Friday, May 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየአምቡላንስ ተደራሽነት እስከምን?

የአምቡላንስ ተደራሽነት እስከምን?

ቀን:

በኢትዮጵያ ተላላፊ ያልሆኑና የሆኑ በሽታዎች ሥርጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንጂ የመቀነስ አዝማሚያ እንደማያሳይ በተለያዩ ጊዜያት የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በከተማና በገጠር ያላቸው ሥርጭት የተለያየ ቢሆንም በስኳር፣ በልብ፣ በካንሰር፣ በሂፒታይተስ፣ በኤችአይቪና በሌሎች በሽታዎች የሚሞቱት ቁጥርም በዚሁ መጠን እየጨመረ ይገኛል፡፡

 ከእነዚህ በሽታዎች ጎን ለጎንም በድንገተኛ አደጋዎች ለከባድ የአካል ጉዳት የሚዳረጉ ሲያልፍም የሚሞቱ ብዙ ናቸው፡፡ በተለይም በትራፊክ አደጋ በርካቶች ለማይካስ ጉዳት ሲዳረጉ፣ ብዙዎች ሕይወታቸው እንዳልነበር ሆኖ ተቀይሯል፡፡ በየዓመቱ ከ4000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በትራፊክ አደጋ ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ ከአሥር ሺሕ በላይ የሚሆኑ ደግሞ ለቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ይዳረጋሉ፡፡

ከአንዱ የጤና ችግር ወይም አደጋ ራስዎን ለማዳን የሚያደርጉት ሙከራ ውጤታማ ቢሆንም፣ በሌላኛው ሊጠቁ ይችላሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት በገዛ ቤትዎ ውስጥ ሆነው እንኳ ከትራፊክ አደጋ ማምለጥ የማችሉበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ግድግዳ ጥሰው መኖሪያ ቤት ውስጥ ዘው የሚሉ ተሽከርካሪዎች፣ መንገድ ስተው የቤት ጣሪያ ላይ የወጡ መኪኖች ለዚህ ዓይነተኛ ማሳያ ናቸው፡፡

- Advertisement -

እነዚህ ሁሉ የጤና ችግሮች ዜጎች ሕይወታቸው በማንኛውም ቅፅበት አደጋ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ማሳያዎች ናቸው፡፡ በዚህ ሰዓት አሥጊ የሚባሉ የጤና ችግሮች ባይኖርበትም ከየት መጣ ሳይባል የሚከሰት ድንገተኛ አደጋ ሰለባ የሚኮንበት አጋጣሚም ጥቂት አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ በተለይም በአዲስ አበባ የሚኖሩ ከሆነ ለተባሉት ችግሮች በተለይም ደግሞ በትራፊክ አደጋ ለሚደርሱ ጉዳቶች ያለዎት ተጋላጭነት ሰፊ ሊሆን ይችላል፡፡

ከአኗኗር ዘይቤ ጋር ተያይዘው የሚከሰቱ የጤና ችግሮችም በከተሞች አካባቢ እየበዛ እንደሚገኝ ሪፖርቶች ያሳያሉ፡፡

ከዚህ አንፃር ማንኛውም የጤና ችግር ወይም ድንገተኛ አደጋ ሰርክ እንደ ጥላ በየአጥናፉ ይከተላል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በስኳር በሽታ አጉል ቦታ ወድቀው፣ የደም ግፊት ድንገት ጨምሮ ወይም ቀንሶ ራሳቸውን ስተው፣ አሊያም ፓራላይዝድ ሆነው ሆስፒታል እስኪደርሱ ሕይወታቸው ያለፈ ቁጥር ቀለል አይደለም፡፡ ሞት አፋፍ ደርሰው የተመለሱም ያጋጥማሉ፡፡ አሊያም ከእነዚህ ሁሉ አደጋዎች ለጥቂት የሚተርፍ ይኖራል፡፡ ነገር ግን አጋጣሚዎቹ በአንድም ይሁን በሌላ ሞት እንደ ጥላ እንደሚከተል ማሳያዎች ናቸው፡፡

