ኢትዮጵያና ኬንያ የዓለም ንግድ ምክር ቤቶች ጉባዔ ለማሰናዳት ለገቡት ፉክክር ውሳኔ የሚሰጠው አንድ ቡድን አገሪቱ ያላትን አቅም ለመገምገም ወደ ኢትዮጵያ ሊመጣ ነው፡፡
በዓለም ንግድ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ፒተር ሚሆክ የሚመራው ይህ ቡድን በመጪው ሳምንት አዲስ አበባ የሚገባ ሲሆን፣ ይህንን ዓለም አቀፍ ጉባዔ ለማስተናገድ የሚያስችሉ የስብሰባ አዳራሾች፣ ሆቴሎችና ተያያዥ መሠረተ ልማቶች በመጎብኘት ለውሳኔ የሚረዳውን መረጃ እንደሚያሰባስብ ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎች በመያዝ ከሚታወቁ ጉባዔዎች አንዱ የሆነው የዓለም የንግድ ምክር ቤቶች ጉባዔ በየሁለት ዓመቱ የሚካሄድ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. በ2021 የሚደረገውን ጉባዔ ለማዘጋጀት ኢትዮጵያ ዕጩ የሚያደርጋትን ጥያቄ ያቀረበችው ባለፈው መስከረም የዓለም ንግድ ምክር ቤቶች ጉባዔ በሲድኒ በተደረገበት ወቅት ነው፡፡
በወቅቱ ቀጣዩን ጉባዔ በአፍሪካ ለማድረግ በተወሰነ ውሳኔ መሠረት ለዚህ ጉባዔ ዝግጅት ኢትዮጵያና ኬንያ ጥያቄ በማቅረብ ፉክክር ውስጥ ገብተዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2021 የሚካሄደውን ጉባዔ ለማስተናገድ ከኬንያና ከኢትዮጵያ ሌላ ወደ አራት አገሮች ራሳቸውን ዕጩ ያደረጉ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ እንደ ዱባይ ያሉ አገሮች ይገኙበታል፡፡
አሁን ባለው አመለካከት ጉባዔው አፍሪካ ውስጥ ይደረግ የሚለው ሐሳብ እያመዘነ በመሆኑ፣ ዋነኛ ተፎካካሪ የሚሆኑት ኢትዮጵያና ኬንያ ይሆናሉ፡፡ በዚሁ ጉዳይ ላይ የሁለቱ አገሮች የንግድ ምክር ቤቶች ተገናኝተው እስከመምከር የደረሱበት አጋጣሚ ቢኖርም፣ አንዱ ለሌላው ለመልቀቅ ፍላጎት ሳያሳዩ ቀርተዋል፡፡
ጉባዔው ከሚያስገኘው ጥቅም አንፃር ሁለቱም አገሮች በየፊናቸው ጉባዔው በአገራቸው እንዲስተናገድ የሚያስችል የተለያዩ ጥረቶችን እያደረጉ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ዕድሉን ለማግኘት ጥያቄውን ካቀረበችበት ጊዜ ጀምሮ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን እያደረገች መሆኑን የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅሷል፡፡ ኢትዮጵያ ይህንን ጉባዔ ለማስተናገድ እያደረገች ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ እንዲሁም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው የልዑካን ቡድን ስለሚያካሂደው ግምገማ ይዘት በመጪው ሳምንት መግለጫ እንደሚሰጥ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ መላኩ እዘዘው (ኢንጂነር) ገልጸዋል፡፡
ከሁሉም አገሮች የሚወከሉ የንግድ ምክር ቤቶች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑ ኩባንያ መሪዎችን ጨምሮ ከ2,000 በላይ ተሳታፊዎችን የሚይዘው ይህ ጉባዔ፣ ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄድ ነው፡፡
የዓለም ንግድ ምክር ቤቶች ፌዴሬሽኑን ከ100 በላይ አባላት አገሮች ውስጥ ያሉ ንግድ ምክር ቤቶችን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን፣ ከኢትዮጵያም የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትና የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት የዚህ ፌዴሬሽን አባላት ናቸው፡፡
እንደ ንግድ ምክር ቤቱ መረጃ በመጪው ሳምንት በዓለም አቀፍ የንግድ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት የሚመራው የልዑካን ቡድን ኢትዮጵያ ጉባዔውን ለማዘጋጀት ያላትን አቅም ከመገምገም ባሻገር ከኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ጋር በመገናኘት ይመክራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