Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅ‹‹. . . እኛም በኩሽኔታ›› ስድስት ኪሎ አንበሳ ግቢ አካባቢ

‹‹. . . እኛም በኩሽኔታ›› ስድስት ኪሎ አንበሳ ግቢ አካባቢ

ቀን:

ፎቶ ከድረ ገጽ

በል ንፈስ በል ንፈስ አንተ ሞገደኛ የክረምት ወጨፎ

በል ንፈስ፤ በል ንፈስ፤ አንተ ሞገደኛ፤ የክረምት ወጨፎ

ምንም እንኳን ባትሆን የዚያን ያህል ክፉ

ምስጋና እንደካደ እንደሰው ልጅ ጥፉ፡

እስተዚህም ባይሆን የጥርስህ ስለቱ፤

ሆኖም ብትሰወር ምንም በትታይ፤

ስትንፋስህ ጭምር ባልጎ የለም ወይ፡፡

ሆያ ሆዬ በሉ! ሆያ ሆዬ በሉ!

ለዛፍ ለቅጠሉ፣

የሸፍጥ ከሆነ አብዛኛው ሽርክና፤

አብዛኛው ፍቅርም ተራ ድንቁርና፤

ለዛፍ ለቅጠሉ፤ ሆያ ሆዬ በሏ!

የዚች ዓለም ኑሮ፤ አቤት መጣፈጧ፤

ከዊሊያም ሼክስፒር/ ስድ ትርጉም በዳዊት ዘኪሮስ

*************

 

‹‹ማንም ቢሆን ዕድሜ ልኩን ፕሬዚዳንት ሊሆን አይችልም››

ኢትዮጵያን ለሁለት ቀናት የጎበኙት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሐምሌ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት አዳራሽ ተገኝተው ከተናገሩት ውስጥ የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡

 • ‹‹አፍሪካ የሰው ዘር መገኛና በዓለም ከሚገኙ አህጉራት በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የምትገኝ ናት፡፡››
 • ‹‹አንድ መሪ በሥልጣን ለመቆየት ብሎ በሥልጣን ላይ እያለ ሕጐችን ሲቀይር የአገሩን መረጋጋትና ተግባብቶ መኖር አደጋ ላይ ይጥላል፤ እንደ ብሩንዲ፡፡››
 • ‹‹ሰዎች ለምን በሥልጣን ረዥም ጊዜ መቆየት እነደሚፈልጉ አይገባኝም፡፡ በተለይ ብዙ ሀብት እያላቸው፡፡››
 • ‹‹ማንም ቢሆን ዕድሜ ልኩን ፕሬዚዳንት ሊሆን አይችልም፡፡ እኔ ሁለተኛ የሥልጣን ዘመኔ ነው፡፡ በእኛ ሕገ መንግሥት መሠረት ድጋሚ መወዳደር አልችልም፡፡ አሜሪካን ወደፊት ለማራመድ እኔም ብዙ መሥራት እፈልጋለሁ፡፡ ሆኖም ሕግ ሕግ ነው፡፡ እናም ማንም ከሕግ በላይ ሊሆን አይችልም፡፡ ፕሬዚዳንትም ቢሆን፡፡››
 • ‹‹የሰዎች መብት እስካልተከበረ ድረስ ሕዝቦች ነፃነትን ሊያጣጥሙ አይችሉም፡፡››
 • ‹‹ጋዜጠኞች ሥራቸውን በመሥራታቸው የሚታሠሩ ከሆነ፣ መንግሥት ሲቪል ሶሳይቲውን ሲያሽመደምድ አክቲቪስቶች አደጋ ላይ የሚወድቁ ከሆነ ዴሞክራሲ በስሙ ሊኖር ይችላል፡፡ ሆኖም ዴሞክራሲ በተግባር የለም፡፡››
 • ‹‹በአፍሪካ የሙስና ካንሰር እስካልጠፋ ድረስ ማንም ቢሆን የአህጉሪቷን እምቅ የኢኮኖሚ አቅም የተቆለፈበትን ቁልፍ ሊፈታ አይችልም፡፡ በአህጉሪቷ የተንሰራፋውን ሙስና ሊያጠፉ የሚችሉት አፍሪካውያን ብቻ ናቸው፡፡››
 • ‹‹የአፍሪካ መንግሥታት ችግራቸውን ለመፍታት መሥራት ሲጀምሩ፣ አሜሪካም ከጐናቸው ትቆማለች፡፡››
 • ‹‹የአፍሪካ ዕድገት በአፍሪካ ሰላምና ደኅንነት ላይ የሚመሠረት ነው፡፡ አፍሪካ ሽብርና ግጭትን ለማጥፋት ስትቆም፣ ዩናይትድ ስቴትስ ከእናንተ ጐን እንደምትቆም ላረጋግጥላችሁ እወዳለሁ››

