Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአገራዊ መግባባት የናፈቀው የሥነ ምግባር ትምህርት 

አገራዊ መግባባት የናፈቀው የሥነ ምግባር ትምህርት 

ቀን:

አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ባደረገች ማግስት ነበር የትምህርት ፖሊሲ ለውጥ የተደረገው፡፡ ፖሊሲው በትምህርት ሥርዓቱ ልዩ ልዩ የትምህርት ዘርፎች እንዲካተቱ አድርጓል፡፡ ከተካተቱም መካከል አንዱ የሥነ ዜጋና የሥነ ምግባር ትምህርት ይገኝበታል፡፡ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ሥራ ላይ ከዋለ የሁለት አሠርታት ዓመታት ዕድሜ አስቆጥሯል፡፡

በትምህርት ሚኒስቴር አጠቃላይ የትምህርት ዘርፍ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ፕሮግራም ዳይሬክተሩ አቶ ዳንኤል አበበ እንደገለጹት፣ የሥነ ዜጋና ሥነ ምግባር ትምህርት ለመጀመርያ ጊዜ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ከአካባቢ ሳይንስ፣ እንዲሁም ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ድረስ ደግሞ ከማኅበራዊ ሳይንስ በውህድ ይሰጥ ነበር፡፡ 1991 እስከ ከ1996 ዓ.ም. ድረስ ደግሞ በዚሁ ስያሜ ለከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መስጠት ተጀመረ፡፡

ይህም ትምህርት በ1998 ዓ.ም. ሲፈተሽ በሚፈለገው ደረጃ ለውጥ ማምጣት የማይችል መሆኑ ተደረሰበት፡፡ በዚህም በአገሪቱ እሴቶች ላይ ትኩረት ያደረገ ጥናት እንዲካሄድ ተደረገ፡፡ በተካሄደውም ጥናትም ወደ 88 የሚሆኑ መሠረታዊ እሴቶች ከኅብረተሰቡ ተለይተው እንዲወጡ ተደረገ፡፡

ነገር ግን እሴቶቹ ስለበዙ ተመሳሳይነት ያላቸውን ወደ አንድ የማምጣት ሥራ ተከናውኖ ወደ 11 ወረዱ፡፡ እሴቶቹ የተጠኑትና ወደ 11 የማምጣቱ ወይም የማጠቃለሉ ሥራ የተከናወነው በተለያዩ መስኮች በተሰማሩ ምሁራን አማካይነት ነበር፡፡

አሥራ አንዱ እሴቶች የዴሞክራሲ ሥርዓት፣ የሕግ የበላይነት፣ እኩልነት፣ ፍትሐዊነት፣ የአገር ፍቅር፣ የኃላፊነት ስሜት፣ ጠንካራ የሥራ ባህል፣ ራስን መቻል፣ የቁጠባ ባህል፣ ንቁ ሕዝባዊ ተሳትፎና ዕውቀትን መሻት ናቸው፡፡ በእነዚህም እሴቶች ላይ ሥርዓተ ትምህርቱ ተዘጋጅቶ እስከ 1996 ዓ.ም. ድረስ ትምህርቱ እንዲሰጥ ተደርጓል፡፡

ይህ ከሆነ ከሁለት ዓመታት በኋላ ማለትም በ1998 ዓ.ም. የተወሰነ ለውጥ መሣጣቱን ለማወቅ የሚያስችል ጥናት ተካሄደ፡፡ ጥናቱ በርካታ ክፍተቶችን እንዳሳየ፣ ከክፍተቶቹም መካከል ትምህርቱ የአንድ ፖለቲካ ድርጅት ፕሮግራም ማስተማሪያና ትምህርቱን የሚያስተምሩ መምህራን ደግሞ የፖለቲካ ድርጅቱ ‹‹ካድሬ›› አድርጎ የመውሰድ ነገር እንደነበር ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

ከዚህም ሌላ የመማሪያ ማስተማሪያ መጻሕፍት በጥራት አለመዘጋጀት፣ ደጋፊ የትምህርት ግብዓት አለመኖራቸው፣ መምህርን በዘርፉ ላይ ትኩረት ያደረገ ሥልጠና አለመወሰዳቸው፣ ፍላጎት ያላቸው መምህራን ብቻ ይሳተፉበት የነበረና በአጠቃላይ ትምህርቱ ባለቤት የሌለው ሆኖ መገኘቱ ከክፍተቶቹ መካከል ተጠቃሾች መሆኑንም ጠቁዋል፡፡

ክፍተቶቹን ለይቶ ባወጣው በዚሁ ጥናት መሠረት በትምህርቱ ዘርፍ ላይ የክለሳ ከ1999 ዓ.ም. እስከ 2002 ዓ.ም. ድረስ የክለሳ ሥራ ተሠራ፡፡ በክለሳውም በጥናት የተለዩ ክፍተቶችን የመሙላት፣ በዋናነትም የማስተካከል ሥራ ተከናወነ፡፡ ትምህርቱ ባለቤት እንዲኖረው የማድረጉ ሥራ ተከናወነ

በዚህም መሠረት በዩኒቨርሲቲዎችና በኮሌጆች ዲፓርትመንቱ እንዲከፈት ተደረገ፡፡ በትምህርት ሚኒስቴር ውስጥ ደግሞ ቴክኒክና ሙያን ጨምሮ የአጠቃላይና ከፍተኛ ትምህርት ዘርፎችን የሚመራ አካል በዳይሬክቶሬት ደረጃ ተመሠረተ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በሁለተኛ ዲግሪ ደረጃ ሁሉ መምህራን እየተመረቁ የሚገኙ ሲሆን፣ ይዓም የነበረውን የመምህራን ክፍተት ለመሸፈን አስችሏል፡፡

ይኸው ክለሳ ምን ያህል ውጤታማ መሆኑን የሚያሳይ በ2008 ዓ.ም. በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ጭምር ሌላ ጥናት ተካሂዶ ነበር፡፡

በጥናቱ በ1998 ዓ.ም. የነበረው ክፍተት አሁንም እንደቀጠለና እንዲያውም መባባሱ የተካተቱት እሴቶች ወይም ይዘቶች ሁሉ በዕውቀት ላይ ብቻ የተመሠረቱ እንደሆኑ፣ በአመለካከት ረገድ በተማሪዎች ላይ ለውጥ ለማምጣት ያለው አቅም ዝቅተኛ ሆኖ እንደተገኘ አቶ ዳንኤል ተናግረዋል፡፡

ተማሪዎች በዚህ የትምህርት ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት የሚያስመዘግቡ ሲሆን፣ በተግባር ግን ሊቀይራቸው አልቻለም፡፡ ጥናቱ ያመላከተው ሌላ ክፍተት የትምህርቱ ይዘቶች አብዛኞቹ ትኩረት የሚያደርጉት በሥነ ዜጋው ላይ ሲሆን፣ በሥነ ምግባር ላይ ግን ክፍተት አለበት፡፡ ተማሪው በመልካም ሥነ ምግባር እንዲቀረጽ ከማድረግ አንጻር የተካተቱት ይዘቶችም በጣም ዝቅተኛ ሆነው ተገኝተዋል፡፡

የትምህርቱ ይዘቶች በአብዛኛው ትኩረት የሚያደርጉት መብት ላይ ብቻ ነው፡፡ ተማሪው ግዴታውን እንዲወጣ ትኩረት አላደረጉም፡፡ በዚህ ትምህርት ብቻ ተካትተው በሚሰጡት ይዘቶች ወጣቱ ውጤት ያመጣል ብሎ መጠበቅ አስቸጋሪ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ወጣት በመልካም ሥነ ምግባር እንዲቀረጽና አገር ተረካቢ ዜጋ እንዲሆን ለማድረግ በአንድ በተወሰነ ተቋም ብቻ ሳይወሰን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ እንደሚባ ጥናቱ አመላክቷል፡፡

