Saturday, June 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የመዛግብት ሙያ ትኩረት የሚያሻው የልማት አጀንዳ

በታገል ፍቅረ ማርያም

በዓለማችን ያሉ የመዛግብት ሙያተኞችና የሙያው ደጋፊዎች ሰኔ ፱ ቀን በጋራ ድምፃቸውን በማሰማትና ስለመዛግብት ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በአንድ ላይ በመሰብሰብ ግንዛቤ በመፍጠር በዓሉን ያከብራሉ፡፡ ዓለም አቀፍ የመዛግብት ካውንስል (ICA) እ.ኤ.አ. ከ1948 ጀምሮ ሰኔ ፱ የመዛግብት ቀንን ሲያከብር ቆይቶ፣ የተባበሩት መንግሥታ ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2004 ዓ.ም. በቬና በአደረገው ዓለም አቀፍ ስብሰባ 2,000 የጉባዔው አባላት በተሰበሰቡበት የመዛግብት ቀን እንዲከበር የጋራ መግባባት ላይ ደርሰዋል፡፡ ዩኔስኮ በፓሪስ ከተማ ባካሄደው 33ኛው አጠቃላይ ስብሰባ ላይ ጥቅምት 27 እ.ኤ.አ. የቀረፃ ድምፅና ምሥል መዛግብት ቀን ሆኖ እንዲከበር ወስኗል፡፡ ይህም የቀረፃ ድምፅና ምሥል በአግባቡ ተጠብቆ ለትውልድ እንዲተላለፍ  ግንዛቤ ለመፍጠር ለጥበቃና እንክብካቤ ያለው አስተዋጽኦ ትልቅ ግምት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በአገራችንም ሰኔ 23 ቀን 2007 ዓ.ም የመዛግብት ቀን ለመጀመሪያ ጊዜ በድምቀት ተከብሯል፡፡ ይህም በሙያው ለውጥ ለማምጣት መነሻ ነጥብ ነው፡፡

የመዛግብት ቀንን ማክበር ያለው ጠቀሜታ

በዓለም አቀፍ ደረጃ የመዛግብት ቀን  አከባበር  የደበዘዘና የቀዘቀዘ ገጽታ ያለው ዓመታዊ ቀን ነው፡፡ በአገራችን ያለውን እውነታም ስናጤን ስለሪከርዶችና ስለመዛግብት ያለን ግንዛቤ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የመዛግብትን ቀንን ስናከብር የሚከተሉት ጠቀሜታዎች እንዳሉት ግልጽ ነው፡፡

  • ስለሪከርዶች አፈጣጠርና አጠባበቅ ማኅበረሰቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ማድረግ፣
  • ፖሊሲ አውጪዎችና ከፍተኛ የመንግሥት አካላት ሪከርድን ለመልካም አስተዳደርና ለልማት እንዲያውሉት ለማስቻል፣
  • ግለሰቦች፣ መንግሥታዊ ድርጅቶችና የግል ድርጅቶች ስለመዛግብት ጠቀሜታ ግንዛቤ እንዲኖራቸው ለማድረግ፣
  • የትም ቦታ የሚገኙ ዶክመንቶች በመዛግብት ማዕከላት እንዲጠበቁ ለማድረግ የታለመ ነው፡፡

የመዛግብት ባለሙያዎች እነማን ናቸው?

የመዛግብት ባለሙያዎች ሪከርዶች ለቀጣይ ትውልድ ተጠብቀው እንዲቆዩ መዛግብትን በማደራጀት፣ የጠበቁትንም ትርጉም በሚሰጥ መንገድ እየተደራጁ ለአገልግሎት እንዲውሉና ለታሪክ ምሁራንም ሆነ  መረጃ ለሚፈልግ የኅብረተሰብ አካል መዛግብትን እንዲጠቀሙባቸው የማድረግ ኃይል አላቸው፡፡ የመዛግብት ባለሙያዎች በተጠያቂነት፣ በፍትሐዊነት፣ በታማኘነት፣ በግልጽነት መዛግብትን የሚያደራጁ፣ የፖለቲካ አመለካከቶቻቸው ለማንም የማይወግንና ሙያው በሚፈልገው የሥነ ምግባር ደንብ መሠረት ሥራቸውን የሚሠሩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡

እ.ኤ.አ. በ2006 የአሜሪካ የመዛግብት ማኅበረሰብ (The Society of American Archivist) ባዘጋጀው ዓመታዊ ስብሰባ በቀረበው ጥናት የምርምር ጸሐፊው ጀመርሰን ራንድል ስለመዛግብት ጠቀሜታ ሲገልጹ፣ ‹‹በሕይወቴ ስለመዛግብት ሳስብ የማልረሳው ነገር የ65 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ ወደ መዛግብት ማዕከሉ መጥተው የሚኖሩበትን የሐርትፎርድ ከተማ የመራጮች የምዝገባ ሪከርድ ጠይቀውኛል፡፡ ይኼም በምርጫው ወቅት ያስመዘገቡትን ዕድሜ ጡረታ ከወጡበት ቀን ጋር ለማገናዘብ ነው፡፡ እንግዲህ የመዛግብት ጠቀሜታ በታሪካዊ ሰነድነት ባለፈ የዜጎችን መብትና ጥቅም የሚያስጠብቅ ከሊቅ እሰከ ደቂቅ ከባለጠጎች እስከ ዝቅተኛ ሀብት ያላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች መዛግብት ያለው ጠቀሜታ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ አንድ ሰው ለምን የመዛግብት ባለሙያ ሆንክ? ብሎ ቢጠይቀኝ ምላሼ ግልጽ ነው፡፡ የጥንቱን ቅርስ ጠብቄ ለትውልድ ለማቆየት፣ የዜጎችን መብት ለማስጠበቅ አፌን ሞልቼ እላቸዋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

 የታሪክ ምሁራን የመዛግብት ባለሙያዎች መሆን ይችላሉ?

ይህንን ጥያቄ ከመመለሴ በፊት በአውሮፓ በታሪክ ትምህርት በፒኤችዲ የትምህርት ዘርፍ በማስተማር ላይ ያለውን ምሁር ምላሽ እንስማ፡፡ ምሁሩ ለበርካታ ዓመታት በታሪክ የትምህርት ክፍል በማስተማር በጥናትና ምርምር አሳልፏል፡፡ ምሁሩ የመዛግብት ባለሙያ ለመሆን ሕልሙን ለማሳካት በመዛግብት አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪውን ለመማር ቢፈልግም ከማስተማሩ ጋር ሊሄድለት አልቻለም፡፡ ምሁሩ የጠየቀው ጥያቄ ባለኝ የታሪክ ዕውቀት የመዛግብት ባለሙያ መሆን እችላለሁ? የሚል ነው፡፡

የታሪክ ተመራማሪው ገለጻ፣ ‹‹እንደ ታሪክ ባለሙያነቴ ራሴን እንደ መዛግብት ባለሙያ መቁጠር አልችልም፡፡ የመዛግብት ባለሙያ ነኝም ብዬ አላምንም፡፡ እንደዚህ ማሰቤም ትክክል አይደለሁም፡፡ በመዛግብት ለታሪክ የሚሆኑ ነገሮችን ማንብብ እችላለሁ፡፡  ሆኖም መዛግብቱን ግን ለማደራጀት አልችልም፡፡ በእርግጥ ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ቤተ መጻሕፍት በማነብበት ወቅትም ሆነ ለሥራ በምሰበሰብበት ወቅት፣ በመዛግብት ማደራጀት ያለኝ ድርሻ ዝቅተኛ ነው፡፡ እንደተረዳሁት መዛግብትን ለማደራጀት የማበረክተው አስተዋጽኦ የለም፡፡ የመዛግብት ባለሙያዎች እንዳሉት  ታሪክን ማወቅ ብቻ የመዛግብት ባለሙያ አያደርግም ስለዚህ እኔ የታሪክ ባለሙያ ነኝ የመዛግብት ባለሙያ ግን አይደለሁም፤›› የሚል ነው፡፡