ዋናው ነገር እነዚህ ሁሉ ችግሮች እንዳያጋጥሙ መደረግ ያለበት ጥንቃቄና ከደረሱ በኋላም አፋጣኝ መፍትሔ መስጠቱ ላይ ነው፡፡ አደጋዎች በደረሱ ቅፅበት ተጎጂው አፋጣኝ ሕክምና የሚያገኝበትን አማራጭ መፈለጉ ቀዳሚው ተግባር ነው፡፡

አስፈላጊውን የመጀመርያ ዕርዳታ እንዲያገኝ ማስቻል ወሳኝ ሲሆን፣ ይህንን ለማድረግም የአምቡላንሶች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ ከመጀመርው የዓለም ጦርነት ጀምሮ አፋጣኝ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎችን፣ በመርዳት ላይ የሚገኙት የአምቡላንስ መኪኖች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ማገልገል ከጀመሩ ዘመናት አልፏቸዋል፡፡ አፋጣኝ ዕርዳታ የሚያስፈልገውን ታካሚ ይዘው በየጎዳናው እየጮሁና ቀይ መብራታቸውን እያብለጨለጩ ሲከንፉ የማያውቃቸው የለም፡፡

በቅፅበት ውስጥ ልታልፍ የምትችልን ሕይወት የማትረፍ ሚና የሚጫወቱ እነዚህ ነፍስ አድን ተሽከርካሪዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በበቂ አለመገኘታቸው ግን አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተሠራጭተው የሚገኙ አምቡላንሶች ካለው የሕዝብ ቁጥር አንፃር ሲታዩ ቁጥራቸው እዚህ ግባ አይባልም፡፡ የጤና አገልግሎት ሽፋን በበቂ ባልተደረሰባቸው እንደ ሱማሌ ክልል ባሉ ደግሞ ቁጥራቸው እጅግ ዝቅተኛ ሆኖ ይገኛል፡፡

የሶማሌ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ እድሪስ አህመድ እንደሚሉት፣ የክልሉ ነዋሪዎች ኑሯቸውን የሚገፉት ከቦታ ቦታ በመንቀሳቀስ በመሆኑ ያለባቸውን የጤና ችግሮች መፍታት የሚችል ፖሊሲ መቅረፅ ትልቅ ችግር ነው፡፡ ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ተንቀሳቅሶ ተገቢውን የጤና አገልግሎት ለማድረስም ያለው ደካማ የትራንስፖርት መሰረተ ልማት ትልቅ ችግር ነው፡፡ በተለይም ለጉዞ የማይመቹ አቀበታማና ቁልቁለታማ የሆኑ አካባቢዎችን አቋርጦ ገብቶ ተፈላጊውን የጤና አገልግሎት ማቅረብ ደግሞ ይበልጥ ፈታኝ ነው፡፡ እነዚህ ተግዳሮቶች በክልሉ ያለው የጤና ሽፋን ከ60 በመቶ እንዳይበልጥ አድርጎታል፡፡

ቀሪውን ያልተደረሰውን 40 በመቶ የጤና አገልግሎት ክፍተት ለመሸፈንም የክልሉ መንግሥት 29 ተንቀሳቃሽ የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ቡድኖችን አደራጅቶ ወደ ሥራ ከገባ ቆይቷል፡፡ ክልሉ በ93 ወረዳዎችና በስድስት የከተማ አስተዳድሮች የተከፋፈለ ነው፡፡ በክልሉ አገልግሎት የሚሰጡ አምቡላንሶች ቁጥር ግን 143 ብቻ ናቸው፡፡ እነዚህ አምቡላንሶች ናቸው በክልሉ ወደሚገኙ 218 የጤና ተቋማት ህመምተኞችን ይዘው የሚከንፉት፡፡