**************

የሰዓት ገደብ የተጣለባቸው የአውስትራሊያ ድመቶች

የአውስትራሊያ የድመት ባለቤቶች ድመቶቻቸውን በቤት ውስጥ ብቻ እንዲያስቀምጡ ገደብ ተጣለ፡፡ በአውስትራሊያ አንዳንድ ከተሞችም ገደቡ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡

ዘ ሰንዴይ ሞርኒንግ ሄራልድ እንደዘገበው፣ መንግሥት ድመቶች 24 ሰዓት ሙሉ ከቤት እንዳይወጡ ገደብ የጣለው በአገሪቷ የሚገኙ ብርቅዬ ፍጥረታትን እያጠቁና እያጠፉ በመምጣታቸው ነው፡፡

በአውስትራሊያ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ ድመቶች በቀን 75 ሚሊዮን የሚጠጉ እንስሳትን ይገድላሉ፡፡ ተብሎ ይገመታል፡፡ አገሪቷም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ብርቅዬ እንስሳቷን አጥታለች፡፡ አውሮፓውያን ወደ አውስትራሊያ መግባት ከጀመሩበት ካለፉት 200 ዓመታት ወዲህም 29 አጥቢ ብርቅዬ እንስሳቷን አውስትራሊያ አጥታለች፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከአውሮፓውያን ጋር አብረው ወደ አውስትራሊያ የገቡ ድመቶች ናቸው፡፡

የአውስትራሊያ መንግሥት ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑ ድመቶችን ለመግደልም ያቀደ ሲሆን፣ ዕቅዱ በእንስሳት መብት ተሟጋቾች ተቃውሞ ገጥሞታል፡፡

*********

‹‹አባትህ  መሃላ ተላልፎ ባንተ ላይ ደርሶብህ ይሆናል››

ነብርና ድኩላ በአንድ ጫካ ውስጥ አብረው እየኖሩ ሣለ ነብሩ ድኩላውን ለማደን ቢሞክርም አልቻለም፡፡

እናም አንድ ቀን ነብሩ ድኩላውን ጠርቶ እንዲህ አለው፡- ‹‹ጓደኛዬ ድኩላ ሆይ፣ እኔን ለምን ትሸሸኛለህ? ባልንጀሮች መሆን እንችላለን፡፡ አንተ የምትበላውን እኔ አልበላም፡፡ የሚያጣለን ምንም ነገር የለም፡፡ አሁን ከእንግዲህ ወዲህ አንተም በህይወትህ ሁሉ እኔን እንዳትፈራኝና እኔም ጓደኛ ልሆንህ እንማማል፡፡››

