Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹እግር ኳሱ በ ‹ኔት ወርክ› እና በእከክልኝ ልከክልህ የተሳሰረ ተቋም እየሆነ ነው››...

‹‹እግር ኳሱ በ ‹ኔት ወርክ› እና በእከክልኝ ልከክልህ የተሳሰረ ተቋም እየሆነ ነው›› አቶ ግርማ መስፍን የቀድሞ ተጫዋች

ቀን:

ከአብዛኛው የዓለም አገሮች አሠራር በተቃራኒ ከሚተገበሩ የእግር ኳስ አሠራሮች መካከል፣ የሙያ ክህሎትን ለማዳበር ታስቦ የሚሰጠው የእግር ኳስ አሠልጣኞችና የባለሙያዎች ሥልጠና አንዱ ነው፡፡ ግልጽ የሆነና ዓለም አቀፋዊ መሥፈርቱ እያለ በዘልማድና በዘፈቀደ እየተሠራበት የሚገኘው ይኼው የሙያ ማሻሻያ ሥልጠና አገሪቱ ወደፊት እደርስበታለሁ ብላ የምታልመውን የእግር ኳስ ራዕይ የሚያጨፈግግ ከመሆኑም በላይ ሕገወጥ አሠራር እንደሆነ የሚተቹ አሉ፡፡ ተችዎቹ ከልምዳቸውና እግር ኳስ ባደገበት አገር ኖረውና ተምረው ከተመለከቱት አሠራር ተነስተው የእግር ኳስ ስፖርት አሠልጣኝ (መምህር) የሚከተሉትን መመዘኛዎች ያሟላና ብቃቱ በዚህ መንገድ የተረጋገጠ መሆን እንደሚገባው ይሞግታሉ፡፡ ከሕፃናት ጀምሮ በሁሉም የዕድሜ ክልል ከሚገኙ ስፖርተኞች ጋር ለመሥራት ጥልቅ ፍላጎትን ከመጨበጥ ጀምሮ የማስተባበርና በዕቅድ የመመራት ስትራቴጂን መንደፍ መቻል ይጠበቅበታል፡፡ ይህ ዘርፍ ከፍተኛ አካላዊና አእምሯዊ ብቃትን ከመጠየቁም በላይ ጠንካራ ሰብዕና፣ ሥነ ምግባርንና የጎላ ድምፅ የታደለ ግለሰብ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ይህም በትዕግሥት በበሰለ አሠራር ራስን የማስቻል መንገዶችን የሚገልጽ ይሆናል ይላሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ታዲያ ‹‹ኢንስትራክተር›› የሚለው ማዕረግ ያላቸው እንዲሆኑ ግድ ይላል፡፡ የዚህ ሙያ ባለቤቶች ከዚህም ባሻገር ስፖርተኞችንም ሆነ የሥልጠና ተካፋዮችን በየጊዜው በፈገግታ በመልካም አቀባበል መጠበቅን፣ በየሳምንቱና እንደየሁኔታው የሚሰጡ ሥራዎችንና እንቅስቃሴዎችን የመተንተንና የማስረዳት፣ ሥልጠናዎችን በአጽንኦት የማጥናትና የማበረታታት ጥሩ ሲሠሩም የማነቃቂያ ተሞክሮዎችንና ሽልማቶችን መለገስን እንደሚያካትት ጭምር ይገልጻሉ፡፡ የእግር ኳስ ኢንስትራክተርነት ከሁሉም በላይ መሠረታዊ የእግር ኳስ ቁም ነገሮች በውል የተገነዘበ፣ በሁሉም የሥራ ጊዜ የማይቀያየር አግባብ ያለው ባህሪን ለታዳጊ ወጣቶች ማሳየት የሚጠበቅበት ይሆናል፡፡ አንድ ኢንስትራክተር እንደአሠልጣኝም አስፈላጊውን የሥልጠና ቁሳቁስ ተረድቶ የሚያሰባስብና ደኅንነታቸውን የመጠበቅ ኃላፊነት ያለበት ራሱንም በተሟላ የሥልጠና ትጥቅና ቁሳቁስ ዝግጁ ሆኖ መቅረብ እንደሚገባው ይታመናል፡፡ ከዚህ አኳያ ታዲያ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ኢንስትራክተር የሚባለውን ማዕረግ የያዙ ባለሙያዎች እነማንንና በምን ዓይነት የሙያ ዘርፍ ያሳለፉ አሠልጣኞችን ነው እያሠለጠኑ የሚገኙት? የሚለውንና ተያያዥነት ያላቸውን ጥያቄዎች በመያዝ ደረጀ ጠገናው ከቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ብሔራዊ ቡድን ተጨዋች አቶ ግርማ መስፍን ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- የእግር ኳስ አሠልጣኞች በሙያው ደረጃውን የጠበቀ የሙያ ፈቃድ ማረጋገጫ እንዲኖራቸው የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ቴክኒክና ልማት ዲፓርትመንት ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡ እስካሁንም የ‹‹ሲ››፣ ‹‹ቢ›› እና ‹‹ኤ›› ሥልጠና ሰጥቶ ከ1,400 በላይ የእግር ኳስ አሠልጣኞች የሙያ ፈቃድ ማረጋገጫ ባለቤት እንዲሆኑ ማስቻሉንም ይፋ አድርጓል፡፡ የሚሉት ይኖርዎታል?