ከልምዴ የምነግራችሁ ነገር ቢኖር በአውሮፓ ውስጥ ከሚገኝ ትልቅ የጥናትና ምርምር ቤተ መጻሕፍት በውስጡም በርካታ የመዛግብት ክምችት ከሚገኝበት ቤተ መዛግብት በምሠራበት ጊዜ፣ በመዛግብት ባለሙያዎችና በታሪክ ባለሙያዎች ትልቅ ልዩነት መኖሩን ተገንዝቤያለሁ፡፡ የታሪክ ባለሙያዎች አንድም የታሪክ ማስረጃ እንዳይጠፋ ድርሻቸው ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ የታሪክ ምሁራን የሪከርዶች ምዘና ዝውውርና አወጋገድ ላይ ታሪካዊ ፋይዳ ያላቸውን ሪከርዶች ለመምረጥ በሚሠራው ሥራ፣ ጥናትና ምርምር በማድረግ ሪከርዶች በሚመዘኑበት ወቅት የታሪክ ምሁሩ ድርሻ የትየለሌ ነው፡፡

የቤተ መጻሕፍትና የመዛግብት ባለሙያዎች የመረጃ ሀብቶችን በማሰባሰብ፣ በማደራጅት ለጥናትና ምርምር እንዲውሉ ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ ነው፡፡ የታሪክ ባለሙያው ታሪካዊ መዛግብትን ከመምረጥ አንፃር የተለየ ድርሻ አለው፡፡

እኚሁ ጸሐፊ ዶክተር ሲሎ እንደጻፉት የፒኤችዲ ትምህርታቸውን በመዛግብት ሙያ ለመቀጠል እንደተገነዘቡት፣ የቤተ መጻሕፍት ሙያ ሳይንስና የመዛግብት ሙያ ከታሪክ ትምህርት የቀለለ የትምህርት ዘርፍ አድርጋችሁ አትቁጠሩ፡፡ ሁሉም ሙያ የራሱ ዕውቀትና ክህሎት ይጠይቃል፡፡ የቤተ መጻሕፍት ሙያ ሳይንስና የታሪክ ትምህርት የመዛግብት ሙያን ለመቀጠል አስፈላጊ የትምህርት ዘርፍ ናቸው ብለው ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

እንግዲህ ከላይ ለዚህ ጽሑፍ መነሻ ላደረኩት ሐሳብ የታሪክ ምሁራን የመዛግብት ባለሙያዎች መሆን ይችላሉ? ለሚለው ጥያቄ መልሱ ቀላል ነው፡፡ በመዛግብት ሙያ ከተማሩ የመዛግብት ባለሙያ መሆን ይችላሉ፡፡ ካልተማሩ ግን የታሪክ ባለሙያዎች እንጂ የመዛግብት ባለሙያዎቸ አይደሉም፡፡ ለጽሑፌም ያነሳሳኝ ምክንያት የሪከርድ ማዕከላት (መዝገብ ቤቶች)  ክፍት የሥራ ቦታ Anchorማስታወቂዎች ሲወጡ ተፈላጊ ችሎታ የታሪክ ትምህርት ብለው ያወጣሉ፡፡ አግባብነት ያለው ሙያ አይደለም፡፡ እንደ እነዚህ ዓይነት ስህተቶችን ማረም ይገባናል፡፡ ምንም ዓይነት ሳይንሳዊ መነሻም የላቸውም፡፡

በአገራችን ኢትዮጵያ የመዛግብት ሙያተኞች ስለሌሉን ምናልባት በየጊዜው እንደሚወራው በአገራችን ሁለት ባለሙያዎቸ ነበሩን የሚለውን ጉንጭ አልፋ ወሬን ትተን፣ ለዘርፉ የሠለጠነ የሰው ኃይል ከዩኒቨርስቲዎቻችን አብራክ ሊፈጠር ይገባል፡፡ የመዛግብት ሙያ ዘርፍም ችላ ሊባል አይገባም፡፡

በአገራችን መዛግብትን የሰበሰቡ ሊቃውንት አባቶችና እናቶች፣ ግለሰቦች የታሪክ አካል የሆኑ ሰዎች ምሥጋና ይድረሳቸውና ጥቂት የማይባሉ መዛግብት በአገራችንም በአግባቡ ተጠብቀው ለቀጣይ ትውልድ ለማቆየት እየተሠራ ቢሆንም፣ ፕሮፌሽናል የመዛግብት ባለሙያ ያለመኖር በዚህ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ሊታሰብ ይገባል፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

                        

 

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles