Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የሕክምና ራስ ምታት

በእፁብ ድንቅ አበራ (ዶ/ር)

ይህንን ጽሑፍ እንድጽፍ ያነሳሳኝ በአንድ የሕክምና ሆስፒታል ውስጥ ሕፃን ልጇን አቅፋ ስታለቅስ ያየኋት ዕድሜዋ በ40ዎቹ ውስጥ የምትገመት እናት የሐኪም ወረቀት ይዛ መመልከቴ ነው፡፡

ለቅሶዋ አሳስቦኝ ብጠጋት ችግሮቿን ለማወቅ ጠየቅኳት፡፡ የታዘዘላትን መድኃኒት እያሳየችኝ የነፃ ታካሚ መሆኗን ገለጻልኝ፤ ልጇን ለማሳከም ከሁለት ሳምንት በላይ መመላለሷንና የታዘዘላት መድኃኒት ከነፃ የመድኃኒት መደብር ማግኘት የማትችል መሆኗን ከውጭ ግዥ እንደተባለች መድኃኒቱንም ከውጭ ፋርማሲ ለመግዛት የሚያስችል ምንም ገንዘብ እንደሌላት በመማረር የከረረ ለቅሷን ስመለከት ልቤ ተነካ፡፡

ይህ እኔን ብቻ ሳይሆን ሌሎቹንም የሆስፒታል ባልደረቦቼን የሚያጋጥም መሆኑን አውቃለሁ፡፡ የአገራችን ማኅበረሰብ በድህነት ውስጥ የሚኖርና በቀን የሚያስፈልገውን የመመገብና በዚሁ ሳቢያ ለሚከሰት የጤና ችግር የሚረዳውን መድኃኒት የመግዛት አቅም እንደሌለው የታወቀ ነው፡፡ ከዚህ ግንዛቤና ሀቅ በመነሳት አቅም ለሌላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ነፃ ሕክምና እንደተፈቀዱላቸው ሁሉ የመድኃኒት አቅርቦትም ነፃ የሚያገኙበት ሁኔታ ሊመቻችላቸው ይገባል፡፡

ይህም ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ የሕክምና አገልግሎት መስጠት ደፋ ቀና የሚሉ ሐኪሞችም ያሉባቸው ችግሮች ሊታዩላቸውና መፍትሔ ሊበጅላቸው ግድ ይላል፡፡ ከችግሮቻቸውም መካከል አንድ ሐኪም ለ40,000 ታካሚዎች የቆመ መሆኑ፣ ለ36 ሰዓታት ያህል ያለ ዕረፍት መሥራታቸውና በዚያው ልክ የሚከፈላቸው ደመወዝ ደግሞ በጣም አነስተኛ መሆን ናቸው፡፡

መንግሥት ለችግሩ እንደ ብቸኛ መፍትሔ አድርጎ የወሰደው የሐኪሞችን ቁጥር ማብዛት ላይ ነው፡፡ ይህንን ማድረጉ ባይከፋም ነገር ግን ከቁጥር የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ብቸኛ መፍትሔው በሥነ ምግባር የታነፀ ባለሙያ መፍጠር፣ የደመወዝ ማሻሻያ ማድረግና አበረታች የሥራ ውጤት ላሳየ ሐኪም ማበረታቻ መስጠት ነው የሚል የፀና እምነት አለኝ፡፡ ከዚህ ውጭ የሚከናወነው ግን የሐኪሞችን ተነሳሽነት የሚያጠፋ አሳፋሪ አማራጭ መሆኑን መታወቅ ይኖርበታል፡፡

