Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የመቃወምም ሆነ የመደገፍ ጉዳይ የኢትዮጵያዊያን ብቻ ነው››

‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የመቃወምም ሆነ የመደገፍ ጉዳይ የኢትዮጵያዊያን ብቻ ነው››

ቀን:

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ

በመላ አገሪቱ ለስድስት ወራት የተጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የመቃወምም ሆነ የመደገፍ ጉዳይ የኢትዮጵያዊያን እንደሆነ ተገለጸ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ሐሙስ የካቲት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ ሲሰጡ እንደተናገሩት፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የመደገፍም ሆነ የመቃወም ጉዳይ የኢትዮጵያዊያን ብቻ ነው፡፡

አገሪቱ በጣለችው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና በአገሮች ተቃውሞ ላይ ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ቃል አቀባዩ፣ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ የኢትዮጵያውያን እንጂ የሌላ አገር ጉዳይ አይደለም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹በአገር ቤት የምናደርገውን ነገር በተመለከተ ሞግዚት አያስፈልገንም፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጠቅላላ ጉባዔ ፕሬዚዳንት ሜሮስላቭ ላጃካክ በኢትዮጵያ ጉብኝት እያደረጉ እንደነበር፣ የፕሬዚዳንቱ ወደ አዲስ አበባ መምጣት ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር የሚያያዝ እንደሆነ አቶ መለስ በጋዜጠኞች ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹የእሳቸው መምጣት ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አይገናኝም፤›› ብለዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት በዋናነት በሦስት ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥን እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የመጀመርያው ጉዳይ ኢትዮጵያ በተመድ የሰላም ማስከበር ሒደት ውስጥ እያደረገች ባለው አስተዋፅኦ ምሥጋና ለማቅረብ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ አሥራ ሁለት ሺሕ የሰላም አስከባሪዎችን በተመድ የሰላም ማስከበር ሥር አሰማርታ እንደምትገኝ የጠቆሙት አቶ መለስ፣ አገሪቱ በዓለም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ኃይል ያሰማራች በመሆኑ በዓለም መንግሥታት ዘንድ ምሥጋና እየተቸራት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ሁለተኛው ጉዳይ ከስደተኞች ጋር የተያያዘ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ ከስምንት መቶ ሺሕ በላይ ስደተኞችን አስጠልላ የምትገኝ አገር እንደሆነች፣ ይህም በተመድ ከፍተኛ ምሥጋና ያስገኘላት መሆኑን አቶ መለስ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ስደተኞችን በተመለከተ የክፍት በር ፖሊሲ ትከተላለች፤›› ያሉት አቶ መለስ፣ በዋናነት ከኤርትራ፣ ከሱዳን፣ ከሶማሊያና ከሌሎች አገሮች የሚመጡ ስደተኞችን ተቀብላ እንደምታስተናግድ አስረድተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት ምክንያት ከሆናቸው መካከል ሦስተኛው ጉዳይ ከዘላቂ ልማት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ቃል አቀባዩ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የተለያዩ አገሮች እየተቃወሙት ከመሆኑ አኳያ ለአገሪቱ ሊኖረው የሚችለውን አሉታዊ ተፅዕኖ እንዲያብራሩ ከጋዜጠኞች ቢጠየቁም፣ ዝርዝር ማብራርያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ቃል አቀባዩ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ከጠቀሷቸው ጉዳዮች መካከል የሩሲያና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣትን የተመለከተው ይገኝበታል፡፡ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከየካቲት 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅትም ሁለቱ አገሮች በመካከላቸው ያለውን ግንኙነት ይበልጥ ለማጠናከር ቃል የሚገቡበት እንደሚሆን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሩሲያ የሁለትዮሽ ግንኙነት ከጀመሩ 120 ዓመታትን እንዳስቆጠሩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ሁለቱ አገሮች በትምህርት፣ በሳይንስ፣ በግብርናና በሌሎችም ዘርፎች በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት እንደተፈራረሙም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በሌላ በኩል የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ አብዱላሒ ቢን ዘይድ አል ናህያን ከየካቲት 26 እስከ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በኢትዮጵያ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ተገልጿል፡፡ የካቲት 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ሚኒስትሩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር ተገናኝተው ውይይት እንደሚያደርጉም ተጠቁሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...