Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልቴአትርን ከቴአትር ቤት ውጪ

ቴአትርን ከቴአትር ቤት ውጪ

ቀን:

ጣይቱ ሆቴል የእሳት አደጋ ሳይደርስበት በፊት በሆቴሉ በሚገኘው ጃዝ አምባ ላውንጅ ‹‹ከሰላምታ ጋር›› የተሰኘ ቴአትር ዘወትር ሰኞ ይታይ ነበር፡፡ ቴአትሩ ከታየባቸው ቀኖች በአንዱ በላውንጁ ከተገኙ አንዷ በፀሎት ነበረች፡፡ ቴአትሩ የሚታይበት ሰዓት እስከሚደርስ ተመልካቾች ከሆቴሉ የሚፈልጉትን ምግብ አልያም መጠጥ እያዘዙ ይጨዋወቱ ነበር፡፡ ጃዝ አምባ በፀሎት በተለምዶ ቴአትር ከምትመለከትባቸው ቴአትር ቤቶች የተለየ ድባብ እንደነበረው ታስታውሳለች፡፡

አንድ ሰዓት ብቻ ስለሚወስደው ቴአትር ብዙ የሰማችው በፀሎት፣ ቴአትሩ እስከሚጀመር በላውንጁ የነበረውን እንቅስቃሴ ትከታተል ነበር፡፡ ተመልካቾች በቴአትር ቤት ከተለመደው አቀማመጥ በተለየ መደዳውን ይታያሉ፡፡ ከመድረኩ ፊት ለፊት ከነበሩ መቀመጫዎች በተጨማሪ ከመድረኩ በስተቀኝም ወንበሮች ነበሩ፡፡ ሁለት ተዋንያን ብቻ ያሉት ተውኔቱ፣ በሁለት ዳንሰኞች ኮንቴምፓረሪ ዳንስ የታጀበ ሲሆን፣ አጠቃላይ አወቃቀሩ ከዚያ ቀደም ካየቻቸው ቴአትሮች የተለየ እንደነበር ትናገራለች፡፡ ‹‹የታየበት ቦታ፣ መድረኩ፣ ተዋንያኑ፣ ታሪኩና የተመልካቾች አቀባበል ከተለመደው የተለየ መሆኑ አስደስቶኝ ነበር፤›› ትላለች፡፡

ቴአትር አዘውትራ የማታየው በፀሎት፣ ቴአትሮች ከተለመደው በተለየ መልኩ ቢቀርቡ ብዙዎችን ሊማርኩ እንደሚችሉ ታምናለች፡፡ ቴአትር ቤት ለሰዓታት መሰለፍና የተመልካቾች ግርግር እንደሚረብሻት ትናገራለች፡፡ በእሷ እምነት፣ ቴአትርን ለማጣጣም የተረጋጋ ድባብ መፈጠር አለበት፡፡ እንደምሳሌ የምትጠቅሰው ጥቂት ሰዎች በሚገለገሉበት ሆቴል መመልከትን ነው፡፡ ‹‹ብዙ ሆቴሎች ተመሳሳይ አገልግሎት ቢሰጡ ብዙ ቴአትር ማየት እንችላለን፤ የግላዊነት ስሜት ስላለውም ሰው ቴአትሩን ያጣጥማል፤›› ትላለች፡፡

ቴአትርን ከቴአትር ቤት ውጪ በልዩ ልዩ ቦታዎች ማሳየት በሌሎች አገሮች የተለመደ ሲሆን፣ በእኛ አገርም በተለያዩ ጊዜዎች ተስተውሏል፡፡ በርካታ ባለሙያዎች ከቴአትር ቤት ውጪ ያለውን አማራጭ ሙሉ በሙሉ እየተጠቀሙበት ነው ለማለት ባይቻልም ጥቂት ሥራዎች አሉ፡፡

በጅሮንድ ተክለሐዋርያት ተክለማርያም አውሮፓን ተዘዋውረው ከጐበኙ በኋላ ቴአትራዊ አቀራረብ ያለው ትዕይንት መዘጋጀት እንዳለበት ያምናሉ፡፡ ‹‹ፋቡላ፤ የአውሬዎች ኮሜዲያ›› የተሠራውም ለዚሁ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ቴአትር ታሪክ የመጀመሪያው ሥራ እንደሆነ የሚነገርለት ተውኔቱ የታየው ሆቴል ውስጥ ነበር፡፡