በእርግጥ የአገራችን ባለሥልጣናት የሆስፒታሎች አገልግሎት የኅብረተሰቡን ችግር መፍትሔ የሚሰጡ መሆናቸውንና አለመሆናቸውን የሚያውቁት ራሳቸው ወይም ቤተሰቦቻቸው ቢታከሙባቸው ኖሮ አልነበር? ዳሩ ግን በአገራችን የሕክምና ባለሙያና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከመጠቀም ይልቅ መተማማኑ ይሁን ፍላጎቱን ያጡ በሚመስል መልኩ አገር ውስጥ መታከም በሚችል የጤና ችግር ከዚህ ደሃ ሕዝብ በግብር መልክ በተሰበሰበ ገንዘብና አገሪቱ በሌላት የውጭ ምንዛሪ ከአገር ውጭ ሙሉ ወጪያቸው ተችሎ መታከም ስለሚችሉ ታች ወርደው ችግሩን መረዳት ተስኗቸዋል፡፡

ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከቀበሌ የደሃ ደሃ መሆኑን አስመስክሮ ሊታከም ከአያሌ መቶ ኪሎ ሜትሮች አቋርጦ ለመጣ ታማሚ ይህ ምርመራ እዚህ አይሰጥም፣ የላብራቶሪ ግብዓት አልቋልና ከውጭ አሠርተህና (ልብ ይበሉ ከግል ክሊኒኮች ለአንድ የደም ናሙና የሚጠየቀው ዋጋ ከመንግሥት ሆስፒታል ያለማጋነን ከ20 እጥፍ በላይ እየተባለ)፣ አስቸኳይና አስፈላጊ በሆነው የምርመራ መሣሪያ ለመታየት ለአንድ ወርና ከዚያ በላይ በሚቀጠርበት ሁኔታ የአገራችን የጤና አገልግሎት ማደጉ ከአኃዝ የዘለለ ፋይዳው ምኑ ላይ ይሆን?

በአንድ ወቅት ክትትል የማደርግለት ታካሚ የስኳር መድኃኒቱን ለአንድ ቀን ብቻ በማቋረጡ ራሱን ስቶ በድንገተኛ ክፍል አምጥተውት ገጠመኝ፤ በኋላም የነፃ ታካሚ የነበረና መድኃኒቱ አልቋል ተብሎ በግል ለመግዛት አቅም በማጣቱ ብቻ መድኃኒቱ ስለተቋረጠ እንደሆነ ሲናገር ለሚሰማው ባለሙያ ሕመምም ነው፡፡

እንኳንስ ከደሃ ደሃ ለሆነ ግለሰብ ቀርቶ ዝቅተኛ የደመወዝ ገቢ ያለው የመንግሥት ሠራተኛ ለቀላል የሳንባ ምች (ኒሞኒያ) ወይም የሽንት ቱቦ ኢንፌክሽን ለሰባት ቀን የሚሆነውን መዳኛ መዳኃኒት ለመግዛት የአምስት ቀን የደመወዝ መጠን ያስፈልገዋል፡፡

ተጽፎ ከምናነበውና እየተነገረን ከምንሰማው በዘለለ በተጨባጭ የማኅበረሰቡ የኢኮኖሚ ዕድገት ዜጎች የሚያስፈልጋቸውን መድኃኒት መግዛት የሚያስችል፣ ከሙስና እና ከብዙ ውጣ ውረድ የፀዳ አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት ደረጃ ላይ ደርሰን የምናየው መቼ ይሆን? መንግሥት የሆስፒታሎቹን የሕክምና አገልገሎት አሰጣጥ መዋቅራዊ ለውጥ በማምጣት ማሻሻል፣ የባለሙያዎችን ጥያቄ ጆሮ ሰጥቶ ማዳመጥና የነፃ ታካሚዎችን የመድኃኒትና የምርመራ እጥረት መቅረፍ የማኅበረሰቡን ሕይወት ከሞት መታደግ ነውና በአትኩሮት ቢታይ መልዕክቴ ነው፡፡

ጤናችን በዚሁ ችግር ተስተጓጉሎ አንድዬ ዕድሜ እንዳይነሳንና መፍትሔ  በቶሎ ተበጅቶለት ባየነው ምንኛ በታደልን ይሆን?

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ ሌክቸረር ሲሆኑ፣ ጽሐፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ ያንፀባርቃል፡፡ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles