የዓድዋ ድል 122ኛ በዓል ዓርብ የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ም. በመላ አገሪቱ ተከበረ፡፡ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. ከወራሪው የጣሊያን ሠራዊት ጋር ታላቁ ጦርነት በተካሄደባቸው የዓድዋ ተራሮች በዓሉ በከፍተኛ ሥነ ሥርዓት የተከበረ ሲሆን፣ በአዲስ አበባም በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ የጥንታዊት ኢትዮጵያ አርበኞች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት ተከብሯል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ድሪባ ኩማ በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገኝተው የዓድዋ ድል የኢትጵያዊያን ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ሕዝቦች መሆኑን ንግግር አድርገዋል፡፡ የዓድዋ ድል ጀግኖች ኢትዮጵያዊያን በአንድ የአውሮፓ ቅኝ ገዥ ላይ የተጎናፀፉት ታሪካዊና አንፃባራቂ ድል ስለሆነ፣ ዘንድሮ የበርካቶችን ትኩረት ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ስቧል፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ አደባባይ በ122ኛው የዓድዋ ድል በዓል ላይ የተገኙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችም ለዚህ ታሪካዊ የድል በዓል ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር አስተያየታቸውን ሲሰጡ ተደምጠዋል፡፡