በአገሪቱ ቴአትር ቤቶች ከተገነቡ በኋላም በተለያዩ ምክንያቶች ቴአትሮች ከቴአትር ቤት ውጪ ይታዩ ነበር፡፡ ዛሬ ዛሬ እንደ አማራጭ ከሚወሰዱ ቦታዎች ሬስቶራንቶች፣ ሆቴሎችና የግል ሲኒማ ቤቶች በዋነኛነት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን አማራጮች ስለመጠቀማቸው ባለሙያዎች የተለያየ ምክንያት ያቀርባሉ፡፡

መአዛ ወርቁ የ‹‹ከሰላምታ ጋር›› ደራሲና አዘጋጅ ናት፡፡ ቴአትሩ ጃዝ አምባ ከተቃጠለ በኋላ በዓለም ሲኒማ የቀረበ ሲሆን፣ አሁን ግዮን ሆቴል በሚገኘው አፍሪካ ጃዝ መንደር እየታየ ነው፡፡ የመጀመርያ ሥራዋ ‹‹ዝነኞቹ›› ቴአትር በአዲስ አበባ ቴአትርና ባህል አዳራሽ ይታይ ነበር፡፡ ከ‹‹ሰላምታ ጋር››ን ከቴአትር ቤት ውጪ ያሳየችው በመጀመሪያ ቴአትሯ ተሞክሮ ደስተኛ ባለመሆኗ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ ቴአትሩ ተገምግሞ መድረክ እስኪያገኝ የወሰደው ረዥም ጊዜ መአዛ ከምትጠቅሳቸው ችግሮች አንዱ ነው፡፡ ላስገመገመችበት ቴአትር ቤት እንዲሆን የቴአትሩን ቅርፅ፣ የገጸ ባህሪያቱን ሚናና ርዕሱንም ሳይቀር ለመቀየር ተገዳለች፡፡

‹‹የመጀመሪያ ቴአትሬን ለማሳየት ብዙ መስዋእትነት ከፍያለሁ፡፡ መድረክ ማግኘት ቀላል እንዳልሆነም ተረድቻለሁ፤›› ትላለች፡፡ ቴአትሩ እንዲቀርብ በምትፈልግበት መንገድ ለማስኬድ የቴአትር ቤቶች አሠራር የተመቸ እንዳልነበረ ትናገራለች፡፡ በሁለተኛ ተውኔቷ ነፃነትን ሽታ ወደ ሆቴሎች ፊቷን አዙራለች፡፡

‹‹በቴአትር ቤቶች መገፋቴ ‹ከሰላምታ ጋር›ን ፈጥሯል፡፡ በነፃነትም ተሠርቷል፤›› በማለት ትገልጸዋለች፡፡ ከቴአትር ቤት ውጪ መቅረቡ ገበያ እንደፈጠረላት ትናገራለች፡፡ ቴአትሯ ከ25 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎችን ታሳቢ ያደረገ መሆኑንና በዚህ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ተመልካቾች ቴአትር ቤት የመሄድ ዕድላቸው የጠበበ እንደሆነ ትናገራለች፡፡ በእሷ እምነት፣ ረዥም ሰልፍ፣ መደበኛ አቀማመጥና ሌሎችም በቴአትር ቤት የተለመዱ ነገሮችን ለማይፈልጉ ሰዎች በሆቴል መቅረቡ ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮአል፡፡

ከቴአትር ቤት ውጪ ማሳየት ፈታኝ የሚሆንባቸው አጋጣሚዎችንም ትጠቅሳለች፡፡ አንዱ ተውኔት ወዳልተለመደበት ቦታ ተመልካቾች እንዲሄዱ ማነሳሳት ነው፡፡ ሰዎችን ለመሳብ የሚሠራው ማስተዋወቂያ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል ትላለች፡፡ በሌላ በኩል ቴአትር ቤት ከተመልካች የሚጠየቀው ክፍያ አነስተኛ ሲሆን፣ የተሻለ ገቢ ለማግኘት ከቴአትር ቤት ውጪ መሥራት ይመረጣል፡፡ በተጨማሪም ባለሙያዎች በመረጡት ቀን ቴአትራቸው ይታይላቸዋል፡፡