 

አቶ ግርማ፡- ሥልጠናውን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተከታትየዋለሁ፡፡ በግሌ በጣም አሳዛኝና አስገራሚ ነው የሆነብኝ፡፡ ምክንያቱም ለጊዜው ሠልጣኞቹን አቆይተን ወደ አሠልጣኞቹ ስንመጣ እነማን ናቸው የሚለው በራሱ ትልቅ ጥያቄ የሚያስነሳ ይመስለኛል፡፡ ሲጀመር እነዚሁ ሰዎች ራሳቸውን የአሠልጣኞች አሠልጣኝ (ኢንስትራክተር) ብለው የሚጠሩ ናቸው፡፡ ኢንስትራክተር የሚለው ስያሜ በሁሉም ስፖርቶች ይታወቃል፡፡ የዋና፣ የቮሊቦልና የሌሎችም ስፖርቶች ኢንስትራክተር ተብለው የሚጠሩ ይኖራሉ፡፡ ይህ ማለት ግን በማዕረጉ የሚጠሩት ሰዎች በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ እንደምንመለከተው በታወቁ ክለቦችና ቡድኖች እግር ኳስ ተጫውተው ያላለፉና በማሠልጠን ላይ ለሚገኙ ባለሙያዎች የሙያ ፈቃድ ሥልጠና የሚሰጡ ማለት እንዳልሆነ ሊታመን ይገባል፡፡ ኢንስትራክተር ተብለው የሚታወቁ ሰዎች ሥልጠና መስጠት የሚችሉት ሕፃናትን፣ በጥቅሉ ታዳጊ ወጣቶችንና የብዙኃን (ማስ) ስፖርት ሥልጠናን የሚሰጡ ናቸው፡፡ እርግጥ ነው የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ዕውቅና ይሰጣቸዋል፣ ትክክል ነው፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የእግር ኳስ አሠልጣኝነት ሙያቸው ለሆኑ ፕሮፌሽናሎች የሙያ ፈቃድ ሥልጠና ለመስጠት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ባለው አካዴሚ ገብቶ ዕውቀቱና ብቃቱ ያለው ሰው ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይኼ በሌሎም አገሮች የሚሠራበት እውነት ነው፡፡ ለመሆኑ እነዚህ ራሳቸውን የካፍ ኢንስትራክተር ብለው ያስቀመጡ ሰዎች በአገሪቱ ለየትኛው ክለብ የተጫወቱ ናቸው? በግሌ ብዙዎቹን አላውቃቸውም፡፡ አንድ ሰው ትምህርት ቤት ገብቶ ስለተማረ ብቻ ኮሎኔል ተብሎ ወታደራዊ ተቋማትን መምራት እንደማይችል ሁሉ እግር ኳስም በተመሳሳይ ከዚህ ተለይቶ መታየት ይኖርበታል የሚል እምነት ሊኖር አይገባም፡፡ ሌላው በአውሮፓና በሌሎች እግር ኳስ ባደገባቸው አገሮች የሚጫወቱ እንደ ድሮግባና ሳሙኤል ኤቶ የመሳሰሉት ወደ አሠልጣኝነት ሙያ እንግባ ቢሉ አሁን በአገራችን በሚሰጠው ዓይነት የሙያ ፈቃድ ሥልጠና ተሰጥቷቸው ነው ፕሮፌሽናል አሠልጣኝ ተብለው የሚጠሩት? ከዚህ አኳያ እነዚህ የካፍ ኢንስትራክተር ወይም የአሠልጣኞች አሠልጣኝ ብለው ራሳቸውን የሰየሙ ሰዎች እነ ሳላዲን ሰኢድና አዳነ ግርማን የመሳሰሉት ያሳለፉትን የእግር ኳስ የሕይወት ውጣ ውረድ ትምህርት ቤት ገብተው ስለወጡ ብቻ የእግር ኳስ ጨዋታ ምንነትን ሊያስተምሯቸው ይችላሉ? ትክክል አይመስለኝም፡፡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የቴክኒክ ዳይሬክተርና በዙሪያቸው የተቀመጡት ሙያተኛ የተባሉት እነማን ናቸው የሚለው በሚመለከተው አካል መልስ ሊያገኝ ይገባዋል፡፡

