የዘመን ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ በሥራ ላይ ያሉትን የባንኩን ፕሬዚዳንት ለመተካት የተለያዩ ባለሙያዎችን ካወዳደረ በኋላ፣ የአዋሽ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩትን አቶ ደረጀ ዘበነን መረጠ፡፡ የዕጩውን ፕሬዚዳንት ሹመት ለማፀደቅ ለብሔራዊ ባንክ የቀረበው ጥያቄ አዎንታዊም ምላሽ ማግኘቱ ተገለጸ፡፡
የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ የዘመን ባንክ የዳይሬተሮች ቦርድ ለባንኩ ፕሬዚዳንትነት ከስምንት የሚበልጡ ተወዳዳሪዎችን አጭተው ውድድር ውስጥ አስገብተዋቸው ነበር፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አቶ ደረጀ የተሻለ ውጤት በማግኘታቸው ለዘመን ባንክ ፕሬዚዳንትነት ሊታጩ ችለዋል፡፡ በዚሁ መሠረት ባንኩ የአቶ ደረጀን ሹመት እንዲያፀድቅለት ለብሔራዊ ባንክ ያቀረበው ጥያቄም፣ አዎንታዊ ምላሽ በማግኘቱ የሹመቱን መፅደቅ የሚያረጋግጠው ደብዳቤ እየተጠበቀ እንደሆነ ይኸው የምንጮች መረጃ ያሳያል፡፡
የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት ለመሆን ከተወዳደሩት ከስምንት በላይ የባንክ ባለሙያዎች ውስጥ ለመጨረሻው ውድድር የቀረቡት አቶ ደረጀና በአሁኑ ወቅት የዓባይ ባንክ የኮርፖሬት አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው በማገልገል ላይ የነበሩት አቶ በለጠ ዳኘው እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ በሁለቱ የባንክ ባለሙያዎች መካከል ከፍተኛ ፉክክር ከተደረገ በኋላ አቶ ደረጀ ባገኙት ውጤት መሠረት የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት ለመሆን ተመርጠዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አቶ ደረጀ የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት መሆናቸውን የሚያረጋግጠው ደብዳቤ ከጻፈ፣ አቶ ደረጀ የባንኩ አራተኛው ፕሬዚዳንት ይሆናሉ ተብሎ ተገምቷል፡፡
በአዋሽ ባንክ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የቆዩት አቶ ደረጀ፣ በተለይ የባንኩ ዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን መሥራታቸው በዋናነት ተጠቅሷል፡፡ የአዋሽ ባንክ በአዲስ አደረጃጀት ሲዋቀር የባንኩ ኮርፖሬት የስትራቴጂና ትራንስፎርሜሽን ኦፊሰር ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው በማገልገል ላይም ነበሩ፡፡ አቶ ደረጀ በቢዝነስ አስተዳደር፣ በሕግና በማኔጅመንት ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ በባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ20 ዓመታት በላይ ሠርተዋል፡፡ አቶ ደረጀ አዋሽ ባንክን ከመቀላቀላቸው በፊት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና በወጋገን ባንክ ውስጥ ያገለገሉ ሲሆን፣ የጀርመኑ ኮሜርዝ ባንክ ተጠሪ በመሆንና በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ መሥራታቸውንም ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡
ዘመን ባንክን በአሁኑ ወቅት በፕሬዚዳንትነት እየመሩ ያሉት አቶ ፀጋዬ ተጠምቀ ናቸው፡፡ አቶ ፀጋዬን በአዲስ ፕሬዚዳንትነት ለመተካት የተፈለገው የጡረታ ጊዜያቸው በመድረሱ እንደሆነ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል አቶ ደረጀ የዘመን ባንክ ፕሬዚዳንት ለመሆን የሚያስችላቸውን ማረጋገጫ ቢያገኙም፣ እስካሁን በአዋሽ ባንክ ውስጥ ባሉበት የኃላፊነት ቦታ በመሥራት ላይ ናቸው፡፡
ዘመን ባንክ ከ16ቱ የአገሪቱ ባንኮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በዚህ ኢንዱስትሪ ውስጥ ሲቀላቀል ከሌሎች ባንኮች የተለየ አደረጃጀት ይዞ የገባ እንደሆነ ይታወሳል፡፡ በተለይ ባንኩ በአንድ ዋና መሥሪያ ቤት ብቻ አገልግሎቱን ለመስጠት በመወሰን ወደ ሥራ መግባቱ ይጠቀስለታል፡፡ ሆኖም ቅርንጫፎች መክፈት እንደሚኖርበት በተሰጠው ማሳሰቢያ መሠረት፣ አሁን በአዲስ አበባና በተለያዩ ከተሞች ከ23 በላይ ቅርንጫፎችን ከፍቶ እየሠራ ነው፡፡ ዘመን ባንክ የ2009 መጨረሻ ላይ ከታክስ በኋላ 246.5 ሚሊዮን ብር ማትረፉንና የተከፈለ ካፒታሉም 850 ሚሊዮን ብር ደርሶ ነበር፡፡ በዚሁ በጀት ዓመት ጠቅላላ የባንኩ ሀብት 9.7 ቢሊዮን ብር እንደደረሰም መገለጹ ይታወሳል፡፡
ዘመን ባንክ አሁን የሚጠራበትን ስያሜ ከመያዙ በፊት ኢንዱስትሪውን ለመቀላቀል ይዞት የነበረው ስያሜ ‹‹አክሰስ ባንክ›› የሚልም ነበር፡፡