ሌላው ባለሙያዎች በቴአትር ቤት ረዥም ጊዜ መጠበቃቸው ነው፡፡ የመጀመሪያ ተውኔቷ እንዲታይ ሁለት ዓመት መጠበቋን እንደ ምሳሌ ትጠቅሳለች፡፡ ቴአትር በአጭር ጊዜ ለመድረክ በቅቶ ለሌላ ቴአትር ቦታ መልቀቅ እንዳለበት ታምናለች፡፡ መአዛ ‹‹አሁን ቴአትር እንዲታይ ከመጠባበቅ፣ የቴአትሬን ቅርፅና ታሪክ እንደየቴአትር ቤቱ መስፈርት ከመቅረጽ ነፃ ሆኜ ለራሴ መድረክ ፈጥሬአለሁ፤›› ትላለች፡፡

ቴአትር ከተለመደው ቅርጽና መድረክ ውጪ ቢሠራ ትመርጣለች፡፡ ከተለመደው መድረክ በተለየ የተሠራው ‹‹ከሰላምታ ጋር›› ተዋንያኑን ለተወሰነ ጊዜ እንዳስቸገራቸው ሳትጠቅስ ግን አላለፈችም፡፡ በቴአትር ቤቶች መድረክ ተዋንያን ከተመልካቹ ከፍ በሚያደርጋቸው መድረክ ላይ ሆነው፣ ከተመልካቹ በጥቂት ሜትሮች ርቀው ይተውናሉ፡፡ በጃዝ አምባና አፍሪካ ጃዝ መንደር ከዚህ በተቃራኒው መሥራት እንደቻሉ ትናግራለች፡፡

የኃይሉ ፀጋዬ አስቂኝ ቴአትር ‹‹ለዕረፍት የመጣ ፍቅር›› ለመድረክ የበቃው በ1992 ዓ.ም. ነበር፡፡ በወቅቱ በቴአትር ቤትና በኢምፔሪያል ሆቴል አሳይቶታል፡፡ ቴአትር ከቴአትር ቤት ውጪም እየቀረበ ለተመልካቾች አማራጭ መቅረብ እንዳለበት ያምናል፡፡ ‹‹ለዕረፍት የመጣ ፍቅር›› በቴአትር ቤት ሳለ መመልከት ላልቻሉ ግለሰቦች ሁነኛ አማራጭ እንዳቀረበ ይናገራል፡፡ ኃይሉ በቀጣይ ሆቴል ውስጥ ያሳየው ቴአትሩ ‹‹ከራስ በላይ ራስ›› ሲሆን፣ በብሔራዊ ሆቴል ቀርቧል፡፡ በ1994 ዓ.ም. ሸራተን አዲስ ውስጥ ታይቷል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ ከፍተኛ ገንዘብ አውጥተው የሚመለከቱ ተመልካቾችን ለመድረስ የተጠቀመበት መንገድ ነው፡፡ ቴአትሩ አሁን በአዶት ሲኒማ እየታየ ነው፡፡ በ1996 ዓ.ም. ‹‹ምህላ›› የተሰኘ ቴአትሩ በዓለም ሲኒማ ቀርቧል፡፡ ‹‹ቅድስት ካናዳ›› የተሰኘ ተውኔቱ ደግሞ በአቤል ሲኒማ ታይቷል፡፡

አሁን አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ቴአትር ቤቶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትርና ሀገር ፍቅር ቴአትር ናቸው፡፡ በዚህ ምክንያትም ባለሙያዎች አማራጭ መድረክ እየፈለጉ ነው፡፡ ኃይሉ ቴአትር ቤት ተውኔት ማሳየትን ከሌሎች አማራጮች ጋር ከሚያነጻጽርባቸው መስፈርቶች አንዱ የተመልካች ቁጥር ነው፡፡ ተመልካቾች የለመዱት ቴአትር ቤት ተደራሽነቱ ይሰፋል፡፡ ‹‹ቴአትር ቤት ከዓመት እስከ ዓመት ማሳየት ይቻላል፤ ከቴአትር ቤት ውጪ ግን ተመልካችን ማስለመድ ይጠይቃል፤›› ይላል፡፡

