Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርየፍትሕ ናፋቂው ድምፅ

የፍትሕ ናፋቂው ድምፅ

ቀን:

በቅርቡ በመልካም አስተዳደር እጦት የተነሳ ስለደረሰብኝ የበደል በደል ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በ8/2/2007 ዓ.ም. አምስት ገጽ ደብዳቤ ጽፌ ነበር፡፡

ዛሬም ይህንኑ ጉዳይ በሚመለከት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሕግና ፍትሕ አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጥያቄ መልክ ያቀረብኩትን ጽሑፍ በዚህች ደብዳቤ አማካይነት አቀርባለሁ፡፡ ዛሬ በመልካም አስተዳደር ዙሪያ ያለው ችግር እኔን ጨምሮ የበርካታ ዜጎችን ኑሮ እያናጋ በመሆኑ የጻፍኩት ነጥብ ለሕዝብ እንዲደርስልኝ በማሰብ ለጋዜጣው ልኬያለሁ፡፡

ሰኔ 22 ቀን 2007 ዓ.ም. በተካሄደው የአስተዳደር ጉዳዮች ጉባዔ ላይ የሕዝብን አስተያየትና ጥያቄ ለመቀበል በተፈቀደው መሠረት የሚከተለውን ጥያቄ በጽሑፍ ልኬያለሁ፡፡ ጥያቄዬም በአጭሩ በሥራ ዓለም ዕድገትና ሽልማት የሚገኘው በታማኝነትና በትጋት ሠርቶ ውጤት በማስመዝገብ እንጂ ለግል ጥቅም ከተሠለፉ ጥቂት ኃላፊዎች ጋር ተመሳጥረው ዕምነት በማጉደል የኋላ ኋላ ለእስራትና ቤተሰብን ለከባድ ችግር የሚዳርግ መስሎ ይታየኝ ስለነበር፤ ምናልባትም ባልሠራሁት ወንጀል በተንኮል እንኳ ብወነጀልና ጉዳዩ ተጣርቶ ንፁህ ሆኜ ከተገኘሁ መንግሥት እኔን በመወገን አጭበርባሪዎችን ተጠያቂ የሚያደርግ ይመስለኝ ስለነበር ወዘተ ብዙውን ጊዜ ከፍርሀቴ የተነሳ በኃላፊዎቹ ጥርስ ውስጥ ገብቼ በተከታታይ በተወሰደብኝ ዕርምጃ ምክንያት በእኔ ዓለም ተወዳዳሪ የማይገኝለት የአስተዳደር በደል ተፈጽሞብኛል፡፡

- Advertisement -

ለምሳሌ ያህል በአግባቡ እየሠራሁ እስከ መጨረሻው ድረስ የደመወዝ ጭማሪና ማግኘት የሚገባኝ ጥቅማ ጥቅሞችን ሁሉ እንዳላገኝ ተደርጌያለሁ፡፡ ለማቀርባቸው አቤቱታዎች ምላሽ (ውሳኔ) ስለማላገኝ ዛሬም በርካታ መብቶቼንና ነፃነቶቼን እንደተገፈፍኩ እገኛለሁ፡፡

በዚሁ ችግር ምክንያት በየደረጃው 30 ዓመታት ሙሉ ሳቀርባቸው የቆየሁት ከ380 በላይ አቤቱታዎቼ፣ በድምሩ ከ80 በላይ ትዕዛዞችና የውሳኔ ሐሳቦች ብሎም ማስጠንቀቂያዎች ለአስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች ከበላይ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተላለፉልኝ ቢሆንም አንድም ተግባራዊ ሆኖልኝ አያውቅም፡፡

በሆኑም ይህንኑ ችግሬን በዝርዝር በመግለጽ ለቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ሁለት ጊዜ (አንዱ ያልደረሳቸው) እና በቅርቡም በ08/2/2007 ዓ.ም. የተጻፈ አቤቱታዬን ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለመላክ ስገደድ፣ ግልባጩን ለአሥር ዋና ዋና መሥሪያ ቤቶች ለክቡር አቶ አሕመድ አባ ጊሳ የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ እንዲደርስልኝ ማድረጌ ይታወሳል፡፡

ይሁን እንጂ ከዚህ ሁሉ መሥሪያ ቤቶች አንድም ምላሽ ማጣቴ ሌላ ከፍተኛ ሥጋት ያሳደረብኝ ከመሆኑም በላይ፣ በአሁኑ ጊዜ ያለሁበት መሥሪያ ቤትም አቤቱታዬ ተቀባይነት እንደማይኖረው ስለሚያውቅ በይበልጥ ገመዱን እያጠበቀብኝ በባሰ ችግር ውስጥ እገኛለሁ፡፡

ስለዚህ በአጭሩ እንዴት ባደርግ በጡረታ ከመገለሌ በፊት ስለአቤቱታዬ ውሳኔ አግኝቼ ቢያንስ ለአቤቱታ ውጣ ውረድ ከማወጣው የገንዘብ፣ የጊዜና የጉልበት ኪሳራ ነፃ ሆኜ አእምሮዬንም እኔም አሳርፌ መቀመጥ እንድችል አንድ ምላሽ እንዲሰጠኝ በዚህ አጋጣሚ በከፍተኛ አክብሮት እጠይቃለሁ፡፡

(ዲሮ ድሪባ፣ ከጅማ)

*********

የኤጀንሲው ዓላማ መሬት መረከብ አይደለም

ሐምሌ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. በቅጽ 20 ቋጥር 1589 ታትሞ ለንባብ በበቃው ሪፖርተር አማርኛ ገጽ 5 ላይ ‹‹አፋርና ሶማሌ ክልሎች ለግብርና ኢንቨስትመንት ሰፋፊ መሬቶችን ለማዕከላዊ መንግሥት ሊያስረክቡ ነው፤›› በሚል ርዕስ መረጃውን ከኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሙላት እንዳገኛችሁ በመጥቀስ ያወጣችሁትን ዘገባ አንብበነዋል፡፡ ሆኖም በተጠቀሰው ጽሑፍ ከፍተኛ የመረጃ ማዛባት ተግባር የተፈጸመና በኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ያልተገለጸ ጉዳይ እንደተባለ በማስመሰል ሙያዊ ሥነ ምግባርን ባልተከተለ ሁኔታ የቀረበ ዘገባ በመሆኑ፣ ትክክለኛ መረጃውን ለኅብረተሰቡና ጉዳዩ ለሚመለከታቸው አካላት ማድረስ አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን ማረሚያ በቀጣይ ዕትማችሁ ላይ እንድታወጡ እየጠየቅን መታረም ያለባቸውን ጉዳዮች ከዚህ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

በአገራችን የግብርና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ቀዳሚው የሕግ ማዕቀፍ የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በግብርና ኢንቨስትመንት ለሚሰማሩ ባለሀብቶች ዋስትና የሰጠው በአንቀጽ 40(6) የመሬት ባለቤትነት የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ መንግሥት ለግል ባለሀብቶች በሕግ በሚወሰን ክፍያ በመሬት የመጠቀም መብታቸውን ያስከብርላቸዋል በሚል ድንጋጌ ነው፡፡ በአጠቃላይ በአገራችን የግብርና ኢንቨስትመንትን የሚደግፉና የሚያበረታቱ የሕግ ማዕቀፎች ወጥተው በመተግበር ላይ ናቸው፡፡

ይህም በመሆኑ አገራችን እያስመዘገበች ባለችው ተከታታይ የኢኮኖሚ ዕድገትና ባላት የተረጋጋ ሰላም በርካታ የውስጥና የውጭ አገሮች ባለሀብቶች በዘርፉ በመሰማራታቸው የግብርና ኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ ይህንኑ አጠናክሮ ለመቀጠልም በግብርና ልማት የግሉ ዘርፍ ኢንቨስትመንት ተሳትፎና ድርሻ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲያመጣ በማድረግ በግብርና  የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ላይ ተቀምጦ የነበረውን የግብርና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የድርሻውን ያበረከተ ዘርፍ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም፡፡