በእነዚህ የጤና ተቋማት ተሠራጭተው የሚገኙ 143 አምቡላንሶች ቁጥርን ማጣጣም ከባድ ሆኗል፡፡ ስሊዚህም አንዱ አምቡላንስ ለሁለት የጤና ተቋማት ተመድቦ እንዲያገለግል ይደረጋል፡፡ ድርቅ በተደጋጋሚ ጊዜ በሚያጠቃውና ከሌሎቹ የአገሪቱ ክልሎች በተለየ በዕድገት ወደኋላ በቀረው በዚህ ክልል ፈውስን የሚያደርሱ እነዚህ ተሽከርካሪዎች ቁጥር ዝቅተኛ መሆኑ አሳሳቢ ነው፡፡ አቶ እድሪስ እንደሚሉት፣ የክልሉ መንግሥት በዚህ ዓመት 72 አምቡላንሶችን የገዛ ሲሆን፣ 19ኙን ባለፈው ሳምንት ነበር የተረከቡት፡፡ ካለው ፍላጎት አንፃር ግን ይህ ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ያለውን ፍላጎት በበቂ ለመድረስ ተጨማሪ 100 አምቡላንሶቸን በክልሉ ማሠማራት ያስፈልጋል፡፡

ያለው የአምቡላንሶች እጥረት በሱማሌ ክልል በሚገኘው መጠን ሥር የሰደደ ባይሆንም በኦሮሚያና በሌሎች ክልሎችም አሳሳቢ ነው፡፡ የኦሮሚያ ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የጤና ፕሮግራሞች ዳይሬክተሩ ዶ/ር መንግሥቱ በቀለም በዚህ ይስማማሉ፡፡ በክልሉ በጤና ተቋማት የሚወልዱ እናቶችን ቁጥር መጨመር ላይ ያተኮረ ዕቅድ ተይዞ ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ይህም የሆነው እናቶች በብዛት ከወሊድ ጋር በተያያዙ ችግሮች ሕይወታቸውን ስለሚያጡ ይህንን ለማስቀረት ነው፡፡

ንፅሕናው የተጠበቀና በባለሙያ የታገዘ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል የተሠራው ሥራ 70 በመቶ ውጤት ማምጣት ችሏል፡፡ የእናቶችን ሞት ከመቀነስ አኳያ ያሉ ዋና ዋና ችግሮች መካከል ወደ ጤና ተቋማቱ ለመድረስ ያለው የትራንስፖርት ችግርና ርቀት አንዱ ነው፡፡ ከመኖሪያ ቤት ተነስተው ሆስፒታል እስኪደርሱ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ የሚሞቱ እናቶች ጥቂት አለመሆናቸውን ዶክተሩ ይናገራሉ፡፡

እንዲህ ባለ አጋጣሚ ሕይወታቸው የሚያልፍ እናቶች የመጀመርያ ዕርዳታ እየተሰጣቸው ወደ ጤና ተቋም የሚሄዱበት አምቡላንስ በበቂ ቢኖር እንደ ዋዛ ያለፈች ህይወታቸውን መታደግ እንደሚቻል ዕሙን ነው፡፡ እንደ ደም መፍሰስ ያሉ ችግሮች የመጀመርያ ዕርዳታ መስጠት በሚችሉ ባለሙያዎች በቀላሉ መዳን የሚችል ነገር ግን በቀላሉ ለሞት የሚዳርግ ክፉ አጋጣሚ ነው፡፡ 

እንደ ዶክተሩ ገለጻ፣ በክልሉ በሚገኙ 333 ወረዳዎች አንዳንድ አምቡላንስ ተሰቷል፡፡ ለክልሉ ተጠሪ በሆኑ 19 ከተሞችም አምቡላንሶች ተሠራጭተዋል፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ከዓመትና ሁለት ዓመት በፊት ለሁለት የተከፈሉ ወረዳዎች ይገኛሉ፡፡ ወረዳዎቹ ለሁለት ሲከፈሉ አምቡላንሱ የግድ ወደ አንዱ ይሄዳል፡፡ በዚህ ምክንያት አንዳንድ ወረዳዎች አምቡላንስ የላቸውም፡፡