ከሆቴልና ሲኒማ ቤት ተሞክሮው እንደ ተግዳሮት የሚያነሳው የመድረኮቹ መጠን አነስተኛ መሆኑን ነው፡፡ መድረኮቹ ለቴአትር ስለማይሠሩ ክፍተት ይፈጠራል፡፡ ቢሆንም ከቴአትር ቤት ውጪ ያሉ አማራጮችን መጠቀም አዎንታዊ ጎኑ እንደሚያመዝን ይናገራል፡፡ ‹‹ቴአትሮች ይበራከታሉ፤ በተለይም ወጣት ደራስያን፣ አዘጋጆች፣ ተዋንያንና ሌሎች ባለሙያዎች ለሥራዎቻቸው ቦታ ያገኛሉ፤ ቴአትሮች በብዛትና በጥራት ይሠራሉ፤ ባለሙያዎች የሚያገኙት ገቢም ይጨምራል፤›› ይላል፡፡

የግል ሲኒማ ቤቶችና ሆቴሎች ቴአትሮችን ሲያስተናግዱ ማሻሻል የሚጠበቅባቸውን ይዘረዝራል፡፡ ዋነኛው ቦታቸውን ምቹ ማድረግ ሲሆን፣ የሚጠይቁት ክፍያ የቴአትር ባለሙያዎችን አቅም ያገናዘበ መሆን እንዳለበትም ያስረዳል፡፡ ‹‹ብዙዎቹ ለራሳቸው ጥቅም ያደላሉ፤ ለቴአትር ዝግጅት የሚያስፈልጉ ግብዓቶችን ማሟላት ደግሞ ከባድ ነው፤›› የሚለው ኃይሉ፣ ምክንያታዊ ያልሆነ ክፍያ መጠየቅ ባለሙያዎችን ተስፋ እንደሚያስቆርጥ ይናገራል፡፡

የቴአትር ቤቶችን 70/30 የተሰኘ አሠራር እንደ እንቅፋት ይጠቅሳል፡፡ ይህ 70 በመቶ በቴአትር ቤቱ ባለሙያዎች ለተሠሩ ተውኔቶችና የቀረው ጊዜ ከቴአትር ቤቱ ውጪ ለሚሠሩ ባለሙያዎች የሚሰጥበት አሠራር ነው፡፡ ‹‹ቴአትር የውጪና የቴአትር ቤት በሚል መከፋፈል የለበትም፤ ሁሉም እኩል ተጠቃሚ መሆን አለበት፤ አሠራሩ ተለውጦ ብቃት ያለው ሥራ ሁሉ መቅረብ አለበት፤›› ይላል፡፡

ሙሉጌታ ወርቁ የራፋቶኤል አድቨርታይዚንግና ኢቨንትስ ሥራ አስኪያጅ ነው፡፡ ድርጅቱ በቅርቡ ‹‹ፀሐይቱ›› የተሰኘ ሙዚቃዊ ቴአትር አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ቴአትሩ የተመረቀው በአዲስ ጉርሻ ሬስቶራንት ነው፡፡ ቴአትሩ በእቴጌ ጣይቱ የሕይወት ታሪክ ላይ ያተኮረ ሲሆን፣ ለ120ኛው ዓመት የዓድዋ ክብረ በዓል የተዘጋጀ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በአዲስ ጉርሻ ሬስቶራንት በፉከራና ሽለላ ላይ ያተኮረ ሙዚቃዊ ድራማም አሰናድቶ ነበር፡፡

ሙሉጌታ እንደሚለው፣ ሥራዎቻቸውን በሬስቶራንት የሚያሳዩት ቴአትርን በቴአትር ቤት ለማይመለከት ተመልካች ተደራሽ ለመሆን ነው፡፡ ‹‹ለመዝናናት ወደ ሬስቶራንት የሚሄዱ ተመልካቾች ጎን ለጎን ቴአትር እንዲያዩ እንፈልጋለን፤ ታሪክን መሠረት ያደረጉ ተውኔቶች ላይ ስለምናተኩር በተለያየ ቦታ እያሳየን ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ማሳወቅ እንፈልጋለን፤›› ይላል፡፡

