ስም የሚያጠፋና መልካም ስም የሚያጐድፍ ድርጊት እንደፈጸመባቸው አመልክተዋል፡፡

ሐምሌ 16 ቀን 2007 በችሎት የተገኙት አቶ ገነነ በቀረበበት ክስ የሁለት ሺሕ ብር የገንዘብ ዋስትና በማቅረብ፣ ሐምሌ 30 ቀን 2007 ዓ.ም. ምላሽ ለመስጠት የክስ መዝገቡ ተቀጥሯል፡፡

አቶ እርገጤ በወንጀለኛ መቅጫ ሕጉ አንቀጽ 212 በልዩ ሁኔታ የሚፈቅደውን የግል አቤቱታ፣ ወይም ክስ የማቅረብ መብት በመጠቀም ነው አቶ ገነነ ላይ ክስ የመሠረቱት፡፡

ተከሳሽ በመጽሐፉ፣ ‹‹አቶ እርገጤ መድበው በ1969 ዓ.ም. ቀኑና ወሩ ባልተገለጸበት ጊዜ አንድነትና ቴዎድሮስ የሚባሉ የስፖርት ቡድኖችን አቋቁሞ፣ ከከርቸሌ እስር ቤት እስረኞችን በማስወጣት አዲስ አበባ ስታዲየም አጫውቷል፤›› የሚል ከእውነት የራቀ ሐሰተኛ ጽሑፍ በመጻፍ ስማቸውን ማጥፋታቸውን አቶ እርገጤ ለፍርድ ቤቱ ያስገቡት የክስ ማመልከቻ ያስረዳል፡፡

በተጨማሪም ‹‹አቶ እርገጤ መድበው በሥልጣኑ ገደብ የለውም፣ አምባገነን ነው፣ የሚያስፈራ ነው በማለት ስምን ለማጥፋት በማቀድ የፈጠራ ወሬ በማቅረብ የህሊና ጉዳት ስም የማጥፋት ወንጀል በመፈጸሙና የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 በመተላለፍ እንዲጠየቁ፤›› በማለት በግል ክስ አቅራቢነት የመሠረቱት ክስ ያስረዳል፡፡

ከሳሽ አቶ እርገጤ ላቀረቡት የወንጀል ክስ በምስክርነት የጠሯቸው በደርግ ዘመን የአዲስ አበባ ከተማ አጠቃላይ ምክር ቤት ሊቀመንበርና ከንቲባ የነበሩት ዶ/ር ዓለሙ አበበ፣ በወቅቱ የከፍተኛ 10 ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ፈቃዱ ባህሩ፣ በወቅቱ የከፍተኛ 8 ሊቀመንበር የነበሩት አቶ ዓለማየሁ ዴኬሮ ይገኙበታል፡፡

አቶ እርገጤ መድበው የከፍተኛ አንድ ሊቀመንበር በነበሩበት ወቅት በቀይ ሽብር በተፈጸሙ ወንጀሎች ምክንያት በቁጥጥር ሥር ውለው ከተከሰሱ በኋላ፣ እስራት ተፈርዶባቸው መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡

አቶ ገነነው መኩሪያ (ሊብሮ) በእግር ኳስ ተጫዋችነት ለሜታ ቢራና ለሸዋ ምርጥ ክለቦች የተጫወተ ሲሆን፣ ሊብሮ በሚል መጠሪያ ይታተም የነበረው የስፖርት ጋዜጣ ባለቤት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በብሥራት ኤፍኤም 101.1 የሬዲዮ ጣቢያ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ያዘጋጃል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...