ሪፖርተር፡- ለዚህ ተጠያቂ ማን ነው? ምክንያቱም እርስዎም ሆኑ ሌሎች አካላት በሚተቹዋቸው ኢንስትራክተሮች እግር ኳስ ሙያቸው ሆኖ ተጫውተውና አሠልጥነው  አሁንም እያሠለጠኑ የሚገኙ ፕሮፌሽናሎች የሙያ ፈቃድ ሥልጠናውን ወስደዋል፣ እየወሰዱም ናቸው፡፡

አቶ ግርማ፡- ለጥያቄው መልስ ከመስጠቴ በፊት በአገሪቱ እግር ኳስ በአሁኑ ወቅት ከብሔራዊ ቴክኒክ ኮሚቴው እስከ ቴክኒክና ልማት ዲፓርትመንቱ ሁሉም ቦታውን የተቆጣጠሩት በእግር ኳስ ሙያ ያሳለፉ አይደሉም፡፡ ይኼ በሆነበት አደረጃጀት አንድ ትክክለኛ ባለሙያ ‹‹ለምን›› የሚል ጥያቄ ቢያነሳ ምን ዓይነት የማጥፋት ዘመቻ እንደሚደርስበት የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ የሙያ ወረራ የተፈጸመው ይህንኑ ሽፋን በማድረግ ይመስለኛል፡፡ ወንጀልም ነው፡፡ በአገሪቱ እግር ኳስ ባህሉ የሆነ የኅብረተሰብ ክፍል ፍላጎትና ስሜት ከመግደል ተለይቶ አይታይም፡፡ የሩቁን ትተን የቅርቡን ብንመለከት የኢትዮጵያ ቡድን በተሸነፈባቸው ጨዋታዎች ሕይወታቸውን ያጡ ታዳጊ ወጣቶች እንዳሉ ልናስታውስ ይገባል፡፡ 

ሪፖርተር፡- በተቋሙ ውስጥ በ‹‹ኔትዎርክ›› የሚሠራ አደረጃጀት ተፈጥሯል እያሉ ነውን?

