Wednesday, June 12, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ውኃ ልማት ፈንድ ለስድስት ከተሞች የ400 ሚሊዮን ብር ብድር አቀረበ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • 89 ከተሞች ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ ብድር አግኝተዋል

የውኃ ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ከስድስት አነስተኛ ከተሞች ጋር ለንፁህ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ የሚውል የ411.3 ሚሊዮን ብር የብድር ስምምነት ተፈራረመ፡፡

ከብድር ገንዘቡ ተጠቃሚ የሆኑት ከተሞች መካከል በኦሮሚያ ክልል የሚገኙት አዋሽ መልካ ቁንጡሬ፣ ሰቃ፣ ሼኪ፣ ኤጄሬ እና ሆጃ-ዱሬ እንዲሁም ከደቡብ ክልል የዳሎቻ ከተማ መሆናቸውን የካቲት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በተደረገው የስምምነት ሥነ ሥርዓት ላይ ተገልጿል፡፡

 የውኃ ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ዋና ዋኬ፣ ከየከተሞቹ አስተዳደር ኃላፊዎችና የውኃ አገልግሎት ተጠሪዎች ጋር የብድር ውል ስምምነቱን ፈርመዋል፡፡

በስምምነቱ ወቅት እንደተገለጸው፣ ከ411 ሚሊዮን ብር የብድር ገንዘብ ውስጥ 60 በመቶውን ማለትም፣ 260 ሚሊዮን ብር የውኃ ልማት ፈንድ በብድር መልክ በቀጥታ ለከተሞቹ ያቀርባል፡፡ ቀሪውን 40 በመቶ ስድስቱ ከተሞች በወጪ መጋራት መርኅ፣ የከተሞቹ አስተዳደሮች የክልሎቹ ባለድርሻ አካላት በሚያወጡት ገንዘብ እንደሚሸፈን አቶ ዋና እንዲሁም ባልደረቦቻቸው ባቀረቡት ማብራሪያ ተገልጿል፡፡

የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶቹ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚከናወኑ  ዋና ዳይሬክተሩ ሲናገሩ፣ ፕሮጀክቶቹ አገልግሎት መስጠት በሚጀምሩበት ወቅትም 81 ሺሕ ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ የውኃ ልማት ፈንድ ጽሕፈት ቤት የብድር ፋይናንስ ዳይሬክተሩ አቶ ዓለማየሁ ታከለ አስረድተዋል፡፡

ከተመሠረተ ከ15 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የውኃ ፈንድ ጽሕፈት ቤቱ፣ በቅርብ ጊዜያት ወዲህ በርካታ የፋይናንስ ድጋፎችን ከውጭ መንግሥታት ማግኘት ችሏል፡፡ ባለፈው ዓመት ከዓለም ባንክ የ450 ሚሊዮን ዶላር ብድር ማግኘቱ አይዘነጋም፡፡ ብድሩን የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር በመፈራረም ለፈንድ ጽሕፈት ቤቱ ያስተላልፋል፡፡ ጽሕፈት ቤቱ ለአነስተኛ ከተሞች የሚሰጣቸው ብድሮች ዝቅተኛ ወለድ የሚታሰብባቸውና ከ20 እስከ 40 ዓመታት ውስጥ ተከፍለው የሚጠናቀቁ የተዘዋዋሪ ፈንድ ሥርዓትን የሚከተሉ ብድሮች ናቸው፡፡

ከዓለም ባንክ ባሻገር የጣልያን፣ የፈረንሳይና የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ በተደጋጋሚ ለጽሕፈት ቤቱ ብድር በማቅረብ ይታወቃሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ከሦስቱ አካላት የ82 ሚሊዮን ዩሮ ብድርና ዕርዳታ ማግኘቱ ተዘግቦ ነበር፡፡ የአፍሪካ ልማት ባንክና ሌሎችም ዓለም አቀፍ ተቋማት ለጽሕፈት ቤቱ ፋይናንስ ሲያቀርቡ ቆይተዋል፡፡

በመሆኑም እስካሁን 89 ከተሞች ከስምንት ቢሊዮን ብር በላይ የፋይናንስ አቅርቦት በማግኘት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚደርሱ የንፁህ ውኃ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት እንደቻሉና በግንባታ ሒደት ላይ እንደሚገኙ ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች