Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

በአዶልፍ ፖርለሳክ ተጽፎ በተጫነ ጆብሬ መኮንን ተተርጉሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ለኅትመት የበቃው ‹‹የሐበሻ ጀብዱ›› መጽሐፍን ያነበቡ በሙሉ ጨርሶ የማይረሱት አንድ ታዳጊ ጀብደኛ አርበኛ አለ። የ16 ዓመቱ አብቹ። እስካሁን ድረስ ባደረግኩት ጥረት አብቹ ከዚህ መጽሐፍ ውጪ ታሪኩ በየትኛውም መንገድ ተነግሮ አያውቅም። እንደ መጽሐፉ ትረካ፣ በ1928ቱ የጣልያን ወረራ ወቅት ከተለያዩ የአገራችን (ግዛቶች) ሁሉም ኢትዮጵያውያን በሰሜኑ የጦር አውድማው ተሰባስበው የጀግንነት ሥራ ሲሠሩ፣ ከወረ ጃርሶ የመጡ ሁለት ፊታውራሪ ወንድሞቹ በውጊያው ላይ ሞተው የአንዱን አስክሬን አግኝቶ ሲቀብር የአንዱን በማጣቱ፣ ‹‹ወንድሜ አልሞተም ታስሮ በስቃይ ላይ ነው ያለው፤›› ሲል ‹‹እሱን ነፃ አወጣለሁ›› ብሎ፣ እንዳይዋጋ ትዕዛዝ ከተጣለበት ዋናው ጦር ወጥቶ፣ 200 የዕድሜ እኩዮቹን አስከትሎ ጣሊያንን ለብቻው በሽምቅ መዋጋት የጀመረውን የአብቹን ታሪክ መጽሐፉ አጓጊ አድርጎ ይተርካል።

የዚህ ታዳጊ ትረካ እጅጉኑ አስገራሚ ሆኖ ያገኘሁት በዕድሜው ማነስ ብቻ ሳይሆን እንደ መጽሐፉ አገላለጽ ‹‹ከሶስት ወገን ጠላት ያፈራ›› የሁሉንም አድናቆት ግን ያገኘ ጀግና መሆኑ ነበር። ዋናው የኢትዮጵያ ጦር ‹‹ያልተፈቀደ ውጊያ በማድረግ ላይ ነህ›› ብሎ ሊያስቆመው ሲሞክር፣ የሚዘርፉትን ያሳጣቸው ሽፍቶች በጠላትነት ያሳድዱታል። ጣሊያን ደግሞ ከዚህ ትንሽ ልጅ የማይጠበቅ ተደጋጋሚ ጥቃት ስለደረሰበት አፀፋውን በዋናው ጦር ላይ የአየር ድብደባ እያደረሰ ይበቀላል። አብቹ በ16 ዓመቱ ታላላቅ ጀብዶችን ሲፈጽም የሚተርከውን መጽሐፍ (የሐበሻ ጀብዱ) የዛሬ ሦስት ዓመት ግድም እንዳነበብኩት ይኼን ግዜ በሕይወት ይኖር ይሆናል ስል አሰብኩ። ተመኘሁም። በወቅቱም ከፊልም ጸሐፊው ማማሩ ተስፋ ጋር በመሆን የአብቹን ታሪክ ወደ ፊልም ለመቀየር ጥናቶችን ማድረግ ጀምረን ነበር። ከትውልድ አገሩ ወረ ጃርሶ (ጎሐ ጽዮን) ጀምሮ ታሪኩ እስከተነገረባቸው ቦታዎች ድረስ ባደረግነው ጥረት፣ የአብቹን ጉዳይ ሊያጠናክር የሚችል መረጃ ማግኘት አልቻልንም።