አቶ ግርማ፡- ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በፌዴሬሽኑ ያለሙያቸው ተቀምጠው የሙያውን አሠራር እያበላሹ ያሉ ሰዎች ራሳቸውን በመጠየቅ ሙያቸው ወደሚፈቅደው የሙያ ዘርፍ ለመሄድ ጊዜ ባልወሰደባቸው ነበር፡፡ ባለው ሁኔታና ተቋሙም የሙያ ነፃነቱ ስላልተጠበቀለት እግር ኳሱን ወዳልተፈለገ ውድቀት እየወሰዱት ነው፡፡ ለዚህ ማረጋገጫ በእነዚህ ሰዎች እስካሁን ድረስ ከ1,400 በላይ የሙያ ፈቃድ ሥልጠና ተሰጥቷል፡፡ ሥልጠናውን የሰጡትንና የሠልጣኞቹ የሙያ ብቃት እንደተጠበቀ፣ ለመሆኑ እነዚህ ሁሉ አሠልጣኞች የትኛውን ክለብ ነው እንዲያሠለጥኑ የሚጠበቀው? ለመሆኑ በአገሪቱ ምን ያህል ክለቦች ናቸው ያሉት? ይህንን የሙያ ፈቃድ ሥልጠና የወሰዱት በትክክለኛው የኳስ ሙያ አልፈው የመጡ ለመሆናቸው ማረጋገጫው ምንድነው? በዚህ መንገድ የመጡት አሠልጣኞች እንዴት ነው ሕዝብና መንግሥት የሚፈልጉት የእግር ኳስ ዕድገት እንዲያመጡ የሚጠበቀው? በፌዴሬሽኑ ባለው አሠራር  የተማረሩ ትክክለኛ የሙያው ሰዎች ሳይወስዱ በግድ በሌላ የሙያ ዘርፍ እየተሰማሩ ናቸው፡፡ በአገሪቱ በሚገኙ ትልልቅ የልማት ተቋማት ውስጥ በኃላፊነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ለምንድን ነው የእነዚህን ሰዎች ዕውቀት የማንጠቀመው? በፌዴሬሽኑ ያለሙያቸው የተቀመጡ ሰዎችስ ሙያቸው ወደ ሚፈቅደው ተቋም ሄደው መሥራት የማይችሉበት ምክንያት ምንድን ነው? ተጣርቶ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሙያን ለባለሙያ በሚባልበት በዚህ ወቅት እኛ ወዴት እየሄድን እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው እግር ኳሱ በ‹‹ኔትወርክ›› እና በእከክልኝ ልከክልህ የተሳሰረ ተቋም እየሆነ ነው ለማለት ያስደፈረኝ፡፡ ስለሆነም የሌለህን ለመሆን መታተር የለብህም፡፡

ሪፖርተር፡- በስፖርቱ አካባቢ የሚገኙ ኃላፊዎች ስፖርቱን ለመምራት ‹‹የሙጥኝ›› የሚሉበት ምክንያት ይኖረው ይሆን?