የቅንጅት ሥራ አለመሥራት፣ የወላጆች ክትትል ማነስ፣ ወይም ክትትሉ ቀድሞ ከነበረው እየላላ መምጣትና ትምህርቱን ካለው ሥርዓት ጋር የመፈረጅ ሁኔት መታየቱ ጥናቱ ካሳያቸው ክፍተቶች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመው ይህም የሆነው ከግንዛቤ ማነስ የተነሳ እንደሆነም አስታውቀዋል፡፡

ተማሪዎች ስለሙስና አስከፊነት፣ በዕድገትና ልማት ላይ ስለሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ በክፍል ውስጥ በንድፈ ሐሳብ ይማራሉ፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ወይም መሬት ላይ በተግባር የሚያዩት ግን በንድፈ ሐሳብ ከተማሩት ጋር ይጋጭባቸዋል፡፡ ይህም ሠርቼ፣ ደክሜ፣ በማገኘው ገቢ ራሴን፣ ቤተሰቦቼንና አገሬን እለውጣለሁ ብለው እንዳያስቡ ያደርጋቸዋል፡፡

በጥናቱ ተለይተው በወጡት ክፍተቶች ከውጭ አገሮች ተሞክሮ፣ እንዲሁም በዚህ ዓመት መጀመሪያ ወቅት በተካሄደው የትምህርት ንቅናቄ ሳምንት ላይ 600,000 የሚጠጉ የትምህርት ማኅበረሰብ በክፍተቱ እንዲወያዩበት ተደርጓል፡፡

በአገሪቱ ወደ 41,000 የሚጠጉ መምህራን እንዳሉ እነኚህም መምህራን በክፍተቱ ላይ የጋራ መግባባት ፈጥረው ለውጤታማነቱ በባለቤትነት መንፈስ እንዲንቀሳቀሱ ለማድረግ የሚያስችል ሥልጠና እንደተዘጋጀላቸው፣ በዚህም መሠረት ከፍ ብሎ ከተጠቀሱት መምህራን መካከል ለ1300 ያህሉ ከአንድ ወር በፊት አዳማ ላይ የአሠልጣኞች ሥልጠና እንደተሰጣቸው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ ከዩኒቨርሲቲዎች፣ ከኮሌጆች፣ ከትምህርት ሚኒስቴር፣ ከመምህራን የተውጣጡ ባለሙያዎች በጥናቱ ተለይተው በወጡት ክፍተቶች ዙሪያ በሰፊው ከተወያዩ በኋላ የሥነ ምግባርና ሥነ ዜጋ ትምህርት ዘርፍ ላይ የተወሰኑ ማሻሻያዎች አድርገዋል፡፡ በረቂቅ ደረጃ የተከናወነውም ማሻሻያ ሰነድ ሐሳብና አስተያየት እንዲሰጥበት ለ200 ተቋማት ተሠራጭቷል፡፡

ሰነዱ ከተላከላቸው ተቋማት መካከል የክልል ትምህርት ቢሮዎች፣ 36 የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት፣ 40 ዩኒቨርሲቲዎች፣ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይገኙበታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ሰነዱ በመሰብሰብ ላይ ሲሆን፣ በቅርቡ አገራዊ መድረክ ተፈጥሮ አስተያየት እንዲሰጥበት ከተደረገና ከፀደቀ በኋላ ወደ ትግበራ ይገባል፡፡ እንደ አቶ ዳንኤል ማብራሪያ በዚህ ዓይነቱ የትምህርት ዘርፍ ላይ አገራዊ መግባባት መፈጠር አለበት፡፡ ይህም ማለት ወላጆች፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትና ኅብረተሰቡ ሁሉ ሊወያዩበትና ትምህርቱ ወጣቱን ትውልድ በመልካም ሥነ ምግባር በመቅረጽ አገሪቱ በምታካሂደው ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያደርግ የሚችል ዜጋን ለማፍራት ጠቀሜታ እንዳለው አምነው ሊቀበሉት ይገባል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...