ድኩላውም በዚህ ተስማምቶ ድኩላው ዛፍ ስር፣ ነብሩ ደግሞ ዛፉ ላይ ይተኛሉ፡፡

ከዚያ በፊት ግን ድኩላው ‹‹መሃላው ምን መሆን አለበት?›› ብሎ ጠይቆ ነበር፡፡

ነብሩም ‹‹አንደኛችን ይህንን መሃላ ብንተላለፍ የወለድነውን ልጅ እግዚአብሔር ይገድለዋል፡፡›› ብሎ መልሶለታል፡፡

በዚህም ተስማምተው ድኩላውም ነብሩን ሳይፈራ ኖሮ መወፈርና ነብሩን ማጓጓት ጀመረ፡፡ ነብሩም ወፍራሙን ድኩላ ባየ ጊዜ ጉጉት አደረበት፡፡ መሃላውንም በመስበር ድኩላውን ሊሰለቅጠው ፈለገ፡፡

ነብሩም እንዲህ አለ ‹‹የፈለገው ይምጣ እንጂ ስለመሃላው ግድ የለኝም፡፡ ልጄ እንጂ እኔ አልሞት! ልጅ ደግሞ የለኝም፡፡›› ብሎ አሰበ፡፡

እናም ነብሩ ድኩላውን ለመያዝ ከዛፉ ዘሎ ሊወርድ ሲሞክር ከዛፉ ቅርንጫፍ ውስጥ ስለተወሸቀ ቅርንጫፉ ሆዱን ወግቶ ይዞ አንጠለጠለው፡፡ ሊሞትም ተቃረበ፡፡

ድኩላውም ዘሎ በመነሣት ‹‹ቢአአ፣ ቢአአ›› እያለ ነብሩ ላይ ጮኸበት፡፡

ነብሩም እያጣጣረ ‹‹ምነው ጓደኛዬ እንደዚህ ሆኜ እያየህ ጥለኸኝ ልትሄድ ነው? መሃላውን ከተላለፍን ልጃችን ይሞታል ብለን ተስማምተን አልነበረም?›› አለው፡፡

ድኩላውም ‹‹ምናልባት አባትህ ይህንን ዓይነት መሃላ ተላልፎ ባንተ ላይ ደርሶብህ ይሆናል፤›› አለው ይባላል፡፡

 • በመጋቢ እንየው ገሰሰ የተተረከ የአማራ ተረት (ከኢትዮጵያ ተረቶች ገጽ)

*****

የ79 ዓመቱ ሰማዕት አቡነ ጴጥሮስ

አቡነ ጴጥሮስ፦ የመጣሁበትን ሳልፈጽም ወደኋላ አልመለስም፤ ብችል ጠላት በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ያለውን ግፍ በቅርብ ርቀት ሆኖ የሚመለከተውን ሕዝብ በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሣ አደርገዋለሁ፤ ካልሆነ ደግሞ እዚሁ እሞታለሁ።

አንዱ “ሶላቶ የኢጣሊያን ገናናነት አምነው የቪክቶር አማኑኤልንና የሙሶሎኒን ገዢነት ተቀብለው በሃይማኖቶ ይስበኩ፤ እኛም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሪነትን ፣ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ሊሬና የተንጣለለ መኖሪያ እንሰጦታለን።

አቡነ ጴጥሮስ፦ የኢጣሊያን ገናናነት እንዳምን የአማኑኤልንና ሙሶሎኒን ገዢነት እንድቀበል ነው የፈለጋችሁት?