አቶ ግርማ፡- ለጥያቄው ትክክለኛውን መልስ መስጠት የሚችሉት ራሳቸው ቢሆኑ በተሻለ ተአማኒነት ይኖር ነበር፡፡ ይህንን ዕውነት ለመግለጽ ግን ሞራሉ ስለማይኖራቸው መናገር ያለብኝን እናገራለሁ፡፡ አንዱና ዋናው ምክንያት በአገሪቱ በሁሉም ስፖርቶች ኃላፊነት ላይ የሚገኙ ባለሙያዎች በቀድሞው የደርግ ሥርዓት በአብዛኛው ወደ ምሥራቅ አውሮፓ ለከፍተኛ የትምህርት ተልከው ከመሠረታዊ ሙያ ይልቅ ቋንቋና የስፖርት ጽንሰ ሐሳቦችን ቀስመው የመጡ ናቸው፡፡ ሌላውና ሁለተኛው ደግሞ በአገሪቱ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሰውነት ማጎልመሻና ተያያዥ የትምህርት ዘርፎችን አጥንተው በተለይ በእግር ኳሱ ከሥልጠናው ጀምሮ የተሰገሰጉ ይበዛሉ፡፡ የችግሩ መስንኤ ከዚህ ይጀምራል፡፡ ከዚህ ባልተናነሰ ደግሞ ትልቁ ስህተት ብዬ የምወስደው  የትኛው የሙያ ዘርፍ ለየትኛው ዕውቀት የሚለው ተለይቶ አለመቀመጡ ነው፡፡ እግር ኳስ የተግባር ሙያ ነው፡፡ የእንግሊዝና ሌሎች የአውሮፓ አገሮች የእግር ኳስ ዳይሬክተሮች በፕሮፌሽናል ደረጃ እግር ኳስ ተጫውተው ያሳለፉ እንጂ ቀጥታ ከትምህርት ቤት የመጡ አይደሉም፡፡ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ የኢትዮጵያ ከእነዚህ አገሮች ተለይቶ የሚታየው ለምንድን ነው? ተቋሙን የሚመሩ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በፌዴሬሽኑ በሙያተኛ ስም የሚነግዱ ሰዎችን በመለየት አቅምና ችሎታቸው በሚፈቅደው የሥራ ዘርፍ ሊመድቧቸው ይገባል፡፡ ይህን ካላደረጉ ተጠያቂ ናቸው፡፡ ለትክክለኞቹ ሙያተኞች ጥበቃና የሙያ ዋስትና ሊሰጡ ይገባል፡፡ ፌዴሬሽኑ የአሠራርና የአደረጃጀት ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ ለውጡ እግር ኳሱን ባህሉ ላደረገው የእግር ኳስ ቤተሰብ ሲባል እንጂ ብቀላ ተብሎ መወሰድ የለበትም፡፡

ሪፖርተር፡- በአገሪቱ ተቺ እንጂ የለውጥ ሰው የለም የሚሉ ወገኖች አሉ፡፡ ይህን አባባል እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ግርማ፡- እውነቱን ለመናገር ለውጥ የማይፈልግ የኅብረተሰብ ክፍል የለም፡፡ ነገር ግን እንዴት ወደሚለው ስመጣ፣ ሒደቱ እንዲህ ቀላል እንደማይሆን ግልጽ ነው፡፡ አጋጣሚ ሆኖ የኢትዮጵያን እግር ኳስ በተመለከተ በተንቀሳቀስኩባቸው አውሮፓም ሆነ አሜሪካ ከማገኛቸው ወገኖች ጋር እናወራለን፡ እያወራንም ነው፡፡ የቀድሞ ተጨዋቾች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለአገራቸው እግር ኳስ ይቆጫሉ፡፡ ይኼ ለረዥም ዓመታት የሆነ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ግን እግር ኳሱም በማይታመን ሁኔታ ወደ ኋላ እየሄደ ነው፡፡ ሙያተኞች ያልሆኑ እንደፈለጉ እየፈነጩበት ነው፡፡ ጠያቂ  የለም፡፡ ይኼ አሁን የሚስተዋለው ችግር እንግሊዞች ከ100 ዓመት በፊት የገጠማቸው ነው፡፡ ወደ መፍትሔው ለመምጣት የተጠቀሙበት ብቸኛ አማራጭ ሙያውንና ሙያተኛውን በማክበርና በማስከበር መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ተጨዋቾች ማኅበር (ፒኤፍኤ) አቋቁመው እግር ኳሳቸውን እንደታደጉ ይነግሩናል፡፡ እግር ኳሳቸው ዛሬ ምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ እየተመለከትን ነው፡፡ የሀብታቸው ምንጭ ሆኗል፡፡ ሌላው ለእግር ኳሳቸው ምን ያህል እንደሚጨነቁ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ ፕሪሚየር ሊጉ በተለይ በሳምንቱ መጨረሻ የሚደረጉ ጨዋታዎች፣ በእነሱ ሰዓት ሦስት ሰዓት ላይ የሚደረጉ ጨዋታዎች ይበዛሉ፡፡ ሁሉም ጨዋታዎች በአገሪቱ የቴሌቪዥን ሥርጭት እንዲተላለፍ አይፈቀድም፡፡ ይህንን ሁሉ ኃላፊነት የሚወስዱ ኤፍኤና ፒኤፍኤው ናቸው፡፡ ምክንያቱም ወደ ስታዲየም የሚገባው ተመልካች እንዳይቀንስ በማሰብ ነው፡፡ በአገራችን የእግር ኳስ ባህል አለ፡፡ ይኼ ከሆነ ደግሞ የውድቀታችን መንስዔ ምንድነው ብለን መነጋገር ይገባናል፡፡ በግሌ ይህንን ኃላፊነት በመውሰድ ነው ቃለ መጠይቁን ለመስጠት መነሳሳቱ ያደረብኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ከመነሳሳቱ ጎን ለጎን ሐሳብዎ እንዲሳካ በጉዳዩ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት ለማነጋገር አልሞከሩም?