ታዲያ የዛሬ ሦስት ዓመት ግድም የቅድመ አያቴ ወንድም (የአባቴ አጎት) በዘጠናዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኘው አርበኛው አባ በላይ ተፈሪ (በሌ ጎመራ) ዘንድ በመሄድ፣ የልጅነት የአርበኝነት ታሪኩን እንዲያጫውተኝ ስለአብቹም የሚያውቀው ነገር ካለ ብየ 870 ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጬ ሰሜን ጎንደር ጨው በር ድረስ በመዝለቅ፣ የድካም ጊዜውን ከሚያሳልፍበት ደሳሳ ጎጆው ደረስኩ። የናፍቆት ሰላምታዎቻችንን ለረጅም ጊዜያት ተለዋውጠን እንዳበቃን መቅረጫዬን አዘጋጅቼ ጥያቄዎቼን ማቅረብ ጀመርኩ። የአብቹን ታሪክ ከሥሩ ጀምሬ ተረኩለት። ሳበቃም ጥያቄ አስከተልኩለት። ‹ይህን ሰው ታውቀዋለህ?› ስል ጠየቅኩት። ‹‹አዎ እንዴታ በደንብ እንጂ›› አለኝ። ደስታና ድንጋጤ ውስጥ ገባሁ። ‹‹ማነው?›› አልኩት። ‹‹እኔ ነኛ!!›› አለኝ በኩራት። ድንጋጤዬ ደስታዬን አጥፍቶት የሰማሁትን ማመን አቃተኝ።

- Advertisement -

‹‹አዎ። አሁን የነገርከኝ የኔ ታሪክ ነው፤›› አለኝ። ሊሆን የማይችል መሆኑን አስረግጬ ማስረዳት ጀመርኩ። አብቹ የወረ ጃርሶ የሰላሌ ሰው መሆኑን ደግሜ ደጋግሜ ስነግረው ሳቀብኝ። ‹‹አንት ቀለሀ ጥርስ›› (የሁል ጊዜ ስድቡ ነች) ‹‹አሁንም ያ ኩታራ ጨቅላ ነው ብለህ ነው ምትፈልገው?›› አለኝ። ‹‹የነገርከኝ ታሪክ እኮ የእምዬ ‹ኢቶጵያ› ታዳጊ ኩታሮች በሙሉ ታሪክ ነው፤›› አለኝ። ‹‹ማለት? አልገባኝም ንገረኝ?›› አልኩት። ‹‹ልታደክመኝ ነው ወደኋላ ጎትተህ?›› አለኝና ‹‹አርበኝነቱን የገፋነው የዕድሜ እኩዮቼ ኢትዮጵያውያን ነን። ታላቆቻችንማ ጥቂቶቹ አርበኝነቱን ሲመሩ ብዙዎቹ ደግሞ ከጣሊያን ጋር አብረው እኛን ያሳድዱን ነበር። ስንት ጀብዱ የሠራን ኢትዮጵያውያን ያን ጊዜ ጨቅላዎች ነበርን። ማን ቆጥሮን ብለህ ነው?››

አባ በላይ አልጋው ላይ እንደተጋደመ ታሪኩን ባጭር ባጭሩ ይተርክልኝ ጀመር። ከፉከራ እና ሽለላ ጋር አጅቦ። ‹‹በ1928 ዓ.ም. የ17 ዓመት ልጅ ሳለሁ ጦራችን ተበትኖ አብሬያቸው የዘመትኩት አባቴ ብላታ ተፈሪ ሞተው ቀብሬ ስመለስ፣ ያባቱን ደም ሊመልስ ነው ብሎ ማጆር ገመላታ የሚባል ጥልያን አዳርቃይን ተቆጣጥሯት ሊገለኝ ይዞኝ ሳለ፣ አንድ ሊቋሽ የተባለ የሐማሴን ሰው አስመልጦ ሰደደኝ። ማጆሩ በማምለጤ ተናዶ ፈልጎ ሊገለኝ ያሳድደኝ ገባ። ከቆላ ወገራ ደንቢያ ጉር አምባ በእግሬ እየተጓዝኩ ስሸሽ ቆይቼ ተመልሼ በስሜን አድርጌ ቅዱስ ያሬድ ገባሁ። ከቅዱስ ያሬድ ደግሞ አባ ተክሌ የሚባሉ ዋሻ የሚኖሩ የበቁ ሰው አገኘሁ። ‹አይዞህ እጅህን አትስጥ። ይህ ደንቆሮ ሊሄድ ነው ነገ። ኢትዮጵያም አይገዛውም›› ብለው ትንቢት ነገሩኝ። በዚህ ተበረታታሁ። ከዕድሜ እኩዮቼ ጋር ተስማምተን መስጥረንና መክረን አድብተን ስናበቃ የጀግና ጀብድ ፈጽመን ድንገት አደጋ በመጣል ገጥመን፣ ያሳድደኝ የነበረውን ማጆር ገመላታ ደምስሰን አደርቃይን፣ ብር ማርያምን፣ ዛሪማንና ጨው በርን ነፃ አወጣናቸው።

