Wednesday, December 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየዩኒሴፍ ፈርጦች

  የዩኒሴፍ ፈርጦች

  ቀን:

  ቤተሰቦቿ ኢትዮጵያዊ ቢሆኑም ተወልዳ ያደገችው ካናዳ ነው፡፡ ስለ ወላጆቿ አገር ሲነገር መስማቷ እንድትጎበኘው ጉጉት አሳድሮባታል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን የጎበኘችው የሰባት ዓመት ታዳጊ ሳለች ነበር፡፡ የወላጆቿን ቤተሰቦች ለማየት ወደ ኢትዮጵያ በመጣችበት ወቅት ጓደኛ አፍርታ ተመለሰች፡፡ ከዓመታት በኋላ በድጋሚ ስትመጣ ግን የብዕር ጓደኛ አደረገቻት፡፡

  በዙሪያዋ ስለምታስተውላቸው ሁኔታዎች ከብዕር ጓደኛዋ ጋር የመወያየት ፍላጎት ስለነበራት ደብዳቤ በብዛት ትጽፍላት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከጓደኛዋ ምላሽ አግኝታ አታውቅም፡፡ ሁኔታው ግራ ሲገባትም ጓደኛዋን በቅርበት የሚያውቁ ቤተሰቦቿን ስለጉዳዩ በስልክ አነጋገረቻቸው፡፡ የሰጧት ምላሽ ግን ልብ የሚነካ ነበር፡፡ ‹‹የምትጽፍበት እርሳስ የላትም›› የሚል፡፡

  አጋጣሚው አርፋ እንድትቀመጥ አላደረጋትም፡፡ ይልቁኑ በሕዝቡ ዘንድ በበጎ አድራጊነት እንድትታወቅ የረዳትንና ‹‹ፔንስል ማውንቴን›› ብላ የጠራችውን ፕሮጀክት ነድፋ መንቀሳቀስ ጀመረች፡፡ በካናዳ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በመዘዋወርም 25,000 እርሳሶችን ማሰባሰብ ቻለች፡፡

  በሰበሰበችው እርሳስ ደስተኛ ብትሆንም ያላሰበችው ጉዳይ ሥራዋን ወደኋላ ይጎትተው ጀመር፡፡ እርሳሶቹን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የትራንስፖርት ችግር አጋጠማት፡፡ ጥረቷን የተመለከቱት ቤተሰቦቿ ለትራንስፖርት የሚሆን ገንዘብ ማሰባሰብ በመጀመራቸው የታዳጊዋ ህልም ዕውን ሆነ፡፡ እርሳሶቹ በኢትዮጵያ በሚገኙ ትምህርት ቤቶች ተሠራጩ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ሰብስባ ለተማሪዎች ያከፋፈለቻቸው እርሳሶች ከግማሽ ሚሊዮን በላይ እንደሆኑ ትናገራለች፡፡ የፔንስል ፕሮጀክት መሥራች ሃና ጐደፋ አሁን 17 ዓመት ሆኗታል፡፡

  ታዳጊዋ ለትምህርት ጠንካራ አመለካከት አላት፡፡ በተሳተፈችባቸው መድረኮች ሁሉ ትምህርት ለስኬት ቁልፍ መሆኑን ሳትናገር እንደማታልፍና በተለይም በአገር ውስጥ የሚታዩ ችግሮችን በትምህርት መለወጥ እንደሚቻል ትናገራለች፡፡ በሕፃናትና በትምህርት ላይ ባሳየችው ቁርጠኝነትም እ.ኤ.አ በ2013 በዩኒሴፍ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆና ተመረጠች፡፡ ተቋሙ በጤና፣ በትምህርት፣ በሕፃናት ጥበቃ፣ በሥርዓተ ምግብና በንጽሕና ላይ በሚያደርገው እንቅስቃሴ ውስጥ መሳተፍም ጀመረች፡፡ አጋጣሚውም በአገር ውስጥ ያለውን ችግር በቅርበት እንድትመለከት ረዳት፡፡

  በተገኘችባቸው ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች ላይም በሕፃናትና በትምህርት ዙሪያ የታዘበቻቸውን ችግሮች በመግለጽ መፍትሔ እንዲሰጥባቸው ጠይቃለች፡፡ ባደረገቻቸው ግብረ ሠናይ ተግባራትም ጥቂት የማይባሉ ሽልማቶችን አግኝታለች፡፡ በቅርቡ በአማራ ክልል ያደረገችውን ጉብኝት በተመለከተ ሐምሌ 17 ቀን 2007 ዓ.ም.  በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በተዘጋጀው የሻይ ቡና ፕሮግራም ላይ በቆይታዋ ስላከናወነቻቸው ተግባራትና መደረግ ስለሚኖርባቸው ጉዳዮች  አብራርታለች፡፡ በዕለቱ በዩኒሴፍ የሴቶችና ሕፃናት አምባሳደሯ አቤሎን መለሰም ተገኝታለች፡፡

  የ19 ዓመቷ አቤሎን ተወልዳ ያደገችው ኖርዌይ ነው፡፡ የድምፃዊት ነፃነት መለሰ የወንድም ልጅ ስትሆን እንደ አክስቷ ሁሉ የሙዚቃ ተሰጥኦ አላት፡፡ እሷ እንደምትለው፣ ቤተሰቦቿና ሌሎች በቅርበት የሚያውቋት ድምፀ መረዋ መሆኗን ይነግሯታል፡፡ የራሷን ሙዚቃ እንድትሠራም ያበረታቷት ነበር፡፡ እሷም አስተያየቱን እንደዋዛ አላየችውም፡፡ በኖርዌይ ጋት ታለንት (የኖርዌይ አይዶል ሾው) የድምጻውያን ውድድር ተሳተፈች፡፡ በውድድሩ ከአንድ ሺሕ የሚበልጡ ተወዳዳሪዎች ቢኖሩም እስከ መጨረሻው ከዘለቁት አሥር ተወዳዳሪዎች መካከል ሆነች፡፡