ተጨማሪ አምቡላንሶች ገዝቶ ለእነዚህ አዳዲስ ወረዳዎች ቅድሚያ ሰጥቶ ለማስተላለፍ እንቅስቃሴዎች ተጀምረዋል፡፡ ‹‹በዚህ ዓመት እንኳ 79 የሚሆኑ አምቡላንሶች አከፋፍለናል፡፡ በዚህ ለአዲሶቹ ወረዳዎች ቅድሚያ የተሰጠ ሲሆን፣ ካላቸው የሕዝብ ቁጥር አንፃር ተጨማሪ ለሚያስፈልጋቸው ወረዳዎችም ጨምረን ሰተናቸዋል፤›› በማለት ዶ/ር መንግሥቱ ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም በሕዝብ ተሳትፎና በመንግሥት በጀት ወደ 600 አምቡላንሶች ግዥ እየተፈጸመ ይገኛል፡፡ እያንዳንዱ አምቡላንስ ግምታዊ ዋጋም ከስምንት ሺሕ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ በእነዚህ አምቡላንሶች ውስጥ ሆነው የመጀመርያ ዕርዳታ መስጠት የሚችሉ የሠለጠኑ ባለሙያዎች መኖራቸውን የሚናገሩት ዶክተሩ፣ አሽከርካሪውን ሳይቀር ባለሙያ የማድረግ ዕቅድ መኖሩን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹አንዳንድ አካባቢዎች የጤና ተቋማት ካሉበት ቦታ በጣም ርቀው ነው የሚገኙት፡፡ እናቶች ወደ ጤና ተቋም ሳይደርሱ ሊወልዱ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እንዲህ ባሉ አጋጣሚዎች አምቡላንሱ ውስጥ አስፈላጊውን የሕክምና ዕርዳታ መስጠት የሚችሉ ብቁ ባለሙያዎች ሊኖሩ ይገባሉ፤›› ይላሉ፡፡

ተጨማሪ ይገዛሉ የተባሉት አምቡላንሶች ችግሩን በተወሰነ ደረጃ መቀነስ ቢችሉም ካለው የህዝብ ቁጥር አንፃር ግን በቂ አይደለም፡፡ ‹‹በአንዳንድ ወረዳዎች ከ100,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ይኖራሉ፡፡ አሠፋፈራቸውም በተበታተነ ሁኔታ ስለሆነ ባለው አምቡላንስ ብቻ በቂ አገልግሎት መስጠት አይቻልም፡፡ ቢያንስ በእያንዳንዱ ወረዳ ከሦስት እስከ አራት የሚሆኑ አምቡላንሶች ያስፈልጋሉ፤›› ብለዋል፡፡ ይህ እንዲያውም ካለው ውስን አቅም አንፃር እንጂ፣ በየወረዳው እስከ ስድስት አምቡላንሶች እንደሚያስፈልጉ አክለው ገልጸዋል፡፡

በክልሉ 70 ነባርና አዳዲስ ሆስፒታሎች፣ እንዲሁም 1,336 ጤና ጣቢያዎች ይገኛሉ፡፡ ሆስፒታሎቹ አንዳንድ አምቡላንሶች ያሏቸው ሲሆን፣ ካለው ውስን ቁጥር አንፃር ሲታይ በቂ ሊመስል ይችላል፡፡ ነገር ግን አምቡላንሶች በየጤና ጣቢያውም እንደሚያስፈልጉ ‹‹አንዳንድ ጊዜ ከአንዱ ጤና ጣቢያ ወደ ሌላው ሪፈር ይጻፋል፡፡ በዚያ ጊዜ ታካሚዎችን ፈጥኖ ወደ ሌላው የጤና ተቋም የሚያደርስ አምቡላንስ ያስፈልጋቸዋል፤›› ብለዋል ዶ/ር መንግሥቱ፡፡

እነዚህን ፈጥኖ በመድረስ ፈውስ የሚሰጡ ታካሚዎችን ከሞት አፋፍ የሚመልሱ ተሽከርካሪዎችን በመንግሥት በጀት፣ እንዲሁም እንደ ቀይ መስቀል ባሉ ለጋሽ ተቋማት በጀት ተገዝተው አገልግሎት ላይ ይውላሉ፡፡ በዚህ መሰረት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕዝብ ፈንድ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች የሚያገለግሉ ሁለት አምቡላንሶችን የሰጠው ከቀናት በፊት ነበር፡፡ ቀዳሚ ተግባሩን ሕይወት ማዳን ላይ ያደረገው ቀይ መስቀል ደግሞ በቋሚነት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች አምቡላንሶችን አሠራጭቶ አገልግሎቱን እየሰጠ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ቀይ መስቀል ቢሮ በከተማው አምስት አምቡላንሶችን አሠማርቶ የከተማዋ ነዋሪዎች አስፈላጊውን ሕክምና እንዲያገኙ እያደረገ ይገኛል፡፡ በ907 ነፃ የስልክ ጥሪ የሚቀርብለትን የድረሱልኝ ጥሪ ተቀብሎ ባሉት አራት ጣቢያዎች የሚገኙ አምቡላንሶችን ጥሪው ወደ ቀረበለት አድራሻ ይልካል፡፡

