‹‹አስተውሎ የማይራመድ ካሰበበት አይደርስም›› የሚባል አገራዊ ነባር አባባል አለ፡፡ ሰፋና ዘርዘር ተደርጎ ሲታይ ካሰቡበት አለመድረስ ብቻ ሳይሆን የከፋ አደጋ ሊያጋጥም እንደሚችል ግልጽ ነው፡፡ ይህንን ጉዳይ ከግለሰባዊ ዕይታ ወጣ አድርገን አገራዊ ገጽታ ስናላብሰው፣ አገሪቱን ከገጠሟት ዘርፈ ብዙ ችግሮች አንፃር በስፋት ያነጋግራል፡፡ አገሪቱ ላለፉት ሁለት ዓመታት በላይ ከገባችበት ቀውስ እንድትወጣ የጋራ የሆነ ዓላማና ግብ ሊኖር ሲገባ፣ በወገናዊነትና በቡድንተኝነት ላይ የተንጠላጠሉ እሰጥ አገባዎችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ አገር የሚበጃት ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ነው ሲባል በምኞት የሚገኝ ምንም ነገር የለም፡፡ ይልቁንም በሰከነ መንገድ በሰጥቶ መቀበል መርህ ለሚያምነው ዴሞክራሲያዊ ባህል መገዛት ያስፈልጋል፡፡ አንዱ ወገን በጉልበት እኔ ያልኩት ካልሆነ እያለ ሲደነፋ፣ ሌላው ደግሞ በመቃብሬ ላይ ነው እንጂ ብሎ ያዙኝ ልቀቁኝ ሲል የምትጎዳው አገር ናት፡፡ ሕይወቱ ለአደጋ የሚጋለጠው ሕዝብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን በእጅጉ የጎደላት ለሐሳብ ነፃነት ዕውቅና መነፈጉ ነው፡፡ ከየትም አቅጣጫ ይነሳ የሐሳብ ነፃነት ካልተከበረና ለመነጋገርና ለመደራደር ምኅዳሩ ከሌለ፣ ጽንፈኝነት እየበረታ መካረርና መተናነቅ ወደ በለጠ ጥፋት ያመራል፡፡ ፍላጎትን በኃይል ለማስፈጸም የሚደረግ ነውጥ ደግሞ ውጤቱ ምን እንደሆነ ከዚህ ቀደም ከመጠን በላይ ለማየት ተችሏል፡፡
በተደጋጋሚ ለመግለጽ እንደሞከርነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ካሉት አኩሪ ፀጋዎች መካከል ዋናው አስተዋይነቱ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ግን አወቅን በሚሉት ዘንድ ከሚያስተውለው ይልቅ በደመነፍስ የሚመራው በመብዛቱና ጭፍንነት በማየሉ አገር ከባድ ችግር ውስጥ እየገባች ነው፡፡ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወደ ሌላ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመሸጋገር ሰላም ለማስፈን የሚደረገው ጥረት፣ አገሪቱ ምን ያህል ችግር ውስጥ መውደቋን አመላካች ነው፡፡ አንፃራዊው ሰላምና መረጋጋት ጠፍቶ አገር አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅባት፣ በመግባባት የጋራ ዘላቂ ሰላም እንዲመጣ ከመቼውም ጊዜ በላይ መትጋት ይገባ ነበር፡፡ ዘላቂ ሰላምና ዴሞክራሲ ሊኖር የሚችለው የአገር ጉዳይ የሚያገባቸው ወገኖች በሙሉ በኃላፊነት ስሜት ግዴታቸውን ሲወጡ ነው፡፡ ይህ እንዳይሆን ግን አስተዋይነት ጠፍቶ አገሪቱ የሚለበልባትን እሳት ለማጥፋት መከራ ታያለች፡፡ አገሩን የሚወድ ማንኛውም ቅን ዜጋ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ መስጠት ያለበት ለአገሩ ህልውና ነው፡፡ ከሥልጣንም ሆነ ከሌላ ጥቅማ ጥቅም በላይ አገር እንዳለች አለማሰብ በሽታ እንጂ ሌላ ሊባል አይችልም፡፡ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚገኙ ወገኖች ማስተዋል የጎደለው ወገናዊነትና ቡድንተኝነት መሥርተው በአገር ኪሳራ ልዩነቶቻቸውን ለማወራረድ ከሞከሩ፣ በታሪክም በትውልድም እንደሚጠየቁ ሊያስቡበት ይገባል፡፡ አገር የመሰሪዎች በቀል ማወራረጃ ወይም በሥልጣን ጥም የተቃጠሉ ወፈፌዎች መጫወቻ አይደለችም፡፡ ይህ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብም መቀለጃ አይደለም፡፡
