Monday, June 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የካይዘን የሥራ አመራር ጥበብን በየቦታው መዝራት አይቻልም

በሒሩት ደበበ

ካይዘን የተባለው የጃፓኖች የሥራ አመራር ጥበብ በአገራችን ተግባራዊ መደረግ ከጀመረ ከራርሟል፡፡ ራሱን ችሎ መሥሪያ ቤት ተቋቁሞለት ባለሙያና የሥራ ኃላፊ አግኝቶ፣ በተለይ ስኳር ፋብሪካዎችን በመሳሰሉ ድርጅቶች ላይ አንዳንድ ምልክቶችን እንዳሰየመ ይናገራል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ በየአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቱ ሁሉ ‹‹የካይዘን ሥልጠና›› የሚል መደነቃቀፍ በመመልከቴ ነው ጉዳዩን ርዕስ አድርጌ የተነሳሁት፡፡

ጃፓን እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ አጋማሽ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፍፃሜ በኋላ የገጠሟትን የጥራትና የምርታማነት ችግሮችን ለመፍታት የካይዘን አመራር ፍልስፍናን መጠቀሟ ይነገራል፡፡ ይህን ጥበብ በጥብቅ ዲሲፕሊን በመተግበሯም በዓለም ጠንካራና ተወዳዳሪ ኢኮኖሚ ለመፍጠር ችላለች፡፡ የካይዘን ፍልስፍናን በተሟላ መንገድ ተንትነው እንደጻፉት የሚነገርላቸው ማስኪ ኢሚይ የተባሉት ምሁር “The Key to Japan’s Competitive Success” በሚለው ሥራቸው ነው፡፡

እንደ ጃፓን፣ ቻይናና ታይዋን ከመሳሰሉ አገሮች በርካታ ልምዶችን እየቀሰሙ እንደሆነ የሚናገረው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ካይዘን› የተባለውን አንድ የአሠራር ዘዴ አጥንቶ ሥራ ላይ ለማዋል መሞከሩ ተገቢ ነው፡፡ ይልቁንም ጥረቱ ያስመሰግነው ይሆናል፡፡ ካይዘን ለምን? እንዴት? መቼ? የት? በእነማን? ለማን? የሚሉ ጥያቄዎችን መመለስ ካልተቻለ ግን ችግር ነው፡፡

እስካሁን ባለፉት 25 ዓመታት በተለይም በቅርቦቹ 13 ዓመታት ያልተጠኑ የሥራ አመራር ዘዴዎች የሉም፡፡ የለውጥ ሥራ አመራር፣ መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ፣ የተመጣጠነ የውጤት ተኮር የምዘና ሥርዓት፣ የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያ፣ የሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ መርሐ ግብር፣ አሁን ደግሞ የለውጥ ሠራዊት ግንባታ (Developmental Army) የሚባሉትን የአሠራር ሥልቶች ለአብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡ እነዚህ ሁሉ የሥራ አመራር መሣሪያዎች (Tools) በሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ እንዲተገበሩ በመሞከራቸው ምን ዓይነት ለውጥ መጣ ማለት ግን ተገቢ ነው፡፡ በመልካም አስተዳደርና በአገልጋይነት ስሜት ረገድስ የመጣው ውጤት ምንድንነው መባል አለበት፡፡ እነዚህ የትግበራ ሥልቶችስ በየትኛዎቹ ተቋማት ተሞክረው ፍሬ አፈሩ? የትኛው ጭንጫ መሬት ላይ ተዘርተው መከኑ? ብሎ የሚመረምር ሊቅ ሊኖር ግድ ነው፡፡

የዘመቻ ካይዘን በሁለም መሥሪያ ቤቶች እንዴት?