አንደኛው ጣቢያ የሚገኘው ወሎ ሠፈር ሲሆን፣ በዙሪያው የሚገኙ አካባቢዎችን እንዲያገለግል የተመደበ አምቡላንስ መቆያ ነው፡፡ ሌላው በአራዳ ክፍለ ከተማ የሚገኘው ጣቢያ ሲሆን፣ በዚህ ጣቢያ የሚቆመው አምቡላንስ ስሜን ፓርክ አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችን ያገለግላል፡፡ በልደታ ጣቢያ የሚገኘው ደግሞ አዲስ ከተማ፣ መርካቶና ኮልፌ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎችን ያገለግላል፡፡ ሌላው አቃቂ ጣቢያ የሚገኘውና አቃቂ ዙሪያና ንፋስ ስልክ አካባቢ የሚያገለግለው ነው፡፡

በቢሮ የፕሮግራም ክፍል ኃላፊው አቶ በሬሳ ከነአ፣ ‹‹ካለው ፍላጎት አንፃር ያሉት አምቡላንሶች በቂ አይደሉም፡፡ በአንድ ወቅት በከተማዋ አገልግሎት ይሰጡ የነበሩ አምቡላንሶች ቁጥር 10 ደርሶ ነበር፡፡ በእርጅና ምክንያት የተቀሩት አምስቱ ቆመዋል፤›› ይላሉ፡፡

ይህ በአዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን በኦሮሚያም የሚታይ ችግር ነው፡፡ በክልሉ የሚገኙ አምቡላንሶች መንገድ የሌላቸውን መንገዶች ሁሉ አቋርጠው ይሄዳሉ፡፡ በዚህ ጊዜ የመገልበጥና በቶሎ የማርጀት ዕድላቸው ሰፊ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሥራ ፈተው የቆሙ አምቡላንሶች መኖራቸውን፣ ጥገና አድርጎ ተመልሰው ወደ ሥራ እንዲገቡ ከማድረግ አንፃርም ክፍተት መኖሩን ዶ/ር መንግሥቱ ገልጸዋል፡፡

በእርጅና ምክንያት ሥራ ፈተው የቆሙ ተሽከርካሪዎች እንዳሉ ሆነው ‹‹ተጨማሪ እንዲገዛ የተለያዩ የዕርዳታ ድርጅቶችን እየጠየቅን ነው፤›› ይላሉ አቶ በሬሳ፡፡ እሳቸው ይህንን ቢሉም፣ የጠብታ አምቡላንስ መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክብረት አበበ በአገሪቱ ያለው ትልቁ ችግር የአምቡላንስ ቁጥር ማነስ ሳይሆን ያሉትን በአግባቡ አቀናጅቶ መሥራቱ ላይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

‹‹ቄራ አካባቢ የደረሰን የድረሱልን ጥሪ ተቀብሎ በአቅራቢያ የሚገኝ አምቡላንስ እንዲደርስ የሚደረግበት የተማከለ አሠራር የለም፡፡ እኛ አምቡላንሶቻችን የት እንደሚገኙ የምናውቀው በጂፒኤስ ነው፤›› የሚሉት አቶ ክብረት ተቀናጅቶ መሥራት ላይ ያለው ክፍተት ያሉትን ውስን አምቡላንሶች በአግባቡ ከመጠቀም እያደገ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡   

‹‹አምቡላንስ መግዛት እኮ ከባድ አይደለም፡፡ የሚከብደው የተገዙትን አምቡላንሶች ተቀናጅተው የሚሠሩበትን የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት ነው፤›› የሚሉት አቶ ክብረት በካናዳ አንድ አምቡላንስ ወደ ተጠራበት ሥፍራ ለመድረስ ስምንት ደቂቃ፣ በአሜሪካ ደግሞ ስድስት ደቂቃ እንደሚወሰድበት፣ ጠብታ ባደረገው የዳሰሳ ጥናት ደግሞ በኢትዮጵያ አንድ አምቡላንስ ካለበት ተነስቶ አደጋው እስከደረሰበት ቦታ ለመድረስ በአማካይ ውስጥ 30 ደቂቃ እንደሚፈጅ ገልጸዋል፡፡