አቶ ግርማ፡- በነገራችን ላይ ይህንን በኢትዮጵያ እግር ኳስ ዙሪያ በተለይ ሙያተኞችን በሚመለከት ያለውን የተመሰቃቀለ አሠራር መስመር ለማስያዝ እንቅስቃሴ ከጀመርን ከአምስት ወራት ያላነሰ ጊዜ አስቆጥረናል፡፡ ከሚመለከታቸው አካላት ማለት ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑና የመንግሥት አካላት ጋር ተወያይተናል፡፡ እንድንገፋበት ድጋፍ እንደሚያደርጉልንም ተረድተዋል፡፡ ይህንን ጉዳይ በሚመለከት ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደሞከርኩት በፌዴሬሽኑ እየተንሰራፋ የመጣውን ኔትወርክ ለማጥፋት ብቸኛው አማራጭ ሙያተኛው ሙያውን የሚያስከብርለትን የሙያ ማኅበር (ፒኤፍኤ) ማቋቋም ነው፡፡ ይኼ ማኅበር ቢኖር ኖሮ አሁን የምንመለከተው የሙያ ወረራ ባልተፈጸመ ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበሩን የማቋቋም ሒደት ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?

አቶ ግርማ፡- የመጣንበት መንገድ ቀላል ባይባልም፡፡ የሙያ ማኅበር እንዲቋቋም የቀድሞዎቹም ሆኑ የአሁኖቹ ተጨዋቾች ሙሉ ፍላጎት ስላለ በአሁኑ ወቅት መስመር ይዟል፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ ግን የእኛ ትውልድ አይደለም የአሁኖቹ እንደነ ጌታነህ ከበደ፣ አዳነ ግርማና ሌሎችም ተጨዋቾች የመጫወቻ ጊዜያቸው ሲያበቃ ነጋዴ ለመሆን ካላሰቡ በስተቀር ሙያተኞች ነን፣ ሙያው ይመለከተናል ብለው ቢነሱ ማንም አያስደርሳቸውም፡፡ አጋጣሚውን ተጠቅመው የሙያ ፈቃድ ሥልጠና የወሰዱ ቢኖሩ ሥልጠናው የጥራት ችግር ያለበት በመሆኑ የኢትዮጵያ ቡና እግር ኳስ ክለብ የቦርድ ሰብሳቢ እንደተናገሩት ‹‹ሪፖርት ማድረግ እንኳን አይችሉም›› እየተባለ ከሙያው እንዲርቁ ምክንያት መሆኑ አይቀርም፡፡ የፒኤፍኤው ሕልውና ከተረጋገጠ ግን ደረጃውን የጠበቀ የሙያ ፈቃድ ሥልጠና ከመሰል ማኅበራትና ከሌሎም አገሮች ፒኤፍኤዎች ጋር በመነጋገር ዕድሎችን ማመቻቸት ቀላል ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ይህንን ማኅበር በሕጋዊ መንገድ ለማቋቋም ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር ተነጋግረናል፡፡ የሚቀረን ደንቡ ከአገሪቱ የስፖርት ፖሊሲና ከሌሎችም ሕገ ደንቦች ጋር የሚጣረስ ነገር እንዳይኖረው ከሕግ አማካሪዎቻችን ጋር እየተነጋገርንበት ነው፡፡ እኛ የምንፈልገው እግር ኳሱ ተቋማዊ ቅርፁን ይዞ ፕሮፌሽናል የሆነ አደረጃጀት እንዲኖረው ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- አሁን የተሰጠው የሙያ ፈቃድ ሥልጠና አግባብነት እንደሌለው እየገለጹልን ነው፡፡ በሒደት በሕግ የምትጠይቁበት አግባብ ይኖር ይሆን?