‹‹ይኼን ሁሉ ፈጽመን በሰሜን ዞረን ሸካቶ የሚባል የጣሊያን ጦረኛ ከልጅ ነጋሽ ጦር ጋር ገጥመነው አሥራ ሁለት ቤት አስደረደርነው። በግንቦት ደባርቅን ተሻግረን ሰኔ፣ ሐምሌና ነሐሴን በሞቀ ደማችን ‹ባስታኔ› የተባለውን ጦራቸውን ወግተነው መስረም 16 ቀን የሞተውን አስደርድረንና ምርኮውን አስቆጥረን ለታላቆቻችን አስረክበን፣ እነሱ በገሐድ በአጀብ ሲጓዙ እኛ ልጆቹ ተሰወርነ። ጣሊያን መልሶ አዳርቃይን ያዘብን። ሕዝቡን በንዴት ፈጅቶ በጥይት ቆልቶት የሕፃንና የሴት አዛውንት አገር አድርጎ ጠበቀን። በስውር ተመልሰን ስንገባ ድንገት አምልጬ ብቻዬን ገጠምኩ። ሁሉም በንዴት ተቀላቅሎኝ አረድናቸው። እንደ አውሬ ዓይቶን የተረፈው ሁላ እየደነበረ እግሬ አውጭኝ ብሎ ሲፈረጥጥ፣ መትረየስ ማርኬ አገሩን ነፃ አድርጌ ምርኮዬን በሙሉ ለደጃዝማች ነጋሽ አስረከብኩ። ደጃች ነጋሽ ሸልመው አጥናፉን እርዳው ብለው ወልቃይት ላኩኝ። ውጊያው ከባድ ኖሮ የከፋ ውድመት ገጥሞን እኔም ቆሰልኩ። አልታከምም ብዬ ቁስሌን ራሴ በብረቴ ተኩሼ ወደ ጦር ወረድኩ። አቦሀይ፣ ብሬ፣ ሥዩም፣ ጥላዬ የተባሉ ከጂዎችን አቁስዬ ማርኬ አስረክቤ ሰባት ጀግና ጣሊያኖችን ገድዬ፣ ሙትና ምርኮውን አስደርድሬ ለደጃች መንግሥቱ አስረከብኩ። እንዲህ እያልኩ ስንቱን ባንዳና ጥልያን ፈጀሁት። እግዚሐር ይቅር ይለኝ ብለህ? ‹ኢትዮጵያን› ስለሚወዳት ለሷ ሲል ካልማረኝ በቀር። [በረጂሙ ፉከራ አሰምቶኝ] እንል ነበር ያኔ ደማችን ፈሶ፣ በባሩድ ሰክረን። ስንቱን ግዳይ ጥለን። ይቅር ይበለን፤›› ሲል አጫውቶ ታዳጊ አርበኞች በዚያ ዘመን እንዲያ በዝተው ሳለ አንዱን ብቻ ነጥሎ ማግኘት ከንቱ ሙከራ መሆኑን አስተማረኝ።

ይህ ጀግና ሰው በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል። የጀግናው አርበኛ በላይ ተፈሪን ነፍስ እግዜሩ ይማርልን። አገሩን ለታደገ ቆርቦ ለሞተ ጀግና ‹‹ክብር ሞቱ ለጻድቅ›› እንጂ ምን እንላለን? የጀብደኛ አገር ወዳድ ልጆች ነን። አያቶቻችን አንድ ያደረጉን። አብቹን የመሰሉ ጀግኖች በሁሉም የአገራችን ክፍሎች አሁንም በሕይወት ሊገኙ ይችላሉና ሞትን ቀድመን ታሪካቸውን እንመዝግብ።

የጀግኖች እናት ነሽ በልጆችሽ ኩሪ
ጠላቶችሽ ይጥፉ ለዘላለም ኑሪ።
ኢትዮጵያዬ።

(ያሬድ ሹመቴ፣ በፌስቡክ ገጹ እንዳሰፈረው)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...