መንግሥት ይህንኑ ፋይዳ ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት ዘርፉን የሚመራና የሚያስተባብር ተቋም የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲን በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 283/2005 አቋቁሞ ወደ ሥራ እንዲገባ በማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራዎች ሲያከናውን ቆይቷል፡፡

የግብርና ኢንቨስትመንት የትኩረት አቅጣጫም ሰፋፊ መሬቶች የሚገኙባቸውንና ሰው ያልሰፈረባቸውን ቆላማ አካባቢዎች፣ ሰፊ የሰው ጉልበት በማይጠይቅ ሜካናይዝድ ቴክኖሎጂ በመቀጠም በግል ባለሀብት እንዲለማ ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የግል ባለሀብቶችን ተሳትፎ ለማሳደግ ለሰፋፊ እርሻዎች የሚውልና ሕዝብ ያልሰፈረበትን መሬት ከክልሎች ጋር በመሆን መለየት፣ መሬቱ ለየትኛው የግብርና ምርት ተስማሚ እንደሚሆን የዳሰሳ ጥናት በማካሄድ በመሬት ባንክ ተደራጅቶ እንዲያዝ ማድረግ፣ ይህንኑ መሬት ለኢንቨስተሮች ማስተዋወቅና ቀልጣፋና ልማታዊ በሆነ አግባብ የአገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች እንዲያለሙት ለዚህ ተግባር የተለዩ ሰፋፊ መሬቶችን ከክልሎች በውክልና በመረከብ ማስተዳደር እንዲቻል የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 26 ቀን 2002 ዓ.ም. ባወጣው መመርያ ንዑስ አንቀጽ 2 መሠረት በመግባቢያ ሰነድ በውክልና ተረክቦ በሊዝ ተመን በኪራይ የማስተላለፍ ሥራዎች ይገኙበታል፡፡

የመግባቢያ ሰነዱ ዋነኛ ዓላማም በግብርና ሚኒስቴርና በክልሎች የጋራ ተሳትፎ የተለዩትን ለሰፋፊ የግብርና ኢንቨስትመንት ምቹ የሆኑትን መሬቶች በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች የኢንቨስትመንት ሕግ መሠረት ለባለሀብቶች በማስተላለፍ ባለሀብቶቹ መሬቱን በአግባቡ በልማት ላይ መዋላቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት ይሆናል፡፡

በዚሁ መሠረት ባለፉት ዓመታት በመግባቢያ ስምምነቱ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከደቡብ፣ ከጋምቤላና ከቤንሻንጉል በድምሩ 3,673,806 ሔክታር መሬት በጥናት ተለይቶ በግብርና ሚኒስቴር የመሬት ባንክ ውስጥ የገባ ሲሆን፣ ከዚህ መሬት ውስጥ 2.43 ሚሊዮን ሔክታር በዘርፉ ለመሰማራት አቅሙና ፍላጎቱ ላላቸው ከ5,670 በላይ ለአገር ውስጥ፣ ዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንና ለውጭ ባለሀብቶች በክልሎችና በፌዴራል ደረጃ በሊዝ ክፍያ ተላልፎ ለግብርናው ዘርፍ ምርትና ምርታማነት፣ ለኢንዱስትሪዎቻችን የጥሬ ዕቃ አቅርቦት፣ ለውጭ ምንዛሪ ግኝት፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና ለሥራ ዕድል ፈጠራ ዕድገት የራሱን የማይተካ ሚና እያበረከተ ያለ ዘርፍ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ከክልሎች ጋር ባለው የመግባቢያ ሰነድ መሠረት በውክልና የተረከበውን መሬት ውጤታማ እንዲሆን የመከታተልና ባለሀብቶችን የመደገፍ ሥራዎችን የሚያከናውን ሲሆን፣ ከዘርፉ ባለሀብቶች የሚሰበሰቡ የሊዝ፣ የመሬት መጠቀሚያ ግብርናና ሌሎች ተያያዥ ክፍያዎች በቀጥታ መሬቱ ለሚገኝበት ክልል ገቢ የሚደረግና ክልሉ ለሚፈልገው የልማት ሥራ የሚያውለው ነው፡፡