አቶ ግርማ፡- ፕሮፌሽናል አሠልጣኝ ለመሆን ፕሮፌሽናል ተጨዋች ሆኖ ማሳለፉን እንደመስፈርት ካነሳን፣ ይኼ አሁን ከ1,400 በላይ የሙያ ፈቃድ ሥልጠና አሰጣጥ ትክክል ነው አይደለም የሚለውን እስከ ካፍና ፊፋ በመውሰድ በሕግ የምንጠየቅበት ሁኔታ እንደሚኖር ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ምክንያቱም እንደዚያ ሲሆን ነው በቀጣይ ተጠያቂነትና ግልጽነት ሊመጣ የሚችለው፡፡ የሌሎች አገሮችን የፒኤፍኤ ተሞክሮዎችን እንወስዳለን፡፡ በዚያውም እንማራለን፡፡ አፍሪካ ውስጥ 18 አገሮች ፒኤፍኤ አላቸው፡፡ የእነሱን ልምድ መጠቀም የግድ ይለናል፡፡ ለዚህ ከፌዴሬሽኑ ኃላፊዎች ጋር ተነጋግረናል፤ ደስተኞችም መሆናቸውን ገልጸውልናል፡፡ እግር ኳሱ የሁላችንም ስለሆነ ተጠያቂነትና ግልጽነትን የተላበሰ ማኅበር ብንመሠርት ጥቅሙ የጋራ እንጂ ጉዳት የለውም ብለን እናምናለን፡፡ ለዚህም ነው በቅርቡ የማኅበሩን መመሥረት ይፋ ማድረግ የሚጠበቅብን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በወቅታዊ ፀጥታና ደህንነት ጉዳዮች ላይ የቀረበላቸውን ምክረ ሐሳብ እያደመጡ ነው]

ችግሩ ምን እንደሆነ በትክልል ለይተነዋል ግን ግን ምን? በይፋ መናገር አልነበረብንም። ለምን? ችግሩን...

የ12ኛ ክፍል የብሔራዊ ፈተና ውጤትና እንደምታው

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) የትምህርትን...

ንግድ ባንክ ከቪዛና ማስተር ካርድ ጋር ተደራድሮ ያስጀመረው የገንዘብ ማስተላለፊያ ቴክኖሎጂና ፋይዳው

ከውጭ ወደ አገር በሕጋዊ መንገድ የሚላክ ገንዘብ (ሬሚታንስ) መጠን...

ይኼ አመላችን የት ያደርሰን ይሆን?

እነሆ ከፒያሳ ወደ ካዛንቺስ። ‹‹አዳም ሆይ በግንባር ወዝ ትበላለህ››...