‹‹በጨው ገደል ብልኅ ያለቅሳል፣ የዋህ ይልሳል››፡፡ ‹‹ጨው ሆይ ለራስህ ስትል ጣፍጥ አለያ ድንጋይ ነህ ብለው ይጥሉሃል››፡፡ እነዚህን ምሳሌያዊ አባባሎች ያስታወሰኝ ሪፖርተር ጋዜጣ ነው፡፡ ጋዜጣው በርዕሰ አንቀጹ፣ በተለይም በፖለቲካ ዓምዱ የሚያቀርባቸውን የየወቅቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና አስተዳደራዊ መረጃዎችና በመረጃዎቹም ላይ በመንተራስ የሚያቀርባቸውን ትንታኔዎች፣ ከዚያም በመቋጫነት የሚለግሳቸውን የችግሮች መፍቻ መፍትሔ ሐሳቦች ሳነብ፣ ‹‹መንግሥታችንን ምን ነካው!›› የሚል ግርምት ይጭርብኛል፡፡
የጨው ገደል እየተናደ ነው፡፡ ጨው ጥፍጥናውን እያጣ ነው፡፡ በጨው ልማታዊ መንግሥታችን መራሔ መንበር ላይ የተቀመጡት የሥልጣን ባላደራዎችን ምን ነካቸው? የሥልጣን ምንጭና ባለቤት ሕዝብ፣ በምርጫ ሳጥን የድምፅ ብልጫ የሰጣቸውን አደራ ማክበርና ማስከበር ምነው ተሳናቸው?
መርጦ ለሥልጣን አብቅቶናል እያላችሁ የምትናገሩለት ሕዝብ እኮ በየቀኑ እየሞተ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽንና አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሳይቀሩ፣ በሕዝብ የፖለቲካ ጥያቄ የተነሳ በየቀኑ የሚሞተውን፣ ምናልባትም የነገዎቹን የሞት ተረኞች ጉዳይ በየዕለቱ እያረዱን ናቸው፡፡
ሪፖርተር ጋዜጣ በተለይ፣ በረቡዕ የካቲት 7 ቀን 2010 ዓ.ም. ዕትሙ ያወጣውን ርዕሰ አንቀጽ፣ ባለሥልጣናቱ ሳትነቡት እንዳልቀራችሁ እገምታለሁ፡፡ በርዕሰ አንቀጹ ትንታኔና የመፍትሔ ሐሳብ ውስጥ ‹‹እንዲህ ነው እንዲያ ነው!›› ብሎ ማለት፣ አጉል ነገር ስለሚሆን፣ ደግሜ ደጋግሜ እንድታነቡት እላለሁ፡፡
‹‹ልርዳሽ ቢሏት፣ መጇን ደበቀች›› እንደተባለላት የዋህ አገልጋይ አትሁኑብን፡፡ አገርን ከጥፋት፣ ንብረትን ከውድመት፣ ሕዝብን ከስደት እናድን፡፡ ወንድሞቻችን ለእኛም ለእናንተም ስትሉ ጣፍጡ፡፡ ካልጣፈጣችሁ ያው ጨው መሆን አይቀሬ ነው፡፡ ከተደማመጥን፣ አሁንም ቢሆን ጊዜ አለን፡፡ አልረፈደም፡፡
‹‹ጆሮ ምነው አታድግም ቢሉት ይህን ሁሉ ጉድ እየሰማሁ እንዴት ልደግ አለ፤›› ይባላል፡፡ ከማያድግ ከማይሰማ ጆሮ ይሰውረን፡፡ የምሰናበተው፣ እኛና ሪፖርተር ጋዜጣ የጨው ገደል መናዱ እያስለቀሰሰን ነንና መላሳችሁን ተወት አድርጋችሁ አላቅሱን በማለት ነው፡፡
- (አባ ገንባው ዘቦሌ፣ አዲስ አበባ)
*********
ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍን የሕዝብ ጥያቄ ይመለስ
ሰላም በቃላት ብቻ አይምጣም፡፡ ለሰላም መሠረታዊው ነገር የሕዝብን ችግር በቅድሚያ መፍታት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየተከሰቱ ያሉ ችግሮችና የኅብረተሰቡ ጥያቄዎች በአግባቡ ካልተመለሱ፣ ወደ አስከፊ አቅጣጫ ያመራሉ፡፡
ይህ እንዳይከሰት የሕዝብን እሮሮ በአንክሮ እያዳመጡ፣ ተግባራዊ መፍትሔ እየሰጡ መጓዝ ለሰላም ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ጠንከር ያለ ሕዝባዊ ውይይት ማካሄድ፣ መነጋገር፣ መተሳሰብ፣ መማማር፣ በአንድነት ሆኖ ችግሮችን በግልጽ ለመፍታት መጣር ለአገር አንድነትና ሰላም ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡
