ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ጎራ ያለው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በሁለት ቀናት ቆይታው ሦስት ሺሕ ሰው ጎብኝቶታል፡፡ ዋንጫው የካቲት 17 ቀን 2010 ዓ.ም አዲስ አበባ እንደደረሰ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) እና ከፍተኛ የመንግሥት፣ የስፖርትና የኦሊምፒክ ሹማምንት በተገኙበት አቀባበል ተደርጎለታል። ዘንድሮ በሩሲያ የሚካሄደውን የዓለም ዋንጫ ውድድር አስመልክቶ ዋንጫው ጉብኝት እንዲያደርግባቸው ከተመረጡ የዓለም 50፣ እንዲሁም ከአፍሪካ 10 አገሮች አንዷ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ኮካ ኮላ ኩባንያ ከፊፋ ጋር ያዘጋጀው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ጉብኝት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 126 ሺህ ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡ የዓለም ዋንጫን ደቡብ አፍሪካ ከስምንት ዓመት በፊት ባዘጋጀችበት አጋጣሚ ዋንጨው ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያ መምጣቱ ይታወሳል፡፡ ከ18 ካራት ወርቅ የተሠራው ዋንጫው የዓለምን ሉል በኅብረት ወደላይ በያዙ ሁለት ሰዎች ምስል የተቀረፀና 6.142 ኪሎ ግራም የሚመዝን ነው፡፡ ከቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እስከ ብሔራዊ ቤተ መንግሥት የነበረውን የዋንጫ አቀባበል ፎቶዎቹ በከፊል ያስቃኛሉ፡፡