ስለዚህ በጋዜጣው ላይ እንደሰፈረው የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ በሚቀጥለው ዓመት ከአፋርና ከኢትዮጵያ ሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታት ለሰፋፊ የግብርና ኢንቨስትመንት የሚውል መሬት ሊረከብ እንደሆነ ተደርጎ የወጣው ዘገባ ትክክል ያልሆነና በኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተርም ያልተሰጠ መረጃ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ከክልሎቹ ጋርም የተደረሰ ስምምነት የሌለው መሆኑን እየገለጽን በቀጣይ በተጠቀሱት ክልሎች ያለውን የልማት አቅም በመጠቀም የክልሎቹን ልማት በመደገፍ ክልሎቹ ብሎም አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ለማሳደግ እንዲቻል ከክልሎቹ ጋር በትብብር የሚሠሩ በርካታ ሥራዎች የሚኖሩ ይሆናል፡፡ በሌላም በኩል በጋዜጣው እንደተጠቀሰው ለአልሚዎች የተላለፈው የመሬት መጠን 2.3 ሚሊዮን ሔክታር ሳይሆን 2.43 ሚሊዮን ሔክታር ነው፡፡ የተላለፈውም ለ86 ባለሀብቶች ሳይሆን ከላይ እንደተገለጸው ለ5,670 ባለሀብቶች ሲሆን፣ ከእነዚህ ባለሀብቶችም ውስጥ 24ቱ የውጭ አገሮች ባለሀብቶች ሲሆኑ፣ የተረከቡትም የመሬት መጠን 314,389 ሔክታር ነው፡፡ ቀሪው ለዳያስፖራ ኢትዮጵያውያንና የአገር ውስጥ ባለሀብቶች የተሰጠ ነው፡፡ በዘርፉ ከተሰማሩት የውጭ አገር ባለሀብቶች ውስጥ የህንድ፣ የቱርክ፣ የሱዳን፣ የፓኪስታን፣ የሳዑዲ ዓረቢያና የእንግሊዝ ባለሀብቶች ይገኙበታል፡፡

በመጨረሻም የጋዜጣው ዝግጅት ክፍል በዘርፉ በአገራችን እየተካሄደ ያለውን እንቅስቃሴ በተመለከተ የሚሰጡትን መረጃዎች ሳይዛቡ ለኅብረተሰብ እንዲቀርቡ እንዲያደርግ እያሳሰብን፣ ኤጀንሲው በማንኛውም ወቅት ያሉትን መረጃዎች ለማቅረብና በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኑን ለማረጋገጥ ይወዳል፡፡

(የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ)

ከአዘጋጁ፡- ባለፈው ሳምንት ‹‹አፋርና ሶማሌ ክልሎች ለግብርና ኢንቨስትመንት ሰፋፊ መሬቶችን ለማዕከላዊ መንግሥት ሊያስረክቡ ነው›› በሚለው ርዕስ የወጣው ዘገባ የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አበራ ሙላት ጋር የተደረገ የስልክ ቃለ ምልልስ መሠረት አድርጎ ነው፡፡

ሪፖርተር ባቀረበው ዘገባ የኤጀንሲው ዓላማ መሬት መረከብ እንደሆነ አላሰፈረም፡፡ ይልቁንም ባደረገው ቃለ ምልልስ ከተጠቀሱት ክልሎች ኤጀንሲው መሬት እንደሚረከብ የተገለጸለትን ለአንባብያን ማድረሱን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

አቶ አበራ ለሪፖርተር በሰጡት ቃለ ምልልስ ኤጀንሲው በአዲስ ዓመት ትኩረት ከሚያደርግባቸው ነጥቦች መካከል ከአፋርና ከሶማሌ ክልሎች ለልማት የሚውል መሬት ይረከባል የሚለው ይገኛል፡፡ መሬቱን የሚረከቡት ግን ከክልሎቹ ጋር ውይይት በማድረግ ስምምነት ላይ ሲደረስ እንደሆነም ገልጸው ነበር፡፡ ሪፖርተም ይህንኑ ዘግቧል፡፡

 

 

   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...