በጉልህ የሚታዩ የኅብረተሰቡ ቅሬታዎችና ችግሮች፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ለመኖር የተገደደው ሕዝብ፣ በኑሮ ውድነት፣ በመጠለያ ችግር፣ ሠርቶ ለፍቶ በቂ ደመወዝ ለማግኘት ባለመቻል፣ በስፋት ተንሰራፍቶ በሚታየው ብዝበዛ ወይም ዘመናዊ ባርነት፣ የሠራተኛውን መብት ካለመጠበቅ በሚመነጩና በአገራችን ሕግ መሠረት የድሃውን መብትና ነፃነት ካለማስጠበቅ የተነሳ በርካቶቻችን ለረሃብና ለበሽታ ተጋልጠን እንገኛለን፡፡
መንግሥት የዜጎችን መብትና ነፃነት የማክበርና የማስከበር ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ በተለይም በጥበቃ ሥራ ላይ የተሰማራን ሰዎች ከአቅም በላይ የሆነ ብዝበዛና የመብት ረገጣ እየተፈጸመብን አማራጭ በመጣታችን ሳቢያ ግን በአደባባይ እየተበዘበዝን እንገኛለን፡፡ የጥበቃ ሠራተኛ የሰው ሕይወትና ንብረት የመጠበቅ ከፍተኛ ኃላፊነት አለበት፡፡ ይህ ሁሉ ግን ግምት ውስጥ አልገባም፡፡ በአገራችን ከተከሰተው የኑሮ ውድነት ጋር ተዳምሮ መረጋጋት የለም፡፡ ስለሆነም መንግሥት የአገሩን ሕግና ደንብ መሠረት በማድረግ በእኛ ዓይነቶቹ ሠርቶ አደሮች ላይ የሚደረገውን ብዝበዛ መቆጣጠር ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲሆን በሕዝቦች መካከል ፍቅር፣ ሰላምና መረዳዳት ይሰፍናል፡፡
ሌላው የተጀመረው ልማትና ግንባታ ቀላል አይደለም፡፡ መንግሥታችን ማኅበራዊ ችግሮችን ለመቅረፍ ከፍተኛ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ በጤና፣ በትምህርት መስክ የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችንና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን በማስፋፋት በኩል ትልቅ የልማት ዕርምጃ ተራምዷል፡፡ በትራንስፖርት በኩል ያለውን ችግር ለማስወገድ ቀላል ባቡርና ቢሾፍቱ አውቶቡሶችን ለሕዝቡ የመጓጓዣ አገልግሎት እንዲሰጡ እያደረገ ነው፡፡
ለልማቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ለመገደብ ያደረገው ድካምና ጥረት በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ስለሆነም ግድቡ የሕዝቦችን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት ለማምጣት ታላቅ የኃይል ምንጭ ከመሆኑም በላይ ለልማት ትልቅ ድርሻ አለው፡፡ ከአግሮ ኢንዱስትሪ ወደ ከፍተኛ ኢንዱስትሪ ለመሸጋገር ሰፋፊ ወንዞችን በመገደብ ታላቅ የኃይል ምንጭ ይፈጠራል፡፡
ይሁን እንጂ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት፣ መንግሥታችን የሕዝቦችን ችግር ወይም እሮሮ በተለይም በየጊዜው እየተከሰተ ያለውን የኑሮ ውድነትና የመጠለያ ችግር መቅረፍ ይጠቅበታል፡፡ ከዚህም ሌላ በከተማችን አዲስ አበባ ጎልቶ የሚታየውን ጉልበት ብዝበዛ በተቻለ አቅም በመቀነስና በመቆጣጠር ለአገራችን የተመጣጠነ ዕድገትና ሰላም ይራመድ እላለሁ፡፡
- (ከዘበኛው አንደበት)
*****
የችግሩ ሰለባ የሆኑ ዜጎች የመፍትሔው አካል ይደረጉ
የኢሕአዴግ መንግሥት በአገሪቱ ለታየው መጠነ ሰፊ ችግር ዋነኛ ምክንያት ራሱን በማድረግና ራሱን ተጠያቂ ነኝ ብሎ ባስቀመጠው መሠረት በተግባር እያሳየ ያለው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነው፡፡ እስረኞችን በመልቀቅ የወሰደው ዕርምጃ እሰየው ያስብላል፡፡
በጥልቅ ተሃድሶ ታየ ከተባለው በላይ እጅግ ከፍተኛ ግፍና በደል በአስፈጻሚው የመንግሥት አካል በኩል በዚች አገር ዜጋ ላይ ደርሶበታል፡፡ በመልካም አስተዳደር ችግር አበሳውን ያየው ተገልጋዩ የኅብረተሰብ ክፍል ብቻ ሳይሆን፣ በየመንግሥት ተቋማት ውስጥ ተቀጥሮ በቅንነት ሲያገለግል የቆየው ሠራተኛ ጭምር መሆኑን ግን መንግሥት የተገነዘበው አይመስልም፡፡
በመርኅ ተመርኩዞ፣ በቅንነትና በእውነት የመሥሪያ ቤቱን ተልዕኮ ለማስፈጸም የድርሻውን ለመወጣት በሐቅ ስላገለገለ ብቻ እንደጠላት እየተቆጠረ ከራሱ አልፎ በቤተሰቡ ላይ ግፍ የደረሰበት የመንግሥት ሠራተኛ በጣም ብዙ ነው፡፡
በጥቅም በተዘረጋ መረብ የሐሰት ክስ እየቀረበበት፣ በግምገማ ሰበብ ከየተቋማቱ ከሥራ ገበታቸው የተባረሩ ሠራተኞችን ጉዳይ መንግሥት ቆም ብሎ ማጣራት ይጠበቅበታል፡፡ ለምሳሌ በማዕከላዊ መንግሥት ደረጃ አንድ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በዚህ መሰል በደል ደርሶብናል የሚሉ በክልልም ሆነ በፌዴራል መሥሪያ ቤቶች ውስጥ (ፖሊሲና መከላከያ መሥሪያ ቤቶች ጨምሮ) ሲሠሩ የነበሩ ዜጎችን አቤቱታ ቢቀበልና ጉዳያቸውን ቢያጣራ የሚከተሉትን ጠቀሜታዎች ሊያስገኝለት ይችላል፡፡
- በስግብግብና አልጠግብ ባይ ሹመኞች የተደራጀ የጥቅም መረብ ተጋልጦ ይበጣጠሳል፤
- ያለ ኃጢያታቸው ከሥራ ገበታቸው ተባረው ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸውን በመካስ ቅሬታን ያጠፋል፤
- የጥቅመኛው ቡድን መረብ አባል በመሆን በስውር መሥፈርት ያለችሎታቸው የተሾሙትን ያስወግዳል፤
- በዚህ አገር ውስጥ ይህን መሰል የመልካም አስተዳደር ችግር ዳግመኛ እንዳይመለስ ይረዳል፡፡ በየመሥሪያ ቤቱ የተሰገሰጉ በደል ፈጻሚ ግለሰቦችን ለይቶ ለማወቅ ያስችላል፤
- የመልካም አስተዳደር ችግርን ለማጥፋት መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን ያሳይበታል፤
- ብልሹ አሠራርን በመታገል ሙስናን ለሚጸየፉ ሠራተኞች ዋስትና ይሰጣል፤
- የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት መርኅን ያረጋግጥበታል፡፡ በማን አለብኝነት ውሳኔ የሚሰጡ ኃላፊዎችንም አደብ ያስገዛበታል፡፡
በመሆኑም ባለፉት በርካታ ዓመታት ውስጥ አቤቱታቸውን የሚያዳምጥ ጠፍቶ ከየመሥሪያ ቤቱ የተገፉ ዜጎችን በመጥራት ቢያንስ ቅሬታቸውን የሚያቀርቡበት መንገድ ቢፈጠር፣ የመልካም አስተዳደር ችግርን ከመታገል አኳያ ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው እላለሁ፡፡ ምክንያቱም የመልካም አስተዳደር ችግር መኖሩ ከታመነ የዚሁ ችግር ሰለባ የሆኑ ዜጎችን የመፍትሔ አካል ማድረግ ብልህነት ነውና፡፡
- (ወንደሰን፣ አዲስ አበባ)