ካለው የትረፊክ መጨናነቅ ጋር ተዳምሮ አምቡላንሶቹ በተባለው ቦታ በፍጥነት እንዳይደርሱ፣ ማኅበረሰቡም በእነሱ ላይ እምነት እንዳይኖረው እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህ የፈጠረው ክፍተትም ሥራ ፈተው የሚውሉ አምቡላንሶች እንዲበዙ፣ አሊያም ለሌላ ተግባር እንዲጠመዱ መንገድ እየከፈተ ይገኛል፡፡ ለዚህም በሽተኛ የጫነ አስመስሎ ጎዳና ላይ ሲከንፍ የነበረውና በተደረገበት ማጣራት የጫነው ሕመምተኛ ሳይሆን ኮንትሮባንድ ሆኖ የተገኘውን የቀይ መስቀል አምቡላንስ ማሳያ ይሆናል፡፡

ወደ ሥራ ከገባ አሥር ዓመታትን ያስቆጠረው ጠብታ አምቡላንስ 13 አምቡላንሶች አሉት፡፡ ሁለት የሞተር አምቡላንሶችንም አሠማርቷል፡፡ በቀን እስከ 50 ሰዎችን የሚያገለግል መሆኑን የሚናገሩት አቶ ክብረት ማንኛውም አስቸጋሪ መንገድ አልፈው የመጀመርያ ዕርዳታ እንዲሰጡ ወደ ሥራ የገቡት ሞተር ሳይክሎች ግን የታሰበውን ያህል መሥራት አለመቻላቸውን ይናገራሉ፡፡

‹‹በእኛ አገር ዋነኛው የድንገተኛ አደጋ መንስኤ የትራፊክ አደጋ ነው፡፡ የወደቀን ሰው ማንሳት በራሱ ሌላ ሳይንስ ነው፡፡  ነገር ግን እኛ እስክንደርስ ሰዎች ተጎጂውን አፋፍሰው፣ ጨባብጠውና ቆልምመው ስለሚያነሱት የምንደርሰው ጉዳቱ የከፋ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ነው፤›› የሚሉት አቶ ክብረት በቀላል ሕክምና መፍትሔ ሊገኝላቸው በሚችል አደጋ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳያጡ ፈጥነው የሚደርሱ አምቡላንሶችን በየቦታው ማስቀመጥ እንደሚያስፈልግ፣ ለዚህም የተማከለ አሠራር መኖር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ዘርፍም ራሱን የቻለ ጥናት ተደርጎ አስፈላጊው የመፍትሔ ዕርምጃ መወሰድ እንዳለበት ‹‹እንደ ኤችአይቪና ሌሎች ማኅበራዊ ችግሮች ፈንድ የለውም፡፡ ስለዚህ ጥናት የሚያደርግ፣ የማማከር አገልግሎት የሚሰጥ በዚህ ዘርፍ የተሠማራ አንድም ድርጅት የለም፡፡ ወይም ጥናት አድርግልኝ ያለ የለም፤›› በማለት የተዘነጋ ነገር ግን አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ያሉትን አምቡላንሶች በተገቢው መጠን ከመጠቀም አንፃር ከሚያስፈልገው የተማከለ አሰራር በተጨማሪ ማህበረሰቡ አስፈላጊውን ትብብር ማድረግ ይኖርበታል፡፡ መንገድ ቅድሚያ ከመስጠት ጀምሮ ሌሎችም ሀላፊነቶቹን ሊወጣ ይገባል፡፡ ‹‹ባለው ነፃ የስልክ መስመር ደውለው የሚቀልዱ ብዙ ናቸው፡፡ ብዙዉን ጊዜ አገልግሎታችንን የሚፈልጉ ሰዎች መስመራችን በእነዚህ ሰዎች ስለሚያዝ አያገኙንም፤›› ያሉት አቶ በሬሳ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...