  የራፕ ሙዚቃ ተሰጥኦ ያላት አቤሎን ሙዚቃዋን  በውድድር መድረኩ ስታቀርብ እንደማንኛውም ተወዳዳሪ ሳይሆን እንደ ፕሮፌሽናል ሙዚቀኛ ነበር፡፡ ዳኞችም ከድምጿ እንከን ማውጣትን ትተው በድምጿ አብረዋት ሲዝናኑና፣ አንገታቸውን በማወዛወዝም አብረዋት ሲጨፍሩ ይታያል፡፡ ከድምጿ ባሻገር የራሷን ግጥምና ዜማ በመሥራት ኦርጂናል ሥራ ይዛ መቅረቧ ልዩ ያደርጋትም ነበር፡፡

  ሙዚቃዎቿ በዩቲዩብ ድረገጽ ከተለቀቁ በኋላ ዕውቅናን አትርፋለች፡፡ ብዙ ጊዜ ሥራዎቿ በእናት ላይ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ ሕጻናትን የሚመለከቱ ሥራዎችም አሏት፡፡ በዚህም በ2014 ከሃና ጎን የዩኒሴፍ የሕፃናትና እናቶች አምባሳደር ሆናለች፡፡

  ‹‹የዓለማችን ጌጥ

  ልዩ ውብ አበባ

  የነገ ፍሬዎች ሴቶች ናቸውና

  በፍቅር ይኑሩ

  ተሟልቶ ኑሯቸው

  ያሰቡት ይሳካል

  እንሁን ተስፋቸው››

  የሚል የእንግሊዝኛና የአማርኛ ቅይጥ የራፕ ሙዚቃ ለሕዝብ ጆሮ አብቅታለች፡፡ የአማርኛውን ግጥም የጻፉላት ወላጅ አባቷ ሲሆኑ፣ ዜማውንና የእንግሊዝኛውን ግጥም የሠራችው ራሷ ነች፡፡ በአሁኑ ወቅት ትኩረታቸውን እናቶችና ሕፃናት ላይ አድርገው በሚሠሩ ፕሮግራሞች ላይ በመሳተፍ ላይ ትገኛለች፡፡ ‹‹10,000 ሃፒ በርዝደይ›› የተሰኘ ነፍሰጡር እናቶችን የሚረዳ ፕሮጀክት ተቀላቅላ እየሠራች ትገኛለች፡፡ ፕሮጀክቱ በኢትዮጵያና በሌሎችም የአፍሪካ አገሮች ይተገበራል፡፡ በዚሁ ፕሮጀክት በተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ላይም ‹‹ወላጅ እናት›› የተሰኘ የራፕ ሙዚቃዋን አቅርባለች፡፡

  እስካሁን የራሷን ሦስት ሙዚቃዎች የሠራች ሲሆን፣ አንደኛው ሙዚቃዋ ሕፃናት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በባህር ዳር ቆይታዋም ያለ ዕድሜ ጋብቻና ትምህርት ያልደረሳቸው ሕፃናት አጋጥመዋታል፡፡ ያስተዋለቻቸውን የእናቶችና ሕፃናት ችግር ለመቅረፍ እንደምትሞክርና በተቻላት ሁሉ በአምባሳደርነቷ ለመቆየት እንደምትጥር ተናግራለች፡፡

  እ.ኤ.አ. በ1946 ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የተቋቋመው ዩኒሴፍ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፕሮግራም ሲሆን ዋና መሥሪያ ቤቱም ኒውዮርክ ይገኛል፡፡

  ዓላማውም በጦርነት ጉዳት ለደረሰባቸው እናቶችና ሕፃናት የምግብና የጤና አገልግሎት መስጠት ነበር፡፡ ለሚያቀርባቸው አገልግሎቶች መንግሥት ሁለት ሦስተኛውን በጀት ሲያቀርብ የተቀረውን መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ያገኛል፡፡ በኢትዮጵያ የተቋቋመው እ.ኤ.አ. በ1952 ሲሆን በአሁን ሰዓት 190 በሚሆኑ አገሮች ሥራዎቹን እየሠራ ይገኛል፡፡

  ለሥራው መቃናትም የተለያዩ ታዋቂ ሰዎችን በአምባሳደርነት ይሾማል፡፡ የመጀመሪያው የዩኒሴፍ አምባሳደር ታዋቂው አሜሪካዊ አርቲስት ዳኒ ኬይ ነበር፡፡ አርቲስቱ ለረዥም ዓመታት በአምባሳደርነት ያገለገለ ሲሆን በተቋሙ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይነገርለታል፡፡ ሃሎዊን የተባለውን የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም መሥራች ሲሆን ሕይወቱ እስኪያልፍ ድረስም በልዩ ልዩ ሥራዎች ተሳትፏል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በኦሮሚያ ክልል የተፈጸመው ጭፍጨፋና ሥጋቱ

  ኦሮሚያ ክልል ከቀውስ አዙሪት መላቀቅ ያቃተው ይመስላል፡፡ ከ200 በላይ...

  እናት ባንክ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ወሰነ

  መጠባበቂያን ሳይጨምር የባንኩ የተጣራ ትረፍ 182 ሚሊዮን ብር ሆኗል እናት...

  ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ማሻገር ቻለ

  ቡና ባንክ በ2014 የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔውን ለመጀመርያ...