አስተዋይነት የተሞላበት ፖለቲካ ቅድሚያ የሚሰጠው ለቀውስ አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ ለዓመታት የተዳፈነው የፖለቲካ ምኅዳር እንዴት እንደሚከፈትና ሥልጡን የሆነ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሒደት የሚጀመርበትን መንገድ ማመላከት ነው፡፡ ከሥልጣን በፊት የሕግ የበላይነት ተከብሮ የመንግሥት ሥልጣን ልጓም እንዲበጅለት፣ የተልፈሰፈሱት ዴሞክራሲያዊ ተቋማት ነፍስ እንዲዘሩ፣ እጅና እግራቸውን የተያዙት ሲቪክ ማኅበራት ተጠናክረው እንዲወጡ፣ የዜጎች የመነጋገርና የመወያየት ባህል እንዲጎለብት፣ በሕግ ዋስትና ያገኙ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ መደላድል መፍጠር፣ የሐሳብ ልዩነትን ማክበር፣ ወዘተ. የሠለጠነ ማኅበረሰብ ለመገንባት ይጠቅማሉ፡፡ ከዚህ ውጪ በተገኘው የመገናኛ ዘዴ ወጣቶችን በመኮርኮር ለጥፋት ማሰማራት ውጤቱ ዕልቂትና ውድመት ነው፡፡ በዚህ ዓይነቱ የጥፋት መንገድ ተጉዞ ዴሞክራሲን ያሰፈነ አገር በዚህ በሠለጠነ ዘመን ታይቶ አይታወቅም፡፡ ይልቁንም የባሱ አምባገነኖችንና ሥርዓተ አልበኞችን በመፈልፈል አገር ማውደም ነው የሚከተለው፡፡ አስተውሎ አለመራመድ ማለት ይኼ ነው፡፡
የአገሪቱ ፖለቲካ እልህና ግትርነት ከመጠን በላይ ስለሚጫኑት አማካይ የሚባለው ሥፍራ እየጠፋ ነው፡፡ ነጩን ወይም ጥቁሩን እንጂ ግራጫውን ማየት አልተቻለም፡፡ ሁለት ጽንፍ የረገጡ አመለካከቶችን በማግባባት ወደ ውይይትና ድርድር ከማምጣት ይልቅ፣ ዳር ቆሞ ይለይላችሁ ማለት የቀለለ ነው፡፡ ከሁለት ጎራዎች ውጪ የራሳቸው አመለካከት ያላቸው ወገኖች አደባባይ ቢወጡም ተሰድበውና ተዋርደው ነው ወደ መጡበት የሚመለሱት፡፡ በማኅበራዊ ሚዲያዎች ውስጥ በስፋት የሚታዩት ጽንፈኛ ድጋፎችና ተቃውሞዎች ከአስተዋይነት ጋር የተጣሉ በመሆናቸው፣ ከቆሙለት ቡድን ዓላማ በላይ የሆነው የአገር ህልውና ጉዳይ አያሳስባቸውም፡፡ አገር ዘመናትን የተሸጋገረችው በፈታኝና በአደገኛ ጎዳናዎች ላይ በመረማመድ መሆኑን የመገንዘብ አቅም ያጡ ግለሰቦችና ቡድኖች፣ ኃላፊነት በጎደለው ድርጊታቸው አስተዋይነትን እየሳቱ ነው፡፡ በጣም የሚገርመው ደግሞ የሕግ የበላይነት በተከበረባቸው የዴሞክራሲ አገሮች ውስጥ እየኖሩ፣ ደም የሚያፋስስና አገርን የሚያፈርስ ቀረርቶ ማሰማታቸው ነው፡፡ ይህንን አውዳሚ ቅስቀሳ በደመነፍስ የሚከተሉ ደግሞ ለጥፋት ሲነሱ፣ ውጤቱ የምናውቀው አሳዛኝ የንፁኃን ሞትና የደሃ አገር ጥሪት ውድመት ነው፡፡
ለዚህች ታሪካዊትና የተከበረች አገር የሚያስቡ ዜጎች በአስተዋይነት ሊሞሉ ይገባል፡፡ የአገር ጉዳይ አንዴ ካመለጠ መመለሻው ከባድ ነው፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ፣ የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች የአገር ኃላፊነት አለባቸው፡፡ አገር የሚያስተዳድረው መንግሥት ደግሞ አገሪቱ እዚህ ደረጃ እንድትደርስ ለተጫወተው አሉታዊ ሚናም ኃላፊነት አለበት፡፡ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖረው ይህ ጨዋና ማስተዋልን የታደለ ሕዝብ አገሩ እየተመሰቃቀለችና ሕይወቱም አደጋ ውስጥ እየወደቀ መቀጠል የለበትም፡፡ ይህ የተከበረ ሕዝብ የሚያስፈልገው ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ነው፡፡ በገዛ አገሩ በነፃነት እየኖረ በእኩልነት የሚተዳደርበት ሥርዓት ነው የሚያስፈልገው፡፡ ኃላፊነት የማይሰማቸውና ከሥልጣን በላይ አገር የምትባል የጋራ ቤት መኖሯን የዘነጉ፣ ወይም እያወቁ እንዳላወቁ የሚሆኑ አስመሳዮች መጫወቻ መሆን የለባትም፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ዴሞክራሲ በምልዓት ሊሰፍን የሚችለው በግምት ወይም በይሆናል ሥሌት ሳይሆን፣ የዴሞክራሲን መሠረታዊ ምሰሶዎች ተግባራዊ በማድረግ ብቻ ነው፡፡ የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነው ሕዝብ ሲከበርና ሲደመጥ ብቻ ነው፡፡ ሥልጣን የሚገኘውም በጠመንጃ አፈሙዝ ወይም በግርግር ሳይሆን፣ በነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ያለበለዚያ ‹‹አርሜ ከርክሜ የሎሚ ዘንጌን፣ መልከኛ ወሰዳት ወይ ገባር መሆን፤›› የሚለውን አገራዊ ብሂል በዚህ ዘመን ማንጎራጎር ይከተላል፡፡ ይህ ደግሞ የውድቀት ማሳያ ነው፡፡
ኢትዮጵያችን ከዚህ ውጥንቅጥ ውስጥ ወጥታ የሰላምና የዴሞክራሲ አገር እንድትሆን የሚፈልግ ማንኛውም ቅን ዜጋ፣ ከምንም ነገር በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ለሰላም መሆኑን መጠራጠር አይገባም፡፡ ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት ነው፡፡ ሰላምን የማስፈን ጥረትም የአንድ ወገን ብቻ ሳይሆን ሕዝብን ማዕከል ያደረገ የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ የሚፈልግ ነው፡፡ ይህ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ በሕግ ዋስትና ያገኙ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ፣ ዜጎች በነፃነት ተዘዋውረው እንዲሠሩና ሀብት እንዲያፈሩ፣ የሥልጣንም ሆነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እኩልነት እንዲፈጠር፣ የተለያዩ አመላካከቶች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ፣ ሕገወጥነትና ማናለብኝነት አደብ እንዲገዙ፣ የአንድ ጎራ የበላይነት አባዜ በሕግ እንዲገደብ፣ በፖለቲካ ምኅዳሩ ውስጥ ሁሉም ተፎካካሪዎች በነፃነት የሚወዳደሩበት ዕድል እንዲፈጠር፣ ለብሔራዊ መግባባት የሚረዱ መድረኮች በስፋት እንዲኖሩ፣ ከስሜታዊነት ይልቅ ምክንያታዊነት እንዲጎለብት፣ ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶችና ብልሹ አሠራሮች እንዲወገዱ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት መርህ እንዲሆኑ፣ በሕዝቡ ውስጥ ያሉት የአንድነትና አብሮ የመኖር ፀጋዎችና እሴቶች ይበልጥ እንዲጎለብቱ፣ በሕዝብ መካከል መጠራጠርና ጥላቻ የሚዘሩ እንዲታቀቡ፣ ለታሪካዊ ጠላቶች መግቢያ ቀዳዳ የሚከፍቱ ተላላኪዎች አደብ እንዲገዙ፣ ወዘተ. መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ውጪ አገርን ለማተራመስና ሕዝብን የማይወጣበት ቀውስ ውስጥ ለመክተት የሚደረጉ፣ ከዚህ ቀደም ተሞክረው ፈተና የወደቁ ከንቱ ድርጊቶች አይጠቅሙም፡፡ በዚህ ወሳኝ ጊዜ የሚፈለገው አስተዋይነትና አርቆ አሳቢነት ነው፡፡ ምክንያታዊነት ነው፡፡ ይህንን ማድረግ ካልተቻለ ግን በማስተዋል መራመድ የማይችል እግር ሕዝቡንም አገሪቱንም ወደ ዘንዶ ጉድጓድ ከማድረስ የዘለለ ፋይዳ አይኖረውም!