ድርጅቱ ወጣት ባለሙያዎች የተሰባሰቡበት መሆኑን በመጥቀስ፣ ሥራዎቻቸውን በተቻለው ፍጥነት ለሕዝብ የማድረስ ጉጉት እንዳላቸው ይናራል፡፡ ‹‹መድረክ ማግኘት  በተለይ ለወጣቶች ይከብዳል፤ እኛ ባገኘነው ቦታ ሥራችንን ማሳየት መርጠናል፤ በተለያየ ዕድሜ ክልል ያሉ ተመልካቾችንም መድረስ ችለናል፤›› የሚለው ሙሉጌታ፣ ቀጣይ ሥራዎቻቸውን በዚሁ መንገድ እንደሚያሳዩ ይገልጻል፡፡

በጉዳዩ ላይ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበባት ኮሌጅ ዲን ነቢዩ ባዬን አነጋግረናል፡፡ እሱ እንደሚለው፣ የአንድ ቴአትር ዘውግ ቴአትሩ የሚታይበትን ቦታ ይወስናል፡፡ ቴአትር ተመልካች ባለበት ሄዶ እንዲታይ የሚፈለግባቸው ተውኔቶች ከቴአትር ቤት ውጪ መቅረባቸው የተለመደ ነው፡፡ አሳታፊ ቴአትሮችና የመንገድ ላይ ቴአትሮችን (ስትሪት ቴአትር) እንደምሳሌ ይጠቅሳል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ቴአትር ቤቶች ከመከፈታቸው በፊትም ይሁን በኋላ ከቴአትር ቤት ውጪ ተውኔቶች የታዩበትን አጋጣሚ ያጣቅሳል፡፡ የመላኩ አሻግሬ ሥራዎች ከአዲስ አበባ ውጪ ቴአትር ቤት በሌለባቸው ከተሞች ዛፍ ስር፣ ገበያ ውስጥም ታይተዋል፡፡ ህብር ባህል አዳራሽ የቀረበውን የአባተ መኩሪያ ‹‹የሐምሌ ጨረቃ ጉዞ››ም ይጠቅሳል፡፡

እንደ ነቢዩ ገለጻ፣ የቴአትራቸው ቅርጽ አስገድዷቸው ከቴአትር ቤት ውጪ የሚያቀርቡ ባለሙያዎች እንዳሉ ሁሉ፣ ቴአትር ቤቶች በሚሰጡት አገልግሎት ባለመርካት አማራጭ የሚፈልጉም አሉ፡፡ ካነጋገርናቸው የቴአትር ባለሙያዎች ጋር የሚስማማው ለተመልካቾች አማራጭ መፍጠር እንደሚገባ ነው፡፡ ‹‹ተውኔቶች ከቴአትር ቤት ሲወጡ ለአዳዲስ ፈጠራ ክፍት ይሆናሉ፤ ለተውኔት የሚሆኑ ቦታዎችን መገልገል ጠቀሜታው የጎላ ነው፤›› የሚለው ነቢዩ፣ አሠራሩ በስፋት ቢለመድ መልካም እንደሆነ ይጠቁማል፡፡

በቴአትር ቤት መድረክ መታየት ያለባቸው ተውኔቶች ከቅርጻቸው ውጪ ከቴአትር ቤት መውጣት እንደሌለባቸው በአጽንኦት ይናገራል፡፡ ቴአትሮች በቴአትር ቤት መታየት እያለባቸው በሌላ መድረክ ያለአግባብ ከቀረቡ ተመልካቹ ልማድ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ ይላል፡፡ ቴአትር ካለው ዘርፈ ብዙ ቅርጾች ኢትዮጵያ ውስጥ ሥራ ላይ የዋሉት ጥቂት መሆናቸውን በመግለጽ፣ አዳዲስ መንገዶች ቢስፋፉ የሚበረታታ መሆኑን ያክላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...