ሶላቶዎች በትክክል! ማመን ብቻ በቂ ነው። ከዚያ ሥልጣኑ ፣ ገንዘ…

አቡነ ጴጥሮስ፦ በቃችሁ… በቃችሁ… ይህች ክብሯን የደፈራችኋት አገር ለመሆኑ ‘መኳንንት ከግብፅ ይወጣሉ፣ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪ ትዘረጋለች’ የተባለላት ቅድስት ሀገር መሆኗን ታውቃላችሁ? ይህች የቆማችሁባት ምድር ለእብሪተኞች ረመጥ፣ እንደ እሳት የምታቃጥል መሆኗን ብታውቁ ምን ያህል በኀዘን ጥርሳችሁ እየተፋጨ በተንገጫገጨ ነበር፣ ግን ግብዝ ሆናችኋል በኃይላችሁ ተማምናችኋል። እኔ የምፈራው የሰው ሰይፍ አይደለም…. የእናንተ ጉልበት የእናንተ እብሪት ትንሽ ጉም ነው፣ ትንሽ ነፋስ የሚበትነው…… እና የፋሽስት ኢጣልያንን የበላይነት ከምቀበል ሞቴን እመርጣለሁ። ወደ እግዚአብሔር እጆቿን የዘረጋችውን ቅድስት ሀገሬን እብሪተኛ ሲደቀድቃት እንዲኖር አልፈቅድም፤ እምነቴም ይህንን ፍጹም አይፈቅድልኝም። እናንተ የኢጣልያን ገዢነት የተቀበላችሁ ሁሉ አወግዛችኋለሁ፣ የኢጣልያን ገዢነት ከተቀበለ እንኳን ሰው ምድሯ የተረገመች ትሁን!!!

ፋሽስት ዳኛ፦ ካህናቱም ሆነ የቤተ ክህነት ባልሥልጣኖች ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የኢጣልያንን መንግሥት ገዢነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመፁ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?

አቡነ ጴጥሮስ፦ አቡነ ቄርሎስ ግብፃዊ ናቸው፣ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ ……. እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፤ ግን ተከታዮቼን አትንኩ።
[ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም. ጡሩንባ ተነፍቶ በግድ የተሰበሰበው ሕዝብ ፊት አቡኑ የሕዝብ አባትነት አደራቸውን ሳይዘነጉ ከጠዋቱ አራት ሰዓት ግድያው ከሚፈጸምበት ቦታ አራዳ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በታች ከአትክልት ተራ ፊት ካለው ጉብታ ላይ...]
የፋሽስት መልእክተኛ፦ ዐይንዎን በጥቁር ጨርቅ እንዲሸፈኑ ይፈልጋሉ?

አቡነ ጴጥሮስ፦ እናንተ እንደፈለጋችሁ አድርጉት፤ እንደ እኔ ምርጫ ግን የወራሪን ፣ የእብሪተኛን ሞት ፊት ለፊት ገጥሜ ድል አድርጌ መሞት ስለምፈልግ ባትሸፍኑኝ ደስ ይለኛል።

[ጳጳሱ ፊታቸውን ወደ ምዕራብ እንዳዞሩ ስምንት ወታደሮች የመሣሪያቸውን አፈሙዝ ጳጳሱ ላይ አነጣጠሩ… ሕዝቡ አጉረመረመ፤ ሰማዩም እኩል አጉረመረመ። ኮማንደሩ “ተኩስ” የሚል ትእዛዝ ሲሰጥ የግፍ ቃታዎች ተሳቡ… ሥልጡን ነን ፣ ሰብአውያን ነን የሚሉ ነጮች አረመኔያዊ ድርጊት ፈጸሙ። በስምንት ጥይቶች ተደበደቡ…. ከአንገታቸው በታች ሰውነታቸው ተበሳሳ። አቡነ ጴጥሮስ ስለ ነጻነት ራሳቸውን ሰጡ። ይሁን እንጂ ለአመኑበት ውሳኔ ሕይወታቸውን የሰጡት ጳጳስ ቢወድቁም ሰውነታቸው በጥይት ቢበሳሳም ነፍሳቸው አልወጣችም ነበር። ኮማንደሩ ሽጉጡን ከክሳዱ በመምዘዝ በሦስት ጥይት ጭንቅላታቸውን መታቸው፤ ያኔ ሕይወታቸው አለፈች። አቡነ ጴጥሮስ እሚያፈቅሩት የኢትዮጵያ አፈር ላይ ዝርግፍ ብለው ወደቁ። የኢትዮጵያ መወረር የእሳት አሎሎ ሆኖ ሲቃጠል የነበረ አንጀታቸው ተሰብስቦ ተኛ።]

 • ፍጹም ወልደማርያም ‹‹ያልተዘመረላቸው›› (2005 ዓ.ም.)

 

 

 

 

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...