‹‹የሰው ልጅ እየተግባባ ያለው የሚግባባው በቋንቋ ብቻ የሚመስለው አለ፡፡ የሰው ልጅ ለመግባባት ቋንቋውን፣ ዕውቀቱን እና ፍላጎቱን ነው የሚጠቀመው፡፡ ሁሉም ለመግባባት የየራሳቸው ድርሻና ቦታ አላቸው፡፡ በቋንቋ ቋንቋውን ከሚያውቅ ጋር ይግባባል፡፡ በእውቀት ቋንቋውን ከሚያውቅም ከማያውቅም ጋር ቋንቋውንም እውቀቱንም በመጠቀም ይግባባል፡፡ በእውቀት በፍላጎትም ከተግባባው ጋር እየተግባባ ነው የሚኖረው፡፡›› ይህን መሠረት ሐሳብ በመንደርደርያው ውስጥ የያዘው ‹‹ቋንቋ እውቀት አይደለም›› በሚል መጠርያ የታተመው መጽሐፍ ነው፡፡
በአንድነት ኃይሉ የተዘጋጀው መጽሐፍ በዐውደ ቋንቋ ላይ ያጠነጠነ ነው፡፡ ከሰው እስከ ብሔር ምንነት፣ ከብሔር ጭቆና ምንነት እስከ ቋንቋ ባለቤት ጨምሮ በ19 ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሐሳቡን አኑሯል፡፡ ‹‹ቋንቋ እውቀትና ፍላጎት›› በሚል በቀረበው ሐተታ ውስጥም የሚከተሉት ነጥቦች ይገኛሉ፡፡
‹‹በየትኛውም ቋንቋ የትኛውንም ያክል የጠለቀም፣ የመጠቀም ከባህል፣ ከአስተሳሰብ ጋር የተሳሰረ ቢሆን ቋንቋ ቋንቋ ነው፣ እውቀት አይደለም፤ የሰው ልጅ ምንም ዓይነት ቋንቋ ቢኖረው የሚግባባው በቋንቋው ብቻ ሳይሆን በእውቀቱና ፍላጎቱም ነው፡፡ የትኛውንም እውቀቱን ሐሳቡን ለመግለጽ ቋንቋን እንደ ግብዓት ቢጠቀመውም ሐሳቡ ወይም እውቀቱ ቋንቋ አይደለም፡፡ ቋንቋ ሐሳብን ለመግለጽ ግብዓት ሆነ እንጂ ሐሳቡ እውቀት ነው፡፡ አንድን እውቀት ምንም ነገር ሳይቀንስና ሳይጨምር በተለያየ ቋንቋ መግለጽ መቻሉ የሚያሳየው እውቀትና ቋንቋ የተለያዩ መሆናቸውን ቋንቋ ለእውቀት ግብዓት መሆኑን፣ ነገር ግን ሁለቱም ለመግባባት ቢያስፈልጉም ቋንቋ ከእውቀት ማነሱን ነው፡፡
አሁን እየተፈጠረ ያለው የቋንቋ ችግር መንሥኤውንም መጽሐፉ እንዲህ ይገልጸዋል፡፡ ‹‹አንዳንድ ሰው ቋንቋውን ልዩ ማንነቱ አድርጎታል፡፡ ካለው ነገር በላይ ቋንቋው የሚበልጥበት የሚጠቅመው ይመስለዋል፡፡ ሁሉንም ትቶ ቋንቋውን ብቻ እየሆነ ነው የሚኖረው፣ በገንዘብ ስለሆነ የራሱን እውቀት እንኳን ረስቶታል፡፡ ቋንቋ የሚደነቅ ነገር የለውም፡፡ ሁሉም ቋንቋ ስላለው ብቻ ሳይሆን በቋንቋው ተጠቅሞ መኖር የቻለ ስለሌለ ነው፡፡ ቋንቋ ላይ አጥብቆ መሥራት ማንንም አይጠቅምም፡፡ እሱም አገሪቷን፣ አገሪቱም እሱን ታጣለች፡፡ በእውቀት የምትኖር አገር ግብዓት የማይሆናት ምንም ነገር የለም፡፡
እንኳን የሰው ልጅ፣ ሕይወት የሌለውን ነገር ሕይወት ዘርታ ለሕይወት ግብዓት ታደርጋለች፡፡ ስለዚሀ ሁሉም ነገር አስፈላጊና ምክንያት አለው፡፡ የገዛ ማንነቱን ከቋንቋው ጋር ያጣበቀ ሰው ኢኮኖሚያዊ ማኅበራዊና በፖለቲካዊ አጠቃቀሙና አመለካከቱ ከቋንቋ ጋር ስለሚያያይዘው እውቀቱ በጣም የተዛባ ስለሚሆን፣ በፍፁም ለአገር ልማት ግብዓት የመሆን ዕድሉ የጠበበ ነው፤ ይህ ደግሞ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖው በጣም ከባድ ነው፡፡ የአንድ ሰው ብክነት ትልቅ ኪሳራ ነው፡፡›› ይላል፡፡
በ151 ገጽ የተደራጀው መጽሐፍ በ50 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