በአገራችን የተተገበሩ ብዙዎቹ የለውጥ መሣሪያዎች አተገባበር ላይ ችግር እየፈጠረ ያለው፣ ሁሉም መሥሪያ ቤቶች አንድ ዓይነት ቁምጣና ሹራብ እንዲለብሱ መፈለጉ ነው፡፡ የፕሮፓጋንዳ (ወሬ) አምራቹና ብረታ ብረት ወይም ሲሚንቶ አምራቹ መሥሪያ ቤት አንድ አይደሉም፡፡ በየቀኑ በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ተገልጋዮችን የሚያስተናግደውና ሕግና መመርያ በማውጣት ወደ ትግበራ የሚመራው ተቋም መመዘኛም ሊመሳሰል አይችልም፡፡

ካይዘን በአብዛኛው ከምርት ጥራት፣ ከምርት አያያዝ፣ ከአሰባሰብና ከአጓጓዝ ጥራትና ዜሮ ብክነት አንፃር ሲታይ ከፍ ያለ ፋይዳ አለው፡፡ ከዚህ አንፃር ሊተገበር የሚባው በአብዛኛው ማኑፋክቸሪንግና አምራች በሆነው ዘርፍ ነው፡፡ እርግጥ በኮንስትራክሽንና ሜጋ ፕሮጀክቶችን በመሳሰሉት ተግባራትም ፋይዳ አይኖረውም ሊባል አይችልም፡፡ ይሁንና ጃፓን ስለተቀየረች እኛም መቀየር እንችላለን በሚል የግብታዊነት አመራር፣ ጥበቡን በሁሉም ሥፍራ እንደ ፀበል መርጨት የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም፡፡

በጃፓን የካይዘን ተሞክሮ ውስጥ አንዱ ተጠቃሽ ኩባንያ የቶዮታ መኪናዎች አምራች ድርጅት ነው፡፡ ይህ ተቋም ካይዘን ከመጀመሩ በፊት ከአሜሪካና ከአውሮፓ ተመሳሳይ ኩባንያዎች ጋር ሲወዳደር ምርታማነቱ አንድ አሥረኛ ነበር፡፡ ይህንን ክፍተት በሦስት ዓመታት ውስጥ ለማሟላት ዕቅድ ሲነድፍ ዕቅዱን ለማሳካት የረዳው ካይዘን እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይኼውም ከዕቅድ አንስቶ ግልጽ፣ ተደራሽና አሳታፊ በማድረግ ያለውን ሀብት ለይቶ፣ ቆጥሮና አደራጅቶ ወደ ሥራ በማስገባት፣ የሰው ኃይሉን አብቅቶና ለአንድ ዓላማ አሠልፎ የማበረታቻ ሥርዓትን ዘርግቶ የዕውቀት ሥራ አመራርን (Knowledge Management) በመከተሉ ነው፡፡

ወደ አገራችን ብዙዎቹ አምራች ኩባንያዎች ስናማትር የዕቅድና የአመራር ጉድለት በዝቶ ባይታይ እንኳን በሰው ኃይልና ሀብት (ሪሶርስ) አስተዳደር ላይ ያልተፈታ ችግር ይስተዋላል፡፡ በቀዳሚነት የሰው ሀብታችን ተነሳሽነት፣ የሥራ ፍቅርና ለተሠለፈበት ዓላማ ያለው ቁርጠኝነት ዝቅተኛ ነው፡፡ በቅርቡ በአንድ የመንገድ ፕሮጀክት ላይ በሥራ አስኪያጅነት የሚሠራ ቻይናዊ፣ ‹‹አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ሠራተኛ እንደ ሮቦት (ማሽን) ስትገፋው ብቻ የሚሠራ ነው፡፡ አለቃና አሠሪ ሲያይ የሚሮጠውን ያህል ከልብ የመነጨ የሥራ ተነሳሽነት የለውም፤›› ሲል እንደ ማኅበረሰብ ያለብንን ችግር በድፍረት ተናግሮ ነበር፡፡

ምናልባት እዚህ ላይ የክፍያ ማነስ፣ የማበረታቻ ሥርዓት ዝቅተኛ መሆንና የእኔነት ስሜት አለመዳበር የፈጠሩት ጫና ሊኖር እንደሚችል ይገመታል፡፡ ከሁሉ በላይ የፈጠራና የምርምርም ሆነ አዲስ ነገር የማምጣት ተነሳሽነት የለንም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት ምርምርና ፈጠራን ለማዳበር የሚያስችሉ የተለያዩ ሙከራዎችን እያደረገ ነው፡፡ ይሁንና የረዥም ጊዜ ባህላችን ይኼ አልነበረም፡፡ ሌላው ቀርቶ በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ ያሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ጥናቶችና መመረቂያ ጽሑፎች ወደ ተግባር ሲውሉ አይታዩም፡፡ የምህንድስናና መሰል ሠልጣኞች እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ከንድፈ ሐሳብ ወጥተው በየኢንዱስትሪውና በየሥራ መስኩ በመሰማራት፣ ዕውቀትና ክህሎትን የማዳበርና አዲስ ነገር የማምጣት ጉዟቸው ገና እንጭጭ ነው፡፡

እንደ አገር የሀብት መረጃ አያያዝና አጠቃቀም በከፋ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ለዚህ አብነቱ አዲስ የተመረቁ ሸቀጥና ቁሳቁስ አያያዝ ብቻ አይደለም፡፡ አላቂ (አሮጌ) ወይም ለሌላ ጥቅም የሚውል ተረፈ ምርትን እንዴት እንደምንይዝ ያጤኗል፡፡ ዛሬ በየመሥሪያ ቤቱ ባልተገባ አኳኋን ተበታትነው (ለፀሐይና ዝናብ ተጋልጠው) ‹‹የጨረታ›› ጊዜ የሚጠብቁ ተሽከርካሪዎች፣ ማሽነሪዎች …የሕዝብ ሀብት አይደሉምን?

ግንባታቸው ተጠናቆ ወደ ሥራ በገቡ ድልድዮች፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶች፣ አዳዲስ ፋብሪካዎች … ውስጥ በትርፍነት ተከምረው የሚስተዋሉ ብረቶች፣ ሲሚንቶና አሸዋን የመሳሰሉ ግብዓቶች ወይም ሌሎች ቁሳቁሶች መጀመሪያ እንዴት ትርፍ ሊሆኑ ቻሉ መባል አለበት (ከዕቅድ አኳያ)፡፡ ሁለተኛ ሳይበላሹና ሳይባክኑ እንዴትና በፍጥነት ለሌላ ጥቅም ይዋሉ የሚል ትጋት የሚያመነጭ አመራርና ፈጻሚ ሊፈጠር ግድ ነው፡፡ ስለካይዘን በአገሪቱ ከተነገረበት ጊዜ አንስቶ በምርታማነት ረገድ ያመጣው ተጨባጭ ለውጥ ካለ ሊነገረን ይገባል፡፡

ሌላው የኢትዮጵያውያን ዋነኛ ጉድለት የመረጃ አያያዝ፣ አተናተንና አጠቃቀም ልምዳችን ነው፡፡ ዛሬ ከቤተሰብ አንስቶ እስከ አገር ድረስ የውልደት፣ የልደት፣ የዕድገትና የሞት ዓይነት መረጃዎችን አሟልቶ የሚይዝ ከስንት አንዱ ነው፡፡ በየተቋማቱ በዕቅድ አፈጻጸም፣ በበጀት፣ በአሠራርና በአመራር ላይ የተደነቀረው ሳንካም ይኼው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ችግር ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ማነስ፣ ከድህነትና ከኋላቀርነት ጋር ሊያያዝ ይችላል፡፡ ለመረጃና ለታሪክ ካለን የተዛባ አተያይም ሆነ ዘልማዳዊ አኗኗር ጋርም የተቆራኘ ነው፡፡ ከሁሉም በላይ የግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራሩ ሽባ መሆን መረጃን ‹‹እንደ ጨው ዘር›› የተበታተነ አድርጎታል፡፡

የካይዘን መሠረታዊ ፍልስፍና በተለይ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ይተግበር ከተባለ መምጣት ያለበት የመረጃ አያያዝ መወለካከፍን ለማረም መሆን ነበረበት፡፡ እንኳን ማሽነሪና የምርት ክምችት የግቢ ፅድ መቁረጫ መቀስ በሌላቸው መሥሪያ ቤቶች ውስጥ፣ ስለሎጂስቲክስ አያያዝ ከመነጋገር መረጃን እንደ ሀብት ቆጥሮ እንዴት? የትና በማን ይያዝ? በምን ሁኔታ ጥቅም ላይ ይዋል? መባል አለበት፡፡ እዚህ ላይ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ 590/2000 በክፍል ሦስቱ ‹‹መረጃ የሕዝብ ሀብት ነው›› ሲል ይህንኑ ለመደንገግ ነበር፡፡ ምንም እንኳ አዋጁ በሙሉ ጉልበቱ ሥራ ላይ ባይውልም፡፡

የካይዘን መሪዎችም ሆነ ተቋማት የፍልስፍናውን ግብ ወስነው ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር መመልከት አለባቸው መባሉም ለዚሁ ነው፡፡ ተገልጋይ ተኮር የሆነ የሥራ ማሻሻያ ሲነደፍ በቀዳሚነት መረጃ ያለውን ወሳኝ ድርሻ ተገንዝቦ በጥንቃቄ ካልተሄደበት ጥቅም አይኖረውም ማለት ነው፡፡

‹‹ካይዘን የቡድን ሥራና ቅንጅታዊ ርብርብን፣ እንዲሁም ውሳኔ ሰጭነት ያዳብራል፤›› ይላሉ የመስኩ ሙያተኞች፡፡ ከዚህ አንፃር በአገራችን በአምራቹም ሆነ በአገልግሎት ሰጪው ዘርፍ የሚታየውን ቁልፍ ችግር ሊፈታ ይችል ይሆናል፡፡ ዛሬ ብዙዎቹን መንግሥታዊ ተቋማት ለከፋ የመልካም አስተዳደር እጦት እያጋለጣቸው ያለው የውሳኔ ሰጪ ማጣት ነው፡፡ ኮሚቴ፣ ካቢኔ፣ 1ለ5፣ ግብረ ኃይልና ቡድን አልወሰነበትም እየተባለ በረጅም ቀጠሮና ውጣ ውረድ ተገልጋይን የሚያማርረው ጉዳይ ስንቱ ነው፡፡

በተለያዩ የአሠራር አግባቦች (ቼክና ባላንስ) እየተረጋገጠ በአንድ የሚመለከተው የሥራ አመራር ሊወስን የሚገባውን ጉዳይ ሁሉ ‹‹ወደማይተማመኑ ባልንጀሮች›› ተርታ ማውረድ የኋላቀር አስተዳደር መገለጫ ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ውሳኔን ማሳለፍ ሲባል በሒደቱ ግልጽነትና ተጠያቂነትን ማስፈን ማለት እንጂ፣ ከውሳኔ ሰጪነት ራስን ማቀብ ማለት አይደለምና፡፡ በፍርኃት፣ ልበ ሙሉ ባለመሆንና በአመራር ብቃት መጓደል የራስን ድክመት ለመሸፈን ሁሉንም ጉዳይ ‹‹ወደ ካቢኔና ኮሚቴ›› የሚመራን የሥራ መሪ አስተሳሰብ የሚገለብጥ የካይዘን ባህልና ግፊት ሊኖር ግድ ነው፡፡

በጥቅሉ የካይዘን ሥራ አመራር ወይም የለውጥ ሥራ በመላው አገሪቱ ቦታና ሥራ ሳይለይ ይተግበር መባሉ የትም አያደርስም፡፡ ይልቁንም ጉዳዩ በግልጽ ተተንትኖ ማን ምን ያህል መጠን (ዶዝ) እንደሚያስፈልገው ተወስኖ መቅረብ አለበት፡፡ በቅድሚያ አንገብጋቢው ችግር ተለይቶ እሱን ለመፍታት ርብርብ ሊደረግም ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን የጃፓን ቶዮታ ኩባንያ በካይዘን ሥራ አመራር ተቀይሯል ብሎ በኢትዮጵያ ቆላና ደጋ ምድር ሁሉ መዝራት የሚያስከፍለው ዋጋ ቀላል አይሆንም፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊዋን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles